ዳንኤል ብርሃኔ ባልተለመደ የትግርኛ ፅሁፉ /ያሬድ ጥበቡ/

ዳንኤል ብርሃኔ ባልተለመደ የትግርኛ ፅሁፉ /ያሬድ ጥበቡ/

ዳንኤል ብርሃኔ ባልተለመደ የትግርኛ ፅሁፉ “በድርጅት ታዝዤ ነው በሚል በትግራዋይ ንብረትና ህይወት መቀለድ አይቻልም ፣ በግለሰብ ደረጃ ተጠያቂነት የጎላበት ወቅት ላይ ነን፣ ይህን ሃላፊነት በግል መሸከም የማትችሉ የህወሓት መሪዎች ገለል በሉ፣ የሚችሉ ወደፊት ይምጡ ወይም አመራሩን ይጨብጡ” የሚል ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፏል ። ይህም የግል አስተያየቱ ብቻ ሳይሆን የመላ ተጋሩ ጥያቄ ነው እያለ ነው ። ከብዙዎችም ድጋፍ ያገኘ ይመስላል ። ለመሆኑ ዳንኤል ይህን ቀጭን ትእዛዝ ከየት አመጣው?

ከወር በፊት በድል ተጠናቀቀ የተባለው የወያኔ አመራር ስብሰባ እንደገና ተጠርቶ ከሳምንት በላይ በር ዘግቶ በተቀመጠበት ሁኔታ ዳንኤል ያስተላለፈው ትእዛዝ የራሱ ይሆን ወይስ በአመራሩ ውስጥ ያለውን ክፍፍልየሚጠቁም? ከዚህ ስብሰባ ወያኔ ሹም ሽር አድርጎ ሊወጣ እንደሚችል መገመት ይኖርብን ይመስለኛል። ማን ያሸንፍ ይሆን? ልዩነታቸውስ ምን ይሆን? መቼም በየክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉትን የትግራይ ተማሪዎች መመለስ ዋነኛው አጀንዳ ሊሆን አይችልም ። መብታቸውን በመጠየቅ ላይ ያሉትን የኦህዴድና ብአዴን መሪዎች ምን እናድርጋቸው ነው የወያኔ አመራር ስብሰባ ጭንቀትና ክፍፍል ሊሆን የሚችለው ። የደህንነትና መከላከያ አቅማችንን ተጠቅመን ፀጥ እናርጋቸው በሚል እብሪተኛ መስመርና፣ የዚህን አደጋ በሚያዩ መሃል ሊሆን ይችላል ዋነኛው አለመስማማት ። እነ ዳንኤልና እነ መሐሪ የትግራይ ተማሪዎች ተለቃቅመው ይምጡን ሲሞግቱም በራሱ አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ ሳይሆን፣ ብአዴንና ኦህዴድን ለመጨፍለቅ በሚወሰደው እርምጃ የትግራይ ተማሪዎች የጥቃት ኢላማ ሊደረጉ ይችላሉ ከሚል ፍርሃት ሊሆን ይችላል።

ለመሆኑ ኦህዴድና ብአዴን ወያኔ በመሃሉ ያለውን ክፍፍል ጨርሶ፣ ካራውን ስሎ እስኪመጣ ዝም ብለው እየጠበቁ ይሆን ወይስ ባህርዳር ላይ መክረዋል? ለእኔ እንደሚታየኝ፣ የአባዱላን የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈጉባኤነት ተጠቅመው፣ በምክርቤቱ ውስጥ ያላቸውን የድምፅ የበላይነት ይዘው፣ የወያኔን ምሽግ መስበር ይጠበቅባቸዋል ። አሁን የማመንቻው ወቅት አይደለም። በእንዲህ ያለ ወቅት እያንዳንዱ ሰአት ውድ ነው። ይህን አለመረዳት ደግሞ ውድ ዋጋ ያስከፍላል ። ዛሬ አባዱላ፣ ለማ፣ አቢይና ገዱ ማድረግ ያለባቸው፣ እጃቸው ላይ የወደቀው እድል ታሪካዊ መሆኑን ተረድተው፣ ሆኖም ትልቅ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ሊረዱ ይገባል ። ህይወታቸውን ሊሰጡለት መወሰን አለባቸው ። ለመግደል አላልኩም፣ ለመሞት መወሰን አለባቸው ። ያን ሲያደርጉ የፍትህ አምላክ አብሮአቸው ይቆማል፣ ብርታትም ይሰጣቸዋል ። አሁን የማወላወያ ሰአት አይደለም ። አሁን የመዝረክረኪያ ሰአት አይደለም። አሁን ወያኔን አስገድዶ፣ የህዝብን ጩኸት እንዲሰማ ወይም ተገዶ ከኢህአዴግ ራሱን እንዲያገል ተፅእኖ ማድረጊያ ወቅት ነው ። ይህ ሊደረግ እንደሚችል ብሩህነትና ጥንካሬ ያስፈልጋል ።

ፓርላማው ተሰብስቦ ስለተፈናቀሉት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኦሮሞዎች ጉዳይ አጣሪ ኮሚሽን ሊመሠርት ይችላል ። ከአብዲ ኢሌ ሚሊሺያ ጋር ተባብረው ወንጀል የፈፀሙት የመከላከያና ደህንነት ባለስልጣናት ጉዳይ እስኪጣራ የሁለቱ ተቋማት ቁንጮ መሪዎች ለጊዜው ከሥራቸው እንዲገለሉና፣ በምትካቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነትና የመከላከያውን ቺፍ ኦፍ ስታፍ አዲስ ጊዜያዊ ሹመኞችን እንዲያቀርቡ ፓርላማው መመሪያ መስጠት ይችላል ። ከዚያ በአፋጣኝ እነዚህ ሁለት ተቋማት የሃገሪቷን ብሄራዊ ተዋፅኦ በሚያንፀባርቅ መልኩ የአመራር እርከኑ መልሶ እንዲደራጅ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይችላል ። ደህንነቱና መከላከያው ከተስተካከሉ የፖለቲካ ሥርአቱ በረጅም ሰላማዊ ሰጥቶ መቀበል ሂደት፣ ሁሉን ወዳሳተፈ ሽግግር መረማመድ ይቻላል። ወያኔ ግን በመከላከያውና ደህንነቱ መዋቅር ላይ ያለው የበላይነት ሳይለወጥ፣ የፖለቲካ ጥገና ግቡን ይመታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል ። ቁርጠኝነት ያለው (ራሱን ለአላማው ለመሰዋት የተዘጋጀ) እና የጊዜን ጥቅም የተረዳ የሚያሸንፍበት የትግል መድረክ ላይ ነን ። አይዞን!

LEAVE A REPLY