የአቃቢ ህግ ሰበብ እስረኞችን ለአመታት… /ማህሌት ፋንታሁን/

የአቃቢ ህግ ሰበብ እስረኞችን ለአመታት… /ማህሌት ፋንታሁን/

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸውን በእስር ሆነው ከሚከታተሉት ውስጥ የአብዛኛዎቹ ጉዳያቸው ፍርድ እስኪያገኝ ሁለት እና ሶስት አመታት ይቆጠራሉ። ከዚህም የሚበልጥ ጊዜ የሚቆዩ አሉ። ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ( Solomon Kebede) “ከማእከላዊ እስከ ቂሊንጦ” በሚለው አዲስ መፅሃፉ ላይ እሱ በእስር ቤት በቆየባቸው 3ት አመታት ውስጥ አሱ በነበረበት ዞን (ዞን 3) ብቻ በሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ 2 ሰዎች ከሶስት አመት በላይ ቆይተው እንዲሁም 13 ሰዎች ደግሞ ከ2ዓመት ከ8 ወር በኋላ “ነፃ” መባላቸውን ይጠቅሳል። በተመሳሳይ ብዙ አመት በእስር ቆይተው “ነፃ” ሚባሉ እንዳሉ በተለያየ አጋጣሚ እንሰማለን። ይህን ያክል ጊዜ ቆይተው በፍርድ ወይም በብይን “ነፃ” ተብለው ከእስር ሲወጡ ብዙ ሁኔታዎች እንደሚቃወስባቸው መገመት ቀላል ነው።

የፍርድ ሂደትን ከሚያጓትቱ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለማሰማት የሚወስደው ጊዜ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሽብር የተከሰሱ ግለሰቦች በተደጋጋሚ ምሬታቸውን ያሰማሉ። አቃቤ ህግ ምስክሮቹን አቅርቦ ለማሰማት ከአመት በላይ ጊዜ ሊወስድ ይችላል።

“ምስክሮቻችንን ባስመዘገቡት አድራሻ አላገኘናቸውም ብርቱ ጥረት አድርገን በቀጣይ ቀጠሮ እናመጣለን”፣ “ምስክሮቹ መጥሪያ ደርሷቸው አልቀረቡም ስለዚህ ተለዋጭ ቀጠሮ ታስረው እንዲቀርቡ ይታዘዝልን”፣ “ምስክሮች አልቀረቡልንም ዛሬ የመጀመሪያ ቀጠሮ ስለሆነ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን እና እናቀርባለን”፣ “ምስክሮችን ለማምጣት የበጀት እጥረት ስላለብን ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን”፣ “ምስክሮችን ፈልገን ስላጣናቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠንና በደንብ እንፈልጋቸው”፣ “ምስክሮች ራቅ ያለ ቦታ ስላሉ ረዘም ያለ ቀጠሮ ይሰጠን እና መጥሪያ እናደርሳቸዋለን” እና ሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶችን ነው አቃቤ ህጎች በተደጋጋሚ የሚያቀርቡት። እነዚህ ምክንያቶች ተከሳሾቹን አያሳምኗቸውም፤ ይልቁንም እነሱን በሃሰት የከሰሰው አቃቤ ህግ እነሱን በእስር ለማቆየት እና የሃሰት ምስ ክሮችን ለማቅረብ ጊዜ ሊወስድባቸው እንደሆነ ነው ሚናገሩት። “እኛን ለማሰር ጊዜ አይፈጅባችሁም ምስክሮቻችሁን ለማምጣት ግን ሰበብ ተደረድራላችሁ”፣ “የእውነት ምስክሮቹ ቢኖሩ ፖሊስ አግኝቶ እንዲመሰክሩ ለማድረግ ቀላል ነበር”፣ “ምስክሮቹን አጣን የምትሉት እኛን ለማንገላታት እና ለማሰቃየት ነው”፣ “አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ኬት ነው ሚያመጣው? ወይስ አሰልጥኗቸው እስኪጨርስ ነው ተለዋጭ ቀጠሮ ሚጠይቀው?”፣ “እናንተ እቤታችሁ ከልጆቻችሁ እና ቤተሰቦቻችሁ ጋ ቁጭ ብላችሁ እኛን የኛ ስቃይ አይገባችሁም” እና መሰል በምሬት የተሞሉ አስተያየታቸውን ለፍርድ ቤቱ ያሰማሉ። ዳኞቹም በብዛት አቃቤ ህግ እና ፖሊስ የሚያቀርበውን ምክንያት በመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮዎች ሲሰጡ ይታያል። በተደጋጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ ከሰጡ በኋላ ነው ምስክር የማሰማት ሂደቱን የሚያቋርጡት።

ባሳለፍነው ሳምንት ግን አንድ ዳኛ በልዩነት ሃሳብም ቢሆን ጥሩ ነገር ሲናገር ሰምቼዋለው። በመዝገቡ አቃቤ ህግ 8 ምስክሮችን ቆጥሮ ነበር። ከ8ቱ ውስጥ 4ቱ ከዚህ ቀደም በነበሩ ቀጠሮዎች የተሰሙ ሲሆን በእለቱ ቀጠሮ ተይዞ የነበረው ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ነበር። ለምስክር ሲቀጠር ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ከቀሩት ምስክሮች ሶስቱ የፖሊስ አባል ናቸው። አቃቤ ህግ ምስክሮቹ ለስራ ወደ ሌላ ቦታ ስለሄዱ ማቅረብ እንዳልቻለ ገልፆ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል። አቃቤ ህግ ያቀረበው ሃሳብ አሳማኝ ነው ብለው ሁለቱ ዳኞች ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ የወሰኑ ሲሆን አንዱ ዳኛ ግን፤ ምስክሮችን ለማቅረብ በቂ ጊዜ ተሰጥቶ እንደነበረ፣ ምስክሮቹ የፖሊስ አባል ከመሆናቸው አንፃር በቀጠሯቸው ቀን መቅረብ እንደነበረባቸው፣ ተከሳሾች አቃቤ ህግ ሆን ብሎ ቀጠሮ እየጠየቀብን ነው የሚል አቤቱታ እያሰሙ ተደጋጋሚ ቀጠሮ መስጠት የተፋጠነ ፍትህ መስጠት እንደማይቻል ገልፆ ለሌላ ጊዜ አሰራራቸውን እንዲያስተካክሉ ለአቃቤ ህጎች ነግሯቸዋል። ሁሉም ዳኞች ቆራጥ አቋም ይዘው የአቃቤ ህግ የሚዘረዝራቸውን ሰበቦች (በስንፍናም ሆነ ሆን ብሎ) መቀበል ቢያቆሙ የታሰሩትን ሰዎች ስቃይ በጥቂቱም ቢሆን ይቀንሱላቸው ነበር።
[ምኞት አይከለከልም]

LEAVE A REPLY