ጭብጡ ላይ አተኩሩ…. አታስቀይሱ!
ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ – የእምቧይ ካብ ”
ዮፍታሔ ንጉሴበዚህ ወራት ወይም ስሞን በዕውነት የታጨቀ ጽሁፍ ለቅቄ ነበረ። ”ከአድርባይ ብዕር ባዶ ወረቀት ብዙ ይናገራል” ነበር ያለው ነፍሱን ይማረውና በዓሉ ግርማ። ብዕሬ አቀባብላ የተኮሰችው ጥይት ዕውነት ነው። ዕውነት ለመናገር የደፈርኩበት ጽሁፍ እኔንም ሆነ ዕውነት ማድመጥና ማንበብ የናፈቃቸውን አርክታለች። ሃሰትን ለመናገር ባልደፈረችው ‘እስኪሪብቶዬ’ ህሊናዬ ነጻ ነው። ከምንም በላይ እኔን የሞሞግተኝ ብዕር ከሰገባው አላወጣሁምና ውብ እንቅልፎች መደዳውን ወስደውኛል። ”ተመስገን” እንዲሉ:- ‘ተመስገንን’ አዜምኩኝ።
”ከሺህ ጦረኛ አንድ ወሬኛ እፈራለሁ። ”አዶልፍ ሂትለር
በዘር ፍጅት የሚጠቀሰው ሂትለር የተናገረውን ነው ከላይ ያሰፈርኩት። ስልጣን ከመያዙ በፊት እራሱ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሲያገለግል የነበረው ሂትለር ”የታንክ ጋጋታን፣ የመድፍ እሩምታን አያስፈራኝም” ማለቱ ነበር። ከዚያ ይልቅ ”ሚዲያን እፈራለሁ” ማለቱ ነው። ከዕውነት ጋር መሟገት አቅም የለኝም፤ ሚዲያን ከመሟገት ባጠፋቸው ይቀለኛል ማለቱ ነው። ቆይቶም ቢሆን ዕውነት ማፈንገጧና ህይወት መዝራቷ ላይቀር ብዙ የሚዲያ ሰዎችን ደም፣ በደም አድርጓል። ዕውነትን ለማፈን ተወራጭቷል። የቀድሞ ባልደረቦቹን፣ ወዳጆቹን ሁሉ ቀልቷል። ዕውነት ሰርስራ ከመውጣቷ ግን ሊያቆማት አልቻለም። መጨረሻውም፣ አሸናፊውም ዕውነት ሆነና ሂትለር ከሃሰት አመለካከቱና ከጦር ብዛቱ ጋር አብሮ ተደረመሰ። እስከወዲያኛው ሃሳቡም ህልሙም ጨለመ።
ብዕሬ ዕውነት እንድታወራ፣ እንድትዘክር እንድታነባ አስገድዳታለሁ እንጂ ዕውነትን እንድታዛባ የ”ማሪያም መንገድ…” አትጠይቅም። ”ባዶ ወረቀት ብዙ ይናገራል…” እንዲል በዓሉ ግርማ… ባልጽፍ ይሻለኛል። ጨጓራዬን እያነበብኩ ብፈጭ። አድር – ባይ ብዕሮች ሳነብ ያቅለሸልሸኛል። ወደ-ላይ ይለኛል። በራሳቸው ሃሳብ የማይሄዱ የብዕር ድኩማኖች ያሳዝኑኛል። በል ሲባሉ የሚጮሁ የሃሰት ብዕር የሚለቁ በቁማቸው የሞቱ ይመስለኛል። በራሳቸው ሃሳብ የሚንጠራወዙ ፈጣሪ የሰጣቸውን ህሊና የሚጠቀሙና ለዕውነት ታች ላይ የሚሉ ብዕረኞች ሃሳብ ሳነብ አክብሮትም ፍቅርም ኖሮኝ እመለከታለሁም። አነባለሁም።
ሳይበር ሴኩሪቲ
በያለንበት ሃገር ከሁለት በላይ የምንወያይባቸው የኢሜል ግሩፖች፣ መድረኮች፣ ፖልቶኮች ወዘተ… በዕይታ ቁጥጥር ስር ናቸው። ይሄንን የማያስተውሉ ዜጎች የፖለቲካ ጨቅላዎች ብቻ ሳይሆኑ ነፈዞች ናቸው።( ”ነፈዝ” ማለት ስድብ አይደለም። አስተውሎት ወይም ጥበብ የጎደለው ማለት ነው።) ስም ለውጦም ይሁን በዕውነተኛ ስሞች የሚለቀቁ ብዕሮች፣ ድምጾች የሽብር ተግባራቶች እንዳይፈጸሙና ጤናማ ኑሮን እንዳያዛቡ ይደመጣሉ፤ይታያሉ። ማንም በቁጥጥር ስር ነው። የሃሰት ተግባሮችም ከዚሁ ዙሪያ ለማምለጥ ምንም መንገድ የላቸውም። ዕውነትን ለመኖር ከመታተር ውጭ። በየምንኖርባቸው ሃገራቶች በሰላም ወጥተን ለመግባት የሚያስችለን መዋቅርም የጥበቃችንም አካል ነው።ይሄውና ይሄው ነው። ዝምታ ወይም ዕውነት ነው ከ”ሳይበር ሴኩሪቲ” ጥቃት የሚከላከልልን። ከጥየቃም ከጸጸትም የሚያድነን።ለህሊና ተጠቂነት መታደል ቢያስፈልግም ከህግ ተጠያቂነት ለመዳን መሞከር ተገቢ ይመስለኛል። በያለንበት ሃገር ለሃቅና ለዕውነት ስንኖር ሰላሙን፣ዲሞክራሲውን የሃሳብ ሽርሽሩን የምናጣጥመው ከዚህ ውጭ አይደለም። በዚህ ተጠቃሚዎች ዕውነተኞች እንጂ ወንጀለኞችና ሃሰተኞች አይሆኑም። ”ወንጀለኛን ደብቅልን፤ የኛ ጋሻ መከታችን ነው’‘ ወዘተ የሚል ምስክርነት ወይም ምልጃ በ”ሳይበር ሴኩሪቲ” ቁጥጥር ስር ናቸው። ወንጀለኛን ደጋፊዎች የሚጫወቱት ጨዋታ፣ በራሳቸው ላይ የቦንቡን ቀለበት ነቅሎ ማፈንዳት ነው። ስለዚህም ወንጀለኛን መከላከል ወይም መደበቅ አይቻልም። በደምና ሃጢያት የጨቀዩትን መከላከል እዚያው ሶስተኛው ዓለም ወይም ሃገራችን ላይ ብቻ ነው የሚሰራው። ”እከክልኝ – ልከክልህ” የሚያከትመው ኬላ ሲሻገሩ ነው።
የተጨመቀ ሪፖርት
”የትላንቱ ካሳሁን አድማሱ የዛሬው ዳንኤል አበበ ማነው?” የሚለውና እኔም ገፈት – ቀማሽ የሆንኩበት ሁለተኛው መጣጥፌ ግቡን መትቷል። ዋናው ዓላማዬ በቀበሮ ባህታዊ ወገኖች፣ዜጎች እንዳይነዱ ያሳሰብኩበት ደውል ነበርና በኖርዌይ ኦስሎ ነዋሪ የሆኑትን አንቅቷል። ከስልሳ በላይ ወገኖች የተገኙበትና በትላንቱ ካሳሁን አድማሱ በዛሬው ዳንኤል አበበ አስመራጭነት ሊካሄድ የነበረው የምርጫ ክንዋኔዎች ለሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት እንጂ በተካሄደው ስብሰባ ሳይከናወን ቀርቷል። የቀበሮ ባህታዊው ገና ገበታ ወይም ሰርግ ሳይሆን ከረባት አድርጎ በስፍራው ቢገኝም ከፊት ለፊት ሳይቀመጥ ሲንከላወስ የተመለከቱት ”የቁም ሞቱን ሱፍ ለብሶ አከበረ” ሲሉ የተሳለቁበት ሪፖርት ደርሶኛል። አንዳችም የምርጫም ይሁን የስብሰባው ዓላማ ሳይሳካ ተበትነዋል። ይሄ ወገኖቻችን ለመረጃዬ የሰጡትን ክብደትና የብዕሬን ጉልበት ያየሁበት ነው። ረክቻለሁ። በትንሾች ዕውነት የብዙዎች ሃሰት ሁሌም ሲናድ የምናውቀውና ወደፊትም ሁሉም ዕውነትን ምርኩዝ ለማድረግ ቢታትር ለአካባቢያችን ንጽህናም ለኑሮአችንም ማስተማመኛ ቤትም ማህበርም መገንባትና ማቆም ይቻላል ከሚለው ዕምነቴ ነው።
¤¤¤
ወሽመጥ
1. ከወንጀለኞች ጋር ድርድርም ሆነ ውይይት አላስፈላጊም ብቻ ሳይሆን ቁስልን በፕላስተር መሸፈን ነው። መከለል ነው። ዝንቦች ቁስሉ ላይ እንዳያርፉ መታገል ይ መስለኛል። ወሳኙ መድሃኒት ማድረጉ ነው። ለመፈወስ መሞከር። ወንጀለኞችን ነቅሎ ”ጦሴን ጥምቡሳቴን” ብሎ መጣል። በእርግጥ ለዚህ ቁርጠኝነት ይጠይቃል።
2. የ”ዲያስጶራ ይሁዳዎች” የሚለውን ጽሁፌን ለፖለቲካ ትርፍ መጫወት የሚፈልጉ ወንጀለኞችና ደቀመዝሙሮች ተመልክቻለሁ። ”እረፉ!!”… የጽሁፌን ”አንኳር” (ጭብጥ) እንጂ ”እንኩሮውን – አታንኩሩ…(ጭብጡ ላይ አተኩሩ…. አታስቀይሱ!።)
3. የትላንቱ አቃቢ ህግ ዛሬ በተቃዋሚ ጎራ ስለተቀመጠ፤ ”ብዙዎችም የወያኔን ጎራ ለቅቀው ስለመጡ ጉዳዩን ከኤርሚያስ ለገሰ ጋር መመልከቱ ተገቢ ነው” የሚል መልዕክትም አይቻለሁ። ኤርሚያስ ለገሰ ከነጋሶ ጊዳዳ ቀጥሎ የ”ይቅርታን” ግምብ የደረመሰና ከዚያም አልፎ ዕለት በዕለት የወያኔን ገመና ሲገላልጥ የሚውል እንጂ ስሙን ለውጦና ደብቆ የተቃዋሚን መድረክ ከለላና መከታ አድርጎ ከወያኔ ጋር የሚሞዳሞድ አይደለም። ”ማሞ ሌላ – መታወቂያ ሌላ” ጨዋታ ይቀፋልም ብቻ ሳይሆን ለኛ ለተጠቂዎች ለትላንት ገፈት – ቀማሾች ሌላ ቶርች መሆኑን መግለጽ ግድ ይላል።
ድርጅትን ከ”ወንጀለኛ” መነጠል!
ባነበብነውም ሆነ ባየነው ኢትዮጵያ ብዙ ስቃዮችን አስተንግዳለች። ባለፉት መቶ ዓመታት ውስጥ ያሉትን ጥቂት መምዘዝ ይቻላል። የዛሬዋ አዲስ አበባችን በጥቂት ቀናት ውስጥ ሰላሳ ሺህ በላይ ዜጎችን በሞት አስተንግዳለች። ህጻናት፣ አዋቂ፣ አዛውንቶችን። በአምስት ዓመቱ የኢትዮጵያና የጣሊያን ያርበኝነት ታሪክ። ታዲያ ከወዲያና ወዲህ የተጠራሩ፣ የቆረጡ፣ ”ሀገሬ” ያሉ ንጹሆች ናቸው ግዙፉን ሃይል ለመናድ ጊዜ ያልወሰደባቸው። ባጭር ጊዜ ለድል እንዲበቁ ያደረጋቸው። ሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ”ሆ!” ብሎ የተቀዳጀው የነጻነት ትግልና ድል ነው ብለን የምናስብ ከሆነ ስህተት ነው። ኢትዮጵያውያኖች ሆነው በባንዳነት ያደሩት ከግማሽ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ። ጥቅም፣ ከርስ ያላሸነፋቸው አርበኞች ያቆዩንን ምድር ነው ዛሬ ልጆቿ ”ታፍራና ተከብራ ባባቶቻችን ደም….” የሚለውን ዜማ የምናዜመው።
¤¤¤
ስለዚህም የጠሩ፤ የበቁ፤ ለዕውነትና ለሃገር የቆሙ አርበኞች የኢትዮጵያ መጻኢ – ግብ ላይ የሚጫወቱት ሚና ቀላል እንዳልሆነ በትልቁ ማስመር እፈልጋለሁ። ወንጀለኛንና ድርጅትን ወይም ያርበኛነት ትግልን ከባንዳዎች መለየትና ማጥራት እሻለሁ። የባለፉት ጽሁፎቼ ለማጥራት የተጫወትኩትና የወረወርኩት ሚጢጢ ብዕር ለድርጅት የተኮስኩት ጥይት ያደረጉ ግለሰቦች ገጥመውኛል። ወያኔን ማስፈራሪያችን ግንቦት ሰባት ወይም የአንድነት ሃይሎች የሚያቋቁሙት ድርጅትና ቤት ላይ የምወረውረው ድንጋይ የለኝም። የለውጥ ሃዋሪያቶችንና ባንዳዎችን የመለየት ሚና ነው የተጫወትኩት። ለዕውነት ደፋ – ቀና የሚሉ ብዙ ከብዙም በላይ አውቃለሁና በነሱ ላይ የሚፈጸመውን የማሸማቀቅ ተግባር ለመከላከል ከሰገባ ያወጣሁት ብዕር ነው። በዓለም ላይ ያሉ ሃገሮች ኢትዮጵያውያኖች የላኩልኝ መልዕክቶች ማበረታቻ ቢሆነኝም የሚያስፈነድቀኝ ኣይደለሁም። ምክንያቱም ዕውነትን የመዘከርና የመግለጽ የሙያ ግዴታ አለብኝና። የውዴታ – ግዴታ።
ንጹህ ወገኖች በቀበሮ ባህታዊ እንዳይጠፉ የመመከት ሃላፊነት። በዚህና መሰል ጽሁፌ ተጠቃሚ የሚሆኑት ድርጅቶች ናቸው። ለወንጀለኛ ጥብቅናን ወይም ዕውቅናን የሚሰጥ እራሱ ወንጀለኛ ከመሆን አያመልጥም። ዕውነት የመደርመስ ችሎታዋን እረዳለሁና ሁሉም ”ነግ በኔን” ቢያስብ መልካም መሆኑን መጠቆም ግድ ይለኛል። በአንጻሩም የዕውነት ፍላጻዬ የሰባበራቸው እኩዮች የሃገሬን ጉዳይ የግሌ፣ ወይም ወደ ጎጥ ተራ ለመከለል ሲራወጡ፣ሲቅለበለቡ ማየቴ የዲያስጶራ ይሁዳዎችን ጽሁፍ አንኳር (ጭብጥ) ያልተረዱ ኢላማዬንም፣ ዓላማዬንም ያላገናዘቡ ናቸው። እኔ ዜግነት እንጂ ዘር የለኝም። ዘረ – ቢስ በሉኝ ደሞ:-)
እናም ለዕውነት ታች – ላይ ለሚሉ አክብሮት ለደካሞችም መጽናናትንና አስተውሎትን የምመኘው በደፋሩ ብዕሬ እንጂ በአድርባይ ቀለም ለውሼ አይደለም። ወንጀለኞች ስራችሁ ያውጣችሁ! አንኳሩን ትታችሁ እንኩሮ ለማነኮር አትራወጡ። ድርጅትን ከ”ወንጀለኛ” ለመነጠል ባትተባበሩ እንኳን ከህሊናና ከህግ ተጠያቁነት ለመዳን ሞክሩ።
ትንሽ ማሳያ (ጨረፍታ)
በሚጨበጥ ጉዳይ ላይ መጻፍ ደስ ይለኛል። ልክ በአሜሪካ ያሉ ዲያስጶራ ወገኖች ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ የትራፊክ መጨናነቅን በመፍጠር ወይም መንገድ በመዝጋት ሰላማዊ አመጽን ለማድረግ በኦስሎ ኖርዌይ ከተለያዩ ክፍላተሃገራት- ወገኖች ኦስሎ ከተቱ። ያሰቡትን ለማድረግና የሚዲያ መስህብ ለማግኘት። የቆረጡ ወገኖች ባልቆረጡና ተልዕኮ ባላቸው ያመራር ስፍራ በተቀመጠው ወንጀለኛ ታገዱ። ”አይደረግም!” ሲባሉ ተከለከሉ። በ”ወረቀት ጥያቄያችሁ ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል” የሚል ሰንካላ ምክንያት ነበር እገዳው የተጣለባቸው። አንጀታቸው ያረረ ወገኖች ቆሽታቸው እያረረ ገለጹልኝ። ”ከክፍለሃገር ድረስ መጥተን ያሰብነውን ሳናሳካ…” ብለው ተብከነከኑ።ውሎውን ማምሻውን ከማንና በምን ጉዳይ እንደተጠመደ ስለማውቅ ማስታወሻዬ ላይ ከመያዝ ውጭ የማደርገው አልነበረም። በእርግጥ ለአመራሮች ለመግለጽ ሞከርኩኝ። ”ጅብ ካለፈ ውሻ ጮኽ….” ጩኽት። ተቃዋሚን ከወያኔ ማጥራት ወይም ይሁዳዎችን መፈተሽ ስራዬ ብዬ ያዝኩት።
በሃገር ቤት ብዙ ወጣቶች አዛውንቶች የድርጅት ደጋፊዎች አባሎች በመሆናቸው የእስርና የስቃይ ሰለባ ይሆናሉ። ለዓላማ ማናቸውም መስዋዕትነት አባሎች መክፈላቸው ዕውነት ነው። በሚከፍሉት መስዋዕትነት መነገድ ተገቢ ኣይደለም። በሚከፍሉት መስዋዕትነት ውጤታቸውን ማግኘት ይገባቸዋል። የሰው ልጅ እርካታው ፍላጎቱን አሳክቶ እፎይ ማለት ነውና። ትግሎች ሁሉ የኋሊት ሩጫ እንዳይሆኑ የውስጥን ህጸጽና ቆሻሻ ማጥራት ግድ ይላል። ድርጅትን ከወንጀለኛ ማጥራት ከድርጅት ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር የለምና። ድርጅት የወንጀለኞች ከለላ ከሆነ የ”ማፊያ ቡድን” ከመሆን አያመልጥም። በውስጥ ያሉ ዕውነተኛ ዜጎች ህጸጽን ማጥራት አይችሉም። በድርጅት መርህ ታስረዋልና። ተጠርንፈዋልና። ስለዚህም የእንደኔ ዓይነት ነጻ – ብዕር ለድርጅቶች ፈውስ ወይም መድሃኒት እንጂ በሽታ አይሆንም። በፖለቲካ ትርፋማ መሆን የሚቻለውና በዕውነትም ወደፊት ለምትፈጠረዋ ሃገራችን ደፋ – ቀና የምንል ከሆነ ”ኣክትን”ና ”ኣክቲቪስት”ን መለየት ግድ ይላል። ”አክት’‘ እዩኝ – እዩኝ ማለት ሲሆን አክቲቪስት ደግሞ ለሃገርና ዕውነት ትንሽ ትንሽ መሞት እንደማለት ነው። መካሪ አያስፈልገንም ማለት አይቻልም። በመውደድና በመጥላት አይደለም ጸሃፊዎችን መግታት የሚቻለው። እኔ በገዛ ፈቃዴ እስኪሪብቶዬን ሰባብሬ ካልጣልኩት ምንም ሊያቆመኝ ኣይችልምና። ስለዚህም የምወረውራቸውን መረጃዎች ለመጠቀምመሞከር ብልህነትም ብስለትም ነው። የእኔ ሾተል ወንጀለኞችን ነጥቃ ታወጣለች። የ”ዲያስጶራ ይሁዳዎች” ስትል ተከታታይ ትረካዋን ታቀርባለች። ጨው መጣፈጥ የሚችለው ለራሱ ነው። አለበለዚያ ድንጋይ ሆኖ ይሽቀነጠራል። ወይም እንዳለንበት ሃገር በረዶ ብቻ ነው የሚያቀልጠው።
የጋዜጠኛ ብቃት መረጃና ዕውነትን ማቀበል ነው። ተጠቃሚው የተረዳው ብቻ ነው። ያልተረዳው ላይ አያገባኝም። አልሟገትምም። አንኳሩን ትቶ እንኩሮው ላይ መርመጥመጥ አስፈላጊ አይደለም። በሚቀጥለው መጣጥፍ ይዤ ብቅ እላለሁ። መረጃ ሰንቄ። መረጃ ፍለጋ አልባዝንም። እጄ ላይ ያሉት ከበቂ በላይ ናቸው። በስንትና ስንት ትግል ከደላላ ውጣ – ውረድና ከወያኔ መንጋጋ ያመለጡ ሴት እህቶቻችን የ”ድጋፍ ወረቀት ይጻፍላችኋል” በሚል ሰበብ የሚደርስባቸውን አውቃለሁ። የሚደርስባቸውን እያወቅሁና ቃለ – መጠይቅም አድርጌ በእጄ ላይ ይዤ ቀዳደህ ጣለው የሚለኝ የለም። እኔም ብዕሬን የመግታት ሞራል የለኝም። ዕውነቱን ከማፍረጥ ውጭ። ስለዚህም ድርጅትን ከለላ ያደረጉ ወንጀለኞች ለዕውነት የቆሙና የለውጥ ሃዋሪያቶች ላይ በሚንቀለቀል የትግል ስሜታቸው ላይ የሚቸልሱትን ቀዝቃዛ ውሃ ለማቆም ባልችል እንኳን አሰክናለሁ።ወይም አመክናለሁ። ድርጅቶች ለራዕያቸውና ለርዕዮተ ዓለማቸው እንዲባዝኑ እጠቁማለሁ። ሁሉም እራሱን የሚመረምርበት መስታወት እልካለሁ ማለት ነው። ትንሽ ማሳያ (ጨረፍታዬን) ላሁኑ መግታት ግድ ይለኛል። በነጻነት እና በሰላም የምንኖርባት ሃገር ላይ በድፍረት ለመጻፍ የሚያግደኝ አንዳችም ሃይል የለም።”…. እንዳንተው ለሚሞት ሰው ምን አሽቆጠቆጠህ!” እንዲል መጽሃፉ። ስለዚህም የዲያስጵራ ይሁዳዎች!…. ጭብጥ ላይ አተኩሩ….አታስቀይሱ! ነው – የዛሬው ጽሁፌ።
መውጫ:-)
በውጭ ሃገር አንድ ኢትዮጵያዊ ይሞታል። እናም የሞተውን ኢትዮጵያዊ አርቆ ለመቅበር ከተለያዩ ቦታዎች በቀብር ስፍራው ላይ የሃበሻ ዘር ሁሉ ተሰበሰበ። በዚህ ጊዜ ከሩቅ ሆኖ ቀብሩን በአንክሮ የሚመለከት አንድ ህንዳዊ ወደ አንዱ ኢትዮጵያዊ (ሃበሻ) ጠጋ ብሎ:-
”ለምን በጉድጓድ ውስጥ ትቀብሩታላችሁ?… እንደኛ ሃገር ማቃጠሉ አይሻልም?” ሲል ይጠይቀዋል።
ሃበሻውም በፍጥነት
”አይ እኛ የምናቃጥለው በቁሙ ነው” ሲል መለሰ።
እናም እባካችሁ በቁማችን አታቃጥሉን። ኢሜሌ ይሄው:- girma077@gmail.com
ድንቅ ብዕር ነው።በምእራፍ ነጥሎ የመምታቱን ክህኖት ወደድኩልህ።