በአዋሽ ሰባት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከ551 ሺህ ዶላር በላይ ሲያሸሹ የተያዙ ግለሰቦች በእስራት...

በአዋሽ ሰባት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከ551 ሺህ ዶላር በላይ ሲያሸሹ የተያዙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ባለፈው ነሐሴ ወር በአዋሽ ሰባት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከ551 ሺህ ዶላር በላይ ሲያሸሹ ተገኙ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ገንዘቡን በህገ-ወጥ መንገድ ሲያስተላልፉ በተያዙት በአቶ ሀበኔ አረብኑር ላይ የስምንት ዓመታት እስራትና የ100 ሺሕ ብር ቅጣት ሲወስን፤ በአቶ ሐመድ መሐመድ ላይም ተመሳሳይ የስምንት ዓመታት ጽኑ እስራት እንደተበየነባቸው የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። በህገ-ወጥ መንገድ ሊያሸሹት ነበር የተባለው 551,771 ዶላርም በቅርቡ ከኢትዮጵያ-ሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች እንዲውል ፍርድ ቤቱ ጨምሮ መወሰኑን መረጃው አመልክቷል።

የሶማሊ ክልል መንግስት አካል ነው የተባለው አቶ ሀበኔ አረብኑር ባለፈው ነሐሴ ወር 551771 ዶላርና ብር ከአዲስ አባባ ወደ ሶማሌ ክልል ሲያጓጓዝ አዋሽ ሰባት አካባቢ ባለ የጉምሩክ ኬላ መያዙ የተዘገበ ሲሆን ገንዘቡ ምናልባትም የህወሓት ባለስልጣናትና የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ ሳይሆን እንደማይቀር የተለያዩ ግምቶች ተሰጥተው ነበር።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የምንዛሬ(ዶላር) እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሄደ ሲሆን በቅርቡም ዶላርን ጨምሮ በሌሎች የውጭ ሀገር ገንዘቦች ላይ የምንዛሬ ማሻሻያ መደረጉ የሚታወስ ነው።

LEAVE A REPLY