አስቸኳይ አዋጁ በሌላ መልክ መጣ

አስቸኳይ አዋጁ በሌላ መልክ መጣ

በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የስርዓቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተካተቱበት የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በሀገሪቱ ላይ የተከሰቱ ችግሮችን ይፈታል የተባለ አዲስ እቅድ አወጣ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የክልል መሪዎች፣ የከተማ ከቲባዎች፣ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ሀይሎች፣ የመከላከያ ሰራዊት አዘዦች የተሳተፉበት የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ትናንት በዝግ ስብሰባ ካደረገ በሗላ ምክር ቤቱ አወጣው የተባለውን ለአንድ ዓመት የሚቆይ አዲስ እቅድ የወያኔው መከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈርጌሳ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት የጸጥታ ሃይሎች ከእንግዲህ የሚካሄዱ ህገ ወጥ ሰልፎችን ለማስቆም እንዲችሉ መመሪያ ተሰጥቷል ብለዋል። በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የወሰን አካባቢ በተነሳ ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችም ወደ ቦታቸው የመመለስ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል። የኦሮሚያና ሶማሌ ግጭቶችን ጨምሮ በተለያዩ ሰልፎች ለጠፋው ህይወትና ንብረት በህግ የሚጠየቁ አካላት እንደሚኖሩም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ያወጣውን አዲስ እቅድ የሀገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ የታለመ ነው ቢልም በተዘዋዋሪ ግን የዜጎችን የመቃወም፣ ሀሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት መብቶች የሚገድብ ነው ተብሏል። አዲሱ እቅድ በዝርዝር የተብራራ ባይሆንም ትናንት የመከላከያ ሚኒስትሩ በገለጹት መሰረት ባለፈው ዓመት ለአስር ወራት ተግባራዊ ተደርጎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚተካ ነው የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።

LEAVE A REPLY