ህወሓት ቀውስ ዉስጥ መሆኗ ይታወቃል። ለዚህ ምክንያትም የቀድሞ የህወሓት አመራር ብልሹነት ነው። የህወሓት መሪዎች የግል ስልጣናቸው ማደላደል እንጂ ተከታይ መሪዎችን ማፍራት ላይ አልተሰማሩም ነበር። ይሄው ህወሓት ያለ ብቁ መሪ ኦና ሆና ቀረች። ህወሓት እንደ ፓርቲ የቆመችው ስልጣንን ተገን አድርገው ሃብት ለመሰብሰብ በተሰባሰቡ ሙሰኞች እንጂ የሚያገናኝ ርእዮተ ዓለም ስላላቸው አይደለም።
ህወሓት በአመራርና መርህ እጦት ምክንያት ምሁራን በጠላትነት ፈርጃ አላስጠጋ ብላለች። ወጣቶችም ለመመለመል ፍቃደኛ አይደለችም። በተፈጠረው ክፍተት ምክንያት አቶ አባይ ወልዱ ለሊቀመንበርነት ደረጃ በቅቷል። ትግራይም ምንም ለውጥ ሳታሳይ ለብዙ ዓመታት ደርቃ ቆይታለች።
አሁን አባይ ወልዱ ከስልጣን እንዲወርድ የሚወተውት በዝቷል። አባይም ስልጣኑን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አይደለም። ግን አባይ ስልጣን ቢለቅ ማን ሊተካው ነው? ህወሓትኮ ሰው የላትም። በቃ መሪ ሊሆን የሚችል ሰው የለም፤ አባረው ጨርሰውታል።
አባይ ወልዱ ትግራይ ዉስጥ ያለውን ኔትዎርኩ በመጠቀም አልወርድም ሲል የተበታተነው የነ ስብሃት ነጋ ቡድን ደግሞ ተመልሶ ለማንሰራራት ሲል አባይን ከስልጣን ለማውረድ እየሞክረ ነው። የነ ስብሃት ነጋ ቡድን ከአባይ ወልዱ በፊት ስልጣን ተቆጣጥሮ የነበረና በቤተሰባዊ ሙስና የተጨማለቀ ነው። የአባይ ቡድን የስብሃትን ኔትዎርክ በጣጥሶ መበተኑ አድናቆት አትርፏል። ምክንያቱም የነ ስብሃት ቡድን በጣም አድላዊ እንደነበር ይታወቃል።
በነ አባይ ወልዱና በነ ስብሃት ነጋ ቡድን ያለው ልዩነት የነ ስብሃት ቡድን ተንኮል መሰረት ያደረገ የቤተሰብ ስርዓት ለመመስረት የሚንቀሳቀስ ሲሆን የነ አባይ ወልዱ ቡድን ደግሞ ድንቁርና መሰረት ያደረገ የመሃይማን ስብስብ ነው። የነ ስብሃት ቡድን ስልጣን ቢይዝ ትግራይ በኔትዎርክ አሳስሮ የተወሰኑ ግለሰቦች ተጠቃሚ አብዛኛው ህዝብ ግን ተመልካች ያደርገዋል። በጣም መርዘኛ ነው። የኣባይ ቡድን በስልጣን ቢቀጥል ደግሞ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያመጣ ትግራይ የኋሊት ጉዞዋን ትቀጥላለች።
በዓረና ፓርቲ ላይ የሚኖራቸው አቋም ደግሞ፤ የነ አባይ ቡድን ዓረና በትእዛዝ እንዲጠፋ መፈለጋቸው አይቀርም። የነ ስብሃት ቡድን ግን በዓረና ጉዳይ በቀጥታ ሳይገቡ ሰው ልከው ለማፍረስ ይሞክራሉ። ግን ሁለቱም አይሳካላቸውም። ምክንያቱም የህዝብ ድጋፍ የላቸውም። መሪነት የላቸውም።
አባይ ወልዱ ከስልጣን ዉረድ ሲባል “ከስልጣን መውረድ ካለብን፣ ሁላችን እንውረድ፤ አለበለዚያ ግን ከስልጣን የመውረዱ ጉዳይ እኔ ላይ ብቻ የሚያነጣጥር ከሆነ የያንዳንዳቹ የሙስና ወንጀል አጋልጥና ወህኒ ትወርዳላቹ” ሲል አስፈሯርቷቸዋል። ይህን ስትባል ሙሰኛ ሁላ ጥያቄዋን ትታ ተበተነች። የአባይ ወልዱ ብቃት ሙሰኛ አለመሆኑ ብቻ ነው። ሌልው ሁሉ በሙስና የጨቀየ ነው። እናም አባይን ዉረድ ለማለት ሞራል ያንሰዋል። እናም አባይ ትግራይን ይዞ ገደል መግባቱ አይቀሬ ነው፤ ህወሓት በግዜ ካልተወገደ።
አባይን ከስልጣን ለማውረድ ገምጋም ሳይሆን ሎቢ ነው የሚያስፈልገው። አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ያለበት የ አቶ አባይን ለማግባባት ጥረት ጀምሯል። አባይ ከስልጣን ለመውረድ ፍቃደኛ እንኳ ባይሆን አዲስ የካበኔ አባላት ሊያዋቅር ግን ይችላል። ግን ያልነበረው ከየት ያመጣል? ምሁራን ሊሾም ? ከምሁራን ጋር እንዴት ሊግባባ? ወጣቶች ሊመርጥ ? እንዴት ወጣቶችን ያምናል? ወጣቶችና ምሁራን ማመን ኮ የህወሓት ባህል አይደለም።
እናም አማራጭ ፓርቲ ያስፈልጋል። ህወሓት ማስወገድ እንጂ መጠገን አይቻልም።