የግራ ዳኛው በወልቃይት ጉዳይ አቋም የያዙ ሰው በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ትግሬ በመሆናቸው...

የግራ ዳኛው በወልቃይት ጉዳይ አቋም የያዙ ሰው በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ትግሬ በመሆናቸው እንዲዳኙኝ አልፈልግም /የወልቃይት ጉዳይ ኮሚቴዎች/

/ማህሌት ፋንታሁን/

የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን በከፍተኛ ፍርድቤት 4ኛ ችሎት እየተከታተሉ የሚገኙ የወልቃይት ጉዳይ ኮሚቴዎች እና በሌላ መዝገብ የሚገኙ ተከሳሾች የግራ ዳኛው አቶ ዘርአይ ወ/ሰንበት እንዲነሱ ወይም እንዳይዳኟቸው በዛሬው ችሎት ጥያቄ አቅርበዋል።

ዛሬ ከቀኑ 5ሰአት ላይ (የመሃል ዳኛው አቶ ዮሐንስ ጌሲያ ዳኛ ጎድሎባቸው ሚሰየምላቸው ሲጠብቁ መዘግየታቸውን በመናገር ይቅርታ ጠይቀዋል) ችሎቱ እንደጀመረ በእነ መብራቱ ጌታሁን በሚባል መዝገብ ያሉ የወልቃይት ኮሚቴ አባል አቶ አታላይ ዛፉ ሃሳብ እንዳላቸው ለዳኞች ካሳወቁ በኋላ ፤ “ዳኛ አቶ ዘርአይ እንዲዳኘን አንፈልግም። እሳቸው በወልቃይት ጉዳይ በማህበራዊ ሚዲያ ፅሁፋቸው ተሰራጭቷል እንዲሁም በቴሌቭዢን አቋማቸውን ሲያሳውቁ ነበር። ወልቃይት በምንም ሁኔታ የአማራ አይደለም የሚል ነው አቋማቸው። እኛ ደግሞ የታሰርነው በወልቃይት የአማራ ማንነት ጉዳይ ነው። ስለዚህ ሊዳኙን አይገባም” ሲሉ ያላቸውን ተቃውሞ አቅርበዋል።

2ኛ ተከሳሽ አቶ አታላይ ተቃውሟቸውን እያቀረቡ እያለ ዳኛ አቶ ዘርአይ ወልደሰንበት “ክሳችሁ ሽብር ነው የወልቃይት ጉዳይ የሚለው የሚታይ ይሆናል” ብለዋል።

በሌላ መዝገብም በችሎቱ በዛሬው እለት ቀጠሮ ኖሯቸው በችሎቱ የተገኙ ተከሳሾች መዝገባቸው እየታየ ባይሆንም ሁሉም ተነስተው አቶ አታላይ ባቀረቡት ሃሳብ እንደሚስማሙ እና ጥያቄያቸው የነሱም ጥያቄ እንደሆነ ገልፀዋል። ተከሳሾቹ እንዲቀመጡ እና መዝገባቸው መታየት ሲጀምር እነሱም ጥያቄያቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ የማህሉ ዳኛ አቶ ዮሐንስ ከነገሯቸው በኋላ ከነ መብራቱ ጌታሁን ውጪ ያሉ ተከሳሾች መዝገባቸው እስኪጠራ ቁጭ ብለዋል።

ሌላ ተመሳሳይ የግራ ዳኛ (አቶ ዘርአይ ወ/ሰንበት) ይነሳልን ጥያቄ ያነሱት እነ ክንዱ ዱቤ ናቸው። በመዝገቡ 1ኛ ተከሳሽ የሆነው ክንዱ የግራ ዳኛው በወልቃይት ጉዳይ አቋም የያዙ ሰው በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ትግሬ በመሆናቸው እንዲዳኙኝ አልፈልግም ብሏል። ለዚህም ምክንያቱን ሲያስረዳ “እኛ ማእከላዊ ከ5ት ወር በላይ ስንቆይ በማንነታችን እየተሳለቁ ሲደበድቡን እና ሲያሰቃዩን የነበሩት ሁሉም ከአንድ ብሄር ናቸው። ትግሬዎች ነበሩ። ስለዚህ ጥላቻ ሳይሆን ትክክለኛ ፍርድ ይሰጡኛል ብዬ አላምንም። ይህ የግል አቋሜ ነው። እናንተ የፈለጋቹትን ልትሉ ትችላላችሁ። ያቀረብኩትን ምክንያት ላትቀበሉት ትችላላችሁ። እኔ ግን የማምንበት ጉዳይ ነው።”

በተመሳሳይ መዝገብ 2ኛ ተከሳሽ የሆነው ዘመነ ጌቴም “የኔ ምክንያት ክንዱ ካቀረበው ይለያል። ያ የግል አመለካከቱ ነው። እኔ ግን ዳኛው በወልቃይት ጉዳይ ላይ የህውሃትን አቋም ይዘው ሲናገሩ ስለሰማኋቸው እኛን የከሰሰን ደግሞ ህውሃት ስለሆነ (ዳኛ ዘርአይ ‘የከሰሳችሁ ህውሃት ነው?’ የሚል ጥያቄ አቅርበውለት አዎ ብሎ መልሷል።) ፍርዳችን ላይ የፖለቲካ ወገንተኝነት ሊኖር ስለሚችል እንዲዳኘን አልፈልግም።”

የገረመኝ ነገር ――――
በሌሎች 2ት መዝገቦች ላይም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበው ከጠበቃዎቻቸው ጋር ተማክረው በፅሁፍ እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። በእነ ክንዱ ዱቤ መዝገብ የመቃወሚያ ብይን ለመስራት ከሰኔ 2009 ጀምሮ እየተቀጠሩ መሆኑን እና እንደዘገየባቸው ተናግረዋል ሆኖም እነ ክንዱ ዱቤም ሆነ በሌሎች መዝገቦች የሚገኙ ተከሳሾች ከክሳቸው ጋር የተያያዘውን ጉዳይ ዳኛ ይቀየር የሚለው ጥያቄ እልባት ሳያገኝ እንደማይሰራ ተነግሯቸዋል።
ዘረዳኛ ይቀየርልን የሚል ጥያቄ ካቀረቡት ውስጥ አንድ ተከሳሽ ብቻ ያለበት መዝገብ ታይቶ ነበር። ጌታሁን አቧሃይ ይባላል ተከሳሹ። ዛሬ ተቀጥሮ የነበረው የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ነበር። 2ት ምስክሮች ቀርበው የነበረ ቢሆንም ዳኛ ይቀየርልን የሚለው ጥያቄ ብይን ሳያገኝ መመስከር እንደማይችሉ ገልፀው፤ ጥያቄው በፅሁፍ እንዲገባ ቀጠሮ በተሰጠበት ቀን (18–3–2010) ተመልሰው እንዲቀርቡ ነግረዋቸዋል ዳኛ ዘርአይ ወ/ሰንበት። የዳኛ ይቀየር ጥያቄ በ18 ገብቶ የዛኑ እለት ውሳኔው ተሰጥቶ የዛኑ እለት እንዴት ምስክር ሊሰማ ይችላል? ወይስ ውሳኔውን አውቆታል ማለት ነው? እያልኩ እያሰብኩ አቃቤ ህግ “ለ18 በተሰጠው ቀጠሮ ላይሰሙ ስለሚችሉ ሌላ ቀጠሮ ቢሰጥልን” ሲል ጠይቋል። ዳኛ ዘርአይም ከሌሎቹ ዳኞች ከተነጋገረ በኋላ፤ ምስክሮቹን የሚመሰክሩበትን ቀን መጥሪያ በአቃቤ ህግ እንደሚደርሳቸው ነግሮ ለዛሬ አሰናብቷቸዋል።

LEAVE A REPLY