ፍርድ ቤት በችሎት የተሰየሙትን ዳኛ እና ተከሳሾቹን ሊያከራክር ነው

ፍርድ ቤት በችሎት የተሰየሙትን ዳኛ እና ተከሳሾቹን ሊያከራክር ነው

/በጌታቸው ሺፈራው/

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ የቀረበባቸውንና የ4ኛ ወንጀል ችሎት የግራ ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበትና ተከሳሾቹን ሊያከራክር ነው። ሁለቱ ወገኖች በፅሁፍ ያቀረቡትን ሀሳብ መርምሮ ዳኛው ከችሎት ይነሱ አይነሱ የሚለውን በቀጣይ ቀጠሮ እንደሚወስን ገልፆአል።

ዛሬ ታህሳስ 3/2010ዓም ዳኛው እንዲነሳ በጠየቁት መሰረት ውሳኔውን ለመስማት ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበሩት በእነ ክንዱ ዱቤ ክስ መዝገብ የተከሰሱ 10 ተከሳሾች እንዲሁም ጌታሁን አቡሃይ የተባለ ተከሳሽ “የዳኛውን መልስ አይቶ ለመወሰን” በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የዛሬውን ቀጠሮ የተከሳሾቹን አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ሰጥቶ እንደነበር አስታውሶ ፣ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ይህን ባለበት ወቅት የግራ ዳኛ ሆነው የተሰየሙት ዘርዓይ ወልደሰንበት በቀረበባቸው አቤቱታ ላይ ” እነሳለሁ ወይም አልነሳም” የሚል አስተያየታቸውን በፅሁፍ እንዲያቀርቡ ለመጠበቅ ለጌታሁን አቡሃይ ለታህሳስ 10 እንዲሁም ለእነ ክንዱ ዱቤ ለታህሳስ 12/2010 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

ፍርድ ቤቱ የችሎቱ የግራ ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ከችሎት እነሳለሁ ወይም አልነሳም የሚል መልሳቸውን ከቀጠሮ በፊት ሊያስገቡ እንደሚችሉ የገለፀ ሲሆን መልሳቸው አልነሳም ከሆነ የችሎቱ ቀሪ ዳኞች ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዳኛ ይነሳልን አቤቱታና የዳኛውን መልስ አይተው ውሳኔ እንደሚሰጡ ገልፆአል።

በሌላ በኩል በእነ ክንዱ ዱቤ ክስ መዝገብ 8ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ አያሌው፣9ኛ ተከሳሽ መላኩ ዓለም እንዲሁም 10 ተከሳሽ ለገሰ ወ/ሀና በቀጠሯቸው ያልቀረቡ ሲሆን የቂሊንጦ እስር ቤት ተወካይም ያልቀረቡበትን ምክንያት አላውቅም ብሏል። ሆኖም ለገሰ ወልደሃና ትናንት ቀጠሮ ያላቸው እስረኞች በሚመዘገቡበት ወቅት እንዲሁም ዛሬ ጠዋት ቀጠሮ እንዳለው ለእስር ቤቱ ፖሊሶች ቢገልፅም ሊያቀርቡት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ከእስረኞች እንዳረጋገጡ ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

LEAVE A REPLY