አረረችን ያዬ በሳት አይቀልድም! /አገሬ አዲስ/

አረረችን ያዬ በሳት አይቀልድም! /አገሬ አዲስ/

ትምህርት ወይም እውቀት ከመደበኛ ትምህርት ቤት ብቻ  የሚገኝ  አይደለም።ለእውቀት የተለዬ ቦታ የለውም። በቅርብ ከሚዳስሱት፣ ከሚቀምሱት፣ ከሚያሸቱትና በሩቁ ከሚያዩትና፣ከሚሰሙት፣ የተፈጥሮ አካል ሁሉ እውቀት ይመነጫል። ሌላው ከደረሰበት ተመክሮና የምርምር ውጤት ትምህርት ይቀሰማል። በዕድሜ ጀልባ እየቀዘፉ በሚያልፉበት የተፈጥሮ  ውቅያኖስ የሚገበዩት ተመክሮና እውቀት ጥልቅና ሰፊ  ነው።ለዚያም ነው ዕድሜ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው የሚባለው። በዕድሜ የሚገኘው  ትምህርት በዲፕሎማና በዲግሪ የሚወሰን የዕውቀት ደረጃ የለውም፤ ምህዳሩ የሰፋና ጥልቀት ያለው በመሆኑ በሚዛን አይለካም፤ ወይም በቁና አይሰፈርም።ዕውቀት መጀመሪያና መጨረሻ የጊዜ ገደብ የለውም፤በእያንዳንዷ ደቂቃ በሚከሰተው ክስተት እውቀት ይገበያል።

በዕድሜና በተመክሮ የሚገኘው ዕውቀት ለመደበኛው ትምህርት መሰረት ነው።በጊዜ  ጎተራ የተጠራቀመው የሰው ልጆች ታሪክ፣ተመክሮና የምርምር ውጤት በተግባር ተፈትኖ የወጣ በመሆኑ ከስህተት የማዳን ሃይሉና አስተማማኝነቱ ከፍተኛ ነው።ለክፉም ሆነ ለደጉ እራስም ሆነ ሌሎች ያለፉበትንና የደረሱበትን ማስተዋሉ ከብዙ ስህተትና አደጋ ያድናል።መልካምም ውጤት ያለው ከሆነ ተቀብሎ በማሳደግ የዕውቀት ምህዳሩ እንዲሰፋ በማድረግ ለተሻለ ኑሮና ያስተሳሰብ ደረጃ ያበቃል።የዛሬው ትውልድ በትናንቱ ትውልድ ህሴት ላይ ካላረፈ ስር የሌለው ዛፍ ይሆንና ይመነምናል፤ደርቆም ገለባ ሆኖ በንፋስ ይበታተናል፤ በቋያ እሳትም አመድ ይሆናል። የዘንድሮው ከአምናው፣የአምናው ከሃቻምናው፣ የዛሬው ከትናንቱ፣የትናንቱ ከዚያ በፊት ከነበረው ቀን፣ የነገው ከዛሬ፣የወደፊቱ ከአሁኑ እየተቀባበለ፣ አንዱ ለሌላው መስተዋትና መነሻ እርከኑ እየሆነው የማደግ ወይም የመቀጨጭ ባህሪ እያሳዬ የመሄድ ጸባይ ይኖረዋል እንጂ የነበረውን ቀብሮ ከአዲስ አይጀምርም።ለመቀጨጩ ወይም ለማደጉ ማነጣጠሪያው ሚዛኑ የነበረው፣ያለበትና የሚደርስበት ቦታ  ወይም  ደረጃ ነው።ጉዳትና ጥቅሙ የሚለካው በነበረውና  በሚደርስበት ውጤት፣ትርፍና ኪሳራ ይሆናል።ስለሆነም ለአዲስ አስተሳሰብም ሆነ ለትውልዱ እድገት የትናንቱ ትውልድ ባለውለታ ነው።

የአንድን ነገር ጥቅምና ጉዳቱን ለማወቅ የሚረዳው መሳሪያ በአካባቢና በሩቁ ቦታ የተደረገውን፣ባለፈው ጊዜ የሆነውንና በገሃድ የሚታይና የሚሰማውን የሚሰበሰበው መረጃ  ነው።የመጥፎ ወይም መልካም ውጤት መረጃና ግንዛቤ ለወደፊቱ ጉዞ አቅጣጫ መሪ(ኮምፓስ)ይሆናል።መልካሙን ጠብቆና ተንከባክቦ ለመጓዝ፣ጥፋትም ካለ ተመሳሳይ ጥፋት ውስጥ ላለመግባትና አደጋ ላይ ላለመውደቅ የማስጠንቀቂያ ደወል ከመሆኑም በላይ በግልም ሆነ በቡድን ወይም በአገርና በህብረተሰብ ላይ  ሊደርስ ከሚችለው አስከፊ ውጤት፣ከጥፋትና አደጋ ለመራቅ ይረዳል።የመልካም ስራ ውጤት ተመክሮም በግልም ሆነ ማህበራዊ ኑሮ  መልካሙ ገጽ እንዲጎለብት ያግዛል።

በርእሱ ላይ  የተቀመጠው አባባል እንደሚጠቁመው ከሆነ በእሳት ስትጫወት ተቃጥላ፣ተንጨርጭራ  የሞተች መኖሯንና በእሳት መጫወት አደገኛ መሆኑን  ያመላክታል። መጠሪያ  ስሟ በደረሰባት ቃጠሎ ተተከቶ« አረረች» በሚለው ተቀይሮ  እንደ እሷ ላለመቃጠል በእሳት መጫወት አደገኛ መሆኑን የሚያስረዳ መካሪና  አስተማሪ አባባል  ሆኗል።አዎ!እሳት በሩቁ ሲያዩት ደስ ይላል፤ጠጋ ሲሉት ሙቀት ይሰጣል፤ግን ጭራሽ ልቀፍህ ካሉትና ከወደዱት ደግሞ ያቃጥላል፤ለሞት ይዳርጋል።ስልጣንም ከሩቁ ያጓጓል፣ሲጠጉትና ሲይዙት ደስ ይላል፣ካፈቀሩትና የሙጥኝ ካሉትም ይጎዳል፤ እሳት ነው፤አያያዙን ካላወቁበት ያቃጥላል፣አንጨርጭሮ ይገላል።አገርና ሕዝብ ይጎዳል።

አትዮጵያ አገራችን አሁን ለደረሰችበት ደረጃ፣ ሕዝቧንም  ለገጠመው መልካምም ይሁን መጥፎ ዕድል መፈተሻ ሊሆነን የሚችለው  በህይወት ያለነው ያለፍንበትን የታሪክ ጎዳና በቅጡ ስንመረምረውና ስንፈትሸው ነው።የረጅሙ ዘመን ታሪካችን ለብዙ የሚያኮሩ ውጤቶች  ባለቤት እንዳደረገን ሁሉ ለብዙ ድክመቶችም እንደዳረገን አይካድም። የሩቁን ሳይሆን የቅርቡን ዘወር ብለን ብንመረምረው በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ስህተቶች ከደረሱት ብዙ ትምህርቶችን ለመቅሰምና ታርመን ካለንበትና ሊገጥመን ከሚችለው ቀውስ እራሳችንንና አገራችንን ለማዳን እንችላለን።ለዚያ ዕድል ልንበቃ የምንችለው ቀና ልብ ይዘን በእውነት እራሳችንን ለመፈተሽ ቆርጠን ስንነሳ ብቻ ነው።በትናንትናው የክህደትና የፍርሃት  አዙሪት የምንሽከረከር ከሆነ፣በትናንትናው ነጋሪትና ጡሩምባ ቅኝት ዳንኪራ የምንረግጥ ከሆነ የወደፊቱ ውጤታችን እንደዛሬው አሳፋሪና ጸጸት የተመላበት ይሆናል።

የዛሬ አርባ አራት ዓመት አገራችን በሕዝባዊ ተቃውሞ ሞገድ ስትናጥ፣ሕዝቡ በየአቅጣጫው የለውጥ ጥሪ ሲያሰማ፤የወታደሩ ቡድን ድምጹን ቀምቶ ስልጣኑን በጨበጠበት ወቅት በሚያሰማው የለውጥ አብሳሪ  ሙዚቃና ፉከራ ተታሎ ደጋፊ የሆነው፣መንግስቱ ሃ/ማርያም የተባለውን ጨካኝና አረመኔ እያቆላመጠ «ከመንጌ ጋር ወደፊት!» እያለ ጉሮ ወሸባዬ! ይል የነበረው፣  በቃል መደገፍም ብቻ ሳይሆን ለነጻነትና ለዲሞክራሲ የቆመውን ሕዝብ በተለይም ወጣቱን ከደርግ ጎን ተሰልፎ የጨፈጨፈ የቀበሌ ሹም፣አብዮት ጠባቂና ካድሬ በመሆን የሃጥያቱ ተካፋይ የነበረው ቁጥሩ ቀላል አልነበረም። ያንን ተገንና መከታ አድርጎም ነበር የወታደሩ አምባገነን ቡድን ሲረሽን ሲያስር፣ሲያሳድድ ለ17 ዓመታት ስልጣን ላይ ለመቆዬት የቻለው።ካለፈው የሕዝብ ትግል ያልተማረው ወታደራዊ አምባ ገነን ቡድንና ደጋፊዎቹ  ስልጣን ስላወራቸው በእብሪት ሲጀነኑ የግፍ ጽዋው መሙላትና መፍሰሱ አይቀርምና የሕዝቡ አልገዛም ባይነት የያደገ በመሄዱ ከስልጣን ተወግደው በሰፈሩት  ቁና ተሰፈሩ። የሞቱት ሞተው፣ያመለጡትም አምልጠው ለመያዝ የበቁት ግፍ ፈጻሚዎች የሚቃወማቸውን አስረው ያሰቃዩ በነበረበት እስር ቤት ተወረወሩና የእስር ቤቱን ስቃይ ቀመሱት። ጥቂቶቹም ” ከመንጌ ጋር ወደፊት!” የሚል መፈክር ያወርዱ የነበሩት   ዋናው አረመኔ መንግስቱ ሃ/ማርያም አገር ጥሎ ሲፈረጥጥ አብረውት ፈረጠጡና  ያሳደዱት ስደተኛ የሚኖረውን የስደት ኑሮ ለመጋፈጥ ተረኞች ሆኑ።

የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት በወታደራዊው አምባ ገነን ቦታ ላይ የተቀመጠው ተረኛው የጎሳ አምባገነን ደግሞ ከጣለው ወታደራዊ አምባገነን ትምህርት ሳይቀስም በባሰ ዝግጅትና ብዙ ዘርፍ የሕዝቡን መብት ከመርገጡም አልፎ አገሪቱ እንደ አገር እንዳትቀጥል ስልቶች አውጥቶ በማፈራረስ ላይ ተሰማራ።በዚህም አገር አፍራሽ ዘመቻ ላይ ተባባሪ የሆነው ቁጥሩ ቀላል አይደለም።በጎሳ ነጻነትና እኩልነት ስም አንዱን ጎሳ ከሌላው እየነጠለ ከዃላው በማሰለፍ እርስ በርሱ እንዲጋጭና የብዙ ንጹሃን ዜጎች ደም በከንቱ እንዲፈስ  አድርጎል።ለገንዘብና ለጥቅም ያደሩ ሆዳሞችን በሚፈልጉት መንገድ እየሳበ አጃቢና አጨብጫቢው አድርጓቸዋል።በልማት ስም ነዋሪውን ሕዝብ እያፈናቀለ ያገሪቱን ለም መሬት ለባዕዳን እየሸጠ ድጋፍና ገንዘብ መሰብሰቢያ አድርጎታል።ተቃዋሚውን እየጨፈጨፈ፣እያሰረና እያሳደደ ካለፈው ስርዓት በባሰ መልክና ደረጃ ወንጀል በመፈጸም ላይ ነው።አሁንም እንደ ደርጉ ዘመን  ወንጀል የሚፈጽሙና ይህንን ሁሉ ግፍና በደል እያዩና እየሰሙ ስርዓቱን የሚደግፉ አሉ፤ካለፈው ስርዓት ደጋፊዎች ውድቀት ትምህርት አልቀሰሙም።« ከአረረች» መንጨርጨር አልተማሩም።ምናልባትም  የልብ ልብ የሰጣቸው ሲወድቅ ተሰደን እንኖራለን የሚል ምኞት ስላላቸው ይሆናል ። እድል ገጥሟቸው የሚሰደዱ ቢኖሩ ከደርግ ደጋፊዎች ከነበሩት ስደተኞች ለየት የሚያደርጋቸው በባዶ እጃቸው የሚሰደዱ አለመሆናቸው ብቻ ነው።የዝርፊያው ተባሪዎች በመሆናቸው በውጭ አገር በራሳቸው ወይም በዘመድ አዝማድ ስም ያስቀመጡት ገንዘብ ሳይኖራቸው አይቀርም።ማወቅ የሚኖርባቸው ጉዳይ ግን አሁን ማንም ዘርፎና ገሎ በፈለገበት አገር የመኖሩ ዕድል እየጠበበ መምጣቱን፣ማንም ወንጀለኛ ከፍትህ ሊያመልጥ የሚችልበት ዓለም እንዳልሆነ ነው።

የመንግስታቱንና የደጋፊዎቻቸውን ውጣ ውረድና ያደረሱትን፣የደረሰባቸውንና ሊደርስባቸው የሚችለውን በጥቂቱም ካየን በተቃዋሚው ጎራ ላለፉት አርባ ዓመታት የታዩትን ተመክሮዎች ለትምህርት ይሆኑ ዘንድ መፈተሹ አስፈላጊ ነው።አሁን በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት ድርጅቶች  ለምን አይነት ለውጥ እንደቆሙና አጃቢና ደጋፊዎቻቸው  ለምን አይነት ድርጅት እንደተሰፉ  የሚያዩበት መነጽር ይሆናቸዋል።

በወታደራዊው አምባ ገነን ላይ ተነስተው የነበሩት አሁን ለስልጣን የበቁትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ድርጅቶች የጎሳ ነጻነትን መርሆ አድርገው የተነሱ ሲሆኑ በሌላው ጎራ ደግሞ በሕብረብሔር ደረጃ በፖለቲካ ድርጅትነት የተሰለፉ የቀድሞ መንግስት ባለስልጣኖችን ያካተተ  የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት(ኢዲዩ) እንዲሁም  በግራው የፖለቲካ ፍልስፍና እረድፍ ኢሕአፓና መኤሶን ነበሩ።ምንም እንኳን ሕብረ ብሔራዊ ዓላማ ቢኖራቸውም፣ እርስ በርሳቸው የሚፋጩ በመሆናቸው ሃይላቸውን አስተባብረው ደርግን የጋራ ጠላታቸው አድርገው ታግለው ለመጣል አልበቁም።እንደውም ጊዜና ጉልበታቸውን እርስ በእርስ በሚያደርጉት የመጠፋፋት ትግል ላይ አባክነውት ነበር።መኤሶን የተባለው ድርጅት ከተቀናቃኙ  ከሆነው ኢሕአፓ ጋር በነበረው ልዩነትና ጥላቻ የተነሳ ከወታደሩ አምባ ገነን ጉያ ስር ገብቶ የወንጀሉ ተካፋይ በመሆን ለጥቂት ጊዜ ለመንቀሳቀስ ቢችልም የፖለቲካው አዝማሚያ እየለዬ ፣የስልጣን ትግሉ ግለት ሲጨምር ደርግም የስልጣን ኮርቻውን ሲያደላድል መኢሶንን ከተጠቀመበት በዃላ በጠላትነት ፈርጆት የጥቃት ሰለባ አደረገው።መኢሶን  ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሆኖ አረፈው።ከሌላ አገሮች እንደታዬው ተመክሮና ልማድ ቢሆንማ ኖሮ የወታደር መንግሥት አስተማማኝ ለውጥ እንደማያመጣና አምባ ገነንነት እንደሚሰፍን  ለመኢሶን መሪዎችና ደጋፊዎች የተሰወረ አልነበረም፤ ብዙ አመላካቾችም ነበሩ።ከወታደሩም ክፍል የደርግን አካሄድና የወታደራዊ መንግሥቱን መመስረት የሚቃወሙ የአርሚ አቪዬሽን፣የአየር ሃይል፣የመሃንዲስና የክብር ዘበኛ ክፍሎች የሚጠቀሱ ናቸው።እነዚህ የጦር ክፍሎች አደገኛነቱን ተገንዝበው እስከ ሞት ድረስ ሲታገሉ፣ሲታሰሩና ሲሰደዱ፣በሌሎች አገሮች በወታደራዊ መንግሥት ስር የሚተዳደሩትን ሕዝቦች ስቃይና መከራ እያዩ፣ ብዙ የፖለቲካ እውቀት የነበራቸው ምሁራን ግን ዓይኔን ግንባር ያርገው ብለው ከወታደራዊው መንግሥት ስር ተሰለፉ።ቅድሚያ የሰጡት ተቀናቃኝ የሆናቸውን ኢሕአፓን እማጥፋቱ ላይ ነበር።ደርጉን በግራ ና ቀኝ ክንፍ በሚል ፈሊጥ ከፋፍለው በመመልከት የተፈጥሮ ጸባዩን ዘንግተው በፈጸሙት ስህተት  እነሱም የእሳት እራት ሆኑ።የአረመኔው መንግሥቱ  ወታደራዊ ቡድን በፈጠረው ፈሪና እበላ ባዮች በተጠቀጠቁበት ኢሰፓ በተባለ ካባ ድርጅት ስም እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ ለ17 ዓመት በስልጣን ላይ ቆዬ።

ደርግን ይቃወሙ የነበሩት ህብረብሄር ድርጅቶች በሚያደርጉት የእርስ በርስ ግጭት ላይ የወታደሩ ጥቃት ተጨምሮበት አቅማቸው ተዳከመ።ይህ መዳከም በፈጠረው ልዩነት  በውስጣቸው  ቅራኔ ወልዶ ለመበታተን ዳረጋቸው፤በዚህ አጋጣሚ የተጠቀሙት  በጎሳ ነጻነት አውጭ ስም ተደራጅተው በውጭ ሃይል እርዳታ የሚንቀሳቀሱት ነበሩ።የማታ ማታም ድሉ ለነዚሁ ለጎሰኞቹ ሆነ።

ታሪክ እራሱን ይደግማል እንደሚሉት ሆነና አሁን በስልጣን ላይ የተቀመጠው ወያኔ መራሹ አገር አጥፊ ቡድን ካለፈው ስርዓት አልተማረም፤ደጋፊዎቹም ካለፈው ስርዓት ደጋፊዎች አልተማሩም። የሚወድቅበትን መንገድ እየጠረገ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።ይህ ሕዝብ የሚጠላው ጸረ አገርና ጸረ ሕዝብ የሆነ ቡድን እንደሚወድ ቅጥርጥር የለውም። የስርዓቱ መሪዎችና  ደጋፊዎች ይህንን የተገነዘቡት አይመስልም። እያጨበጨቡ ወደ አብሮ መጥፋቱ እየነጎዱ ነው።

አሁንም እንደ ደርግ ጊዜ  በተቃዋሚው ጎራ ያለው ካለፉት ጥፋቶች አልተማረም። በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ስህተት ሲፈጽም ታይቷል፤እየታዬም ነው። ከኢሕአፓና ከመኢሶን ውድቀት በዃላ ደጋፊውን የተረፈው ነገር ቢኖር መጸጸት ነበር።ያ ግን ከዳግመኛ ተመሳሳይ ስህተት አላዳነውም።መድህን የተባለ ድርጅት አጅቦ ሆይ ሆይ ይል የነበረው፣ገንዘብና ጉልበቱን ያፈሰሰው ያለፉት ድርጅቶች ደጋፊ የነበረው ነበር። የተሰጠው የድል ተስፋ፣ከሰላሳ ሽህ በላይ ድንበር ላይ ተሰልፎ የሚጠባበቅ ጦር እንዳለው ይነገረው የነበረው ቱሻ ያሳለፈውን ስህተት እንዳያይና እንዳያስታውስ ጋርዶት ነበር። የዃላ ዃላ ውሸት መሆኑ ሲታወቅ፣ያፈሰሰው ገንዘብ የት እንደገባ ሳያውቀው ተበታትኖ የጸጸት ሰለባ ሆነ።አሁንም ከዚያ ስህተት ለመማር አልተቻለም። በተከታዩም በዘመነ ቅንጅት እንዲሁ አገር ወዳዱ ከዳር እስከዳር ደግፎ ያበረከተው ተሳትፎና ተስፋው በድርጅቶቹ መሪዎች የስልጣን ሽኩቻ ላይ የወያኔ ተንኮልና የስለላ መረብ ተጨምሮበት መና ሆኖ ቀረ። በደጋፊው ዘንድ ብስጭትና ጸጸትን ወለደ።ከዚያም ስህተት ያልተማረው አገር ወዳድ እንደገና  ለሶስተኛ ጊዜ  ለጸጸት በሚዳርገው አካሄድ ሲነጉድ ይታያል። የሚመክሩትንም እንደጠላት ቆጥሮ አካኪ ዘራፍ ይላል።እንደ  መድህኑ  በተመሳሳይ ደረጃ የሌለውን ሃይል እንዳለው አድርጎ የሚያምታታ፣በኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ ላይ የጠራ ራዕይ የሌለው፣የወያኔን ሕገ-መንግስት የሚቀበል፣ኤርትራን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ከወሰደ ፣የባሕር በር እንዳይኖራት ካደረገ፣የኢትዮጵያ ሕዝብ  አንድ ቁጥር ጠላት ከሆነው ሻእብያ ከተባለው  ጋር በመመሳጠር ከነጭራሹ በወያኔ መልክ እንገነጠላለን ብለው ባንዲራ ሰፍተው በነጻ አውጭ  ስም  የሚንቀሳቀሱትን የጎሳ ድርጅቶች ሰብስቦ ተቃዋሚ ነኝ የሚለውን ግንቦት ሰባት የሚባል ድርጅት በሚነዛው ፕሮፓጋንዳና ድራማ ተስቦ ገንዘቡንና ጉልበቱን የሚያፈሰው አገር ወዳድ ቁጥሩ ቀላል አይደለም።ይህ  ከመድህን ፓርቲና ከቅንጅት ውድቀት ለመማር ያልቻለ ስብስብ፣ ነገ ጧት ለሚደርስበት ተመሳሳይ የሞራል ስብራት እንደሚጋለጥ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።በመድህንና በሌሎቹ ድርጅቶችና ደጋፊዎች ላይ ከደረሰው አለመማሩ« የአረረችን» ታሪክ መድገም ማለት ነው።እየተሳሳቱ መታረም ተገቢ ሲሆን ሳይታረሙ መሳሳት ግን እርግማን ነው።

ኢሳያስ አፈወርቂ የሚፈልገውን የሚያገኝበት አስተማማኝ ዘዴ ካልሆነለት  በስተቀር ማንም በተለይም ለኢትዮጵያ ጥቅም የቆመ እንኳንስ በኤርትራ መሬት ቀርቶ በከባቢውም የሚንቀሳቀስ ሃይል እንዲኖር አይፈቅድም።ታዲያ ኢሳያስንና  ግንቦት ሰባትን ምን ጥቅም አስተሳሰራቸው?”የጋራ ጠላታቸው ወያኔ ስለሆነ ነው” የሚለው ሚዛን አይደፋም።ለሻእብያ ከወያኔና ከኦነግ የተሻለ አጋር በኢትዮጵያ ውስጥ የለውም።የግንቦት ሰባት ደጋፊ የሆነው አገር ወዳድ ይህንን ቀርቶ የሚከፍለው ገንዘብ የት እንደገባ የመጠየቅ ድፍረቱ የለውም።አምጣ ሲሉት መስጠትን፣አጨብጭብ ሲሉት ማጨብጨብን ስራዬ ብሎ ይዞታል።

የፖለቲካ ስራ ሳይንስ ነው። እውቀት፣ ጥበብና ችሎታን የሚጠይቅ ኪነት ነው።ጭፍን ጥላቻ፣ጭፍን ድጋፍ፣ደም ፍላት፣ ጋጠ ወጥነትና ወገንተኝነት ፣ዓላማ ቢስና ፈሪ መሆንም  የፖለቲካ ስራን ብቻ ሳይሆን አገርና ሕዝብን የሚጎዳ እብደት ነው።ከዚህ ልክፍትና ድክመት መላቀቅ እራሱን የቻለ እውቀት ነው።

አሁንም አልመሸም።ለአገር አንድነት፣ሰላምና ብልጽግና በእውቀት ላይ መሰረት ያደረገ ራእይ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ፈጥሮ መታገል ይቻላል።«ሰው ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ»ሆነና  ተስፋ የሚጣልበት መሪ ድርጅት አለመኖሩ  የአገራችን የፖለቲካ መስክ ለማይረቡ ቡድኖች መጋለቢያ ሜዳ ሆነ። አገር ወዳዱ አማራጭ ሲያጣ እነዚሁ የሚጋልቡት ፈረስ ሆነ።ከዚያ  ስህተትና ውድቀት ለመዳን ያለፉትን አይቶና አመዛዝኖ ለነገው ሰልፋችን የምንዘጋጅበትን እቅድ ማሰቡ ብልህነት ነው።

የ«አረረች» ተመክሮ ከእኛም አገር አልፎ ለሌሎቹ ያፍሪካ መሪዎችና ሕዝቦች የሚሰጠው ትምህርት አለ።ከቀናት በፊት በዚምባብዌ መሪ በሮበርት ሙጋቤ ላይ የደረሰው ጉድ ከትናንትናዎቹ  አምባ ገነን መሪዎች ውድቀት ያለመማር ድክመት ያመጣው ጣጣ ነው።ከሙጋቤም ውድቀት የማይማሩ ብዙ ያፍሪካ መሪዎች አሉ። የጊዜ ጉዳይ ነው እነሱም አይቀርላቸውም።ለብዙ ዓመታት በስልጣን ላይ ተቀምጠው አገራቸውን የግል ንብረት አድርገው የሚቆጥሩ፣ስልጣኑን አሳልፈው ላለመስጠት ወንጀል የሚፈጽሙ፣በዕድሜ መንዛዛት ማስተዋል የተሳናቸው፤ የወጣቱን ትውልድ ፍላጎትና  ልቦና ማወቅና መረዳት ያቃታቸው መሪዎች ብዙ ናቸው።የዚምባቡዌው ሮበርት ሙጋቤ ቢታደል ኖሮ በመልካም ምግባራቸው ተወዳጅና ምሳሌ ከሆኑት በቅርብ ከሚያውቃቸው ያፍሪካ መሪዎች፣ከደቡብ አፍሪካ መሪዎች ፣ከኔልሰን ማንዴላና ታቦ እምቤኪ፣ከዛምቢያው ኬኔት ካውንዳ፣ከታንዛንያው ጁሊዬስ ኒሬሬ ትምህርት በቀሰመ ነበር።ከመጥፎ መሪዎችም አሳፋሪ ውድቀት  አጠገቡ ካለው  ከመንግስቱ ሃ/ማርያም ፣በውጭ አገር ሞቶ መቃብሩ ካልታወቀው ከከኮንጎው ሞቡቱ ሴሴሴኮ፣ከዑጋንዳው ኢዲያሚን ዳዳ፣በስደት ሲንከራተት ኖሮ አገሩ ተመልሶ ገብቶ ታስሮ ከሞተው ከሴንትራል አፍሪካው ሃምሳ አለቃ አልበደል ቦካሳ፣ከሊቢያው ጋዳፊ፣ከኢጅብቱ ሙባረክ ውድቀት ቢማር ኖሮ  አሁን ለገጠመው ውርደት አይጋለጥም ነበር።የነጻነት ታጋይነቱና መሪነቱ ተወድሶ ለተተኪው ትውልድ የሚያልፍ የታሪክ ምዕራፍ ባለቤት ለመሆን በበቃ ነበር። እሱን ካጋጠመው እጣ ፈንታ ለመማር ማስተዋልን ያልታደሉት ሌሎቹም አጁዛ መሪዎች የነገው እጣቸው ከሙጋቤ አይለይም።የአንጎላው ሳንቶስ፣የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ፣የኡጋንዳው ሙሳቬሊ፣የኮንጎው ካቢላ፣የሩዋንዳው ካጋሚ፣ለሃምሳ ዓመት አገሪቱን የቤተሰብ ንብረት አድርገው ሲቀባበሉ የኖሩት አባትና ልጁ የቶጎ መሪዎች…ወዘተ የነገው ሙጋቤ ወይም «አረረች»ከመሆን አያመልጡም።

የሁሉም መሪዎች የስልጣን መውደዱ በሽታ  የሚጀምረው ገና በጧቱ የተቃዋሚ ድርጅት መሪ በሆኑበት ወቅት ነው።በስልጣን ላይ በወጡትና በስልጣን ላይ ባልወጡት መካከል ያላቸው ቅርበትና ምስስል በስልጣን ላይ ለመቆዬት ያላቸው ፍቅረ ስልጣን ጸባያቸው ነው።ስልጣን የሁሉም ጥቅም ምንጭ ስለሆነ ያንን ቦታ አሳልፎ ለመስጠት የሚቆርጠው በጣም ጥቂቱ ነው።በአገራችንም የሚታየው በስልጣን ላይ ያሉትና  በተቃዋሚው ጎራ ያሉት መሪዎች የሚጋሩት ወረርሽኝ ይህንኑ ነው።ስልጣኑን ከተወሰነ ጊዜ በዃላ መልቀቅ አይፈልጉም፤ከስልጣን ውረዱ መባልን አይወዱም።በግድ ካልሆነ በዴሞክራቲክ መንገድና በመረካከብ ስለማያምኑ በዋዛ አይለቁም።ተገደው ቢወርዱ የብዙሃኑን ውሳኔ አይቀበሉም፤ይባስ ብለው ተጓዳኝ ድርጅት ፈጥረው ለማዳከም ይውተረተራሉ።በተወናበደና በጥቅም በተገዛ ደጋፊ ጫጫታ ታጅበው መሄዳቸው ዓይነ ህሊናቸውን ጋርዶታል።በሕዝቡ የተወደዱ ያስመስላቸዋል።በሌላው ላይ የደረሰው ይደርስብኛል አይሉም፤ከ«አረረች» አይማሩም።እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል መንፈስ ተለክፈው በመጨረሻው እራሳቸውንም፣ቤተሰባቸውንና ደጋፊዎቻቸውንም ይዘው ገደል ይገባሉ። በአፍሪካ መሬት ጊዜ አስልተው  በጨዋ ደንብ ስልጣኑን አሳልፈው የሰጡ የአገር መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው።

በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ተመሳሳይ ሁኔታ መከሰቱ አይካድም።እንዳይቀጥል በስልጣን ላይ በሚወጡትና በድርጅት አመራር ላይ በሚመደቡት ላይ የዕድሜ ጣራ(ገደብ) መቀመጥ ይገባዋል።በአገሪቱ የመሪነት ቦታ ላይ እምብዛም ጥሬ ሆኖ የተመክሮ ደሃ ሳይሆን፣እምብዛም ያረረ(አጁዛ) ሆኖ ከጊዜው ጋር መራመድ የሚያቅተው ሳይሆን፣ያለፈውን የአሁኑንና የወደፊቱን የመገንዘብ ችሎታ ያለው፣በትውልዱ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ሊያቀራርብ የሚችል፣ ዕድሜው ከ45-65 የሆነ  የመሪነቱን ቦታ ቢይዝ የተሻለ ነው።የስልጣን ጊዜውም ከ10 ዓመት በላይ (ከሁለት ጊዜ ምርጫ )የበለጠ ባይሆን ይመረጣል።ከ65 በላይ ዕድሜ ያለው በስልጣን ላይ እንዳይቀመጥ ሆኖ ግን  የተመክሮ ጌታ ስለሆነ በአማካሪነትና በአገር ሽማግሌነት  ብዙ ቁም ነገር ሊያበረክት ስለሚችል ቦታ እንዳይነፈገው ማድረግ ይቻላል፤ይገባልም።ይህ በሕገ መንግሥቱ ቢደነገግ አሳፋሪውን የመሪዎች ስነምግባርና ፍቅረ ሥልጣን ብሎም አምባ ገነንነትን ይከላከላል።

የስልጣን እብዶችን በመደገፍ ከማይቀረው ውድቀታቸው ጋር አብሮ ላለመውቅ፣ በህሊና ጸጸት ላለማረርና ላለመንጨርጨር  ያለፉትን ውድቀቶችና ስህተቶች ብሎም  የ«አረረችን»ታሪክ እንደ ምሳሌ መውሰዱ ይጠቅማል።

ከ«አረረች» አደጋ ይሰውረን!!

LEAVE A REPLY