የአማራው መደራጀት አስፈላጊነት፦ ለአቶ ተክለሚካዔል አበበ /ከሙሉጌታ አሻግሬ /

የአማራው መደራጀት አስፈላጊነት፦ ለአቶ ተክለሚካዔል አበበ /ከሙሉጌታ አሻግሬ /

አቶ ተክለሚካዔል አበበ ምን እንደነካን ሳይሆን ምን እንደደረሰብንና ለምን እንደምንደራጅ ይህን ፅሁፍ አንብበው ይገባቸው ይሆናል።  ግልጽ ያልሆነላቸውንና ችግር አለበት የሚሉትን ሓሳብ ቢተቹ በቂ ማብራርያ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ።

እራሴን በዚህ መልኩ መግለፅ በጣም ይከብደኛል። ምክንያቱም እራሴን በኢትዮጵያዊነት እንጂ በአማራነት አልገልፅም የሚል ፅኑ አቋም ስለነበረኝ ነው። የዘር አደረጃጀት በመቃወሜና ማንነቴን በብሔር ለመግለፅ ባለመፈለጌ በህወሓት በርካታ ችግሮች ደርሰውብኛል። በግል መታወቂያ ወረቀት እና ሌሎች ዶክመንቶች ላይ ብሔር ለሚለው ጥያቄ አማራ ብዬ ሞልቼ አላውቅም። በዚህ ምክንያት documented የሆኑ ፈተናዎችን ተጋፍጪያለሁ፤ በኑሮ ሂደት ውስጥ በርካታ ነገሮችን አጥቺያለሁ። ቢሆንም መቼም ቢሆን በምንም ፈተና ሊለወጥ ያልቻለ የማነነት ፅናት አለኝ።  አማራ መሆኔን ለአፍታም ዘንግቼ አላውቅም፤ አዎ አማራ ነኝ ። አማራ በመሆኔ የምኮራበት ትልቁ ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን መውደዴ ነው። ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለችኝ። ትምክህተኛም ነኝ። አዎ በኢትዮጵያዊነቴ በጣም እመካለሁ። የነፍጠኛም ልጅ ነኝ። አዎ አያቴና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ነፍጥ ይዘው ቅኝ ገዥዎችን መቆሚያ መቀመጫ በማሳጣት የአሁኑን ነፃነትና ያለመገዛት ሞራል አውርሰውኛል። ከቅኝ ግዛት ነፃ የመሆኔ ትርጉም እጅግ ግዙፍ መሆኑ የገባኝ በቅኝ ገዥዎች መካከል ሆኜ በራስ መተማመን በማደርጋቸው እራስን የመግለፅ ሁኔታና ያልመሰለኝን ነገር ያለመቀበል ድፍረት ነው። እኔ እንደታዘብኩት ቅኝ ተገዝተው የነበሩ ዜጎች የማይደፍሩት ነገር ይህ ነው ። 

አማራውን በማህበረሰብ ደረጃ የማደራጀት ጥያቄና ተፃራሪ እይታ፦

እኔ አማራው እንደሌሎቹ በብሔር ደረጃ ወርዶ መደራጀት አያስፈልገውም ብቻ ሳይሆን ይህ ሁኔታ መታሰብ የለበትም የሚል ፅንፍ ላይ የቆየሁ ነኝ። አማራው በአማራነት መደራጀት አለበት ተብሎ የሚነሳውን ክርክር እራሴን በሚያሳምኑኝ ሁለት ነጥቦች ምክንያት ሳልቀበለው ቆይቻለሁ።

የመጀመሪያው ምክንያቴ፤ ሁሉም አገርወዳድ ዜጋ እንደሚረዳው ዘርን ያማከለ የአደረጃጀት አካሄድ ህወሓት እድሜውን ለማርዘም የተበተበው ወጥመድ በመሆኑና፤ ይህ በህወሓት የተነደፈውን ራስን የማጥበብ መንገድ ባለመከተል ህወሓት የሚፈልገውና እየገፋን ወዳለበት የዘር ቀለበት ውስጥ ላለመግባት ነው።

ሁለተኛው ምክንያቴ ኢትዮጵያን እንደ አገርና ኢትዮጵያዊነት ማንነትን ካለማጣት ጋር የተያያዘ ነው። በከፋፍለህ ግዛ አራማጆችና አቀንቃኞች ዕቅድ መሠረት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየዘሩ ከተከለለና ለእኔ ብቻ የሚለው ወሰን /territory ካዘጋጀ ፤ ልክ አሁን ህወሓት እንደሚያደርገውና ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተራ በተራ እየገደለ ለመኖር ማስተማመኛ መስጠት ይሆናል የሚል እምነት ስለነበረኝ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም በዘር አጥር ውስጥ ከተከለለ አሁን ያለውን የአንድ ብሔር የበላይነትና የሌሎቹን ተገዥነት በኢትዮጵያ ከትውልድ ትውልድ እንዲወራረስና አገር በቀል ቅኝ አገዛዝ እንዲሰፍን መፍቀድ ነው የሚል እምነት አለኝ። በተጨማሪም ሁላችንም በየዘራችን ትናንሽ መንደር ውስጥ ከገባን “ኢትዮጵያ” በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ የሚወከል እና ኢትዮጵያን በአገራዊ ስሜት የሚጠብቅ ዜጋ አይኖርም። በመሆኑም አባቶቻችን በደማቸውና በህይወታቸው ያስረከቡን ኢትዮጵያ የተባለችው አገርና በምንም መለኪያ የማይተመነው ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የመሆን ማንነት አስከ መጨረሻው ይጠፋሉ ማለት ነው። ይህ አመለካከት የእኔ ብቻ ሳይሆን የአማራ ማህበረሰብ ተወላጅ ባይሆኑም ስለኢትዮጵያ ግድ የሚላቸው ኢትዮጵያውያኖች በሙሉ እንደምክንያት የሚያነሱት ነው ብዬ አምናለሁ።

ስለዚህ አማራው በማህበረሰብ ደረጃ ባለመደራጀት ከላይ የጠቀስኳቸውን ሁኔታዎች በኢትዮጵያ እንዳይፈፀሙ የማድረግ የታሪክ ባለአደራነቱን መወጣት አለበት የሚል ፅኑ እምነት ነበረኝ። እዚህ ላይ ስለኢትዮጵያ ግድ የሚለው የአማራ ማህበረሰብ ብቻ ነው የሚል ትርጉም እንዳይሰጠው እወዳለሁ። ምክንያቱም የተነሳሁበት አርዕስት አማራውን ስለሚመለከት ነው እንጅ ኢትዮጵያን እንደአገር ለማሰቀጠል የታሪክ አደራውን በመወጣት እስከ ህይወት የሚደርስ የማይተካ መስዋዕትነት የሚከፍለውንና እየከፈለ የሚገኘውን ከሌላ ማህበረሰብ የተወለደ ኢትዮጵያዊ ማክበር እንደሚገባና ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም።

አማራው በአማራነት እንዲደራጅ የሚገፉ አሰገዳጆች፦

አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ተጨባጭ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ሆነን ስንመለከተው ኢትዮጵያ እንደ አገር አማራው ደግሞ እንደማህበረሰብ ለፈፅሞ መጥፋት ዒላማ ተደርገው እየተሰራበት ነው። ይህ አካሄድ መንግስት ነኝ ብሎ በስልጣን ላይ ያለው ቡድንና ተቃዋሚ ነን ብለው እራሳቸውን በነፃ አውጭነት ያደራጁት የጋራ ስምምነት የሚያስመስለው የጥፋት ደረጃ ተደርሷል። አማራው በአማራነት እንዳይደራጅ ከሚከላከለው ምክንያት ይልቅ አሁን በደረስንበት ተጨባጭ ሁኔታ፤ አማራው እንደ አማራ እንዲደራጅ የሚገፉት አስገዳጅ ሁኔታዎች ጎልተው መታየት ጀምረዋል።

እነዚህም፦

1. አማራ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረ የፖለቲካ ዘዬ

የተማሪወች ንቅናቄ ተብሎ የሚጠራውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ባለፈው 40 አመት “በነፃ አውጭነት” ስም የሚደራጁ ቡድኖች በሙሉ አፍ መፍቻ ቃላቶቻቸው በሙሉ ገዥው አማራ፣ ነፍጠኛው አማራ ፣ ትምክህተኛው አማራ የሚሉት ናቸው። እነሱ ማህበረሰባቸው ላይ ሊያመጡት ያልቻሉትን የእድገት ለውጥ በሙሉ እንደ ችግር በመቁጠር የችግሩን መንስዔ የአማራው ማህበረሰብ ነው በማለት ይከሳሉ። አማራው በነበረው አካባቢያዊና አለም አቀፋዊ መስተጋብር የፈጠረውና የሚከተለው ስልጣኔ አለ። ብሔር ተኮር ነፃ አውጭዎች ይህን ማከናወን ያልቻሉበትን ምክንያት ከመፈለግ ይልቅአማራውን እነሱ ስልጣኔን እንዳያመጡ ያደረገ አካል በማድረግ ተጠያቂ ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የቀደሙትን ንጉሣዊ አገዛዝ መሣፍንትን እና የወታደራዊ መንግስት ሃላፊዎች በሙሉ የአማራነት ስያሜ በመስጠት ደረሰብን ለሚሉት በደልና ችግር በሙሉ ይህ ያልተበደረውን የታሪክ ዕዳ እንዲከፍል የተፈረደበትን ማህበረሰብ/አማራውን ተጠያቂ ያደርጉታል።

ለምሳሌ ህወሓት ከተሓህት(ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ) ማኒፌስቶ ጀምሮ በግልፅ በስም እየጠቀሰ በጠላትነት የፈረጀው ማህበረሰብ ቢኖር አማራውን ነው። ደርግ ጨፍጫፊ ነው፤ ደርግ ጨቋኝ ነው ብሎ የትግራይ ህዝብን በሚያነሳሳበት ወቅት ሁሉ የነገሩ ማሳረጊያ “ደርግ ማለት አማራ ነው” የሚል ነው። ስለሆነም አብዛኛው የትግራይ ማህበረሰብ በደርግና በአማራ መካከል ልዩነት የለም ብሎ እንዲያምን ተደረጓል። የትግራይ ተራራዎች የአማራ መቃብር ይሆናሉ፤ ትግራይ አማራን ገዳይ እያሉም ዘፈኑበት። አሁንም በትግራይ ማህበረሰብ ዘነድ ደርግ ማለት አማራ ነው የሚል የተዛባ አመለካከት አለ።

እየተንከባለለ የመጣው አማራን በጠላትነት የማየት የውርርስ የጥላቻ ዘዬ በአሁኑም ግዜ ቢሆን ‘ነጻ አውጭ’ ተብለው በሚቀፈቀፉ ብሔርተኛ ቡድኖች ጭምር አማራን ዒላማ አድርጎ ይነሳል። መንግስት ተብሎ የተሰየመው አካልም ለትግል ተነሳሁበት የሚለው ምክንያት አማራውን በጠላትነት በመፈረጅ በመሆኑ ሌሎች ነፃአወጭዎችም ሆነ መንግስት እንደፈቀዳቸው የሚዘልፉትና የሚፈነጩበት ማህበረብ ይህ አማራው ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እነዚህ ቡድኖች በዚህ ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሱትን ክስ፤ ከዚያም ሲያልፍ ተደራጅተው ማህበረሰቡ ላይ የሚፈፅሙትን ግድያና ማፈናቀል ሊያስቆም የሞከረ አካል አልታየም።

****ስለዚህ የአማራው ማህበረሰብ እራሱን ከእልቂት ለመከላከል የሚያሰችል ቁመና መፍጠር ይገባዋል።

2. የመንግስት ከለላ የሌለውና ፍርድ ያጣው የአማራ ማህበረሰብ እልቂት

2.1. በአማራው ማሀበረሰብ ላይ የደረሰው ጭፍጨፋና የህወሓት ምላሽ፦

በበደኖ ፣ ወተር፣ አርባጉጉ እና ሌሎችም ስፍራዎች በዘር ተኮር አስተሳሰብና ከዚህ ጋር ተያይዞ በመጣው ጅምላ ፍረጃ ጨቅላ የአማራ ማህበረሰብ ተወላጆች ለእልቂት ተዳርገዋል። ሁሉም በትክክል የሚያስብ ሰብዓዊ ፍጡር እንደሚገነዘበው፤ በኦነግና ህወሓት መካከል የእርስ በእርስ መካሰስ ምክንያት ተጠያቂነት ያጣውን የአማራ ማህበረሰብ ህፃናትን ገደል ያስጨመረ አካሄድ መንስዔው ምኒልክ አማራ ነው የሚል ጭፍን ፍረጃ ነው። ከዚህጋር ተያይዞ የታዘብኩትን እዚህላይ ማንሳት ግድ ይላል።

ከላይ በጠቀስኳቸው ስፍራዎች ለደረሱት እልቂቶች በሙሉ ህወሓት ተጠያቂ ነው በማለት የሚፈርጀው አካል ኦነግ የተባለውን ድርጅት ነው። ይህን ውንጀላ ለማጠናከር ሲባልም እልቂቱን ያሳያል የተባለ ዶክመንተሪ ፊልም ተዘጋጅቷል። እንዲሁም በኦህዴድ ሃላፊዎች የተዘጋጀ መፅሓፍ ታትሟል። ኦነግ የተባለው ድርጅትም በበኩሉ ይህን እልቂት ህወሓት እንጂ እኔ አልፈፀምኩም በማለት ይከራከራል። ሁለቱ ቡድኖች በሚያፌዙት ፌዝ ምክንያት ለፈሰሰው የወገኖቻችን ደም ጠያቂም ሆነ ተጠያቂ የሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ለነገሩ በሰውና በፅሑፍ የተደራጀ መረጃ እና ማስረጃ በእጃችን ስለሚገኝ እነሱ የሚያፌዙበትን ወንጀል ማን ፣ መቼ፣ እንዴት እና ለምን እንደተፈጸመ እናውቃለን፤ ግዜውም ሲደርስ ፍርድ ይሰጥበታል።

እዚህ ላይ የአማራው ማህበረሰብ መንግስታዊ ከለላና የመብት ተሟጋች እንደሌለው የሚያሳይ እንቆቅልሽ ማንሳት ግድ ይላል። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የደረሰን ወንጀል በተለይ በሰብዓዊነት ላይ ለደረሱት እልቂቶች ወንጀለኛውን ለፍርድ ማቅረብና ፍርድ መስጠት የግድ ነው። ለዚህም ነው በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በሰው ልጅ ላይ እልቂት ያደረሱ እና የደረሰውን እልቂት አቀነባብረዋል የተባሉ ወንጀለኞች በሙሉ እስከ አሁን ድረስ በከዘራና በwheelchair እየተገፉ ፍርድ ፊት እየቀረቡ የእጃቸውን እያገኙ ያሉት። ፍርድ መቼም ቢሆን አትዘገይም የሚባለውም ለዚህ ነው።

ህወሓት በሚያቀርበው ክስ መሠረት ከላይ የተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ የተፈፀመውን አማራ ላይ ያነጣጠረ እልቂት ያደረሰው ኦነግ ተብሎ የሚጠራው ድርጅት ነው። ስለዚህ በኦነግ ለተፈፀሙትም ይሁን ለሚፈፀሙት አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ክስተቶች ሃላፊነቱን የሚወስዱት ድርጅቱን በወቅቱ የመሩ ግለሰቦችና አመራሩ ናቸው። ለምሳሌ ናዚዝም እና ፋሺዝም ላደረሱት ወንጀል የስርዓቱ ሃላፊዎች እስከዛሬ ድረስ በዓለም ዙሪያ ሁሉ ይታደናሉ ፣ ይፈለጋሉ። በተገኙም ግዜ ተይዘው ፍርድ ፊት ቀርበው ይዳኛሉ። በአማራው ማህበረሰብ ላይ የደረሰውን እልቂት ያደረሰው ኦነግ ከሆነ፤ ኦነግን በወቅቱ ሲመሩና ሲወክሉ የነበሩ ግለሰቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፍርድ ማግኘት ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ። በኢትዮጵያ የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነው።

ከጥቂት ዓመት በፊት የኦነግ የዚያን ግዜ መሪ ሌነጮ ለታ አዲስ አበባ ድረስ ሄዶ ነበር። ነገር ግን የህወሓት የደህንነት ሰዎች ሰውየው አገር ቤት እንዳይገባ መከልከል እንጂ ኦነግ ፈፅሞታል ለተባለው ወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ያደረጉት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አልነበረም። ይህ ነገር ለምን ሆነ ብለን እንድንጠይቅ የሚያሰችሉ ሁለት ነጥቦች አሉ።

I. የመጀመርያው ነጥብ የኦነግ አቀንቃኞች እንደሚሉት የግድያውን ወንጀል የኦነግ ቡድን አልፈፀመም ማለት ነው። የዚህ ማሳያ የሚሆነው ሌንጮን በዚህ ወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ህወሓት ያሳየው ምንም እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ነው። ህወሓት ሌንጮን ይዞ ለፈርድ ለማቅረብ ጭፍጨፋውን ኦነግ ስለመፈፀሙ የሚያሳይ ምንም አይነት ተጨባጭ መረጃ የለውም ማለት ነው። አሊያም ሌንጮን ለፍርድ ቤት ቢያቀርበው ሚዛናዊ የፍርድ ሂደት አለ ብለን ብንገምት የወንጀሉ ጭብጥ እና እውነታው ወደ ህወሓት አቅጣጫ ያሳያል የሚል የህወሓት ፍራቻ አለ ማለት ነው። በዚህ አተያይ እንደኦነግ አባባል ወንጀሉን የፈፀመው እራሱ ህወሓት ነው ወደሚል ድምዳሜ ይወስደናል።

II. ሌላኛው ነጥብ ኦነግ ይህንን ወንጀል ፈፅሟል የሚል ነው። ከላይ እንደቀረበው የዚሀን ወንጀል በፊልም ቀርፆ ሲያሳየን የከረመው ህወሓት ሌንጮን ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ ያልፈለገበት ምክንያት ለአማራ ማሀበረሰብ ያለውን ጥላቻ ለማስረገጥ ፈልጎ ነው። በዚህ ስልጣኔ በገባው ዘመን የእንስሳት ነብስ ያለምክንያት መጥፋት የለበትም የሚል የዓለም ማህበረሰብ ውስጥ ብንገኝም፤ ህወሓት የአማራ ማህበረሰብ ላይ ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ የሰው ልጆች ላይ የደረሰን እልቂት ፍርድ ባለመስጠት አሳይቶናል።

በእነዚህ ነጥቦች የምንረዳው ነገር ቢኖር የአማራው ማህበረሰብ ደህንነቱን የሚከላከልለትና ህልውናውን የሚያስጠብቅለት ወንጀልም ሲፈፀምበት ምንም አይነት መንግስት እንደሌለው ነው።

****ስለዚህ የአማራው ማህበረሰብ እራሱን ከእልቂት ለመከላከል የሚያሰችል ቁመና መፍጠር ይገባዋል።

2.2. የውስጥ ለውስጥ ጦርነት የሚከናወን የአማራው ማህበረሰብ እልቂት

ከዓመታት በፊት በህወሓት ፓርላማ ቀርቦ በነበረው የስታትስቲክስ መረጃ መሰረት በወቅቱ በተደረገው የህዝብ ቆጠራ ውጤት መሰረት የአማራው ማህበረሰብ ሊኖረው ይገባል ከተባለው የህዝብ ቁጥር በሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን አንሶ ተገኝቷል። በወቅቱ በተደረገው ጥንቃቄ የተሞላው ስታትስቲክስ ስራ ይህን ልዩነት ሊያስከትሉ ይችላሉ የተባሉ ሁሉም መላምቶች ተፈትሸዋል። ነገር ግን በሁሉም የስታትስቲክስ ቀመር አሰራር በተደረገው ፍተሻ መሠረት ይህን ያህል የአማራ ማህበረሰብ ተወላጅ ልዩነት የሚፈጥር ክስተት አልታየም።

መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አካል የፈፀመውን ስራ በደንብ ስለሚገነዘብ ፓርላማ ላይ የቀረበውን የ2.5 ሚሊዮን ህዝብ መጥፋት ሪፖርት እንደ ተረት ተረት በመስማት ብቻ ምንም ትኩረት ሳየሰጠው አልፎታል። ስለዚህ የ2.5 ሚሊዮን የአማራ ማህበረሰብ ተወላጅ እልቂት ምስጢር በማህበረሰቡ ላይ የተደረገ የውስጥ ለውስጥ ጦርነት (Silent war) ነው ወደሚል ብቸኛ ድምዳሜ ይወስደናል። በዚህም የአማራው ማህበረሰብ ደህንነቱን የሚጠብቅለትና እልቂቱን የሚያስቆምለት ምንም አካል እንደሌለ ተረድቷል።

****ስለዚህ የአማራው ማህበረሰብ እራሱን ከእልቂት ለመከላከል የሚያሰችል ቁመና መፍጠር ይገባዋል።

2.3. አማራው ማህበረሰብ ላይ የተቀነባበረ የትውልድ ክፍተት መፍጠር

በአማራው ማህበረሰብ ላይ እየተከናወኑ ካሉት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች አንዱ የትውልድ ክፍተት መፍጠርና የዘር ሂደቱን ማቋረጥ ናቸው። ይህ እየተከናወነ ያለው በሁለት መንገዶች ነው።

አንደኛው ለአማራ ማህበረሰብ እናቶችና ህፃናት መደረግ የሚገባውን የጤና ትምህርትና በመንፈግና ተገቢውን የህክምና ክትትል ባለማድረግ ነው። ስለዚህ ወላጅ እናቶች ከወሊድ ጋር በተገናኘ በሚከሰት የጤና ቸግር እና በወሊድ ወቅት በሚከናወን የግዴለሽነት አያያዝ በሚፈስ በርካታ ደም ለሞት የሚዳረጉበት ነው። በተጨማሪም ከወሊድ በኋላ እናቶችና ህፃናት አስፈላጊ የሆነውን ክትትልና ትምህርት እንዳያገኙ በማድረግ የጨቅላ ግዜ ሞት እንዲበራከት ይሆናል። ስለዚህ ከ5 ዓመት በታች የሚታየው የሞት መጠን ከመቼውም ግዜ የባሰ እንዲከፋ ተደርጓል።

ሁለተኛው የአማራ ማህበረሰብ ሴቶችን መውለድ እንዳይችሉ በሚደረግ ወንጀል ነው። ከሌሎች የአገራችን ስፍራዎች በተለየ ለአማራው ማህበረሰብ እናቶችና ወጣቶት እህቶቻችን ላይ ከነሱ ፍቃድና እውቅና ውጭ የእርግዝና መከላከያ እንዲወስዱ ማድረግ ነው። በዚህም ምክንያት በርካታ ሴቶች ልጅ መውለድ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ሁኔታ ልጅ ባለመውለድ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ልጅ ባለመውለዳቸው ምክንያት ከትዳርና ኑሯቸው የሚስተጓጎልበት ሁኔታን ፈጥሯል።

የህክምና ህግና ዲስፒሊን የውሊድ መከላከያ ህክምና የሚያገኘው ግለሰብ ህክምናውን ለመውሰድ ሙሉ ፍቃድና እውቅና መስጠት እንደሚገባው ይነግረናል። ነገር ግን የህወሓት ቡድን ይህን ደርጊት ከእህቶቻችንና እናቶቻችን እውቅና ውጭ በመፈፀም ድርብ ወንጀል እየሰራ ይገኛል። ይህ ወንጀል ትውልድ መሃል ክፍተት በመፍጠር ብቻ የሚቆም ሳይሆን አዲስ ጎጆ የወጡትንም ጥንዶች ልጅ በማሳጣት ትዳራቸው እንዲፈርስ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት የአማራው ማሀበረሰብ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲፋለስ ያደርጋል። በተለይ የዚህ ሰለባ የሆኑት ሴቶች ወደከፍተኛ ስነልቦና ቀውስ እንዲገቡ በማድረግ ቀጣይ ህይወታቸው ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል።

****ስለዚህ የአማራው ማህበረሰብ እራሱን ከእልቂት ለመከላከል የሚያሰችል ቁመና መፍጠር ይገባዋል።

3. የአማራ ማህበረሰብን ዒላማ ያደረገ ማፈናቀልና ግድያ

የአማራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ዋስትና የሌለው ህብረተሰብ ሆኗል። በ1980ዎቹ በወጣው የህወሓት የኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አከላለል እና ካርታ መሰረት፤ የአማራው ማህበረሰብ ሲኖርባቸው የነበሩት ስፍራዎች ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተቀናንሰው ተወስደዋል። በሰሜን ጎንደር ፣ በሰሜን ወሎ፣ በምዕራብ ጎጃም እና በሰሜን ሸዋ የተደረጉትን የማን አለብኝነት የመሬት ዘረፋ እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ይህ ሁሉ ሲከናወን የማህበረሰቡ አባላት ችግራቸውን መንግስት ብለው ላመኑት አካል ደረጃ በደረጃ ለማሳወቅ ጥረት አድርገዋል። ይሁንና ነገሮች ቅርፃቸውን ከግዜ ወደ ግዜ እየቀየሩ የአማራ ማህበረሰብ ተወላጆችን ማፈናቀልና በሌላ አካባቢ ዜጎች መተካት፤ ንቃተ ህሊናቸው የተሻሉና ነገሮችን ቀድመው መረዳት የቻሉትን መግደልና ማሳደድ፤ ሌሎችንም በእስራትና በግርፋት ዝም ለማሰኘት ተሞክሯል።

ይህ ድርጊት የተፈፀመው ማህበረሰቡ በተወለደበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን ፤ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም ከአውሬ እና ከተፈጥሮ ጋር በመታገል ያቀናውን ቀዬ ለቆ እንዲወጣ በመንግስት ደረጃ የተደራጁ አፈናቃዮች ዘምተውበታል። በዚህ እንግልት ውስጥ እርጉዞች፣ አራስ እናቶችና ህፃናት እስከህይወት መጥፋት የደረሰ አደጋ አጋጥሟቸዋል። ይህ ሁሉ ሲደረግ ግን አንድም የመንግስት አካል ለምን ብሎ ሊጠይቅ አልደፈረም። ምክንያቱም ለአማራው ማህበረሰብ የሚቆረቆር መንግስት በኢትዮጵያ ስለሌለ።

****ስለዚህ የአማራው ማህበረሰብ እራሱን ከእልቂት ለመከላከል የሚያሰችል ቁመና መፍጠር ይገባዋል።

ስለዚህ የዚህ ፅሑፍ ዓላማ በአማራው ማህበረሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ጥፋትና ቀጣይ እልቂት ምሳሌዎችን በማቅረብ የማህበረሰቡን በአማራነት ደረጃ የመደራጀት አስፈላጊነት ዓላማ ማሳየት ነው። ከዚህ በላይ የተገለፁት አስገዳጅ ሁኔታዎች አንኳር የሆኑት ብቻ ሲሆኑ፤ በማህበረሰቡ ተወላጆች ላይ በሁሉም ማህበራዊ ሁኔታዎች ማለትም በትምህርት፤ በግብርና ፤ በኢኮኖሚ ፤ በእምነት ፤ በህክምና እና በመሳሰሉት የደረሱና እየደረሱ ያሉ ሌሎች እጅግ በርካታ በደሎች አሉ።

በአገር ወዳዶችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ የታየው ብዥታ

የአማራው ማህበረሰብ ከፍተኛ የሆነ በራስ የመተማመንና የተፈጥሮ ነፃነት ስሜት ባለቤት ነው። ስለዚህ አማራው እንደ አማራ መደራጀት ያስፈልገዋል ሲባል የነፃ አውጭ ድርጅት ያቋቁማል ማለት አይደለም። በበርካታ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ላይ ጥያቄ የፈጠረው ጉዳይ ፦ ስለኢትዮጵያ ሲሞትና ሲታገል የነበረው የአማራ ማህበረሰብ እንዴት አንድ ደረጃ ወደታች ወርዶ በብሔር ይደራጃል የሚል ነው። የዚህም ምክንያት በአገራችን የፖለቲካ አካሄድ የተማርነውና የደረስንበት ልምድ ቢኖር ቡድኖች ቋንቋን መሰረት በማድረግ የሚመሰርቱት ድርጅት አብዛኛው ወደነፃ አውጭነት የሚንጋደድና የኢትዮጵያን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ ነው።

የአማራው መደራጀት ግን ከዚህ የተለየ ቅርጽ አለው። አማራው ኢትዮጵያን በየትኛውም አጋጣሚ ለድርድር አቅርቦ አያውቅም። በታሪክ እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር ለመታደግ ስለኢትዮጵያ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞችና እህቶች ጋር ቈስሏል ፤ ሞቷል። በዚህም ዘመን አማራው ለጥቃት እንዲጋለጥና የዕቁብ ቤት ፖለቲከኛ ነን ባዮች ሁሉ አፍ መክፈቻቸው እንዲሆን የሆነበት ብቸኛ ምክንያት ኢትዮጵያን በማስቀደሙ ብቻ ነው።

ምንም እንኳን የንጉሱን ስርዓት ለመለወጥ የአማራ ማህበረሰብ ተወላጆች ከፍተኛ መስዋዕትነት ቢከፍሉም ከ1966ቱ አብዮት ጀምሮ በዚህ ማህበረሰብ ላይ ተከታታይ እና ቀጣይ ግፍ ሲደርስበት ቆይቷል። በ1970ዎቹ መጀመርያ ላይ በርካታ የማህበረሰቡ ወጣት ልጆች አልቀዋል። ይህ ማህበረሰብ በደርግ ዘመንም አድሃሪ፣ ጉልተኛ ፣ ከበርቴ እየተባለ ብዙ ጫና ሲደርስበት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የደርግን መንግስት እንዋጋለን ብለው የሚነሱ ብሔርተኛ ቡድኖችም የመጀመርያ ዒላማቸው አማራ ነው። ከግዜ ወደግዜ ነገሮች ይለወጣሉ ተብለው ቢጠበቁም በማህበረሰቡ ላይ የሚደርሰው በደልና እልቂት አየተባባሰ መጥቷል። በግንዛቤው ያልበሰለ ጎጠኛ ግለሰብ ፖለቲከኛ የሆነ የሚመስለው አማራን እንደማህበረሰብ መስደብ ሲጀምር ነው። አንድ የጠባብ ቡድን አባል ወይም መሪ አዋቂ የሆነ የሚመስለውና አዋቂነት የሚሰማው “የአማራ ልሂቃን ችግር” ብሎ የማህበረሰቡን ምሁራን መሰደብ ሲጀምር ነው።

ስለዚህ ይህን ቀጣይነት ያለው አማራ ላይ ያነጣጠረ አደጋ ለመከላከልና የማህበረሰቡን ህልውና ለመታደግ አማራው እንደአማራ የመደራጀትና እራሱን የመከላከል ሁኔታ ወቅታዊ ምርጫው ሳይሆን ግዴታው ነው። ይህ አካሄድ የኢትዮጵያ ቀጣይ ህልውና ላይ አደጋ ይፈጥራል ብለው ስለኢትዮጵያ በእውነት ለሚጨነቁ ዜጎች የሚኖረው ምላሽ አንድ ብቻ ነው። የአማራው አደረጃጀት ዋና ዓላማ ማህበረሰቡ የሚደርስበትን ጥቃት መቋቋምና ወደፊት የተጋረጠበትን የዘር ማጥፋት አደጋ ለመከላከል ሲሆን ግቡም የራሱን ህልውና ባረጋገጠ መልኩ ኢትዮጵያን እንደ አገር መጠበቅ ነው። ስለዚህ የአማራው አደረጃጀት ምስጢር የራሱን ማንነትና ክብር ከማስጠበቅ ጎንለጎን ከማንኛውም ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ብሎ ከሚነሳ ሃይል ጋር ተባብሮ በመስራት የኢትዮጵያን ክብር ማስመለስና ህልውናዋን ማሰቀጠል ነው።

በልጆቹ ተጋድሎ የአማራ ማንነት ይከበራ!!!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኖራለች!!!

LEAVE A REPLY