ኦሮሞ ላይ የዘመተው ማን ነው? /በጌታቸው ሺፈራው/

ኦሮሞ ላይ የዘመተው ማን ነው? /በጌታቸው ሺፈራው/

በኦሮሚያና ሶማሊ ክልል አካባቢ “የሶማሊ ክልል ልዩ ሀይል” የሚባል ንፁሃን ኦሮሞዎች ላይ ሲዘምንት እንደሰነበተ ኦህዴድም በግልፅ መናገር ጀምሯል። አብዲ የሚባለው የሶማሊ ክልል ሹም ካለው ስብእና እና የትህነግ ወኪልነቱ አንፃር ኦሮሚያ ውስጥ የቀጠለው ህዝባዊ እምብይተኝነት አቅጣጫ ለማስቀየር በተልዕኮ እየፈፀመው ያለ በህዝብ ላይ የተከፈተ ጦርነት ስለመሆኑ ግልፅ እየሆነ ነው። ነገር ግን ከአብዲ በተጨማሪ የሌላ አካል እጅም እንዳለበት የሶማሊያ ጦር አባል መሳተፉን የሚያሳይ ወረጃ ተገኝቷል። የሶማሊ ክልል ኮሚኒኬሽንና የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ስለዚህ የአህሉሱና ዋልጀማ አባል ነው በተባለ ወታደር ጉዳይ ቪኦኤ ላይ ተከራክረዋል። የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊው የሶማሊያ ወታደር መሳተፉን ገልፀው ተከራክረዋል። ለመሆኑ አህሉሱና ማን ነው? የሚዋጋው ለማን ነው?

አህሉሱና ዋልጀማ የሱፊ እምነትን መሰረት ያደረገ ቡድን ነው። ሶማሊያ ውስጥ የጎላ ታሪክ ባይኖረውም የዚያድባሬ መንግስት ከወደቀ በሁዋላ የተነሱ ” ፅንፈኛ ቡድኖች” ጋር ሲዋጋ እና በዚህ አቋሙ ምክንያት ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት የመሰረተ ቡድን ነው። ከሶማሊያ ጎረቤት ሀገራት መንግስታት መካከል ከዚህ ቡድን ጋር መልካም ግንኙነት ያለው የትህነግ/ ኢህአዴግ “መንግስት”ነው። ትህነግ እስካሁን ሶማሊያ ውስጥ አህሉሱናን የሚያክል እምነት የሚጥልበት ቡድን አላገኘም። ትህነግ ይህን ቡድን ለዘብተኛ ነው ብሎ በማመን እገዛ ሲያደርግለት የቆየ ሲሆን አህሉሱና ትህነግ/ ኢህአዴግ ሶማሊያ ድረስ ጦር የላከባቸውን ቡድኖች ሁሉ ሲዋጋ ቆይቷል። ትህነግ/ ኢህአዴግ በይፋ ወደ ሶማሊያ ጦር የላከው አሊትሃድ አል እስላሚያን ለመውጋት ነው። አህሊሱና ዋል ጃማ ሶማሊያ ውስጥ ከአሊትሃድ ጋር ሲዋጉ ከነበሩ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው። ትህነግ/ ኢህአዴግን በቅርብ ረዳትነት አስቀምጠው ምዕራባዊያኑ የመሰረቱት የሽግግር መንግስትን ጨምሮ ሶማሊያ ውስጥ የተመሰረቱ ድርጅቶች መሰረታቸው ውሃብያ እስልምና ነው። ይህን እስልምና ትህነግና ምዕራባዊያኑ በፅንፈኝነት ስለፈረጁት በውክልና ጦርነት ተዘፍቀው ቆይተዋል። ምዕራባዊያኑ ትህነግን ወኪል ሲያደርጉ ትህነግ በበኩሉ እዛው ሶማሊያ ውስጥ የበቀሉ እንደ አህሉሱና ያሉትን ቡድኖች ወኪል አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል።

በተለያዩ ጊዜያት ሶማሊያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ሲመሰረት አህሉሱና ዋልጀማ የሽግግር መንግስቱ አካል እንዲሆን ተደርጓል። ይህ ሲሆን የትህነግን ሚና ቀላል ነው ማለት አይቻልም። የሽግግር መንግስት በሚመሰረትበት ወቅት ከአልሻባብና ከሌሎች ከአህሉሱና በተቃራኒ የቆሙ ቡድኖች “አቋም ቀይረናል” እያሉ ወንበር ተሰጥቷቸዋል። እንደ አልሻባብ ያሉ ቡድኖች ቅርበት ያላቸው የማህበረሰብ መሪዎች ተካተዋል። በዚህም ምክንያት የሽግግር መንግስቱ ከጥጉ ሆኖ ከሚጠብቀው ትህነግ/ ኢህአዴግ ጋር አለመተማመን ውስጥ የገባባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይህ ሲሆን ግን አህሊሱና ከትህነግ የሚያቀራርበውን አቋም ሲያራምድ እንዲየውም ትህነግ በጥርጣሬ የሚያያቸውን የሽግግሩ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ” አክራሪዎች” በሚል ፈርጆ ከሽግግሩ ለመውጣት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ትህነግን የሚጠረጥራቸው የሽግግር መንግስቱ ፖለቲከኞች ጋር የለየለት ውዝግብ ውስጥ ገብቷል።

ምንም እንኳ ትህነግ ከሸሪያ ህብረት፣ ከዛም በሁዋላ አልሻባብ እና ሂዝቡል እስላም ወጥተው “የሽግግር መንግስት” ውስጥ የሚገቡት ላይ እምነት ባይኖረውም አልሻባብን የመሰሉ ቡድኖች ለማዳከም፣ በምዕራባዉያኑ ውሳኔና በአረብ ሀገራት ረዥም እጅ ራሱ ትህነግ/ ኢህአዴግ “ጀሃድ አውጀውብኛል” ብሎ ወደ ሶማሊያ ጦር እንዲልክ ምክንያት ያደረጋቸው ግለሰቦች የሽግግር መንግስት አካል ሲሆኑ ምንም ማድረግ አልቻለም። በሁዋላ ከእነዚህ ግለሰቦች ጋር ግጭት ውስጥ የገቡትን አህሉሱና አይነት ቡድን ድጋፍ ከመስጠት ውጭ።

አህሉሱና የእስልምና እምነት አይነት ሳወዲና መሰሎቿ ከሚደግፉት እንዲሁም አብዛኛው የሶማሊያ ህዝብ ከሚያምነው ውጭ በመሆኑ ይህ ቡድን እንደተፈለገው ሊጠናከር አልቻለም። ሆኖም ባለፉት 10 አመታት ለምዕራባዊኑ ጠንካራ የሶማሊያ ወኪል ለነበረው ትህነግ ጥሩ መንገድ መሪና በአቅሙም ወኪል ሆኖ አገልግሏል። ትህነግ/ ኢህአዴግ ከተዋጋቸው አሊትሃድ፣ አልሻባብና ሂዝቡል ኢስላም ጋር ብቻ ሳይሆን ከኦብነግም ጋር የተዋጋ ቡድን ነው። አህሉሱና ዋልጀማ ትህነግ የገጠመውን ሲገጥም፣ የጠላው ጋር ሲጣለ የቆየ በሚቆጣጠረው መሬት፣ የህዝብ ተቀባይነትና አደረጃጀትም ደካማ እና አናሳ ቡድን ነው። አብዛኛው ህዝብ ሱኒ አማኝ በሆነበት ሶማሊያ የተለየ እምነት ይዞ ስልጣን ለመውጣት የውጭ ሀገራትን ይሁንታ የሚፈልግ የትህነግ ወኪል ነው።

አህሉሱና ዋልጀማ ለትህነግ ወኪል ብቻ አይደለም። ትህነግ ይህን አናሳ ቡድን ሞዴልም ጭምር አድርጎ ተጠቅሞበታል። ትህነግ/ ኢህአዴግ በ ካድሬ ስልጣና መልክ የሚሰጠው እና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ ለመጫን እየጣረ ያለው ” አህበሽ” የሚባል እምነት የአህሉሱ እንደ ቡድን የሚከተለውና መንግስት ቢሆን አስፋፋዋለሁ የሚለው የ እምነት ነው። አህሉ ሱናን ምን አልባትም እንደ መንግስት እውቅና የሰጠው የትህነግ/ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ነው። ከእሱ በሁዋላ የኖወይ መንግስት እውቅና ሰጥተው ግንኙነት መስርቶ እንደነበር መረጃዎች አሉ። የትህነግን ያክል ግን ከአህሉሱና ጋር ግንኙነት ያለው የለም።

ለትህነግም የአህሉሱናን ያህል ታማኝ፣ ትህነግ የሚወጋቸው አልሻባብ፣ ሂዝቡል እስላምና እና ኦብነግ ጋር የተዋጋ የሶማሊያ ቡድን የለም። በግልፅ ከትህነግ ጋር ግንኙነት ያለው የሽግግሩም ሆነ የአሁኑ መንግስት የአህሉሱናን ያህል ታማኞች አይደሉም። የኦብነግ ከፍተኛ አመራር ተላልፎ ሲሰጥ ደስተኛ ያልሆኑ የሶማሊያ መንግስት አመራሮች እንዳሉ ከመታወቃቸው በተጨማሪ የሽግግሩም ሆነ የአሁኑ መንግስት ውስጥ ያሉ የትህነግ ጥቂት ታማኞች ካልሆኑ በስተቀር እንደ ቡድን ወይም መንግስት ኦብነግ ሞቃዲሾ ውስጥ ሲንቀሰቀስ ቢያንስ እንዳላዩ የሚያልፉ፣ ከዚህ ገፋ ሲል የሚደግፉ ናቸው። አህሉሱና ግን ከኦብነግ ጋር ጦርነት የገጠመባቸው ጊዜያትም አሉ። ለትህነግ ታማኝ በመሆኑ።

የአብዲ ” ልዩ ሀይል” ተሳተፈበት በተባለው ጦርነት የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር መታወቂያ ያለው እና በተለያዩ ጊዜያት መንግስት ሲቋቋም የትህነግ/ ኢህአዴግ ድጋፍ ሳይለየው ወንበር የሚሰጠው የአህሉሱና አባል መሆኑ ተነግሯል። በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው እንቅስቃሴ ለመንበሩ አደጋ መሆኑን የተረዳው ትህነግ/ ኢህአዴግ የህዝብን አቅጣጫ ለማስቀየር በሶማሊ ክልሉ ወኪሉ እንዲሁም ሶማሊያ ውስጥ ትህነግ የጠላውን በአቅሙ ሲዋጋ የኖረው በሶማሊያው ወኪሉ በአህሉ ሱና ዋልጀማ በኩል ኦሮሚያ ውስጥ ጦርነት እንደከፈተ ግልፅ ነው። ይህ የሶማሊያ ብሄራዊ ወታደር መለያ የያዘ ግለሰብ ጉዳይ ከተሰማ በሁዋላ “የታላቋ ሶማሊያ” አጀንዳም ተነስቷል። ሆኖም ወታደሩ አባል ነው ከተባለለት አህሉሱና ዋልጃማ በላይ ከእሱ ጋር የሚጋጩት የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናት ለዚህ አጀንዳ ቅድሚያ የሚሰጡናቸው። በመሆኑም ይህ ጦርነት ከታላቋ ሶማሊያ አጀንዳ በላይ የትህነግ የበላይነት፣ ህዝብን በቅጥረኛ፣ በውስጥና የውጭ ወኪል አስገድሎ፣ አቅጣጫ አስቀይሮ የመግዛት ፕሮጀክት አካል ነው። በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ ላይ የዘመተው ትህነግ እንጅ ሌላ አካል አይደለም። ሶማሊ ክልልና ሶማሊያ ባሉት ወኪሎቹ በኩል!

LEAVE A REPLY