የሐውልቶች ፖለቲካ-ማሳሰቢያ፡ ቁም ነገር ይበዛዋል /ኢያስፔድ ተስፋዩ/

የሐውልቶች ፖለቲካ-ማሳሰቢያ፡ ቁም ነገር ይበዛዋል /ኢያስፔድ ተስፋዩ/

እንዲህ እንደዛሬው ‹‹ይታየኛል›› ባይ ፈልቶ በየቴሌቪዥን መስኮቱ በየቤታችን ከመምጣታቸው በፊት ነው አሉ……በደርግ ጊዜ….. ወንጌላውያን ሲፀልዩ…አንዱ ከመካከላቸው ‹‹ስላሴዎች ታዩኝ›› ‹‹ስላሴዎች ታዩኝ›› እያለ ጩኸቱን ያቀልጠዋል……. እንደምንም ያረጋጉት እና… ‹‹ምንድነው የሚታይህ›› ይሉታል….

‹‹አይኔን ስጨፍን ሶስቱ ስላሴዎች ይታዩኛል››……

አንዱ ከመካከል ይጠይቃል ‹‹ምን ይመስላሉ?››

‹‹አንደኛው ፂማም ነው ነጭ ፀጉር አለው…..አንደኛው ራሰ በረሃ ነው…..›› ሲል ‹‹የራዕዩ›› ምንጭ የገባው አቋረጠውና

‹‹እንደሚታወቀው ወንድማችን ውሎው መስቀል አደባባይ አካባቢ ነው….እና እዛ የእነ ማርክስ ኢንግልስ እና ሌኒንን ሀውልት ሲያይ ውሎ ነው የቃዠው….››

1983 ዓ.ም እኛ ወደዚህች ምድር ለመግባት ስናሟሙቅ ‹‹ጀግናው›› የኢህአዴግ ሰራዊት አዲስ አበባ ገብቶ ነበር…… የአ.አ ወጣት ሆ ብሎ ወጥቶ መስቀል አደባባይ የሚገኘውን የእነ ማርክስን ሀውልት በማፍረስ ነበር የተቀበለው……. ይህ ከመንጌ ጥይት የተረፈ ወጣት ለምን ሀውልቱን እንዳፈረሰው ይቅርና የእነማንን ሀውልት እንዳፈረሰ ቢጠየቅ ራሱ መልሱን የሚያውቀው አይመስለኝም…….

ከጥቂት አመታት በኋላ ኦነግ ከተማ አንቀጥቅጥ ‹‹ሰላማዊ›› ሰልፍ በፊንፊኔ/አዲስአበባ ጠራ…… መፈክሩም ‹‹የምኒልክ ሀውልት ይፍረስልን›› የሚል ነበር…….

ከተመሰረተ በኋላ አንድ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ በየኔነህ አማርኛ እምጥ ይግባ ስምጥ ያልታወቀ ኢድህ የተሰኘ ፓርቲ ደግሞ በሳምንቱ ‹‹የምኒልክ ሀውልት በፍፁም አይፈርስም›› በሚል መፈክር አዲስ አበባን አንቀጠቀጣት……

ኢህአዴግ መሀል ቤት ፀቡን ስትገላግል ከቆየች በኋላ ሀውልቱ ይፍረስ ባዮችንም አይፈርስም ባዮችንም ‹‹አፈረሰቻቸው›› 😉

ሰሞኑን በምድረ አሜሪካ የኮንፌደሬት ሀውልት ይፍረስ እና አይፍረስ በሚሉት መካከል በተፈጠረ ግርግር በአሳዛኝ ሁኔታ የሰዎች ህይወት ጠፍቷል…….

የኮንፈደሬት ሀውልቶች የነጮችን የበላይነት ያነፀባርቃሉና ይፍረሱ በሚሉት እና የታሪካችን አንድ አካል ነውና መፍረስ የለባቸውም በሚሉት ….መካከል በሚፈጠረው ግርግር የሚጠፉት ነፍሶች ሀውልት ሳይገነባላቸው ያለ አስታዋሽ መቅረታቸው የክ/ዘመኑ ምፀት ነው፡፡

የሀውልቶች ፖለቲካ ለአንዳንዶች ከፍተኛ የገቢ ምንጭም ሆነዋል……. kirk savage, የሀውልቶች ጦርነት monument wars የሚል ባለ 408 ገፅ መፅሀፍ ፅፎ በብዙ ሺህ ኮፒ ተሸጦለታል……….

በቅርቡ ደግሞ ‹‹ራዕይ›› ለማየት ደከመኝ ሰለቸኝ የማያውቁት ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና እግዚአብሄር ‹‹ኢትዮጵያ እንዲህ ድሃ የሆነችው እና ችጋር ውስጥ የገባችው ለአፄ ሀይለስላሴ ሀውልት ባለመስራታችሁ ነው›› ብሎኛል ብለው ሳንወድ በግድ ሲያስቁን ሰንብተዋል……

እንዲህ በአቋራጭ ሀብታም ሀገር መሆን ከተቻለማ አይደለም በሀይለስላሴ ስም በነፍስ ወከፍ በእያንዳንዳችን ስም ሀውልት ቢሰራስ ምን ገዶን?!

የምኒልክ ሀውልትን የኦሮሞ ብሄርተኞች…. የአጼ ዩሀንስ ሀውልትን የወሎ ሙስሊሞች….. የአኖሌ ሀውልትን ‹‹የአንድነት›› አቀንቃኞች….. የአጼ ቴዎድሮስ ሀውልትን ጋሽ መስፍን እየተቃወሙት ከዘመን ዘመን እየተሸገርን አለን፡፡

monument / ሐውልት የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል መነሻ የሆነው ‘monere’ የሚለው የላቲን ቃል እንደወረደ ሲተረጎም ‹‹ማስጠንቀቂያ›› ማለት ነው……

ሀውልትን እንደ ማስጠንቀቂያ ብናየው የትኛውም ሀውልት ቢገነባ ችግር ያለው አይመስለኝም….. ሀውልቱ ሳይሆን ሰለ ሀውልቱ የሚኖረን ትርክት/narrative/ ነው ዋናው ጉዳይ…….. የአኖሌን ሀውልት ስታይ የአማራን ህዝብ እንደ ጥፋተኛ የምታይ ከሆነ ችግሩ ያለው የአንተ ትርክት ላይ እንጂ ሀውልቱ ላይ አይደለም……ምክንያቱም ሀውልቱን አይተው በወቅቱ የነበረውን አስከፊ ንጉሳዊ ስርዓት እንጂ ሌላ ነገር የማይታያቸው አሉ እና!

የምኒልክን ሀውልት ስታይ የአኖሌ ጭፍጨፋ ብቻ የሚታይህ ከሆነ አሁንም ችግሩ ያለው ሀውልቱ ላይ ሳይሆን የአንተ ትርክት ላይ ነው…… ምክንያቱም የምኒልክን ሀውልት ሲያዩ የአድዋ ድል የሚታያቸው አሉ እና!

የቀይ ሽብር ለነጭ ሽብር የተሰጠ ምላሽ ነው የሚለውን ነጭ ውሸት አምኖ የተቀበለ ሰው እንኳን የራሱን ትርክት እንደያዘ ራሱን ከቀይ ሽብር ሀውልት ጋር አስማምቶ መኖር የሚችል ይመስለኛል…….

ሀውልት እንደ ማስጠንቀቂያ ከታየ መደገም የሌለበት እንዳይደገም….. መደጋገም ያለበት ደግሞ ተደጋግሞ ይዘከር ከሚል ያለፈ ትርጉም የሚኖረው አይመስለኝም……

LEAVE A REPLY