ማይናሚር – የሲኦል ምድር /ቴዲ አትላንታ/

ማይናሚር – የሲኦል ምድር /ቴዲ አትላንታ/

በርማ ወይም በአዲሱ ስሟ ማይናሚር የዓለምን ቀልብ ስባለች። ይህ የሆነው ግን በመልካም ሥራዋ አይደለም። በክፉ ሥራዋ እንጂ።

አንድ መንግስት ፣ ህግና ሥርዓት አውጥቶ ወደ አንድ ሚሊዮን አካባቢ የሆኑ የአንድ ጎሳና እምነት ተከታዮችን ለማጥፋት ሲሞክር ማየት በ21ኛው ክፍለዘመን አስገራሚ ነው። ይህ በደል እየደረሰባቸው ያሉት ደግሞ ሮሂንጊያ በሚል ስም የሚጠሩት የአገሪቷ ሙስሊም የአንድ ጎሳ አባላት ናቸው።

********

ሮሂንጊያዎች እነማን ናቸው?

ሮሂንጊያዎች፣ በምዕራባዊው የበርማ (ማይናሚር) ጠረፍ የሚኖሩ ፣ ብዛታቸው 1.1 ሚሊዮን አካባቢ የሚጠጋ ማህበረሰቦች ናቸው። ቋንቋቸው ከስማቸው ጋር ተመሳሳይ ነው። በበርማ በስፋት ከሚነገር ቋንቋም አንዱ ነው። እነዚህ ማህበረሰቦች በ12ኛው ክፍለዘመን አካባቢ ጀምሮ ፣ ከህንድና ከባንግላዴሽ ፈልሰው የመጡ እንደሆኑም ይነገራል። ያን ጊዜ እነዚህ አገራት በርማን ጨምሮ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ውስጥ ስለነበሩ፣ ፍልሰታቸው ከአንድ አገር ወደ ሌላው አገር እንደመሄድ ተደርጎም ታይቶ ነበር።

በርማ የራሷን ነጻነት ተቀዳጅታ፣ ራሷን የቻለች አገር ከሆነች ጊዜ ጀምሮ ግን የሮሂንጊያዎች ፍልሰት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገባ። “የኛ ወገን አይደሉም ፣ ወደመጡበት ይመለሱ” የሚል ዘመቻም ተጀመረ። እናም ለነዚህ ማህበረሰቦች ዜግነት ተከለከለ። ያን ጊዜም በይፋ “አገር የለሽ ማህበረሰቦች” ሆኑ።

ከዚህ የ1948 የበርማ ነጻነት በኋላ ጥቂት ዓመታት ቆይቶ፣ በበርማ ግዛት ቢያንስ ሁለት ትውልድ ያህል የቆዩ ሮሂንጊያዎች ካሉ ዜግነት ይሰጣቸዋል ተባለ፣ ዜግነትም አግኝተው፣ አንዳንዶቹ ለፓርላማ እስከመመረጥ ድረስ ደረሱ።

******************

መፈንቅለ መንግስቱና ጣጣው
በ1962 ዓ.ም በበርማ ወታደሮች መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ሥልጣን ያዙ። ያን ጊዜ ሁሉም የአገሪቷ ዜጎች ልዩ መታወቂያ እንዲያወጡ ህግ ወጣ። በአገሪቷ 135 ጎሳዎች አሉ ተብሎም ተደነገገ፣ ያን ጊዜ ሮሂንጊያዎች እንደ ጎሳ ፣ አንድ ተብለው ሳይቆጠሩ ሆን ተብሎ ተዘለሉ። “እንዳያማህ ጥራው ..እንዳይበላ ግፋው” እንዲሉ፣ ከ1948 ዓ.ም በፊት እዚህ የበርማ ግዛት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር የጽሁፍ ማስረጃ ካመጡ ዜግነት ይሰጣቸዋል ተባለ። ነገር ግን ማንም የዚያን ጊዜ ነዋሪነት መታወቂያ ወይም ማስረጃ በጽሁፍ ማግኘት እንደማይችል ግልጽ ነበር፡፡

በዚህ የተነሳ ሮሂንጊያዎች መስራት፣ መማር፣ መንቀሳቀስ ወዘተ. አቃታቸው። ያለ አገር ፣ ዜጋ የለሽ ሆነው ቀሩ። በ1970 ዓመተ ምህረት ፣ በርማን ከሮሂንጊያዎች ማጽዳት የሚመስል ዘመቻ ተጀመረ። ብዙ ሺህ የሚሆኑትም ወደ ባንግላዴሽና ማሌዢያ ተሰደዱ። ብዙ ስቃይ ደረሰባቸው።

በ2016 ዓ.ም የሮሂንጊያዎች መኖሪያ በሆነው ፣ ራኪን የተባለ ግዛት ውስጥ፣ ስድስት ፖሊሶች ተገደሉ ተብሎ ፣ ግዛቱ በፖሊሶችና ወታደሮች ተወረረ። ያን ጊዜ በሮሂኒጊያዎች ላይ እጅግ ዘግናኝ ዕልቂት ደረሰ። መደፈር፣ መደብደብ፣ መገደል ተራ ነገሮች ሆኑ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኖቬምበር 2016 ላይ ፣ “የበርማ ወታደሮች የሮሂንጊያ ጎሳዎች ላይ የዘር ማጥፋት እርምጃ ወስደዋል” ሲል ይፋ አደረገ። ነገሩ በመካከል ጋብ አለና፣ አሁን በዚህ ዓመት ኦገስት ወር ጀምሮ ደግሞ አዲስ ጭፍጨፋ ቀጠለ።

*****************

አስተዛዛቢው የባንግላዴሽ ምላሽ
በርማዎች፣ እነዚህ ሮሂንጊያ የሚባሉ ሙስሊም ጎሳዎች የኛ ዜጎች ስልልሆኑ አገራችንን ለቀው ይውጡ ይላሉ። ሮሂንጊያዎች ደግሞ አገራችን ነው ለቀን የት እንሂድ ይላሉ። ጎረቤት አገራት የሆኑት እነ ባንግላዴሽ ደግሞ ሊቀበሏቸው አልፈለጉም።

ሙስሊም የሆኑት ሮሂንጊያዎች ጥቃት ሲደርስባቸው፣ ሙስሊም አገር የሆነችው ባንግላዴሽ ለምን አልቀበልም አለች? የሚለው ሌላ አጠያያቂ ጉዳይ ነው። የተባበሩት መንግስታት እንደሚለው፣ ሸሽተው ባንግላዴሽ የገቡ የሮሂንጊያ ጎሳዎች ፣ በባንግላዴሽ ፖሊሶች ተይዘው ወደ በርማ እንዲመለሱ ተደርገዋል።

ካለፈው 2012 ዓ.ም ጀምሮ 168ሺህ የሚሆኑ ሮሂንጊያውያን ተሰደዋል። የተወሰኑት ባንግላሽ ሲገቡ፣ ሌሎች ደግሞ አስቸጋሪውን የውሃ ላይ ጉዞ በጀልባ በማድረግ ማሌዢያ ደርሰዋል። በ1970 የጀመረው የስደት ህይወት፣ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉትን ወደተለያዩ አገራት ተሰደው እንዲወጡ አድርጓቸዋል። የቀሩት ደግሞ ዛሬም ድረስ ስቃይና መከራ እየደረሰባቸው ነው።

********************

የኖቤል ሽልማት ኣሸናፊዋ ሳን ሱኪ
ወይዘሮ ሳን ሱ ኪ ፣ በበርማ ላደረገችው ትልቅ የሰላማዊ ትግል ተጋድሎ፣ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። አሁን ትልቅ ሥልጣን እጇ ላይ ባይኖርም፣ ከበርማ መሪዎች አንዷ ሆና ትቆጠራለች፣ ታዲያ ይህ ሁሉ መከራ በነዚህ ምስኪኖች ላይ ሲደርስ ለምን ዝም አለች? በሚል ሰሞኑን ትልቁ ዘመቻ እሷ ላይ ሆኗል። ወታደሮቹን ለማስቆም ሥልጣን ባይኖራትም፣ ቢያንስ ድርጊቱን ማውገዝ ነበረባት እየተባለ ነው።

አሁን ሮሂኒያዎች ላይ የሚደርሰው ግፍ አንገሽግሾናል የሚሉ ከመካከልቸው የወጡ ቡድኖች ጦር አንስተው ከበርማ ወታደሮች ጋር ተጋፍጠዋል። የተባበሩት መንግስታት ጉዳዩ በጣም አሳስቦኛል ብሏል። በርካታ የሙስሊም አገራት ደግሞ ዓለም ሁሉ ይህን በበርማ ሙስሊም ጎሳዎች ላይ የሚደረገውን ጭፍጨፋ እንዲያወግዝ ጥሪ አስተላልፈዋል። እንደ አል ቃይዳ ዓይነት ድርጅቶች ደግሞ የበርማ መንግስት ላይ የሽብር ጥቃት እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል።

በመካከል ህጻን ፣ ሴት አዛውንት ሮሂንጊያውያን ፣ የሙስሊም አገር ባልሆነው በርማም ሆነ የሙስሊም አገር በሆነው ባንግላዴሽ ዜግነት ተከልክለው፣ በሁለቱ አገራት ጠረፍ ላይ አገር አልባ ሆነው እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ እየደረሰባቸው ይገኛል።

ድርጊቱን ከማውገዝ ባለፈ ተግባራዊ ምላሽ ያስፈልጋል። በሱዳን በዳርፉር እንደደረሰው ሁሉ፣ በበርማ (ማይናሚር) ፣ ራኪን ግዛት ዕልቂት እየተፈጸመ ነው። ልዩነቱ ለዳርፉሩ ዕልቂት ዓለም የተነቃነቀውን ያህል ፣ አሁን ያ ንቅናቄ አለመታየቱ ነው።

ፈጣሪ በተአምሩ ይድረስላቸው።

LEAVE A REPLY