Ethiopia Nege/፦ በደርግ መንግስት የመጨረሻውን ዘመን ከህወሃት/ሻዕቢያና ከኦነግ ጋር በለንደኑ ድርድር የተሳተፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ተስፋዬ ዲንቃ በጥገኝነት በሚኖሩበት አሜሪካ ሀገር ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ በቨርጅኒያ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ህይወታቸው ማለፉ የተገለጸው የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ተስፋዬ ዲንቃ በአጭር ጊዜ ህመም ህይወታቸው ሊያልፍ እንደቻለ ሲገለጽ በደርግ ዘመነ መንግስት የመጨረሻ ጊዜያት ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሚኒስቴርነት ከማገልገላቸውም በተጨማሪ በተለያዩ የስልጣን እርከን በሃላፊነት ይሰሩ እንደነበር ይታወቃል።
በደርግ ባለስልጣናት ዘንድ የከፍተኛ ትምህርት ከተከታተሉ ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ በአምቦ የመጀመሪያ ደረጃ፣ በአዲስ አበባ ዊንጌትን ጨምሮ በአሜሪካንና በቤይሩት በተለያዩ ዩኒቨርስቶዎች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የበስደት አሜሪካን ሀገር መኖር ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ የአለም ባልክን ጨምሮ በልዩልዩ አለማቀፍ መስሪያ ቤቶች አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ከባለቤታቸው ወ/ሮ ትርሲት አበጋዝ ጋር አራት ልጆቻቸውን ያሳደጉ ከመሆናቸውም በላይ አራት የልጅ ልጆችን ያዩት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ በ1939 ዓ.ም እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በአምቦ የተወለዱ ሲሆን በ77 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉን ለመረዳት ችለናል።
አቶ ተስፋዬ ዲንቃ የሽኝትና የጸሎት ስነ ስርአት በነገው እለት ቅዳሜ ታህሳስ 1 ቀን 2009 ዓ.ም እንደሚፈጸም የሽኝት ስነስርአት አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።