የመከላከያ ሚኒስትሩ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ለወንጀለኞች ጥብቅና እየቆሙ ነው አሉ

የመከላከያ ሚኒስትሩ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ለወንጀለኞች ጥብቅና እየቆሙ ነው አሉ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው እንዲያዙ ማዘዣ የወጣባቸውን ግለሰቦች ለመያዝ በሁለቱም ክልሎች በኩል ዳተኝነት መኖሩን ገለጹ።

በዚህ ምክንያት በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ወይም ለግጭቱ መባባስ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ አለመቻሉን ገልጸው፤ በሶማሌ ክልል በኩል ማዘዣ ከወጣባቸው ከ29 ሰዎች ውስጥ 12ቱ ሲያዙ፤ በኦሮሚያ በኩል ደግሞ ከ26 ሰዎች ውስጥ 3 ሰዎች ብቻ መያዛቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያ ክልል በግጭቱ እጃቸው አለበት ተብሎ ከተጠረጠሩት 103 ሰዎች መካከል 98ቱ በህግ ቁጥር ስር መዋላቸውንና በሶማሌ ክልል በኩል ግን ከተጠረጠሩት 29 ሰዎች ውስጥ 5ቱን ብቻ የፌዴራል መንግስት መያዝ እንደቻለ ገልጸው ነበር።

በተለያዪ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጠረውን አለመረጋጋት መንግስት በሀይል አስቆመው የሚለው ሀሳብ ፍጹም ስህተት ነው።አለመረጋጋቱን ያስቆመው የጸጥታ አካላት ሳይሆኑ ህዝቡ ነው በማለት አስተባብለዋል።

የወያኔው መከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ መከላከያ ሰራዊቱ በአንድ ብሄር(ጎሳ) የበላይነት የሚመራ ነው በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በሀገሪቱ ውስጥ እንደ መከላከያ ሰራዊት የብሄር ተዋፅዖ ያካተተ ሌላ ተቋም የለም” ሲሉ ገልጸዋል።

ከ1987ዓ.ም ጀምሮ ነባር ተጋዮች እየተቀነሱ የማመጣጠን ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ ጥያቄ የሚነሳው ከላይ ባሉ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ላይ ነው ብለዋል።እንዲህ አይነት ጥያቄዎች የሚነሱትም ሰራዊቱ በአለም አቀፍ መድረግ ያለውን “መልካም ስም” ለማጠልሸት ታስቦ እንደሆነም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ መከላከያ ሰራዊቱን በበላይነት የሚመሩት ጀኔራሎች 99 ፐርሰንቱ የአንድ ብሄር(ጎሳ) አባላት መሆናቸውን የአደባባይ ሚስጥር ነው።

LEAVE A REPLY