ብአዴን “እሹሩሩ”፣ /መሐመድ አሊ መሐመድ – የቀድሞ ፓርላማ አባል/

ብአዴን “እሹሩሩ”፣ /መሐመድ አሊ መሐመድ – የቀድሞ ፓርላማ አባል/

“የማያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ … ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው …” የሚለውን ዜማ ሁሌም በተመስጦ ነው የምሰማው፡፡ አዎ፣ ለዚያ አስቸጋሪ ወቅት፣ ለዚያ እልህ አስጨራሽ የትግል ሂደት፣ ከፍተኛ ሰብኣዊ እልቂትና የሀገር ሀብት ውድመትን ላስከተለው ለዚያ የተራዘመ ጦርነት በግሌ እውቅና እሰጣለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በዚያ ላይ መቆዘም የኔ ድርሻ አይመስለኝም፡፡ ከኔ ይልቅ ጉዳዩን ለነ YaredTibebu ብተወው ያምራል፡፡

ሆኖም ግን አማራጮች ሁሉ በተሟጠጡበት በዚያ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት “በተሸነፈ መንፈስና” በአንዳች ቀቢፀ-ተስፋ ጥቂት የቀድሞ ኢህአፓ አባላት ያደረጉት ጉዞ ትኩረት የሚነሳው አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያን አንድነት ሲያቀነቅን የቆዬ ድርጅት አባላት ቀን ጨልሞባቸው “የትግራይ ነፃ ሪብሊክ ማቋቋም”ን ዓላማው አድርጎ በረሃ የወረደ፣ በወቅቱ አገላለፅ (ገንጣይ አስገንጣይ) የሚባል ኃይል መጠጋታቸው የበለጠ ትኩረት ይስባል፡፡ በተለይ ደግሞ “አማራውን” በገዥ መደብነት በመፈረጅ ቁጥር አንድ ጠላት አድርጎ የታገለ ኃይል ጋር ግንባር ፈጥሮ ሲያበቃ “የአማራው ወኪል ነኝ” ማለቱ ይበልጥ አነጋጋሪ ነው፡፡

በርግጥ የቀድሞው ኢህዴን/የአሁኑ “ብአዴን” አባላት የአማራው ጉዳይ አሳስቧቸው፣ ጭቆናና በደሉ አንገብግቧቸው የአማራው “ብሶት የወለዳቸው” ናቸው? ወይስ የአማራው ገዥ መደብ የፈጠረው “ብሶት የወለዳቸው” ፀረ-አማራ “ትክሎች” ናቸው? ለመሆኑ የድርጅቱ አንጋፋ መሪዎችስ ከአማራው አብራክ የወጡና የአማራው ሥነ-ልቦናዊ መሠረት ያላቸው ናቸው? ይህን ለውይይት ክፍት ማድረጉ የሚቀል መሰለኝ፡፡

እኔ እንደሚመስለኝ ግን፣ ወያኔ/ኢህአዴግ ደርግን አሸንፎ አገር ከተቆጣጠረ በኋላ ኢህዴን ወደ “ብአዴን” የተቀየረው በወቅቱ በነፕ/ር አስራት ወልደየስ የተፈጠረውን የመዐህድ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለማክሸፍ ነበር፡፡ አማራው እንደማህበረሰብ ለህልውናው፣ ለመብቱና ለጥቅሞቹ መረጋገጥ የጀመረውን እንቅስቃሴ መግታት የሚቻለው በሥሙ የሚጠራ “ብአዴን” የተሰኘ “ፀረ-አማራ” አቋምና ተልዕኮ ያለው የህወሓት አሻንጉሊት በመፍጠር ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህ ባለፈም የአማራውን “አከርካሪ” በመስበር ረገድ “ብአዴን” የህወሓት መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል ማለት ይቻላል፡፡ የአማራው አገራዊ አስተሳሰብና ከጠባብ ብሔርተኝነት ወጣ ያለ እይታው እንደ “ትምክህት” ተቆጥሮ በተኮነነበት፣ በተወገዘበት፣ ከየአቅጣጫው ጥቃት በተሰነዘረበት፣ ሁሉም በየፊናው አንገቱን ለማስደፋት በተረባረበበት፣ አንድም አይበጅም ባይ በጠፋበት “በዚያ ክፉ ዘመን” ብአዴን አባሪ/ተባባሪ እንጅ ጠያቂ/ተቃዋሚ ሆኖ አያውቅም፡፡ አማራው ወልዶ/ተዋልዶ፣ ሀብት/ንብረት አፍርቶ፣ አገሬ/ቀዬዬ ነው ብሎ ከሚያምንበት መኖሪያውና ከአካባቢው በግፍ ሲፈናቀልና ሲሳደድ “ብአዴን” አይቶ እንዳላዬ ዝም ብሏል፡፡ ለሀገር አንድነት፣ ለዳር ድንበር፣ ለሉኣላዊነትና ለነፃነት አጥንትን መከስከስና ደምን ማፍሰስ የሀገር/ታሪካዊ ውለታ መሆኑ ቀርቶ “በነፍጠኝነት” ሲያስፈርጅ “ብአዴን” ይህንኑ ተቀብሎ አስተጋብቷል፡፡ ለአያት/ቅድመ-አያቶቻችን ዘመን ተሻጋሪ የነፃነት ትግልና የአርበኝነት ተጋድሎ ዕውቅና ከመስጠት ይልቅ እንደዋዛ ተሳልቋል፡፡

በአጠቃላይ በአማራው ላይ ለደረሱት ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሥነ-ልቦናዊ በደሎች ሁሉ ከህወሓት ባላነሰ “ብአዴን”ም እኩል ተጠያቂ ነው፡፡ ሰዎች በሰላም ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ታፍነው ወደማሰቃያ ማዕከላት እየተወሰዱ “አማራ” መሆናቸው እንደጥፋት እየተነገራቸው ጥፍራቸው በጉጠት እንደሚነቀል፣ ብልታቸው ላይ በውሀ የተሞላ ሃይላንድ እንደሚንጠለጠልና ሌሎችም ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠሉ ግፎች እንደሚፈፀሙ በፍርድ ችሎቶች ፊት ሳይቀር እየተነገሩ ነው፡፡ ለመሆኑ “ብአዴን” የአማራው መኪል ነኝ ካለ በአማራው ላይ ይህ ሁሉ ግፍና ሰቆቃ ሲፈጠር እንዴት ትንፍሽ አይልም? በሰሞኑ “የእርቅ ኮንፈረንስ” ላይስ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ተነስተው ይሆን?

በርግጥ “ብአዴን” ውስጥ ይህን ሁሉ ነገር እየሰሙ የሚብከነከኑ እውነተኛ የአማራ ልጆች እንዳሉ ይነገራል፡፡ እኔ በነሱ ቦታ ሆኜ ሳስበው፣

“መስሎ ለመኖር ስል – “ተራማጅ” ነኝ ብዬ፣
ህዝቤን አስበላሁት – እኖራለሁ ብዬ”

በሚል በፀፀት የሚገረፉ እንዳሉ አናጣውም፡፡ ለዚህም ይመስላል የህወሓት አክቲቪስቶች “አጉል እንቡር እንቡር ማለት ጀምሯል” ሲሉ የሚሳለቁት፡፡

እንግዲህ በዚህ መሐል ነው በነለማ መገርሳ የሚመራው “ኦህዴድ” ድንገት እመር ብሎ በመነሳት “ብአዴን”ን እጁን ጎትቶ ሊያስነሳው የሚታገለው፡፡ በሌላ በኩል “ወፌ ቆመች” እያለ ያሳደገው ህወሓት “ብአዴን” ከእንቅልፉ እንዳይነሳ “እሹሩሩ” እያለው ነው፡፡ ህዝቡም “ኧረ ባክህ ንቃ፣ እንቅልፍህ ይብቃ” በሚል “የዝምታ ጩኸቱን” ያስተጋባል፡፡ ሁሉም በየፊናው፣
“እሹሩሩ ማሙሽ እሹሩሩ፣
እሹሩሩ “ብአዴን” እሹሩሩ”
እያለ ነው፡፡ “ብአዴን” ግን ኦህዴድ እንደጀመረው ተስፋ ሳይቆርጥ ጎትቶ ያስነሳው ይሆን? ወይስ የህዝቡን ጩኸት ሰምቶ ይነቃ ይሆን? ወይስ ህወሓት እንደዋዛ እያሻሸ ያስተኛው ይሆን?

ድርጅቱ ተመሠረተ የተባለበትን 37ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የጫጫርኩት መሆኑ ነው፡፡

LEAVE A REPLY