ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዴት? /አበጋዝ ወንድሙ/

ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዴት? /አበጋዝ ወንድሙ/

አገም ጠቀም ሲል ላለፉት አምስት አመታት ሲካሄድ የነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞና ትግል ፣ ብዙ መስዋአትነት አስከፍሎ፣ አንዳንድ የማይናቁ ድሎችን አስገኝቶ፣ ገዢውን ፓርቲ አስደንግጦና፣ በያዘው መንገድ ከቀጠለም ሕልውናው ጥያቄ ውስጥ አንደሚገባ ግልፅ በማድረጉ አስቸኩዋይ ጊዜያዊ ዓዋጅ አንዲያውጅ አስገድዶ አዚህ ደርሰናል። ከአንግዲህ ትግሉ ምን አይነት አቅጣጫ ሊይዝ ይችላል ፣ ምንስ አይነት አቅጣጫ ይዞ ቢሄድ ለሕዝባዊ ትግሉ ስኬትና ብዙዎቻችን ለምንመኘው የሕግ የበላይነት የሰፈነባትና የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች የሚከበሩባት ኢትዮጵያ አውን መሆን ሊያበረክት ይችላል የሚለውን ለማየት ትንሽ ወደሁዋላ ማየት የግድ ይላል።

በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተደረገው ትግል
ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ የተለያዩ ተቃውሞዎች አንደነበሩ ባይካድም በ1997ቱ አገር አቀፋዊ ምርጫ የኢህአዴግን የምርጫ ኮሮጆ ግልበጣና ስርቆት አስመልክቶ ከነበረው ተቃውሞ ቀጥሎ በስፋትና በቀጣይነት የተካሄደው ያለፈው አምስት ዓመት ሕዝባዊ ትግል ፣ አንደኛው ከአንደኛው ልምድ በመማር ሚሊዮኖችን ያሳተፈ፣ የህዝብን የትግል ወኔ ያነሳሳ ልምድን ያጋራና ያዳበረ ፣ ሕዝባዊ አጋርነትን የፈጠረ ፣ ሕዝባዊ አምቢተኝነትን በጠነከረ መልኩ በማካሄድ በገዥው ክፍል ውስጥ ጥርጣሬንና ክፍፍልን ከመፍጠርም በላይ አስገድዶ የመንግስት ውሳኔዎችን ያስለወጠ ሂደት ነበር።
ሁሉንም ነገር በቁጥጥሩ ውስጥ ካላደረገ አንቅልፍ የሚነሳው ኢህአዴግ አዲስአበባ በሚገኘው የአወሊያ ትምህርት ቤት ዉስጣዊ አስተዳደራዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሿሚና ሻሪ ካልሆንኩ በሚል የወሰደውን አርምጃ ተማሪዎቹ በመቃወማቸው፣ ተቃውሟቸውም በቤተሰቦቻቸውና ጉዳዩን በሰሙ ሰፈርተኞች ድጋፍ በማግኘቱ ሁኔታው አስደንብሮት፣ ይቺ ባቄላ የሚል አሳቤ ውስጥ ገባ። ይሄም በመሆኑ ፣መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለበትም የሚለውን የሕገመንግስት አንቀጽ የተጻረረና ባፍጢሙ የደፋ፣ አህባሽ የተባለውን አስላማዊ አስተምህሮ፣ ማጥመቅ በሚመስል መልኩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ ካልጫንኩ ብሎ በመውተርተሩና የመጅሊሱን ምርጫ አስመልክቶ የወሰደው አቋም፣ አብዛኛውን ህዝበ ሙስሊም ያስቆጣ ሀገር አቀፍ አንቅስቃሴ ለመፈጠር ምክንያት ሆነ። መጀመሪያ የተነሳውን ተቃውሞ በተገቢው መንገድ ማስተናገድ ባለመቻሉና ነገሮችን በማባባሱ ለተቃውሞው አዲስ ጉልበት በመስጠት ድርጅታዊ ቅርጽ ይዞ “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴን ” ወለደ።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት፣ የወከላቸውን ህዝበ ሙስሊም ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ረጅምና አልህ አስጨራሽ ውይይቶች ከመንግስት አካላት ጋር በማድረግ ቢቀጥሉም፣ ጥያቄዎችን በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ ችግሮቹን በማባባሱ ተቃውሞው አየከረረ ሲመጣና ሀገራዊ መልክ መያዝ በመጀመሩ መንግስት የሀሰት ወንጀል ፈብርኮ የኮሚቴው አባላትን ለአስር ዳረጋቸው።
ይሄ ምናልባት በመንግስት በኩል ተቃውሞውን ያበርደዋል በሚል አሳቤ የተወሰደ አርምጃ ህዝበ ሙስሊሙን የበለጠ አስቆጥቶ ፣ በአንድ ወገን የታሰሩት ወኪሎቻቸው አንዲፈቱ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ጥያቄያቸው በአግባቡ አንዲመለስ መጠነ ሰፊ አገራዊ አንቅስቃሴ ተቀጣጠለ። ይሄ ባለ በዙ ፈርጅ ሰላማዊ አንቅስቃሴ በየጊዜው ስልቱን አየቀያየረ አዳዲስ የሰላማዊ ትግል አካሄዶችን በመጠቀም፣ የመንግስትን አፈና ተቋቁሞ ቀጣይነት አሳየ። የህዝባዊ ትግሉ እየጎለበተ መሄድና ከአጠቃላይ ህብረተሰቡ ድጋፍ ማግኘት (ለምሳሌ ሰምያዊ ፓርቲ ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ)ያስበረገገው ኢሕአዴግ፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት ያገዛዝ ስርዓት ያልታየ ቤ ተ መስጊድን ደፍሮ ሰዎችን መደብደብ፣ ማሰርና መግደል በአንዋር መስጊድ ጀምሮ በልዩ ልዩ የሀገራችን ከተሞችና ትናንሽ ቀበሌዎች ማካሄዱን ተያያዘው።
ይህ አፈናና ግድያ ግን ትግሉን ለጊዜው ትንሽ ያለዘበ ቢመስልም ‘ድምጻችን ይሰማ’ በሚል የተደራጀው አካል የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ጥያቄ በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንዲሁም ለፍትህ ተቆርቋሪዎች በሰፊው በማስተዋወቅ የኢህአዴግን አስከፊ በደል ለማሳወቅና ትግሉም ቀጣይነት አንዲያገኝ አድርጉአል። ከዚህ ባለፈም በልዩ ልዩ ስልት የተካሄዱት ትግሎች፣ በኋላ የተቀጣጠሉት ሕዝባዊ ትግሎች ጥቅም ላይ ያዋሏቸውና ውጤታማ የሆኑ የትግል ተሞክሮዎች በርካታ ናቸው። በፈይሳ ሌሊሳ አማካኝነት አለም አቀፍ አውቅና ያገኘው ሁለት አጅን አቆላልፎ ወደላይ በማሳየት ተቃውሞን መግለጽ ጅማሮውን ያገኘው በዚሁ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በየመስጊዱ ይካሄድ በነበረው የተቃውሞ አንቅስቃሴ ወቅት ነበር።
በኦሮሚያ የተካሄደውና በመካሄድ ላይ ያለው ትግል
የአዲስ አበባ የተቀናጀ “ማስተር ፕላን” ተብሎ የሚታወቀው በፌደራል መንግስት ተቀርጾ፣ እንደተለመደው ለይስሙላ እንኳን ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ያካባቢ ከተሞች ተጠሪዎችና የህብረተሰብ ክፍል ጋር ምንም አይነት ውይይት ሳይካሄድ የወጣው ሰነድ የዛሬ ሁለት አመት የመጀመሪያ ተቃውሞ የገጠመው አምቦ ዩኒቨርሲቲ ከሚገኙ ተማሪዎች ነበር። ይህን ከተማሪዎች የተሰነዘረ ተቃውሞ፣ በእንዴት ተደፈርኩኝ በሚል፣ መንግስት ርህራሄ በጎደለው መንገድ የወሰደው የቅጣት እርምጃ በአንዳንዶች ግምት ወደ ሰባ የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈና መቶዎችን ያቆሰለ፣ ከዚህ ያለፈ ቁጥር ሰዎችን ወደ እስር የሰደደ በመሆን ተጠናቅቆ ነበር።
መንግስት በወሰደው አረመኔያዊ እርምጃ “ማስተር ፕላኑን “ አስመልክቶ የነበረው ተቃውሞ ለጊዜው ረገብ ያለ የነበረ ቢመስልም፣ ከአመት በኋላ ጊንጪ ከተማ የሚገኝ ትምህርት ቤት ቦታን፣ ለአልሚ ለመስጠት በሚል በተንቀሳቀሱ የመንግስት ህይሎች ላይ ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ያስነሱት ተቃውሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ሰደድ እሳት ወደ አብዛኛው የኦሮሚያ ክልል ተዛመተ። ይሄ ባብዛኛው በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆችን ማእከል አድርጎ መቀጣጠል የጀመረው ተቃውሞ፣ የሁለተኛ ደረጃና ከዛም በታች ያሉ ተማሪዎችን ማካተት ሲጀምርና በተለይም የተማሪዎቹን ቤተሰቦችና የየአካባቢውን አርሶ አደር ወደ ተቃውሞው ጎራ መሳብና ጥንካሬ መያዝ፣የኢህአዴግን መንግስት ትልቅ ድንጋጤ ውስጥ ከተተው።
የተቃውሞው ስፋትና ጥልቀት ያስደነገጠው መንግስት ፣ ተቃውሞውን ይገታልኛል ብሎ ያሰብውና ተግባራዊ ያደረገው የህዝብን ድምፅ ማዳመጥ ሳይሆን፣ የተለመደውን የሀይል እርምጃ በጅምላ ተቃውሞ ታይቷል በተባሉት ስፍራዎች ላይ በማካሄድ ነበር። ይሄ የጅምላ የሀይል እርምጃ ወንድ ከሴት፣ ልጅ ከአዋቂ፣ ሽማግሌና አሮጊት ሳይለይ የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈ በርካቶችን ደግሞ የአካል ጉዳተኛ ያደረገ ነበር። መንግስት የወሰደው አስከፊ እርምጃ ግን፣ መንግስት ያሰበውን ውጤት ሳይሆን በተቃራኒው የህዝብ ቁጣ የበለጠ ገንፍሎ እንዲወጣ በማድረግ፣ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ተቃውሞ በየከተሞችና እንዲሁም በአብዛኛው የኦሮሚያ ገጠር ቀበሌውች ተስፋፋ።
የተቃውሞው ጥልቀት፣ ስፋትና፣ ቀጣይነት ያሳሰበው ኢህአዴግ አድርጎት የማያውቀውን “እኛ ድሮም ያለ ህዝብ ይሁንታ ምንም ነገር አድርገን አናውቅም”በሚል ቅጥፈት “ማስተር ፕላኑ” መታጠፉንና ከእንግዲህም ማናቸውም ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ህዝብን አወያይቶና አሳምኖ ተግባራዊ እንደሚሆን በይፋ አወጀ። በኢህአዴግ ታሪክ የማይታወቀውን በጠቅላይ ምኒስትሩ በኩል የህዝቡን ጥያቄዎች ትክክለኛነት ከመቀበልም በላይ ለሰዎች ህይወት መጥፋት ይቅርታን ጠየቀ። (በጎን እነ አባይ ፀሀዬ ልክ እናስገባዋለን -የኦሮሞን ማስተር ፕላን ላይ ያለ እምቢተኝነትን መሆኑ ነው-ብለው ሲደነፉ ሾልኮ በወጣ የድምፅ ቅጂ የተገኘ ቢሆንም የትግሉ ግለት፣ ይሄንንም እንኳን በአደባባይ ወጥተው እንዲክዱ አስገድዷቸዋል)
ችግሩ ግን ኢህአዴግ ዘገምተኛ በሆነ መንገድ ተጉዞ ውሳኔውችን ወደ መቀልበስና ይቅርታ ወደ መጠየቅ በገባበት ወቅት በኦሮሚያ ውስጥ የሚካሄደው ትግል በታላቅ ፍጥነት በመጓዝ አንዳንድ ውሳኔውችን ከማስለወጥ ባሻገር ፣ ለረጅም ጊዜ ህብረተሰቡን አፍኖ መሬቱን በልማት ስም ዘርፎ አናቱ ላይ የተፈናጠጠውን የኢህአዴግ ስርዓት ከነአካቴው መለወጥ አለበት ወደሚል ድምዳሜ ተሻግሮ ተግባራዊ ትግል የሚያካሂድበት ወቅት ነበር።
በአማራው ክልል የተነሳው ትግል
በኦሮሚያ የሚካሄደው ትግል ፋታ አልሰጥ ብሎ በቀጠለበት ወቅት ለኢህአዴግ እንደ ዱብ እዳ የመጣበት በጎንደር የተቀሰቀሰው ትግል ነው። መነሻው የወልቃይት አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ኮሎኔል ደመቀን ለማፈን በፌዴራል ፖሊሶች የተሞከረውን ከማክሸፍ ጋር የተያያዘ ነው።
የህወሃት ቱባ ባለስልጣናትና ደጋፊዎች የወልቃይት ጥያቄ ትናንት የተነሳ ለማስመሰል ቢሞክሩም ጥያቄው ህወሃት አዲስ አበባ ላይ ስልጣን ይዞ፣ ሀገሪቱን በቋንቋ ፌዴራሊዝም እናዋቅራለን በሚል ማካለል ሲጀመር የአካባቢው ሰዎች በተቃውሞ ድምፃቸውን እንዳሰሙ የትናንት ትዝታ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ህለት አዛውንት ለወቅቱ የሽግግር ፕሬዘዳንት ለመለስ ዜናዊ እርምጃው ወንድማማች ህዝብ ለዘመናት የሚያጣላና ደም የሚያፋስስ ሊሆን ስለሚችል እንዲታጠፍ የማሳሰቢያና የምልጃ ደብዳቤ ፅፈው እንደነበር ይታወቃል።
በጸረ-ደርግ የትግል ወቅት ለአጠቃላይ ስትራቴጂ ጠቀሜታ ይሰጠኛል በሚል የተቆናጠጠውን ወላቃይት ላለመልቀቅ ወስኖ የነበረው ህወሃት፣ የኛን ይዞታ ሊቃወሙ ይችላሉ የሚሉአቸውን ከቀዬው በጦርነቱ ተፈናቅለው ወደ ሱዳን ገብተው የነበሩ ወልቂቴዎች ወደ ቀድሞ ይዞታቸው እንድይመለሱ ትልቅ ዘመቻ በማካሄድ እንዳከላከሉ ገህድ የሆነ ሀቅ ነው። ከዚህም በላይ አዲስ አበባ በገቡበት አመት ከህወሃት በቅነሳ የተሽኙ ሰላሳ ሺ ወታደሮች ከነመቋቋሚያ ገንዘብ ሰፈራ እንዲያካሂዱ የተወሰነውም ወልቃይት ውስጥ ነበር። ሀገሬውም በክፉ አይን ሳያይ እንደወንድሞቹ አስተናግዶ የነበረ ቢሆንም የባለቤትነት ጉዳይ በተነሳ ጊዜ ግን እጅግ በጣም አዝኖ እንደነበር የሚካድ አይደለም። ለዚህ ነው አሁን አንዳንድ የህወሃት ጮሌዎች ምናለ ችግር ካለና የይገባኛል ጉዳይ ከተነሳ በህዝበ ውሳኔ ማለቅ ይችላል የሚለው ስላቃቸው አሳዛኝ የሚሆነው። ይሄ የሚይስታወሰኝ የእስራኤል ሰፋሪዎች በግዥም ሆነ በማፈናቀል የፍልስጤሞችን ስፍራ ወስደው ሲያበቁ፣ በመሬት ላይ ያለው ነባራዊ እውነታ ፍልስጤሞች የኛ መሬት ነው የሚለውን አያንፀባርቅምና ጥያቄያቸው ውድቅ መሆን አለበት የሚል የጉልበተኛ ክርክር የሚያሰሙትን ነው።
የወልቃይት ጉዳይ ጫሪ ምክንያት በመሆን፣ እንቅስቃሴው ቢነሳም፣ ለሃያ አምስት ዓመት በብአዴን አጋፋሪነት ህወሃት በአማራው ክልል የሚያካሂደው በደልና፣ በተለያዩ ጊዜያትና በበርካታ ስፍራዎች፣ ከበደኖ እስከ አርባጉጉና ጉራ ፈርዳ በአማራው ህዝብ ላይ የሚደርሰው ሞት እንግልትና ግፍ ሞልቶ በመፍሰሱ የተፈጠረ ተቃውሞ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ህወሃት ከተቋቋመበት ጅምሮ የአማራውን ህዝብ እንደዋና ጠላት አድርጎ ሲቀሰቅስበት እንደነበረና ስልጣንም ከያዘ በኋላ እስካሁንም ድረስ ትምክህተኛ የሚል ተለዋጭ ስም በህዝቡ ላይ ለጥፎ መከራውን የሚያበላው በመሆኑ፣ አዲሱ ትውልድ በአዲስ ብሄርተኝነትና በቆራጥ ተነሳሽነት በቃኝ ብሎ የተነሳበት አጋጣሚ ነው።
በኢሬቻ በዓል 2009 የብዙ መቶ ዜጎች ሀይወት መቀጠፍና የህዝብ ቁጣ
ዘንድሮ ቢሾፍቱ ላይ ይካሄድ በነበረው የኢሬቻ በዓል ማሳረጊያ ቀን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ በተሰበሰበበት ዙሪያው በውሃና በገደል ፣ቀሪው መውጫና መግቢያ ደግሞ በታጠቁ ወታደሮች የታጠረ መስክ ላይ ወጣቶችሰላማዊ ተቃውሞ በማሰማታቸው፣ በእንዴት ተደፈርን በሚል በስፍራው በነበሩ አለቆች ትዕዛዝ የኢህአዴግ ወታደሮች፣ በአጠቃላይ የተሰበሰበው ህዝብ ላይ አስለቃሽ ጢስና የጎማ ጥይት (ባለቀለህ ጥይት ነው የሚልም ዘገባ አለ)በብዛት አፈንድቶ ሽብር በመፍጠር የተሰበሰበው ህዝብ ነፍሱን ለማትረፍና ከስፍራው ለማምለጥ ሲል በብዙ መቶ ለሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። የሀያ አምስት አመታት ግፍ ሳያንስ ባለፈው አመት በኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ቀበሌዎችና የገጠር ከተሞች ከአምስት መቶ በላይ ንፁሃንን ህይወት ማጥፋት አልበቃ ብሎ፣ በዚህ ታላቅ መንፈሳዊ በዓል ላይ በማንአለብኝነት ኢህአዴግ በወሰደው እርምጃ በህዝብ ላይ በደረሰው አሰቃቂና መጠነ ሰፊ ሞት በቁጣ የገነፈለው ህዝብ፣ ለቀናት የዘለቀ ከመንገድ መዝጋት እስከ ንብረት ማቃጠልና የመሳሪያ ፍልሚያ ያካተተ ተቃውሞውን በመንግስት ላይ አደረገ።
ኢህአዴግ ይሄ ህዝባዊ ቁጣ ያስነሳውን ተቃውሞ በመደበኛ የፖሊስ ሃይል መቋቋም ስለማልችል ሁኔታው አስገድዶኝ ለስድስት ወር የሚቆይ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጄአለሁ ማለቱን በጠቅላይ ምኒስትሩ አማካይነት፣ ተግባራዊ በሆነ ማግስት ለህዝብ አሳውቋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ የህዝቡ ቁጣና የደረሰውም ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በምንም መለኪያ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያሳውጅ ህኔታ እንዳልነበር በርግጠኝነት እየታወቀ፣ መንግስት ለምን ይሄን እርምጃ ወሰደ የሚል ጥያቄ ለማንሳት እንገደዳለን። በአገራችን ባለፉት አመታት በተለይም ደግሞ ባለፉት አስራ አንድ ወራት በኦሮሚያና በአማራው ክልል እንዲሁም በኮንሶና ሌሎች ስፍራዎች በመካሄድ ላይ ያሉት ትግሎች የስልጣን መሰረቱን እንዳናጉበት የተረዳው ኢህአዴግን በበላይነት የሚመራው የህወሃት ቡድን፣ ትግሉን ቢቻል ለመግታት ካልተቻለም ለማዳከም የወሰዳቸው ማስፈራሪያ እስር፣ ድብደባና ግድያን ያካተቱ ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች የታሰበውን ግብ ሊመቱ አልቻሉም።
ከላይ እንደጠቀስኩት በጎንደር የተነሳው ተቃውሞ ለህወሃት ዱብዕዳ የሆነበት በኦሮሚያ ያለው ተቃውሞ ሳይረግብ በመቀስቀሱ ብቻ ሳይሆን፣ ለሃያ አምስት ዓመታት ሲስራበት የነበረው ሁለቱን አንጋፋና የሀገሪቱን ሁለት ሶስተኛ የሚወክል ህዝብ እርስ በርስ የማናከስ ፕሮጀክት “ በኦሮሚያ የሚደረገው የወንድሞቻችን ግድያ ይቁም”“ በኦሮሚያ የሚፈሰው የኦሮሞ ደም ደማችን ነው”… በሚሉ መፈክሮች እንደ ነጎድጓድና መብረቅ በመላው ሀገር መሰማቱ ነው።ጎንደር ላይ በተካሄደው መሬት አንቀጥቅጥ ሰላማዊ ሰልፍ የተስተጋቡት መፈክሮች ለሁለቱ ታላቅ ህዝብ የትግል አጋርነት መልካም ጅማሮነትን ባበሰረበት ቅጽበት፣ የህወሃት መራሹን መቃብር ቁፋሮ መጀመርን ያበሰረ ነበር። የዚህ የትግል አጋርነት ጅማሮ ለስልጣናቸው የሚያመጣውን ዘለቄታዊ ችግር ወዲይውኑ የተገነዘቡት የህወሃት ቁንጮዎቹ ሳይውሉ ሳያድሩ ዋልጌ የ”ኮምዩኒኬሽን” ሚንስትራቸውን አሰማርተው ፣ በየቴሌቪዥንና ራዲዮ ጣቢያ እየተወዛወዘ የአጋርነት ጅማሮውን ለማጠልሸትና ተጨማሪ መርዝ ለመርጨት ሲውተረተር ከርሟል። ዘመቻው በዚህ ብቻ ሳይገታ፣ የጥፋት መልክተኛ የሆኑቱን አባይ ፀሃዬና ስዩም መስፍንን በቴሌቪዥን አቅርቦ፣ የኛን የበላይነት ተቀብላ የማትኖርን ኢትዮጵያ፣ የጦርነት አውድማ አድርገን ህዝቡን እርስ በርሱ በማናከስ እንደ ሀገር የማትኖርበትን ሁኔታ እንፈጥራለን የሚል እንድምታ ያለው አሰልቺና ባዶ ማስፈራራት ለማካሄድ ሞክረው ነበር።
ይሄ እናባላችኋለን የሚል ሰይጣናዊ የማስፈራሪያ ፕሮፓጋንዳ ህዝብን ከማስበርገግ ይልቅ በበለጠ እልህ ትግሉን እንዲያቀጣጥል ተጨማሪ ነዳጅ ሆነ፣ የዛሬ አስራ አምስት አመት ከላይ እስከታች መበስበሱን ያወጀ ድርጅት እስካሁን ድረስ በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጦ ለመቆየቱ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ላለፉት አስራአንድ ወራት የተካሄዱት ህዝባዊ ትግሎች ግልፅ እንዳደረጉት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንግዲህ፣ በራሱ አንደበት በሙስና የተጨማለቀ፣ ራሱ ያፀደቀውን ህገ መንግስት በየጊዜው የሚደፈጥጥና በውስጡ የማፊያ ቡድኖችን አቅፎ የሚጓዝን የገዢ ስብስብ የመሸከም ትከሻ የለውም። ይሄን የተገነዘበው የህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያወጀው፣ በኢትዮጵያ የተቀጣጠለው ህዝባዊው ተቃዎሞ በያዘው ፍጥነትና ስፋት እየቀጠለ ከሄደ መፍረከረከ የጀመረው ድርጅቱ አጠቃላይ ውድቀት ሊደርስበት ይችላል ብሎ በመፍራት ድርጅቱን ለማዳንና በአገሪቷ ላይ ያለውን የበላይነት ለማስቀጠል የወሰደው እርምጃ ነው ለማለት ይቻላል።
ምን ይደረግ?
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መከታ በማድረግ ከአሁኑ በርካታ ሺህ ዜጎችን በእስር እንዳጎረና አንጻራዊ ሰላምም እያሰፈነ እንደሆነ የሚፎክረው የህወሃት መንግስት፣ በዚህ መጠነ ሰፊ እስር ፣ግድያና አጠቃላይ የሆነ መንግስታዊ ሽብር፣ ጊዜያዊ እፎይታ ያገኝ እንደሆን እንጂ፣ የህዝቡ አልገዛም ባይነትና ትግሉ አሁን በደረሰበት ደረጃ ለረጅም ጊዜ ግፊቱን ተቋቁሞ በስልጣን ይቆያል ለማለት አዳጋች ነው። እርግጥ ነው ግፍና ጭቆና አንገፍግፎት ያለ ተቀናጀና፣ በትግል ሂደት የዳበረ ልምድ ያለው ድርጅት አመራር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ወጥቶ በቃኝ! በማለቱ ብቻ ፍትህና ርትዕ የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይቻላል ማለት እጅግ አስቸጋሪ ነው።
ባለፉት ሃያ አምስት አመታት ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያካሂድባቸው አፈናና፣ አላፈናፍን ባይነት ከራሳቸው ከድርጅቶቹ ድክመት ጋር ተዳምሮ፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ያሉትም ሆነ ውጭ ያሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ህዝብን መርቶ ለድል ማብቃት ይቅርና አመርቂ በሆነ መንገድ ለማታገልም በቂ አቅም የላቸውም።
የተጠራቀመው የህዝብ ብሶት በእንዲህ ያለ ስፋት ተቀጣጥሎ አገር አቀፍ መልክ ሲይዝና መንግስትን ሲያርበደብድ፣ ሱሬውን ሳይታጠቅ የተያዘ መንግስት ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎችም ጭምር ናቸው። በዚህ በተዳከመ ሁኔታ ቢሆንም ፣ባሁኑ ወቅት የድርጅቶች ዋና ሃላፊነት አባሎቻቸው በሙሉ ልብ በህዝባዊው ትግል እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በተሳትፎአቸውም አዳዲስ የትግል አጋሮችን ማፍራት፣ ትግሉ አሰባሳቢ የሆኑ እገራዊ አጀንዳዎችን እንዲይዝ ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ፣ ያላቸውንም ሃይል በበለጠ ማሰባሰብ፣ መቀናጀት ከሚችሉት ጋር መቀናጀትና ድርጅታዊ ጥንካሬአቸውን ማጎልበት መሆን ይኖርበታል። አታግሎና ሁነኛ አመራር በመስጠት ህዝባዊ ትግሉን ስኬታማ ሊያደርግ የሚችል ድርጅት ባይኖርም፣ የህዝብ ምሬት አሁን በደረሰበት ደረጃ፣ ምንም እስሩና ግድያው ቢበረታ እንቢተኝነቱ የሚቀጥል በመሆኑ አገሪቷን ወደ ጦር ቀጠናነት ሊለውጥ፣ የሀገሪቱንም ህልውና ሊፈታተን የሚችል አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር እነደሚችል ግልጽ እየሆነ ሄዷል።
የህወሃት ቁንጮዎች አገሪቷ ላይ ያላቸውን ሁለንተናዊ የበላይነት ለማስቀጠል በሚል ያወጁት ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው በአገሪቱ የመከላከያና የደህንነት እንዲሁም የልዩ ልዩ የፖሊስ ሃይል እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህ ተቋማት ሃገራዊ ተቋማት እንደመሆናቸውና አገሪቱም አሁን በምትተዳደርበት ህገ መንግስት ሃላፊነታቸው በዋናነት የሀገሪቷን ህልውና ማስጠበቅና ህገ መንግስቱን ማስከበር እንጂ ስልጣን ላይ ያለውን ፣ ህዝብ በቃኝ መረረኝ ብሎ፣ እንዲወርድ የሚጠይቀውን ቡድን ህይወት ማራዘም እንዳልሆነ ይታወቃል።
ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ አሁን በያዘው ጎዳና ከቀጠለና የሀገሪቷ መከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ሃይሎች የሃገሪቱን ህልውና የማስጠበቅ መሰረታዊ ተግባር ወደ ጎን ትተው፣ የአንድ ጠባብ ቡድንን ዓላማና ፍላጎት ተግባራዊ የማድረግ እንቅስቃሴያቸውን ከቀጠሉና የተደገሰውን የጥፋት ድግስ በህዝቡ ላይ ካደረሱ፣ የሰራዊቱን መፍረክረክ ብቻ ሳይሆን፣ አገራችንን በፍጥነት ወደ መበታተን እንደሚይስኬዷትና ፣በዚህም ታሪክ በፍጹም ይቅር የማይለው ሀገራዊ ክህደት እንደሚፈጽሙ ሊያምኑ ይገባል።
በአሁኑ ወቅት ታሪክ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ታላቅ ፈተና ከፊቱ ደቅኗል። የኢህአዴግ ቁንጮ ሰዎች የፖለቲካ ስልጣኑን በመቆጣጠር ዛሬ እነሱ፣ የስልጣን ማማውን ሙሉ ለሙሉ ካልተቆጣጠሩ፣ የህዝብ ብሶትና በደል፣ ብሎም የሀገር መበታተን ደንታ የማይሰጣቸው መሆናቸውን በግልጽ እያሳዩ ያሉበት ወቅት ነው። በመሆኑም፣ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ልትወጣው ወደ ማትችለው አዘቅት ሊከቱ የሚፈልጉ እኒህ እኩይ አካላት መሳሪያ መሆንን አሁኑኑ ገትታችሁ፣ የሀገርን ህልውናና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታችሁን የመወጣት ታሪካዊ ሃላፊነት ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባችኋል።
ኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን አደጋና የገባንበትን አሳሳቢ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የመከላከያ ሰራዊቱና የፀጥታ ሃይሎች ብቸኛ አማራጭ የሚሆነው፣ መቶ በመቶ ምርጫውን አሸንፈን የህዝብ ይሁንታ አግኝተን ነው መንግስት የመሰረትነው ነው የሚለው የፖለቲካ ስልጣኑን የተቆጣጠረው ቡድን በፍፁም ተአማኒነት የሌለው መሆኑን፣ ህዝብ ወክለን ነው ፓርላም የተቀመጥነው የሚሉትም አንዳችም ውክልና እንደሌላቸው ያለፉት አስራ አንድ ወራት የህዝብ እንቢተኝነት በማያወላዳ መንገድ በማረጋገጡ፣ ቡድኑ ፓርላማውን አሁኑኑ በትኖ አዲስ ሀገራዊ ምርጫ እንዲያደርግ ጠንከር ያለ ጫና ማድረግ ነው የሚል እምነት አለኝ።
በመንግስት አካባቢ የተሰባሰበው ይሄ አጥፊ ቡድን ጫናውን አልቀበልም ብሎ እንቢተኝነትን የሚመርጥ ከሆነ ፣ ለሀገር ህልውናና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ ከስልጣን አግዶ ብሄራዊ መግባባትና ድርድር የሚካሄድበት የጊዜ ገድብ አበጅቶ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሁኔታውን እስከ ማመቻቸት የሚሄድ እርምጃ ሊወስድ እነድሚችልም የመከላከያ ሰራዊቱና የፀጥታ ሃይሉ ማሳወቅ ይኖርበታል። ይሄንን በማድረግም የተቋቋመበትን መሰረታዊ ዓላማ ማለትም የሀገርን ህልውናና ህዝብን ከክፉ መጠበቅን ተግባራዊ ያደርጋል ።
ፓርላማው ይበተን! ሃገራዊ ምርጫ አሁኑኑ ይካሄድ! የህዝብ እንቢተኝነት ወቅታዊ ያደረጓቸው ጥያቄዎች ናቸው።

LEAVE A REPLY