በመካሄድ ላይ ያለው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ለዶ/ር ነጋሶ መኪና አበረከተ

በመካሄድ ላይ ያለው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ለዶ/ር ነጋሶ መኪና አበረከተ

ስብሰባው  የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል 

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ ባለፈው ዕሮብ የጀመረው የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ተገለጸ። “እንደገና የመልማትና ፍሬ የማፍራት መንገድ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ እስካሁን ባደረገው ውይይት የአመራር ለውጥን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል።

ከስድስት በላይ ሰዎችን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት በማንሳት በሌሎች የተካ ሲሆን ከአባልነትም የተነሱት፦ ወ/ሮ አስቴር ማሞ በአሁኑ ሰዓት በካናዳ አምባሳደር፤ አቶ ዘላለም ጀማነህ በሙስና ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ያሉ፤ በአቶ ሙክታር ከድር- የቀድሞው የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት፤ በአቶ ሰፊያን አህመድ-አምባሳደር፤ አቶ በከር ሻሌና አቶ ደምሴ ሽቶ ይገኙበታል።

ማእከላዊ ኮሚቴው ለቀድሞው ፕሬዝደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ V8 የመጓጓዣ መኪና እንዳበረከተላቸው ታውቋል። ኦህዴድ ለዶ/ር ነጋሶ ካበረከተላቸው መኪና በተጨማሪም የህክምና ወጭና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች በፓርቲው እንዲሸፈንላቸው መወሰኑ ተገልጿል። ዶክተር ነጋሶ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በህግ የተደነገገላቸውን ጥቅማጥቅም እንዳያገኙ ተከልክለው ቆይተዋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በሀገሪቱ የንግድ ስርዓት ከአድሎ ነፃና ሁሉንም ህብረተሰብ እኩል ያሳተፈ እንዲሆን እንደሚሰራና የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲቀጭጭ ሲያደርጉ የነበሩ አካላት በህግ እንደሚጠይቅ አስታውቋል። ስብሰባው ዛሬም የቀጠለ ሲሆን ኦ.ቢ.ኤን(የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ) ነጻነቱን ጠብቅ እንዲሰራ የክልሉ መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል። ባለፈው ሳምንት የህወሓቱ ብሮድካስት ባለስልጣን ዘርዓይ አሰግዶም ኦ.ቢ.ኤን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ግጭት በማባባስ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው መካከል አንዱ ነው በማለት መፈረጁ የሚታወስ ነው።

LEAVE A REPLY