በመቱ ዩኒቨርሲቲ ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች ግቢውን ለቆው እየወጡ ነው ተባለ

በመቱ ዩኒቨርሲቲ ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች ግቢውን ለቆው እየወጡ ነው ተባለ

 /ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ በመቱ ዩኒቨርስቲ ለወራት በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ትምርህርት አለመጀመሩንና ተማሪዎችም የዩኒቨርስቲው ለቀው እየወጡ ነው ተባለ።

“እስካሁን ትምህርት አልጀመርንም፣ በአስተዳደሩ በደል እየደረሰብን ነው፣ የማናጅመንት ችግር አለ፣ በተደጋጋሚ ተሰብስበን ተወያይተን ችግሮቻችን ዩኒቨርስቲው ሊፈታልን አልቻለም” በማለት ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች ግቢውን ለቆው ለመውጣት እንደተገደዱ ተናግረዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች፣የኦሮሚያና የአማራ ክልል ባለስጣናት፣ የፌዴራል መንግስቱ አካላትና ኦሮሚያ ፖሊስ ጋር ዛሬ ውይይት ቢደረግም የተማሪዎች የጸጥታ ችግሮች ምላሽ ባለማግኘታቸው ተማሪዎቹ ግቢውን ለቀው ለመውጣት እንደወሰኑ ከተማሪዎች ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።እንደ ተማሪዎቹ ገለጻ፤ ከማንም ጋር የብሄር ግጭት እንደሌለባቸውና ከኦሮሞ ተማሪዎች ጋሪም የሻከረ ግንኙነት እንደሌለባቸው ገልጸዋል። የአማራ ተማሪዎች ከዚህ ውሳኔ ላይ ሲደርሱ የኦሮሞ ተማሪች የአማራ ወንድሞቻቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው እንዳይሄዱ ለማግባባት እንደሞከሩና የአማራ ተማሪዎች የመልቀቅ ውሳኔያቸውን እንደማይቀይሩ ሲረዱ የኦሮሞ ተማሪዎች እስከ መናኸሪያ እንደሸኟቸውም ጨምረው ገልጸዋል።

የዩንቨርስቲ አስተዳደር ዉስጥ ያለው አስተዳደራዊ ችግር ካልተፈታ ትምህርት መቀጠል ስለማይቻል ከዚህ በላይ እዚህ መቆየት ጊዜ ማባከንና ድሀ ቤተሶቦቻችን ማስቸገር ነው በማለት ወደየ ቤተሶቦቻቸው ለመመለስ እንደተገደዱ ገልጸዋል። የተማሪዎቹ ቁጥርም እስከ ሁለት ሺ እንደሚደርስ ታዉቋል። የዞኑ የሀገር ሽማግሌዎች፣የወረዳው አስተዳደር ከቄሮዎች ጋር በመሆን ተማሪዎቹን አግባብቶ በዩኒቨርሲቲው ግቢው ለማቆየት አሁንም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ታውቋል።

መቱ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮውን የትምህርት ዘመን በከፍተኛ የጸጥታ ችግር የጀመረ ሲሆን እስካሁን መደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት አለመጀመሩ ይታወቃል። ከዚህ ቀደምም የትግራይና የሶማሌ ክልል ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወጥተዋል። ከ120 በላይ የሚሆኑ ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪዎች ወደ ጋምቤላ ክልል በማምራት በፌዴራል መንግስቱ ድጋፍ እየተደረገላቸው በጋምቤላ ከተማ እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።

LEAVE A REPLY