በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን የውጭ ኃይሎች ጫናና ሴራ እንዴት ለመቋቋም ይቻላል? የራሳችን ጠላቶች...

በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን የውጭ ኃይሎች ጫናና ሴራ እንዴት ለመቋቋም ይቻላል? የራሳችን ጠላቶች ራሳችን ሆነናል /አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)/-ክፍል ሁለ

በክፍል አንድ ያቀረብኩት አስኳል ሃሳብ እንዲህ ይላል። እኛ ኢትዮጵያዊያን የራሳችን አድርገን የምንቀበላቸው፤ የምንኮራባቸውና የምንመካባቸው መለያዎች አሉን፤ እንቀበላቸው፤ እንመንባቸው። ለተከታታይ ትውልድ እናስተላልፋቸው። እነዚህ መለያዎች በሌሎች አገሮች፤ በተለይ ጥንታዊ በሆኑት በቻይና፤ በጃፓን፤ በደቡብ ኮርያ፤ በታይላንድ፤ በኢንዶኔዢያ፤ በህንድ፤ በኢታሊ፤ በኢራን፤ በግሪስና በግብጽ በተደጋጋሚ ካየኋቸው የአገር ወዳድነትና የዜግነት መለያዎች የተለዩ አይደሉም። የአገሩን ታሪክ የሚያከብርና በዜግነት የተመሰረተን ማንነት የተቀበለ ሕዝብ አይጠቃም። ራሱን ይችላል፤ ኃብታም ይሆናል። በእነዚህና በሌሎች አገሮች ታሪክን ማፍቀርና መቀበል፤ የዜግነት ማንነትን

ለተከታታይ ትውልድ ማስተማር ወዘተርፈ የተለመደና የተከበረ ነው። ከዘላቂና ፍትሃዊ እድገት ጋር ቅጥተኛ የሆነ ግንኙነት
አለው።

በተደጋጋሚ እንዳየሁት፤ በእነዚህ አገሮች ዜጎች መብታቸውን የሚያስከብሩት ቻይናዊ፤ ታይ፤ ኢንዶኔዢያዊ፤ ህንዳዊ፤ ጣሊያናው፤ ግሪክ ወዘተ በሚል የዜግነት መለያ ነው። ለስራ ጉዳይ፤ ቻይና ስመላለስ፤ እኔ “ሃን ነኝ” ብሎ የሚናገር የቻይና ተወላጅ አላጋጠመኝም። እኔ ቻይና ሄጀ “አማራ ወይንም ኦሮሞ ወይንም ወላይታ ወይንም ትግሬ” ነኝ ብል ሰዎች ይስቁብኛል። እኔ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ስል ፈገግ ብለው የተቀበሉኝ ብዙ ናችው። በእነዚህ አገሮች ሁሉ ከጥንት ጀምሮ መለያ የሆኑ የአገር ታሪኮችና ቅርሶች ልክ እንደ እንቁ እንክብካቤ ይደረግባቸዋል።
እነዚህ ሕዝቦች ራሱን ያላከበረ ሕዝብ ማንም አያከብረውም የሚል እምነት አላቸው። ኢትዮጵያ ከብዙ አገሮች በበለጠ ደረጃ የሚያኮራ ታሪክ አላት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእያንዳንዳችን የሚያኮሩንን፤ ከሌሎች አገሮች ሕዝቦች የሚለዩትንና የሚያቀራርቡትን ወርቃማ ቅርሶች አበርክቶናል።

በህወሓቶች/ኢህአዴጎች የበላይነትና በውጭ ደጋፊዎች አማካይነት በብሄርና በኃይማኖት ልዩነቶች ላይ የተደነገገው የፌደራል ስርዓትና መንግሥት (State and Government) ከተመሰረተ በኋላ የአሁኑና የወደፊቱ ትውልድ ሆነ ተብሎ የኢትዮጵያን ረዥምና የሚያኮራ ታሪክ፤ የሕዝቧን የሚያስደንቅ አብሮና ተደጋግፎ የመኖር ታሪክ ፈጽሞ እንዲረሳ ተደርጓል። ይህ ሆነ ተብሎ “የፌደራል” አገዛዝ “ዲሞክራሳዊ ነው” ተብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲቀበለው የተደረገው ዲሞክራሳዊ አገዛዝ ስለሆነ አይደለም። የጥቂቶች፤ ለጥቂቶች የሆነ የጠባብ ብሄርተኞች የበላይነት በየት አገር ዲሞክራሳዊ ይሆናል? በጭቁን ሕዝቦች ነጻነት በማሳበብ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲን የበላይነት የሚያንጸባርቅ አገዛዝ እንዴት ዲሞክራሳዊ ሊሆን ይችላል?

ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጭና ሰላም የሚነሳ አገዛዝ እንዴት ዲሞክራሳዊ ሊሆን ይችላል? የዜጎችን ድምጽና መብት አፍኖ፤ የአገርን ዘላቂ ጥቅምና ደህንነት የሚያጠፋ አገዛዝ እንዴት ዲሞክራሳዊ ሊሆን ይችላል? የመሳሪያ ኃይል በመጠቀም ራሱን የሚካከብር፤ ሆነ ብሎ “የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው! የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጨርቅ ነው! ኢትዮጵያ የባህር በር አያስፈልጋትም! የሚል ቡድን እንዴት ዲሞክራሳዊ ሊሆን ይችላል?

እኛስ ምን ሆኖን ተቀበልነው፤ አስተናገድነው?
እኔ በሰራሁባቸው አገሮች ሁሉ፤ ከሁሉም በላይ የአገሩን ታሪክ ክዶ አገርን የሚያስተዳድር ፓርቲና መንግሥት አላጋጠመኝም። የተለያዩ ስሞች ቢሰጧትም፤ የመጀመሪያው ወሳኝ መርህ ኢትዮጵያ የተባለችው አገር ከአክሱም በፊትና ከአክሱም በኋላ እውቅና እንደነበራት መቀበል ነው። በኢትዮጵያ ቀጣይነት ላይ ድርድር መኖር የለበትም። ከአክሱም በፊት ያለውን አስደናቂ ታሪክ በአጭሩ ገምግሜ አብዛኛውን ወደጎን እተወዋለሁ። የአገር ውስጥና የውጭ የታሪክ ተመራማሪዎች፤ አንትሮፖሎጂስቶችና ሌሎች ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የጻፏቸው ሁሉ ቢሰበሰቡ ብዙ ቤተ መጻህፍቶች ይሞላሉ።

ለምሳሌ፤ ኢትዮጵያና ግብጽ ብዙ የሚጋሯቸው ታሪኮች፤ ባህሎች፤ ጥበቦች ወዘተርፈ እንዳሉ የግብጾችን ቤተ መጻህፍቶች፤ ቤተ መዘክሮችና ሌሎችን ማየት ተገቢ ነው። እኔ ግብጽን በተደጋጋሚ ሄጀ ለማጥናት ሞክሬአለሁ። የኢትዮጵያና የግብጽ ሕዝቦች የሚጋሯቸው ብዙ ነገሮች እንዳሏቸው መስካሪ ነኝ። በተለይ ወደ አስዋን ሄዶ ያለውን ጠንካራ የሕዝብ፤ የባህል፤ የጥበብ ግንኙነት ለማየት ይቻላል። ሆኖም፤ የጥቁር አፍሪካዊያን ታሪክ እውቅና ስላልተሰጠውና እንዲያውም እንደ ሌለ ስለሚቆጠር የኢትዮጵያም ስልጣኔና አስተዋጾ ተደብቋል፤ ታፍኗል። የግብጾ ጎልቶ እንዲታይ ተደርጓል። ወደፊት ግን የኢትዮጵያ ታሪክ ጎልቶ እንደሚወጣ አልጠራጠርም።

የግሪኩ ፈላስፋ አሪስቶትልና ሌሎች ስለ ኢትዮጵያ በሰፊው ጽፈዋል። ሆመር የተባለው ተመራማሪ፤ ፈላስፋና ደራሲ ኢትዮጵያ ተብላ በምትጠራው ምድር የሚኖሩት ሁሉ “ከገነት” የመጡ ወይንም የወረዱ ናቸው ይላል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ከፍ አድርጎ ያቀረበልን ስቴፋኑስ የተባለው የቢዛንቲየሙ ተወላጅ ነው። “Stephanus of Byzantium (author of ‘Ethnica’, a 6th century AD geographical dictionary), voiced the universal testimony of antiquity when he wrote, “Ethiopia was the first established country on earth and (its peoples) were the first to set up the worship of the gods and to establish laws.” ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከየት መጣ? የሚለው ጥያቄ ከተመለሰ ብዙ ሽህ ዓመታት ሆነዋል። ሆኖም፤ የዚህችን አገር ረዢም ታሪክ አንቀበልም የሚሉ ኃይሎች አሁንም ስሟን ይክዳሉ። ተመራማሪዎች እንዲህ ይላሉ። “The name Ethiopia derived, from the Greek form, aithiopia, from the two words aitho, “I burn”, and ops, “face”. It would hence mean the colored man’s land — the land of the scorched faces.” እነዚህና ሌሎች ተመራማሪዎች በመረጃ ተደግፈው ያቀረቡትን ብንመለከት ሁሉም ከግብጽ በታች የሚገኙ አገሮችና ቦታዎች—ለምዳሌ ኑቢያ ኢትዮጵያ በሚለው ስም የተጠቃለሉ ነበሩ። ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብ አገር ናት፤ በመሆኗም የአፍሪካዊያን አገር ናት። ከጥቁር አፍሪካዊያን የሚለየን የለም።

በዚህም መሰረት፤ Afrikana የተባለው የምርምር ተቋም ከላይ የቀረበውን ግምገማ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ፤ አባይ ተብሎ በሚጠራው ወንዝ ዙሪያ የሚኖሩ ሕዝቦች የረቀቀ ስልጣኔ እንደነበራቸው፤ ነዋሪው ሕዝብ ድብልቅና የተሳሰረ እንደሆነ፤ የውስጥ ንግድ እንደተስፋፋ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ የባህር በር
የኢትዮጵያን ረዢም ታሪክ የሚያንጸባርቀው አንድ መሰረታዊ የጅዖ-ፖለቲካ ሃቅ አለ። ይኼውም፤ በመለስ ዜናዊ አዛዢነትና ገፊነት፤ ህወሓት/ኢህአዴግ የባህር በሯን አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ኢትዮጵያ የባህር በር ባለፀጋ መሆኗን ነው። መለስ ዜናዊና ቡድኑ ይኼን የክህደት ስራ ሲፈጽሙ የካዱት የራሳቸውን ታሪክ ጭምር ነው። ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት ለግልና ለቡድን ጥቅም ሲባል ነው።

በአስደናቂው በአክሱም ዘመነ መንግሥት አጼ ካሌብ ኤርትራን፤ ሳውዲ አረቢያንና የመንን ከመግዛታቸው ባሻገር ንግዳቸን አስፋፍተው ኢትዮጵያዊያን እስከ ሕንድ አገር ድረስ ይሄዱ፤ ይነግዱ፤ ታሪክና ባህላቸውን ያስፋፉ ነበር። የሰሜኑ ሕዝብ ወደ ማህል አገር፤ የማህሉ አገር ወደ ሰሜን ይሄድ ነበር። መለስ ዜናዊ ለቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ጽፎ ኤርትራ “ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል እንደግፋለን እንዳለ ታሪክ ይመሰክራል።

Wikipedia—https://en.wikipedia.org/wiki/History of Ethiopia ስንመለከት የአክሱምን አስደናቂ ታሪክና የኢትዮጵያን የባህር በሮች ስፋትና አግባብነት እናያለን። ከላይ ካርታው እንደሚያሳየው፤ የፖለቲካ ስልጣን ከያዙ በኋላ የህወሓት መስራቾችና መሪዎች የተከተሉት ፖሊሲ የአክሱምን ታሪክ በክሎታል። የኢትዮጵያን ደህንነት፤ ዘላቂ የኢኮኖሚን የንግድ ጥቅም አውድሞታል። “The Kingdom of Aksum was an ancient kingdom located in present-day Eritrea and the Tigray Region of Ethiopia. Ruled by the Aksumites, it existed from approximately 100 AD to 940 AD. The polity was centered in the city of Axum. It grew from the proto-Aksumite Iron Age period around the 4th century BC to achieve prominence by the 1st century AD, and became a major player on the commercial route between the Roman Empire and Ancient India. The Aksumite Empire extended its reach over the Arabian Peninsula (modern day Saudi Arabia and Yemen)….The Persian Prophet Mani (died 274 AD) regarded Axum as one of the four great powers of his time, alongside Persia, Rome, and China.” ታላቅና የባህር በር ባለቤት የነበረችውን ኢትዮጵያን ታናሽና የባህር በር አልባ አገር ያደረጓት ህወሓትና ተባባሪ የሆኑት ጠባብ ብሄርተኞች ናቸው። “Under Ezana (fl. 320–360) Aksum adopted Christianity. In the 7th century, early Muslims from Mecca sought refuge from Quraysh persecution by travelling to the kingdom, a journey known in Islamic history as the First Hijra.” ይህችን ክርስትናን ቀደም ብላ የተቀበለችና በራሷ ባህል የራሷ
ያደረገች፤ የነብዩ ሞሃመድን ተከታዮች ያስተናገደችና ለእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች መጠጊያና አገር የሆነችውን ኢትዮጵያችን በኃይማኖቶቿ እንዳትኮራ ያደረጓትም ህወሓቶችና አጋሮቻቸው ናቸው።

የአክሱም ታሪክ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ታሪክ ነው። አክሱም ከፈረሰች በኋላ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት የዛግዌና የሰሎሞን ስርዓቶች የተከተሏቸው መርሆዎች ተመሳሳይ፤ ማለትም የኢትዮጵያን መንፈስ የያዙ ናቸው። ተከታታይነትና ቀጣይነት ያላት መመሪያቸው ኢትዮጵያ ናት ለማለት እደፍራለሁ።

ጠባብ ብሄርተኞች እንደሚሉ ሳይሆን፤ የአክሱም ገዢዎች ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ይጠቀሙ ነበር። “The Kingdom used the name “Ethiopia” as early as the 4th century….Tradition claims Axum as the alleged resting place of the Ark of the Covenant and the purported home of the Queen of Sheba.”

ይህ የኢትዮጵያ ተከታታይነት፤ ቀጣይነት፤ ግዛታዊ እንድነት፤ ዘላቂነትና ሉዐላዊነት ዱብ እዳ አይደለም። ሕዝቧም ከጥንት ጀምሮ የተሳሰረ፤ የተዛመደ መሆኑ ሊካድ አይችልም። “The Ethiopian Empire (Abyssinia) was first founded by Habesha people in the Ethiopian Highlands. Due to migration and imperial expansion, it grew to include many other primarily Afro-Asiatic-speaking communities, including Oromos, Amhara, Somalis, Tigray, Afars, Sidama, Gurage, Agaw and Harari, among others. One of the earliest kingdoms to rise to power in the territory was the kingdom of D’mt in the 10th century BCE, which established its capital at Yeha. In the first century CE the Aksumite Kingdom rose to power in the Tigray Region with its capital at Aksum and grew into a major power on the Red Sea, subjugating Yemen and Meroe and converting to
Christianity in the early fourth century.”

በውጭ ጠላቶች ግፊት የአክሱም ስልጣኔ ሲወድቅ የዚህ አካባቢ ሕዝብ የት ሄደ? ብለን ብንጠይቅ ወደ ማህል አገር የሚል መልስ እናገኛለን። የትግራይ ሕዝብ መጠጊያውና መሸሻው ማህል አገሩ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። ኢትዮጵያዊያን አንድ ነን የምልበት ምክንያት ይኼው ነው። “The Aksumites gave way to the Zagwe Dynasty who established a new capital at Lalibela, before giving way to the Solomonic Dynasty in the 13th century. During the early
Solomonic period Ethiopia went through military reforms and imperial expansion that made it dominate the Horn of Africa.” ታሪካችን ይኼን የመሰለ ሂደት አለው።

በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥትና ከዚያ በፊት የኢትዮጵያ የባህር በሮችና ሌሎች ግዛቶች የተከበሩና የተፈሩ ነበሩ። ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶች በተከታታይ መጠቃት የጀመረችው በግብጾችና በኦቶማን ቱርኮች አማካይንት ሲሆን እነሱና ሌሎች የውጭ ኃይሎች የአገር ውስጥ ድጋፍ ነበራቸው። ይህ የውጣ ውረድና የመበታተን ታሪክ እንዲቆም ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት አጼ ቴዎድሮስ፤ ከዚያም የውጭ ጠላቶችን ለመቋቋም ከፍተኛ ሙከራና መስዋእት የከፈሉት አጼ ዮሃንስ መሆናቸውን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሊያስታውሱት የሚገባቸውን ታሪክ ሰርተው አልፈዋል። ሁለቱም መሪዎች የኢትዮጵያ የባህር በሮች እንዲመለሱ ፍላጎትና እቅድ ነበሯቸው። “Ethiopia was reunified in 1855 under Tewodros II, beginning Ethiopia’s modern history…Under the leadership of Yohannes IV, Ethiopia defended itself from an Egyptian invasion in 1874. He was killed in action in 1889. Under Menelik II, Ethiopia expanded to the south and east, through the conquest of the western Oromo (non Shoan Oromo), Sidama, Gurage, Wolayta and other groups, resulting in the borders of modern Ethiopia. Ethiopia defeated an Italian invasion in 1896 and came to be recognised as a legitimate state by European powers. A more rapid modernisation took place under Menelik II and Haile Selassie. Italy launched a second invasion in 1935.

From October 1935-May 1940, Ethiopia was under Italian military occupation…Ethiopian rebels who never surrendered, managed to drive the Italians out of the country in 1941, and Haile Selassie was returned to the throne. Ethiopia and Eritrea united in a federation, but when Haile Selassie ended the federation in 1961 and made Eritrea a province of Ethiopia, a war for Eritrean independence occurred, lasting until 1991.”

በአጭሩ፤ ኢትዮጵያ ሰላም ያገኘችበት ጊዜ አለ ለማለት አልችልም። ዛሬ የሚታየው አደገኛ ሁኔታ በአገር ውስጥ የሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ብቻ አይደለም። የኦጋዴን ሶማሌ ኢትዮጵያዊያን ከወንድሞቻቸው፤ ከእህቶቻቸው ከኦሮሞ ኢትዮጵያዊያን ጋር እየተጋጩ፤ እየተጋደሉ ነው። ብዙ ሽህ ወገኖቻቸን ከቀያቸው እየተተፈናቀሉ ነው። በሰሜን ህወሓቶች ጎንደሬው እርስ በርሱ እንዲጋጭ፤ እንዲጋደል፤ ለስደት እንዲዳረግ ለማድረግ “ቅማንትና ዐማራ” በሚል በሌለና በፈጠራ መለያ እያጋጩት ነው። ህወሓቶች እርጋታን አይወዱም።

በተመሳሳይ ደረጃ የሚታየው አደጋ የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች የሚያደርጉት ነው። አረቦች ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመዋዋል የቀይ ባህርን በበላይነት ይዘውታል። ሳውዲ አረቢያ፤ ግብጽ፤ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፤ ካታር “የኤርትራን nወደቦች በመከራየት” ኢትዮጵያን ከበዋታል።
በምእራብ ኢትዮጵያ ህወሓት የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን መንግሥት በኪራይ ስም አስተላልፎ የአገሪቱን ደህንነት በክሎታል። በጅቡቲም በኩል ያለው ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም። ይህ ከበባ (Encirclement and Stragulation) አገር ቤት ካለው የእርስ በርስ ግጭት ጋር ሲደማመር የኢትዮጵያ ህልውና ወደ አደገኛ ደረጃ እንደተሸጋገረ ያሳያል።

ይህ ሁሉ አደጋ በግልጽ እየታየ እኛ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ ልሂቃን፤ ምሁራን፤ ልዩ ልዩ ስብስቦች፤ የመንፈስ አባቶችና እናቶች ከትችት ውጭ የምንሰራው ገንቢ የሆነ ስራ አይታይም። የምንጠብቀው ምንድን ነው? የምንመካው በማን ነው? እኛ ኢትዮጵያዊያን መተቸትን፤ በፈጠራ ወሬ ሌላውን መክሰስን እንወዳለን። መተቸት ቀላል ነው። የኢትዮጵያ ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን “ሊታረቁ የማይችሉ (Irreconcialable Differerences)” የሚሉት የብሄርና የኃይማኖት ልዩነቶች ሊያስከትሉት የሚችሉትን አደጋ ቀደም ብለውም ሆነ ዛሬ አላስተዋሉትም። ይህ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ያለምንም ምርምር፤ ያለምንም ጥናት፤ ያለ ምንም መረጃ፤ ያለ ምንም ውይይት ስር እንዲሰድ የተደረገ የፖለቲካ ባህል ዛሬ ስር ነቀል የሆነ ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት መልክ ይዟል። ኢትዮጵያ ተከባለች።

የኢትዮጵያ “ተቃዋሚ” ግለሰቦች፤ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ድርጅቶች፤ የኃይማኖት ተቋሞችና መሪዎች ራሳቸውን የሚመሩት አስተማማኝ ባልሆነ መረጃ ነው። ጥልቀት ካለው ምርምር፤ ጥናትና መረጃ በበለጠ ደረጃ የሚጠቀሙብት የፈጠራ ወሬን፤ ከሚቃወሙት የህወሓት/ኢህአዴግ ፓርቲ የሚወረወርላቸውን የተሳሳተ መመሪያና ፕሮፓጋንዳ ነው። በተለይ “አስደናቂ እድገት” ተካሂዷል ሲባል ይኼን ከህብረተሰቡ ኑሮ መሻሻል ወይንም አለመሻሻል ጋር ለማያያዝ አለመቻላችን ምሳሌ ነው።

“አስደናቂው እድገት” ለማን ጠቀመ ብለን የምንተች ስንቶቻችን ነን? የቋንቋና የብሄር ተኮሩ ፌደራሊዝም ያስከተለውን አገር አፍራሽነት፤ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ለመተቸትና የተሻለ የመንግሥት ስርዓት አማራጭ ለማቅረብ የምንታገለው ስንቶቻችን ነን? ህወሓት/ኢህአዴግ፤ በተለይ ህወሓት የፖለቲካ ጨዋታውን ወደ ሳይንስ ለውጦታል። መከፋፈሉን፤ የዓለምን ሕዝብ፤ በተለይ ደጋፊ መንግሥታትን፤ ኢንቬስተሮችን፤ የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶችን፤ ስደተኛውን ወዘተርፈ ማባበሉን፤ ቅጥፈቱንና ማጭበርበሩን ያውቅበታል። ህወሓት ይኼን የሚሰራው በረቀቀ የስለላ መረብና በረቀቀ ምስጢር ነው። ይህን ቡድን እንቃወማለን የምንለው ግን፤ ህብረ-ብሄርና ብሄር ተኮር የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ፤ የዚህን ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በብቸኛነት የገዛውን ጠባብ ብሄርተኛና ጎጠኛ ፓርቲ ምስጢር ፈልፍለን ለማወቅ አልቻልነም። ትላንትም ዛሬ የምንከተለው የተቃውሞ መንገድ ተመሳሳይ ስለሆነ ህወሓት/ኢህአዴግ የሚወረውርልን አጀንዳ ተቀብለን ምን እንስራ?
እንላለን። የምንከተለውን አጀንዳ የሚያወጣልን ህወሓት እስከሆነ ድረስ የትም አንደርስም።

ብሄራዊ የሆነ የአላማ ጠንካራነትና የዓላማ አንድነት ወሳኝ መሆናቸው የፖለቲካ “ሃ ሁ” ነው። አንድ አገር! አንድ ሕዝብ! ብለን ተባብረን ለመታገል ካልወሰንን ህወሓቶች ኢትዮጵያን እንደ ተራ ቁሳቁስ ሸንሽነው፤ ወንድሙን ከወንድሙ ጋር አጋጭተው፤ መሬቱን እየነጠቁ መኖሪያ አሳጥተውና በራሳቸው የብሄር አባላትና ታማኝ በሆኑ ክፍሎች ተክተው እስከፈለጉበት ጊዜ ድረስ በበላይነት ይገዛሉ። ዛሬ ሚሊየኔር የሆኑት ነገ ቢሊየኔር ቢሆኑ አያስደንቅም። ልጆቻቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲገዙ በሚል ስልት በኢትዮጵያ ሕዝብ ባጀት ውጭ አሰልጥነው ራሳቸውን ተክተዋል።

የኢትዮጵያን ረዥም ታሪክ፤ የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ግዛታዊ አንድነት፤ የኢትዮጵያን የባህር በር፤ የኢትዮጵያን ቀጣይነትና ሉዐላዊነት አንቀበልም ያሉትን ወደ ጎን እንተዋቸው። ትኩረቱ ከእነሱ ላይ አይሁን። እየጠነከርን ስንሄድ ከእነሱ ጋር ድርድር እንጀምራለን። ዛሬ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በኢትዮጵያ የሚያምኑ ወገኖቿ ሁሉ በአንድ ላይ እንዲሰሩ ነው። ለኢትዮጵያ ጠበቃ እንዲሆኑ ነው።

አበተለይ የህብረ-ብሄር ድርጅቶችና የብሄርም ሆነው በኢትዮጵያ ቀጣይነት፤ ሉዐላዊነትና በዜጎች እኩልነትና መብት ላይ እምነት ያላቸው ክፍሎችና ግለሰቦች ቢያስተውሉት ኖሮ፤ በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ፤ ግዛታዊ አንድነት፤ ዘላቂነነትና ቀጣይነት፤ የባህር በር አስፈላጊነት፤ ሕዝብን የስልጣን ባለቤት ባደረገ የዲሞክራሲ ስርዓት አስፈላጊነት፤ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዜግነት መብት መከበር አስፈላጊነት፤ በሕግ የበላይነትና በእውነተኛ እኩልነት መርሆዎች አምነው አንድነት ይፈጥሩ ነበር። አላደረጉትም። ዛሬም፤ ነገም ይሰበሰባሉ እንጅ አንድ ለመሆን ቆርጠው አልተነሱም። ከአሁን በኋላ ካላደረጉት በገዢው ፓርቲ ላይ የሚያካሂዱት ትግል መሰረት አይኖረውም። ሕዝብን ማታለሉ ይቁም!!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀድሞን ሄዷል
ዛሬ እኛ ተከታዮች እንጅ መሪዎች አይደለንም። ታሪክ የሚነግረን ባለፉት አምሳ ዓመታት የተደረገው ጥረት ሁሉ ተደምሮ፤ እንኳን ለዲሞክራሲ ሽግግር ማመቻቸት ቀርቶ፤ ወደ ብሄራዊ መግባባትና ወደ አንድነት ልንሄድ የሚያስችል ሁኔታዎችን አልፈጠርንም። ሁሉም የራሱን “ዘውድ” እና የራሱን ጠባብ ብሄርተኛ የክልል ጥቅም እያመለከና በኪሱ ይዞ “አለመተባበራችን የእኔ ጥፋት አይደለም፤ ጥፋቱ የሌላው ነው” ይላል። ሕዝቡ በመሬት ላይ መስዋእት እየሆነ፤ ራሱንና ልጆቹን፤ ህይወቱን፤ ቤቱንና ኑሮውን መስዋእት አድርጎ ቀድሞን ሄዶ እኛ አሁንም እርስ በርሳችን እንጣላለን።

የጋራ ትኩረታችን በጋራ ዓላማ፤ ለጋራ የሕዝብ ጥቅም፤ ለጋራ ሃገርና ለተከታታይ ትውልድ ደህንነት ስርዓቱን በመተባበር ለመለወጥ የማያቋርጥ ስልታዊ ጥረት ማድረግ ወሳኝ መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም፤ ካለፈው ድክመታችን ለመማር ስለማንፈልግ ወይንም ፈቃደኛ ስላልሆንን፤ እውቀታችን፤ ልምዳችን፤ ግንኙነታችን፤ ገንዘባችን የሚባክነው ከእርስ በርስ መወነጃጀሉ ላይ ነው። ዛሬ የቃላቱ፤ የማህበረሰባዊ መገናኛው፤ የጽሁፉና ሌላው “ጦርነት (The war of ideas and concepts)” የሚካሄደው አሰቃቂ በሆነ ደረጃ የኢትዮጵያዊነት ጨዋነትን፤ ልዩነቶችን በጨዋነት የማስተናገድ መንፈስን፤ የመተማመን ስነ ልቦናን፤ የጋራ አገር አስፈላጊነትን እያመከናቸው ይታያል። ይህ በተቃዋሚው ክፍል በኩል የሚደረገው የጦፈ የፕሮፓጋንዳ “ጦርነት” ከገዢው ፓርቲ የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካ ባህል የተለየ ሆኖ ላገኘውም። በደርግ አገዛዝ ይታይ የነበረው የእርስ በርስ ጥላቻ አሁንም ሊወገድ አልቻለም።

አስታውሳለሁ፤ እኔ አገሬን ለማገልገል ብየ የዓለም ባንክ ስራየን ትቸ፤ እንዳስተምር የጠየቁኝን ዩኒቨርስቲዎች “እግዜር ይስጥልኝ፤ ወደ አገሬ ለመመለስ ወስኛለሁ” ብየ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሸ የውሸት ክስ ናዳውን ነው ያወረዱብኝ። እኔን ለሲአይኤ ለመስራት የሚያስገድደኝ አንድም ነገር የለም። ሌላውን ሁሉ እንርሳው። ዓለም ባንክን ትቶ ለዚህ ድርጅት መስራት ምን ትርጉም አለው። እኔን የከሰሱኝ “በሰላይነት” ነው። ከሳሾቸን አላውቃቸውም። ህሊናቸው ይከሰሳቸው እንጅ እኔ አንዲትም ሰኮንድ ቁም ነገር አልሰጠኋቸውም።

ዛሬ በአንድ አንድ አገር ወዳድ በሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚካሄደው ክስ በጣም የዘገንናል። ቁም ነገሩ አሁንም የዚህ አይነቱ የእርስ በርስ ክስ ይካሄዳል። ይህ መቆም አለበት። ሃጢያት ነውል፤ ወንጀል ነው። “ተቃዋሚ” ተብሎ በሚጠራው ክፍል ያለው ልዩነት የፖለቲካ ስልጣን ጉዳይ ይመስለኛል። አለያ ጥቃቅን ልዩነት ከሆነ በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይትና ድርድር ሊፈታ ይችል ነበር። ይህ “የተቃዋሚው ክፍል” ልዩነት ለገዥው ፓርቲ በገንዘብ ሊሸምተው የማይችለው ጥንካሬና የስልጣን ቆይታ እድል አበርክቶታል። በተጨማሪ አገር ቤትና ውጭ ያለው “ተቃዋሚ ኃይል” በአንድ ድምጽ ለመናገርና በሕብረት አቋም ለመያዝ አለመቻሉ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለሚደረግ ድርድርና ለዓለም
ሕብረተሰብ ለሚቀርበው አቤቱታ ሁሉ መሰናክል ሆኗል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚናገረውን ብናዳምጥ ነንዲህ የሚል ነው። “በተቃዋሚዎቹ መካከል የሚታየው ልዩነት እንደዚሁ ከቀጠለ ለአገራችን አደገኛ ክፍተት ስለሚፈጠር፤ የአሁኑ ስርዓት ቢወገድ ምን አይነት ብሄራዊና አስተማማኝ አማራጭ ስርዓት ሊመሰረት እንደሚችል አሁን ሊታሰብበትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ሊሆን ይገባዋል።” ይኼን ብሂል እኔም ሙሉ በሙሉ አስተናግዳለሁ። ከህወሓት/ኢህአዴግ በኋላ ምን ይሆናል? የሚለውን ጥያቄ ልናስብበትና ልንወያይበት ይገባል!!
ክፍል ሶስት “የኢትዮጵያ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ መግባቱ የአደጋው እምብርት” የሚለው በሳምት ውስጥ ይቀርባል።

LEAVE A REPLY