ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢየሩሳሌም “የእሥራኤል ዋና ከተማ ናት” በማለታቸው አካባቢው ሁከት ተቀሰቅሷል

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢየሩሳሌም “የእሥራኤል ዋና ከተማ ናት” በማለታቸው አካባቢው ሁከት ተቀሰቅሷል

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ኢየሩሳሌምን እንደ እሥራኤል ዋና ከተማ በይፋ ዕውቅና ሰጥተው ቴል አቪብ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲም ወደዚያው የማዛወር ዝግጅት እንዲጀመር ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ፡፡

ኢየሩሳሌም የአይሁድ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን እሥራኤል ከተመሠረተችበት (እአአ) ከ1948 ዓ.ም. አንስቶ የመንግሥቷም ዋና መቀመጫ ነው ብለው የሚያምኑት ሚስተር ትራምፕ ይፋ መግለጫቸውን ከመስጠታቸው በፊትም እርምጃው ‘እጅግ ዘግይቷል’ ሲሉ ተናግረዋል።

“የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት (እአአ በ1995 ዓ.ም.) በሁለቱም ፓርቲዎች እንደራሴዎች አብላጫ ድምፅ ያፀደቀውንና ከስድስት ወራት በፊትም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ያሳለፈውን ውሣኔ ተከታታይ ፕሬዚዳንቶች ተግባራዊ ሳያደርጉት ቆይተዋል” ብለዋል።

አረብና የእሥልምና አራማጅ የሆኑ መንግሥታት መሪዎች “አወዛጋቢ ነው” ያሉት ይህ የፕሬዚዳንት ትራምፕ እርምጃ በአካባቢው ውጥረት እንደሚያባብስና እሥራኤልንና በፍልስጥዔማዊያኑን ለማደራደር አሜሪካ የጀመረችውን ጥረት እንደሚያስተጓጉል በመግለፅ ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው፡፡

ፍልስጥዔማዊያኑ “የቁጣ ቀናት” ብለው በጠሯቸው ሦስት ተከታታይ ቀናት ተቃውሟቸውን ለማሰማት ጥሪዎችን እያስተላለፉ ናቸው። ዛሬም በተጠቃውሞ በተጥለቀለቀችው ቤተልሄም ፍልስጥዔማዊያኑ የፕሬዚዳንት ትረምፕን ፎቶዎች ሲያቃጥሉ ታይተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ስፋት ያላቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እየተደራጁና እየተጠሩም በመሆናቸው የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው በአሮጌዪቱ ኢየሩሳሌም፣ በዌስት ባንክ፣ በቤተልሄምና በኢያሪኮ የግል ጉዞዎችንና እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ እዚያ የሚገኘው የአሜሪካ ጠቅላይ ቆንሲል ፅሕፈት ቤት አሳስቧል።

LEAVE A REPLY