አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሰባት የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ተፈቱ

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሰባት የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ተፈቱ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ በኦሮሚያ የተጀመረውን ህዝብባዊ አመፅ ተከትሎ ሰባት የፖለቲካ እስረኞች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ተፈቱ።በዚህ መሰረትም አቶ በቀለ ገርባ፣ ጉርሜሳ አያና፣ አዲሱ ቡላላ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ ጌቱ ጋሩማ፣ ተስፋዬ ሊበንና በየነ ሩዳ በዛሬው እለት ከቂሊንጦ እስር ቤት መውጣታቸው አረጋግጧል።

በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ አመፅ ምክንያት እነ አቶ በቀለ ገርባ እንደ ሌሎቹ ሁሉ “የተሀድሶ” ስልጠና ሳይወስዱ በአስቸኳይ መፈታታቸውም ታውቋል።

በክልሉ የተጠራው የሦስት ቀናት የስራ ማቆም አድማ በትላልቅ ህዝባዊ ሰልፎች ተደግፎ በሁሉም ከተሞች ለሁለተኛ ቀን ሲካሄድ ውሏል።

በሌላ በኩል ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ “የተሀድሶ ስልጠናውን” አቋርጠው ወደ ቃሊቲ እስር ቤት መመለሳቸው ተሰምቷል። በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል 22ኛ ተከሳሽ የሆኑት ወ/ሮ እማዋይሽ ዓለሙ “ወንድሞቼ ካልተፈቱ በስተቀር ብቻዬን ተነጥዬ አልወጣም።” በማለት “የተሀድሶ” ስልጠናውን በማቋረጥ ወደ ቃሊቲ መመለሳቸው ተረጋግጧል።

በ2001ዓ.ም “መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ አሲራችሗል” በሚል የታሰሩት እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከሚፈቱት መካከል እንደሆኑ ሲጠቀስ ቢቆይም እስኳሁን ምንም አለመባሉን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY