ኬንያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገባት ማቀዷን ገለጸች

ኬንያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገባት ማቀዷን ገለጸች

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ ኬንያ እ.ኤ.አ በ2027 የመጀመሪያውን የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ማቀዷን ገለጸች።ኬንያ እቅዷ የሚሳካ ከሆነ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ አፍሪካዊት የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ባለቤት እንደምትሆን ምንጮችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የግንባታ ቦታው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ዝግጁ እንደሚሆን የኬንያ የኑክሌር ኤሌክትሪክ ሃይል ቦርድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሊንስ ጁማ ተናግረዋል። “የኑክሌር ማመንጫውን ለማቋቋም እ. ኤ .አ ከ2009 ጀምሮ ቅድመ ጥናት ሲደረግ የቆየ ሲሆን በ2024 የግንባታ ሥራዎችን እንደምንጀምር ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዚህም ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለቤት በመሆን በአህጉሩ ሁለተኛ እንሆናለን።” ሲሉ ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

አንድ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 1ሺ ሜጋ ዋት ሃይል የማምረት አቅም እንደሚኖረውና ከአምስት እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ወጪ ያስፈልገዋልም ተብሏል። ኬንያ በኑክሌር ቴክኖሎጂ የአቅም ግንባታ ለመፍጠርና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከአራት ሀገራት ጋር እንደተፈራረመችና የግንባታ ስራውም ከአምስት ሺ በላይ ለሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።

ኬንያ ከሀይድሮ ፓወር፣ ከጅኦተርማል፣ ከሶላር፣ ከነፋስና ከተለያዩ ሀይል ማመንጫ ዘዴዎች ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የምታመነጭ ሲሆን ባሏት በርካታ ፋብሪካዎች ምክንያት አሁንም ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል በየዓመቱ እንደምትገዛ ይታወቃል።

LEAVE A REPLY