“ኢትዮጵያ ኬኛ፣ ጣና ኬኛ …!” ድንቅ መንፈስ! /ነቢዩ ሲራክ/

“ኢትዮጵያ ኬኛ፣ ጣና ኬኛ …!” ድንቅ መንፈስ! /ነቢዩ ሲራክ/

“ጣና ኬኛ!” መልዕክቱ ከእንቦጭ አረሙ በላይ ነው
የመለያየትና የመፈራረስን አደጋ ያከሸፈ መንፈስ
ከኦሮሚያ “ጣና ኬኛ!” እያለ የተመመው ወጣት ክፉውን የእንቦጭን አረም ነቃቅሎ እንደማያስወግድ ግልጽ ነው። ጥቂት ወጣቶች ተሸክመውት ጎጃም የገቡት የኢትዮጵያዊነት የአብሮነት የ”አንድ ነን” ግን መልዕክቱ ግን የእንቦጭ ተራ አረም አይደለም ኢትዮጵያን የማስወገድና የመታደግ መንፈስ የታመቀ መንፈስ አለው። ዛሬ ያየሁት ፍቅር፣ ዛሬ ያየሁት የአብሮነት፣ የህብረትና የአንድነት መንፈስ ከሰፊው የጣናን እንቦጭ አረም በላይ ነው።

“ጣና ኬኛ!” ብሎ ጎጃም የገቡትን ወጣቶች አደግድጎ በክብር ኩራት፣ በአባት አደር ወጉ ወገኖቹን ከደብረ ማርቆስ እየተቀበለ ተመልክተናል። ይቀጥልና እስከ ባህር ዳር ቄጠማ እያነጠፈ ለመቶ እንግዶቹ እልፍ አዕላፉ ለአቀባበሉ የሚያሸረግደ እንግዶቹን የሚቀበልበት ምክንያት ከጣና እንቦጭ በላይ የኢትዮጵያዊ መንፈስ ትንሳኤን ሲያበስረን መሆኑ ዛሬ በፈንጠዝያው መካከል ካልገባን፣ ነገ እውነቱ ሲገለጥልን ይገባናል!

“ጣና ኬኛ፣ ኢትዮጵያ ኬኛ” ይልሃል፣ ለአመታት ጀግናው ብርቱው ወገን … የተሸረበበትን የመነጣጠል መለያየት፣ የአድልኦ መንፈስ አሽቀንጥሮ፣ እንደ ስፖርቱ በአንዲት ሀገር ባንዴራ ማዕቀፍ ተከባብረን ተዋደን እንኖር ዘንድ ህዝብ መናገር፣ መመስከርና ማበሩን አላቆመም። የጎጃም ወገናቸው በነቂስ ወጥቶ ድጋፉን መስጠቱን የመመልከቱ ድንቅ የህብረት መንፈስ ትርጉሙ ከፍ ያለ ሀገራዊ መልክ አለው። በእርግጥም ለ200 ወጣት የኦሮሚያ ግዛት ተጓዥ በጎ ፈቃድ አድራጊ የጎጃም እንግዳ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞው ወጣት የጎጃም ወጣት ሽማግሌ በነቂስ ወጥቶ በክብር የተቀበለበት ሚስጥሩ ለመሰጠረው ግዙፍ ነው። ለእኔ ኢትዮጵያዊው ኦሮሞና አማራው ለአመታት በክፉዎች ከጫፍ እስከ ጫፍ የተረጨበትን የመለያየት መርዝ ስለማክሸፉ ምልክት ነው።

በህዝቦች መካከል ያለው፣ የቆየ የመደጋገፍ መንፈስ ይታይ ዘንድ ከጣናው የእንቦጭ አረም ከፍ ባለ ደረጃ ዛሬ ታይቷል። ክፉዎች ተስፋ ይቆርጡ ዘንድ ኢትዮጵያዊው ኦሮሞ “ጣና ኬኛ” ዘመቻ እያለ ጎጃም ሲገባ ህዝቡ በክፉ በደጉ እንደማይለያይና ህብረትና አንድነቱን ናፋቂ መሆኑን ማሳያ ሆኖናል። በእርግጥም በጣም ጥቂት ወጣቶች በአሸናፊነት መንፈስ ከኦሮሚያ ተመው ጎጃም ሲገቡ የጎጃም ሕዝብ በአንጻሩ መልዕክቱ ደርሶታል። ጎጃሜው ታጥቆ አሸርግዶ የኦሮሞ ወጣት ወንድም እህቱን በክብር በባህላዊ እስክታ፣ ሆታ ጭፈራ ተቀብሏል። የአቀባበሉ መንፈስ ደግሞ የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ የኢትዮጵያውያን የህብረት አብሮነት ፍላጎት ማሳያ ግልጽ መልዕክት ይመስለኛል።

ይህ የአብሮነት መንፈስ ደግሞ እነሆ የኢትዮጵያን ትንሳኤ መልክት ነው። ተስፋችን በሚሰራው ስራ ብን ብሎ ሲጠፋ “ኢትዮጵያ እንደሁ አትጠፋም!” የምንለውን አራቂ መንፈስ አስታውሶ ኢትዮጵያ በልጆቿ ህብረት እንደማትጠፋ በእውን ያሳየን መልዕክት ነው! የኦሮሞ ወጣቶች በጎ መንፈስና የጎጃም አማራው የአቀባበል ደስታ ፌሽታ ስነስርአትን ላስተዋለው የኢትዮጵያዊነት የህብረት አንድነቱን መንፈስ እንመሰክር ዘንድ ያስገድደናል። ይህ ግዙፍ መንፈስ ጣናን ከወረረውን እንቦጭ በላይ ስለ ከበበን ስለወረረን በጎ ተስፋ ሰጭ መንፈስ ይናገራል! ለአመታት ያንዣበብንን የመለያየት የመፈራረስ አደጋ ዛሬ በ200 በጎ አድራጊ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ወጣቶች የከሸፈን ያህል ተደስተናል። ብቻ “በጣና ኬኛ” ድንቅ ዘመቻ ነፍሴ ከፍ ያለ ደስታን አግኝታለች!
“ኢትዮጵያ ኬኛ፣ ጣና ኬኛ …!” ድንቅ መንፈስ!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓም

LEAVE A REPLY