በየ አስር ዓመቱ የሚደረገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መራዘሙ ተጠቆመ

በየ አስር ዓመቱ የሚደረገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መራዘሙ ተጠቆመ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ በኅዳር 2010 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው አራተኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ባልታወቀ ምክንያት ተራዘመ፡፡ለቆጠራው አስፈላጊ የሆኑ የሎጂስቲክ ግብዓቶችና አቅርቦቶች በአብዛኛው ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ቆጠራው መራዘሙ ታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለቆጠራው ያስፈልጋሉ ተብለው የተገዙ 180 ሺሕ ዲጅታል ታብሌት ኮምፒዩተሮችና 126 ሺሕ ፓወር ባንኮች ግዥ መደነቃቀፎች ገጥሞት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን አብዛኛዎቹ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ተነግሯል፡፡

የግዥ መጓተት ለቆጠራው መራዘም ምክንያት ሊሆን ይችላል ቢባልም፣ 665 ሚሊዮን ብር የወጣባቸው ዕቃዎች ግን ባለፈው ሳምንት በአብዛኛው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ለዘንድሮው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ 3.1 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተመደበለት ታውቋል።

በኢህአዴግ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 103 መሠረት በየአሥር ዓመቱ መደረግ እንዳለበት ቢደነግግም “የህዝብና የቤቶች ቆጠራ ላልተወሰ ጊዜ መራዘመኑን ሪፖርተር ዘግቧል።ቆጠራው መራዘሙ የህገ መንግስት ጥሰት እንዳስከተለም ባለሙያዎች አስተያየት እየሰጡ ነው።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ የቆጠራውን መራዘም ያረጋገጡ ሲሆን የተራዘመበትን ምክንያት መንግስት በቅርቡ መግለጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። እንደ አስተያየት ሰጭዎች ግን ቆጠራው የተራዘመበት ዋና ምክንያት አሁን በሀገሪቱ ላይ የተከሰተው “ህዝባዊ አመፆች” እንደሆነ ይናገራሉ።

LEAVE A REPLY