የኦሮሚያ ወጣቶች የተሳተፉበት ጣናን ከእምቦጭ አረም የማፅዳት ዘመቻ ሲደረግ ዋለ

የኦሮሚያ ወጣቶች የተሳተፉበት ጣናን ከእምቦጭ አረም የማፅዳት ዘመቻ ሲደረግ ዋለ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ትናንት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች 700 ኪ.ሜ በላይ አቋርጠው በጎንደር በኩል ባለው የጣና ክፍል ዘምተው የእንቦጭ አረምን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ሲነቅሉ ዋሉ፡፡ ጣናን ከእምቦጭ አረም ለመከላከል ወደ አማራ ክልል ለዘመቻ ከመጡበት ሰዓት ጀምሮ በህዝቡ እየተደረገላቸው ያለው ወንድማዊ እንግዳ አቀባበል እንዳስደሰታቸው ወጣቶቹ እየተናገሩ ነው።ለወገን ፍቅር ወደአለው ህዝብ በመምጣችን እና ጣና ላይ የበኩላችን በማድረጋችን ሀሴት ተሰምቶናልም ብለዋል።

የኦሮሞ ወጣቶች ወደ ባህር ዳር መጓዛቸውን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ “ጣና የኛም ነው፤ ጣና የዓባይ ራስ ነው፤አባይን ደግሞ የአማራ ፣የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ክልሎች በጋራ በዥረቶቻቸው መግበው ያሳድጉታል፡፡አንድነታችንም እንደወንዙ ነው” በማለት በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ አጋርነታቸውን ገልጸዋል። የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው “የኦሮሞ ወጣቶችን በጎ ተግባር በክልሉ ህዝብ ስም አመሰግነዋል።ህብረታችንም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ ጽፈዋል።

የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮም ለበጎ ፈቃድ የመጡትን ወጣቶች ከጣና ባሻገር ባህር ዳርና አካባቢዋን የሚጎበኙበት መርሀ-ግብር እንደተዘጋጀም ይፋ አድርገዋል። የኦሮሞ ወጣቶች የፈጠሩት የትብብር መንፈስ ለርካታ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያን ደስታን የፈጠረ ሲሆን በተለይም አማራና ኦሮሞውን በገፍ እየገደለ ያለውን አምባገነኑ ስርዓት ገርስሶ ለመጣል የሁለቱ አካባቢ ወጣቶች የበለጠ ተቀራርበውና ተደራጅተው እንዲሰሩ በርካታ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።

LEAVE A REPLY