አማርኛ ከክርስቶስ ልደት በፊት /ዮፍታሔ/

አማርኛ ከክርስቶስ ልደት በፊት /ዮፍታሔ/

የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ገና ምኑም አልተነካም። አብዛኛው ተቃጥሏል፣ ወድሟል። ከዚህ የተረፈው ተዘርፏል።

በውጭ ሰዎች የተዘረፈው በየቦታው አለ። ነገር ግን ተተርጉሞና ለምርምር አመቺ በሆነ መንገድ ጸሐፍትና ተመራማሪዎች እንዲደርሱበት ሆኖ ለአገልግሎት አልቀረበም።

በሌላ በኩል በአንዳንድ ታዋቂና “ታዋቂ ያልሆኑ” ሰዎች የተዘጋጁ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ሥራዎች ቢኖሩም ወይ አልደረስንባቸውም ወይም እንደበቀቀን Eurocentric “ፈረንጆች” የሰጡንን ብቻ ይዘን በመጮህ ተጠምደናል። ሌላውንም ቢሆን እነሱ እስኪሰጡን (በሌሎች የተጻፉትን ላለመቀበል ወስነን) እየጠበቅን ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ በየአገሩ ተበትኖ በግለሰቦች እጅ፣ በየሙዚየሙና በየቤተመጻሕፍቱ  ስለሚገኝ በአንድ ደራሲ፣ በአንድ ተመራማሪ ወይም በአንድ ጠቢብ ሥራ ተጠቃሎ እስካሁን ሊቀርብ አልቻለም። በቅርብ ጊዜም አይቀርብም። ለዚህም ነው ዓለም ብቻ ሳይሆን ራሳችን ባለቤቶቹ የሆንነው ኢትዮጵያውያን ስለኢትዮጵያ በየጊዜው አዳዲስ ነገር መስማታችን የተለመደ የሆነው። ምናልባት ታሪክን በተመለከተ አንድ የተሞከረ መልካም ጥረት ቢኖር ደርግ ጉዳዩን ተረድቶት ይሁን ለራሱ የሚጠቅመውን ለመምረጥ ተክለጻድቅ መኩሪያን ወደተለያዩ አገራት በመላክ ያሰባሰባቸው መረጃዎችና የዚያ ውጤት የሆኑት ጥቂት መጻሕፍት ነበሩ። እነርሱም በአጭር ጊዜ የተዘጋጁና በአብዛኛው የቅርቡንና ነገሥታቱን ማዕከል በማድረግ የነበረውን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ውጣውረድ የሚመለከቱ ናቸው።

ከዚሁ ጋር በተመሳሳይ የኢትዮጵያን (የግእዝ) ፊደላት በሚመለከት በአገራችንም ሆነ በውጭ ጸሐፍት ሲጻፍ የኖረው ታሪክ (ከጥቂቶች በቀር) የተዛባ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። በተለይ የኢትዮጵያን ፊደላት አመጣጥና አገልግሎታቸውን በሚመለከት ከእኛ ጸሐፍት ይልቅ የውጭ ሰዎች የሠሯቸው የተሻሉ ናቸው ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል። ለምሳሌ እንዲሆን እ.ኤ.አ በ 2001 Gabriella F. Scelta በተባሉ ተመራማሪ የታተመ የጥናት ወረቀት (The Comparative Origin and

Usage of the Ge’ez writing system of Ethiopia) ከሥር ተያይዞ ይገኛል።

ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መካከል ይህን የመሰለ ጽሑፍ በስንቶች ቀርቦ አንብበናል? መልሱ ግልጽ ነው። ሆኖም የኢትዮጵያን ፊደላት አመጣጥና አገልግሎት በሚመለከት የዶ/ር አየለ በከሪ መጽሐፍ (Ethiopic, an African Writing System: Its History and Principles) ፋና ወጊ መሆኑን መመስከር አስፈላጊ ነው። ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ተመራማሪም የዶ/ር አየለ በከሪን መጽሐፍ እንደማጣቀሻ የተጠቀሙበት በዚህ ምክንያት ይመስላል።

Gabriella F. Scelta የኢትዮጵያ (የግእዝ) ፊደላትን ከሌሎች በርካታ የዓለማችን ፊደላት ጋር በማወዳደር ሌሎች የዓላማችን ፊደላት አንድ አገልግሎት ብቻ (የድምፅ ውክልና) ሲኖራቸው የግእዝ ፊደላት 5 ረቂቅ ባሕሪያት እንዳላቸው በመጥቀስ ሌሎች የዓለማችን ፊደላት (ላቲንን ጨምሮ) የግእዝን ፊደል እንደምሳሌ (እንደሞዴል) በመውሰድ ፊደላቶቻቸውን እንዲያስተካክሉ (ለምሳሌ ዘመናዊው ላቲን ወደጥንቱ እንዲመለስ) በሙሉ ልብ ሐሳብ እስከማቅረብ ደርሰዋል። ይህንን ስንት ኢትዮጵያውያን ጸሐፍት እንዳደረጉት የሚያውቀው አንባቢ ነው።

ሌላው ደግሞ የአማርኛን ቋንቋ የሚመለከት ነው። የአማርኛ ቋንቋ ከክርስቶስ ልደት 120 ዓመት ቀድሞ በኢትዮጵያ በስፋት ይነገር እንደነበረ ግሪካዊው የታሪክና የመልክ ዓምድር ተመራማሪ አጋታርኪደስ ትቷቸው ካለፈ በርካታ መጻሕፍት በአንዱ የተጠቀሰና በርካታ የውጭ አገር መጻሕፍት (አልፎ ተርፎ በርካታ ኢንሳይክሎፒዲያዎች) ደግሞ እርሱን እየጠቀሱ የአማርኛን ምንጭ ከክርስቶስ ልደት በፊት መሆኑን ሲመሰክሩ እስከዛሬ ድረስ ሙያው የሚመለከተው አንድም ኢትዮጵያዊ ተመራማሪም ሆነ ጸሐፊ ይህን ሲጠቅስ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ ያለመታወቁ ነው። ከተሳሳትኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ።

ሲጀመር አጋታርኪደስ ራሱ ታዋቂ የሆነ ግሪካዊ የታሪክና የመልክዓምድር ተመራማሪ ከመሆኑም በላይ በርካታ ጽሑፎችን ትቶ ያለፈ ሰው ነው። ከነዚህም መካከል Ta kata ten Asian (Affairs in Asia) በሚል ርዕስ 10 መጻሕፍት፣ Ta kata ten Europen  (Affairs in Europe ) በሚል 49 መጻሕፍት እንዲሁም Peri tes Erythras thalasses (On the Erythraean Sea) በሚል 5 መጻሕፍትን ትቶ አልፏል። ከነዚህ ሁሉ ስለአፍሪካ ቀንድና ቀይባሕርን ስለሚዋሰኑት አካባቢዎች የጻፈው 5ኛው መጽሐፍ አንዳችም ጉዳት ሳይደርስበት የተገኘ ነው። አጋታርኪደስ ስለአማርኛ የጠቀሰው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሲሆን ቋንቋው “ካማራ/K/Camara”ተብሎ እንደሚጠራና እርሱም ቋንቋውን ተለማምዶ እንደነበረ ዘርዝሮ አስፍሯል። ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ ማለት እንዲህ ነው።

እነዚህ የአጋታርኪደስ መጻሕፍትና ሥራዎቹ በበርካታ ሌሎች የግሪክና ርማውያን ጠበብት (Diodorus SiculusStraboPliny the Elder, Claudius Aelianus, Josephus) ለመጠቀስ የበቁ ናቸው።

ስለአማርኛ የጻፈው ደግሞ በትንሹ በሚከተሉት ቀደምት ሕትመቶች (እ.ኤ.አ 1833 አና ከዚያ ወዲህ) ተጠቅሶ ይገኛል። አብዛኛዎቹ ሥራዎች በርካታ የሙያው ብቃት ባላቸው ጠበብት የሚዘጋጁ ኢንሳይክሎፒዲያዎች መሆናቸው ደግሞ የመረጃውን ተአማኒነት የሚያጠናክር ነው።

 1. The Penny Cyclopedia of the society for diffusion of useful knowledge (1833). Vol I, p. 451
 2. James Cowles Prichard (1837). Researches into the physical history of mankind (containing researches into the physical ethnography of the African races), Vol II (3rd edition), p. 145
 3. Charles Knight (1859). Arts and sciences: or, Fourth division of “The English encyclopedia”, Vol I, p. 276
 4. The national encyclopedia: A dictionary of universal knowledge (1879), Vol I (Liberary edition), p. 620

ስለአማርኛ በአጋታርኪደስ የተጻፈውን ይህን መረጃ የሚጠቅሱ በጀርመን፣ በጣሊያንና በሌሎችም ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሕተመቶች በርካታ ናቸው።

ከዚህ አልፈው የሄዱ ደግሞ አሉ። ለምሳሌ ፕሮፌሰር ቬተር (Professor Vater) የተባለ ተመራማሪ ስለአማርኛ ቋንቋ በአጋታርኪደስ የተጻፈውን አምኖ ከተቀበለ በኋላ ያንን መሠረት በማድረግ በአማርኛ ቋንቋ አነሣስ ላይ የራሱን ሥራ እስከማቅረብ ደርሷል።

እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያዊ የቋንቋ ባለሙያዎች ይህንን ጉዳይ በሥራቸው ለምን አልጠቀሱትም የሚለውን ጥያቄ እያንዳንዳቸው በግል የሚመልሱት ይሆናል።

አዲሱ ትውልድና የአዲሱ ትውልድ ባለሙያዎች ደግሞ በተቀደደላቸው ቦይ የሚፈሱ ብቻ ሳይሆን በየሄዱበት በሙዚየሞች፣ በቤተመጻሕፍት፣ በቅርስ መሸጫዎችና ከግለሰቦች ጋር በመተዋወቅ ስለአገራቸው አዳዲስ መረጃዎችን እንዲያፈላልጉ፣ ያገኙትን መረጃ ሁሉ እንዲያሰባስቡ፣ እንዲመረምሩና ሳይፈሩና ሳያፍሩ ጽፈው ለትውልዱ እንዲያስተዋውቁ ይጠበቅባቸዋል። አበቃሁ!

3 COMMENTS

 1. ዮፍታሔ ጥሩ ጽፈዋል። ግን ስንት ግሩም ሥራ የሠሩ ኢትዮጵያውያንን ከመውቀስ ይልቅ ማመስገን ቢቀድም በተሻለ። ለአማርኛ አገልግሎት የእኛ ሰዎች የሠሯቸው የተሻሉ ናቸው ብለው ስለ እነ ዶ/ር አበራ ሞላ ሥራዎች እየጻፉ ያሉት እነ የሺሐሳብ አበራ ናቸው። የጥንት ኢትዮጵያውያን ከግብጻውያን ጋር በአማርና ትግርኛ ይገበያዩ ነበር ይባላል።
  http://en.academic.ru/dic.nsf/enwiki/7349877
  http://archive.li/q6DSm
  http://www.ethiomedia.com/1000bits/dr-aberra-molla-and-the-ethiopian-alphabet.pdf

LEAVE A REPLY