(ሲያትል በነበረው ስብሰባ ሊቀርብ የነበረ ጽሑፍ ነው፤ ፕሮግራሙ ላይ እንዲቀርብ ለ27 ደቂቃ የተቀዳው ሪከርዱ በቴክኒክ ችግር ባለመሥራቱ መቅረብ አልቻለም፤ እኔም አዘጋጆቹም በጣም አዝነናል፡፡ ይህን ጽሑፍ በማዘጋጀት በአዲስ አበባ እና የጎንደር ዩንቨርሲቲዎች ያሉ የአማራ ምሁራን አግዘውኛል፡፡ ምስጋና ይገባቸዋል፤ ብዙ የአማራ ምሁራን ከጀርባ ሆነው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እጅግ ያስደስታል፡፡ በነጻነታችን ጊዜ ስማቸውን ከፍ አድርገን ሥራቸውን እንዘክራለን፡፡ ለማንኛውም ላቀርበው የነበረውን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል እንሆ)
1. እንደመግቢያ
ወሮበላው የወያኔ ቡድን ሥልጣን የያዘበት 1983 ዓ.ም. ለእኛ ለአማሮች ወገኖቻችን በጅምላ የሚታረዱበትን፣ በገፍ የሚፈናቀሉበትንና በዘረኞች ያለማቋረጥ የሚሰቃዩበትን ዘመን ያዋለደ ክፉ ዘመን ነው፡፡ ይህ ጊዜ የአማራ ሕዝብ ከጨለማ ወደባሳ ጨለማ የገባበት፣ በሕዝባችን ላይ የታወጀው የጥፋት ደወል የተደወለበት፣ በርካቶች በአማራነታቸው የታረዱበት፣ ቤት ንብረታቸውን በትነው ለዘመናት ከኖሩባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉበትና በአገራቸው ባይተዋር ሆነው እንዲኖሩ የተወሰነበት የክፉ ጊዜ መጀመሪያ ነው፡፡ በደርግ አምባገነናዊ አገዛዝ ልጆቹን ሲነጠቅ የኖረው፣ ከየትኛውም ሕዝብ በላይ ልጆቹን ለጦርነት እንዲያዋጣ ሲገደድ እና በኮታ፣ በግብር ወዘተ. ሲማቅቅ የቆየው ሕዝባችን፣ ከመከራ ወደባሰ መከራ እንዲገባ የተደረገበት ጊዜም ነው፡፡
በሺሕዎች የሚቆጠሩ የአማራ ልጆች ለኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩልነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ እንዳልታገሉ እና የንጉሠ ነገሥቱንም ሆነ የደርግን ሥርዓቶች ታግለው መስዋዕትነት እንዳልከፈሉ፣ ሕዝባችን ባለፉት ሥርዓቶች ከሌላው ሕዝብ በተለየ መልኩ እንደተጠቀመና ያለፈው ሥርዓት ተቆርቋሪ እንደሆነ ተቆጠረ፤ መብታቸውን የሚጠይቁ አማሮች ሁሉ ባለፈው ሥርዓት ናፋቂነት፣ በትምክህተኝነት፣ በነፍጠኝነት ወዘተ. እየተወነጀሉ ከየአቅጣጫው የጥቃት ሰለባ ሆኑ፤ የአማሮች ከየአካባቢው መሳደድና መገደል ለማንም የማይገደው ተራ ጉዳይ ሆነ፡፡ በዘመነ ወያኔ በሕዝባችን ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው ግፍ ገና በዝርዝር ሊጠናና ሊተነተን የሚገባው ትልቅ የቤት ሥራ ነው፡፡
ጸረ አማራው የወያኔ ቡድን ንጹሐን አማሮችን እያደነ እንደጨፈጨፈ፣ ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀለ፣ ሁሉም ሕዝብ በአማራ ላይ እንዲዘምት ሰነድ አዘጋጅቶና የመንግሥት በጀት በጅቶ እንደቀሰቀሰ፣ ተስፋ የሚጣልባቸውን የአማራ ልጆች እስር ቤት እያጎረ የቶርቸር ሰለባ ሲያደርግ እንደቆየ ወዘተ. ወዘተ. አይዘነጋም፡፡ በሚያሳዝን መልኩ፣ የአማራ ሕዝብ በዚህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ መጠነ ሰፊ ውርጅብኝ ሲወርድበት የቆየ እና አሁንም ይኸው የዘር ማጥፋት ጦርነት ግልጽ በሆነ መልኩ ታውጆ የቀጠለ ቢሆንም፣ ለሕዝባችን የሚጮህለት ኃይል የለም፡፡ የሕዝባችን በደል የሚገደው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅትም አልተገኘም፡፡ የዚህ ነብሰ ገዳይ ቡድን ወዳጅ የሆኑ ኃያላን አገሮችም በሕዝባችን ላይ የታወጀውን የዘር ፍጅት እያዩ እንዳላዩ ማለፍን መርጠዋል፡፡ በአጭሩ ለአማራ ሕዝብ ከራሱ ውጪ ማንም እንደማይጮህለት፣ ማንም እንደማይገደው በሚገባ ተረጋግጧል፡፡ ለዚህ ነው ሕዝባችን በሕዝብ ደረጃ ተደራጅቶ ከመታገል ውጪ ምርጫ የለውም የምንለው፡፡
እንደአማራ ተደራጅተን የምንታገለው ራሳችንን ከወያኔ የዘር ፍጅት ጦርነት ለመከላከል፣ ራሳችን ከጥፋት ለማዳን፣ የሕዝባችን ቀንደኛ ጠላት የሆነውን ወያኔን ከሕዝባችን ጫንቃ ላይ አሽቀንጥረን ለመጣልና የአማራ ሕዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ለማስቻል ነው፡፡ ትግላችን የአማራ ሕዝብ መሳደድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆምና ሕዝባችን በነጻነት እንዲኖር ለማስቻል ነው፡፡ ትግላችን የአማራ ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡
2. በትግላችን ምን አሳካን?
ከሁሉ አስቀድሞ ለአማራ ሕዝብ ነጻነት ግንባሩን አሳልፎ የሚሰጥ፣ የማይፈራና ጠላትን እረፍት የሚነሳ ታጋይ ትውልድ ፈጥረናል፡፡ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ እስካሁን ባካሔድነው ትግል ማን የአማራ ሕዝብ ጠላት እንደሆነ፣ ማን ወዳጃችን እንደሆነ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ይዘናል፡፡ ይህም በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በሕዝባችን መሃል ተሰግስገው፣ ያጎረሳቸውን እጅ የሚነክሱ ውለታ ቢስ ወያኔዎችን መንጥረን ማስወጣት መጀመራችንም ትልቅ ድል ነው፡፡ ከሁሉ በላይ የአማራ ሕዝብ ልጅ አዋቂ፣ ሴት ወንድ፣ አርሶ አደር ከተሜ ሳይል ሁሉም በአማራነት ተደራጅቶ መታገል እንዳለበት ግንዛቤ መያዙ ትልቅ ስኬት ነው!!!
ባሌ ላይ ያለው አማራ መተማ ስለሚሞቱት ወገኖቹ የሚቆጭበት ብቻ ሳይሆን ጎንደርና ጎጃም ድረስ ሔዶ ትግሉን የሚቀላቀልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ጎንደር ለተገደሉት ወንድሞቻቸው ደሴ ላይ ሐዘን የሚቀመጡ፣ ጎጃም ላይ የታረዱ ወንድሞቻቸውን ደም ለመመለስ ማጀቴ ላይ የሚመክሩ አማሮችን አግኝተናል፡፡ ኅብረቱ ከዚህ በላይ እንዲጎለብትና ሥር እንዲኖረው መኮትኮት ከሁሉም የአማራ ልጆች የሚጠበቅ ትልቅ የቤት ሥራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የአማራ ብሔርተኝነት ማንም ባልጠበቀውና ባልገመተው ፍጥነትና ብስለት ብዙ እርምጃዎች ወደፊት እንደሔደ ታይቷል፡፡
ሕዝባችን ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ያለውን ወገንተኝነት በሳልና አርቆ አስተዋይ በሆነ መልኩ በማሳየት፣ ወያኔ አማራውን እንደጭራቅ ስሎ ሲሰብከው የኖረበትን ጸረ ሕዝብ ተግባር መና አስቀርቶታል፡፡ የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት መመሥረትና አብሮ መኖር እንደሚፈልግ በግልጽ ቋንቋ ተናግሯል፡፡ ይህ ሁሉ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነው፡፡
በሌላ በኩል ወያኔ በአማራና በኦሮሞ ሕዝቦች ትግል ተርበትብቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ በኢትዮጵያውያንም ሆነ በመላው የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ፊት እርቃኑን ቀርቷል፡፡ ይህም በወገኖቻችን መስዋዕትነት የተገኘ ትልቅ ድል ነው፡፡ ብዙዎች ወያኔ አምባገነን መሆኑ እንዲታወቅ ብዙ ለፍተዋል፡፡ ሁላችንም ወያኔ ጸረ ሕዝብና ጸረ ዴሞክራት ቡድን መሆኑን በተመሳሳይ ደረጃ ባለመረዳታቸን፣ አንዱ እስኪ ጊዜ እንስጣቸው እያለ የሚያወላውልበት፣ ሌላው አብሮ እየሠራ ሕዝብ የሚበድልበት፣ ሌላው እውነታው የገባውና ጥያቄ የሚጠይቀው የቶርቸር ሰለባ የሚሆንበትና የሚገደልበት ድብልቅልቅ ያለ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ የዚህ ዓመት ትግል ይህንን ሁኔታ በማያወላውል መልኩ የለወጠ፣ ከሞላ ጎደል ሁላችንም ወያኔ ፍጹም ግፈኛና ጸረ ሕዝብ ቡድን መሆኑን የተረዳንበት እንቅስቃሴ በመሆኑ ትልቅ ስኬት ያስገኘ ትግል ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ወያኔ ሊያጭበረብር የሚችልበት ምንም ዓይነት ዕድል የለውም፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያችን ሲመዘብራት የኖረው አንድ በመሣሪያ ኃይል የተንጠለጠለ ያገጠጠ ያፈጠጠ አናሳና አምባገነን ቡድን መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ሆኗል፡፡
የታወጀው ጸረ ሕዝብ አዋጅ ወያኔ ምን ሊሆን እንደሚችል፣ ሥልጣኑን ለመጠበቅ እስከምን ደረጃ ድረስ ሊዘቅጥና ፋሽስታዊ ተግባር ሊፈጽም እንደሚችል በግልጽ ያሳየ ሰነድ ነው፡፡ ወሮበላው ቡድን ይህን ጸረ ሕዝብ አዋጅ ‹ከሞት ተነስቷል› ያለውን አማራን ለማንበርከክ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እየገደለና በገፍ እያሰረ የቶርቸር ሰለባ በማድረግ እየሠራበት ነው፡፡ ሆኖም ይህ ፋሽስታዊ ቡድን ከዚህ በኋላ የትኛውንም ያህል ቢወራጭ፣ የትኛውንም ያህል ቢገድለንና ልጆቻችን በገፍ እያሰረ ግፍ ቢፈጽም በምንም ዓይነት ሁኔታ ለእነዚህ ግፈኞች የሚንበረከክ አማራ ከቶ አይኖርም፡፡
ወሮበላው ቡድን መብታቸውን የጠየቁ ንጹሐን የአማራ ልጆችን በግፍ ጨፍጭፎ ሲያበቃ፣ በሕዝባቸን ላይ የፈጸመውና በመፈጸም ላይ የሚገኘው ዘግናኝ ፍጅትና ቶርቸር አልበቃው ብሎ፣ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ ለማስቀየስ መሣሪያ ደግኖ ‹በጸረ ሰላም ኃይሎች ተወናብደን ንብረት አውድመናል፤ መንግሥት ለመገልበጥ ተንቀሳቅሰናል፤ ወዘተ.› እያሉ በሕዝብ ፊት አንዲዋረዱና አንገታቸውን እንዲደፉ በየዕለቱ እየሠራ ይገኛል፡፡ ደንቆሮው የወያኔ ቡድን ያልተረዳውና ሊረዳውም የማይችለው ቁም ነገር፣ የተጣላውና ደም የተቃባው የወንድሞቹንና የእህቶችን ደም ሳይመልስ ከማይተኛው በሚሊዮኖች ከሚቆጠረው የአማራ ወጣት ጋር መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ የባንዳ ልጆች ያልተረዱትና ሊረዱትም የማይችሉት ቁም ነገር፣ ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት የአማራ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ እየተበደለ በዝምታ የኖረው ለኢትዮጵያ አንድነት ካለው ቀናዒነት የተነሳ መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ የለየላቸው ወሮበሎችና ነብሰ ገዳዮች ያልተረዱት ቁም ነገር፣ ከዚህ በኋላ የአማራ ልጅ የወንድሞቹንና የእህቶቹን ደም ሳይመልስ፣ ወያኔን አሽቀንጥሮ ጥሎ የአማራን ሕዝብ ነጻ ሳያወጣና የሕዝቡን ክብር ሳይመልስ የማይተኛ መሆኑን ነው፡፡
ወያኔ በሚቆጣጠረው ሚዲያ ቱልቱላውን እንደሚነፋው ይህ አዋጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ሊያመጣ አልቻለም፤ አይችልምም፡፡ ይልቁንም የዚህ አዋጅ መታወጅ ሕዝቡ ‹ወያኔ ከሕዝባችን ጫንቃ ላይ አሽቀንጥረን እስካልጣልን ድረስ ከመታሰር፣ ከመሳደድና ከመሞት አናመልጥም፤ ወያኔ ካልተንኮታኮተ ሰላም የለንም፤ ወያኔ እስካለ ድረስ ከመሸበርና ከመታወክ አንገላገልም› የሚል ግልጽ አቋም እንዲይዝና በሚችለው ሁሉ ይህን ነብሰ ገዳይ ቡድን እንዲታገለው ዕድል ይከፍታል፡፡ መሣሪያ ተደግኖብን፣ በየዕለቱ እየተሳደድን፣ እየታሰርንና ወገኖቻችንን እየተነጠቅን ምንም ዓይነት ሰላም አይኖረንም፡፡ የሰላም ጠላት፣ የሁከትና የሽብር አባት የሆነው የወያኔ ቡድን እስካልተንኮታኮተ ድረስ የአማራ ሕዝብ ሰላም አይኖረውም፡፡ በዚህ ጸረ ሕዝብ አዋጅ የሚሸበር አማራ የለም፡፡
የዚህ አዋጅ መታወጅ ትግሉን ብዙ እርምጃ ወደፊት ያራምደዋል እንጂ አንዲትም ጋት ወደኋላ አይጎትተውም፡፡ ይህ ጸረ ሕዝብ አዋጅ እርስ በርሳችን እንዳንረዳዳ ሊያደርገን አይችልም፤ አዋጁ ድርጅቶቻችን እንዳንደግፍና እንዳናጠናክር ሊያደርገን አይችልም፤ አዋጁ መስዋዕቶቻችንን እንዳናስብ፣ ስለእነሱ የትግል ታሪክ እንዳንጽፍና ቤተሰቦቻቸውን እንዳንረዳ ሊያግደን አይችልም፤ አዋጁ ስለቀጣዩ የትግል ስትራቴጂያችን እንዳንመካከር ሊያደርገን አይችልም፤ አዋጁ ወያኔን እንዳንጠላና እንዳንጸየፍ ሊያግደን አይችልም ወዘተ. ወዘተ. እንዲያውም ከላይ እንደተጠቀሰው ‹ወያኔ ጸረ ሕዝብና ጸረ ዴሞክራሲ ዘረኛ ቡድን ነው› በሚለው መሠረታዊ ሐቅ ላይ ብዥታ የነበራቸው እና ትግሉን ወደኋላ ሲጎትቱ የነበሩ ወገኖች ሁሉ በዚህ አዋጅ ምክንያት ትልቅ ግንዛቤ ስለጨበጡ ትግሉ ብዙ እርምጃ ወደፊት ሄዷል፡፡
(ይቀጥላል)