ኢትዮጵያ በማይመጥኗት መሪዎች ብቻ ሳይሆን በማንመጥናት ዜጎችም ስለተወረረች ነው እዚህ የደረስነው

ኢትዮጵያ በማይመጥኗት መሪዎች ብቻ ሳይሆን በማንመጥናት ዜጎችም ስለተወረረች ነው እዚህ የደረስነው

/መላኩ አላምረው/

ኢትዮጵያ… በማይመጥኗት መሪዎች ብቻ ሳይሆን… በማንመጥናት ዜጎችም ስለተወረረች ነው እዚህ የደረስነው። ማናችንም ይህችን ሀገር አንመጥናትም። ማናችንም በዚህች ሀገር ስም ለመጠራት ብቁ አይደለንም።

ሁሉም… መንግስትም ሆነ ሕዝብ… የሃይማኖት አባትም ሆነ የፖለቲካ መሪ… ጋዜጠኞችም ሆንን “አክቲቪስት” ነን ባዮች… ኢትዮጵያን አንመጥናትም ብቻ ሳይሆን ማፈሪያዎች ነን። ችግሯን ከማባባስ ያለፈ ምንም በጎ ሚና መጫዎት ያልቻልን ደካሞች ነን። በአባቶቻችን ጀግንነት በተገኙ ድሎችና በወረስነው ነፃነት ከመመጻደቅ ያለፈ እነርሱ ለከፈሉት ዋጋ እንኳን ክብር የሌለን “ጉራ ብቻ” ነን።

ሁልጊዜም አንድ ችግር በተፈጠረ ቁጥር የማባባስ እንጅ የማረጋጋት ሚና ስንጫዎት አንታይም። ሁሉም “በለው” ነው። ሁሉም “ቀንህን ጠብቅ” ነው። ሁሉም ጥላቻን መስበክ… ሁሉም ለበቀል መቀስቀስ…. እሽ መፍትሔ በየት በኩል ይምጣ? ሕዝብን የበደሉ አካላትን ለይቶ ለመቅጣትም ሀገርና ሕዝብ ያስፈልጋሉ። ይህችን ሀገር በታላቅነቷ የምናስረክበው ትውልድ በሕይወት መኖር አለበት እኮ። ዝም ብሎ በሀገር መመጻደቅ ምን ዋጋ አለው? የምንመጻደቅባት ሀገር እንድትፈራርስ ተግተን እየሠራን የእኛ ሀገር ወዳድነት ምኑ ላይ ነው? የምንታገልለት ሕዝብ ከወንድሞቹ ጋር ደም እንዲቃባ ብቻ ሳይሆን ተባልቶ እንዲተላለቅ እየቀሰቀስን ማንን ነፃ ልናወጣ ነው?

ጎበዝ… ለሕዝብ ነፃነት መታገልንና ሕዝብን ከሕዝብ ማባላትን እየለየን እንጅ። እኔ ተበደለ ላልሁት ሕዝብ መብትና ነፃነት መታገልም መሟገትም እችላለሁ(መብቱ አለኝ) ማለት ይህ ሕዝብ ሌሎችን ጠላት አድርጎ እንዲነሳና እንዲገዳደል የማድረግ መብቱም ነፃነቱም አለኝ ማለት አይደለም። ሰሚ አገኘን ብለን ነገሮችን ሁሉ ያለ ገደብና ኃላፊነት የምንለቅ ሁሉ ልብ እንግዛ። ሰሚ ካለን ለሕዝቡ የሚበጀውን እንጅ የማይጠቅመውን ለምን እንነግረዋለን? በምንም ልኬት… ለየትኛውም ሕዝብ… መበቃቀልና መገዳደል ጥቅም አይደለም።

የመንግሥት አካላት ደግሞ….. መቼ ይሆን “እየሄድሁበት ያለው መንገድና እየወሰድሁት ያለው እርምጃ ሀገርን ወደ ባሰ ችግር እንጅ ወደ መረጋጋት ሊወስዳት አልቻለም” ብላችሁ ለእውነተኛ መፍትሔ ከሕዝቡ ጋር የምትመክሩት??? ብታምኑም ባታምኑም… ቢገባችሁም ባይገባችሁም… ሀገሪቱንም እናንተንም ከመከራ ሊያድን የሚችል መፍትሔ በሕዝቡ እጅ ነው ያለው። ምሽቱ የበለጠ ሳይጨላልም ሕዝቡን ቆም ብላችሁ ብቻ ሳይሆን ጎንበስ ብላችሁ ይቅርያውንና ምክሩን ብትለምኑ ይበጃችኋል። ሕዝብ የዋሕ እንጅ ሞኝ አይደለምና ሁሌም እንደተረገጠ አይኖርም።

በተለይ የአማራና የትግራይ ገዥዎች(ብአዴን እና ሕወሓት) ለእናንተ ክብርና የትግል ዝና መጠበቅ ብቻ እየተጨነቃችሁም ሆነ በተለዬ የርኩሰት ዓላማችሁ ወንድማማች ሕዝቦችን ደም እያቃባችሁ መሆኑ ይግባችሁ። ይህም ታላቅ ታሪካዊ ስህተት ነው። የትግራይና የአማራ ሕዝብ በባህልም ሆነ በእምነት፣ በታሪክም ሆነ በወቅት ተለያይቶ የማያውቅ፣ ለሀገር ነፃነት አብሮ የሞተ ሕዝብ ነው። ዕድሜ ለእናንተ የዘረኝነትና የጥላቻ ስብከት… ይኸው ዛሬ በየዩኒቨርሲቲውና በየኳስ ሜዳው ሳይቀር የሁለቱ ሕዝብ ልጆች ተቧድነው እየተደባደቡ በአደባባይ ታዩ። ውድ የሰው ሕይወት እስከመጥፋትም ደረሰ። ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው? መቼ ነው ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቃችሁና ከእግሩ ስር ቁጭ ብላችሁ ለመፍትሔ የምታማክሩት? ለትውልዱ ምን አይነት ሀገር ልታስረክቡት ነው የታገላችሁት? ስህተት ናችሁ ከመባልም አልፎ በዓይናችሁ የምታዩት ይህ ሁሉ ችግር ካላስተማራችሁ በምንድነው የሚገባችሁ? በእውኑ የታገላችሁት ለዚህ ነበርን?

በየቡድኑ ያለን “አክቲቪስት ነን” ነን ባይ ነገር አቀጣጣዮች… ምን፣ መቼ፣ ለማን፣ እንዴት … መነገር እንዳለበት እያስተዋልን። ከስሜታዊነት ባሻገር ተረጋግቶ ማሰብ ለማይችል ትኩስ ኃይል የጥላቻ እና በቀል ቅስቀሳን በደም በተነከሩ ፎቶዎች እያጀቡ ማራገብ… ችግርን ከማባባስ ያለፈ ጥቅም የለውም። ለሀገርም የሚበጀው “በሕይወት የሚኖር ትውልድ” ሲቀጥል ነው። ስሜታዊነት በዘር በቀል ሲታጀብ ለየትኛውም ወገን ወደማይጠቅም ብጥብጥ ይወስድና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል። ተለያይቶ ለመኖርም እኮ ፍቅርና ሰላም ያስፈልጋል። መልካም ጎረቤት ለመሆን ማሰብ ታላቅነት ነው። ዘላቂ መፍትሔ ስናስብ…. ከስሜታዊነት እየራቅን። ተበደለ ላልነው ሕዝብ መብት እስከመጨረሻው መታገል አለብን… ግን ከበቀልና ከጥላቻ፣ በተለይም ከመገዳደል ነፃ ሆነን ካልሆነ ሀገራዊና ሕዝባዊ መፍትሔን አናመጣም።

መውጫ፦
እኔ ወልዶ ላሳደገኝና በማንነቱ ተለይቶ እየተገፋ ለኖረው/ላለው ለአማራ ሕዝብ መብትና ማንነት መጠበቅ ጻፍሁ/ተናገርሁ ማለት እኔ በአማራነቴ ለሚደርስብኝ ስድብ፣ አድሎና መገለል ለመታገል እንጅ ሕዝቡን እኔ ነፃ አወጣዋለሁ ማለት አይደለም።(እኔ ማነኝና ነው ሕዝብን ነፃ የማወጣው? እንዲያውም በሕዝቡ ስም ራሴን ወደሆነ ነፃነት ለማውጣት ነው የምታገለው)። አማራን ማንም እንዳይገድለው እንደምፈልገው ሁሉ አንድም አማራ በሌሎች ላይ እጁን በደም እንዲያነሳ አልፈልግም። የሁሉም ሕይወት ከእኔ ሕይወት ጋር እኩል ናትና በማንም ሞት የማንንም ነፃነት አልመኝም። አማራ ማንነቱ ተከብሮ እንዲኖር የምፈልገው ለኢትዮጵያ ታላቅነት ስለሚያስፈልጋት ነው። የሚያስፈልጋት ብቻውን አይደለም። ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በጋራና በአንድነት እንጅ። ደግሞም አማራ መቆም ያለበት ከፍታውን በሚመጥን የአለት መሠረት ላይ እንጅ ወርዶ ነገ ተንሸራቶ በሚጥለው ጭቃ ላይ አይደለ። እኔ ለአማራ ቁመና የምመጥን የአለት መሠረት መሆኔን እስከማረጋግጥ ድረስ ሕዝቡን ና በእኔ ላይ ቁም የምል ሀፍረተ ቢስ አይደለሁም።

LEAVE A REPLY