ዛሬ ዕንቁ መጽሔት ገበያ ላይ በነበረችበት ወቅት እኔ በዓምደኝነት ኤልያስ ገብሩ ደግሞ በአርታኢነት ስንሠራ መጋቢት ወር 2006ዓ.ም. ላይ የአኖሌ የጥፋት ሐውልት በጥፋት ኃይሎች ተገንብቶ ሊመረቅ ሰሞን “የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የመታሰቢያ ሐውልቶች የሠማዕታት ወይስ የቅሱፋን?” በሚል ርእስ ጽፌው በነበረው ጽሑፍ ምክንያት “መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት የወንጀል ተግባር” የሚል አንቀጽ ተጠቅሶብን እኔና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በተከሰስንበት ክስ ቀጠሮ ስለነበረን ነበር ፍርድ ቤት የተገኘሁት፡፡
ለዛሬ የተቀጠርነው የመከላከያ ምስክር ለማሰማት ነበር፡፡ ነገር ግን እንኳን ምስክር ልናሰማ ኤልያስንም የፍርድ ቤት ቀጠሮ እንዳለበት እየነገራቸውም ካሠሩበት ሊያቀርቡት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ኤልያስ ከአናንያ ሶሪና ከዳንኤል ሽበሺ ጋር “በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ በጻፋቹሐቸው ጽሑፎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳቹሀል!” በማለት ኮማንድ ፖስቱ (የዕዝ ሹም ክፍሉ) የዛሬ 42 ቀን ነበር እንዲታሠሩ ያደረጋቸው፡፡
በዚህ ምክንያት ዛሬ ብቻየን ነበር የቀረብኩት፡፡ ጠበቃችን አቶ አምሃ መኮንንም ጭንቅላቱ ውስጥ ደም የመፍሰስ ከባድ ድንገተኛ አደጋ አጋጥሞት የቀዶ ሕክምና ላይ በመሆኑና ሊቀርብ ስለማይችል፡፡
ዳኛው ባለፈው ቀጠሮ በመቅረቴ ታሥሬ እንድቀርብና ዋስትናየ ሊወርድ የማይገባበትን ምክንያት እንዳስረዳ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር በማስታወስ ችሎቱን ጀመሩት፡፡ በሕመም ምክንያት እንደቀረሁ የሕክምና ወረቀቴን በማቅረብ አስረዳሁ፡፡ ይሄና ይሄንን የመሳሰሉ ጉዳዮች እንዳለቁ ዳኛው ምስክሮቹ ቀርበው እንደሆነ ጠየቁ፡፡ የቃሊቲ እስር ቤት ተወካዮች በመከላከያ ምስክርነት የጠራነውን፤ ለዚህች ሀገር እንደዜጋና እንደ ጋዜጠኛ የሚጠበቅበትን ግዴታና ኃላፊነት ለመወጣት በመታተሩ የ18 ዓመታት እስራት በግፍ ፈርደው ወኅኒ ያወረዱትንና በተደጋጋሚ እስር ቤቱ እንዲያቀርበው ሲጠየቅ ሳያቀርብ ቀርቶ የነበረውን እስክንድር ነጋን ይዘው ቀረቡ፡፡ ከእኔ ጎንም አቆሙት፡፡ አቅፌ ብስመው ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ በችሎት ፊት እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ማድረግ “የተከለከለ ነው!” የሚባል ያልተጻፈ ሕግ ስላለ አልቻልኩም፡፡ ሞቅ ያለ የእጅ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡
ችሎት ከመጀመሩ በፊት እስረኞች በሚቀመጡበት ገጽ በቃሊቲ እስር ቤት ኮማንደር (አዛዥ) እና በታጣቂዎች ታጥሮ ማዶ ለማዶ ተያይተን የአንገት ሰላምታ ተለዋውጠን ነበር፡፡ ሌሎች እስረኞች የመለያ ልብስ (ዩኒፎርም) ለብሰው የቀረቡ ሲሆን ከመሀላቸው እስክንድር ብቻውን ጥቁር ሙሉ ልብስ በጥቁር መነጽር አድርጎ ተቀምጧል፡፡ አለባበሱ ከሌሎች በመለየቱም አለባበሱን የወሰኑለት እነሱው እራሳቸው መሆናቸውን ለማወቅ አያዳግትም ነበር፡፡ ለደግነት እንዳይመስላቹህ! በእሱ ላይ የሥነልቡና ጨዋታ ለመጫወት እንጂ፡፡ ሲያመጡት ወደ ፍርድ ቤት ለምስክርነት እንደሚወስዱት አልነገሩትም ነበርና፡፡ እስክንድር ከስቷል፡፡ ለነገሩ እንደሱ ያለ በወያኔ ጨካኝ ጥርስ ተነክሶ የተያዘና በርካታ በደሎች የሚፈጸሙበት፣ ባለብዙ ሐሳብ፣ ባለብዙ ናፍቆት በእስር ላይ ሆኖ እንዴት ሊወፍር ወይም በነበረበት ሁኔታ ሊገኝ ይችላል? እስክንድርን የሚያውቅ ሁሉ ወያኔ እስክንድርን በማሰሩ ርሕራሔ የሚባል ነገር እንደሌለው፣ በምክንያት እንደማይመራ፣ የሞራል (የቅስም) ሕግ የሚገዛው እንዳልሆነ ይረዳል፡፡ እስክንድር ፍጹም ቅን፣ በማንም ላይ በጠላቱም ላይ እንኳን ቢሆን ክፉ ነገርን የማያስብ፣ ክፋትና ለንኮል የሌለበት ሰው ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቱን ሰው በፈጠራ ክስ ወንጅሎ ወኅኒ ለማውረድ የጨከነ ለማን ይራራል? እስክንድርን አምጥተው ሲያስቀምጡት ሳየው አንጀቴ ስፍስፍ ነው ያለብኝ፡፡ እንባ ተናንቆኝም ነበር፡፡
ወያኔ እስክንድርን በወዳጅ ዘመድ የመጎብኘት የመጠየቅ መብቱን በሕገወጥ መንገድ በአንባገነንነቱ ስለነፈገው ስለ እኛ ክስም ሆነ ስለሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ምንም ዓይነት መረጃ የለውምና “ልብስህን ልበስ! አሉኝና አመጡኝ፡፡
ለምን ጉዳይ የት ሊወስዱኝ እንደሆነ የነገሩኝ ነገር የለምና እስኪ ንገረኝ” አለኝ፡፡ የክሳችንን ዓይነትና ለመከላከያ ምስክርነት እንዳስጠራነው ነገርኩት፡፡ “አይዟቹህ በርቱ!” አለ ለሰላማዊ ትግልም ታማኝ እንድንሆን “አደራ!” አለ፡፡ ለውጥ መምጣት ካለበት በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው! ብሎም ጨመረ፡፡ ይሄኔ ነበር እስክንድር ያናደደኝ፡፡ እስክንድር! አልኩት፡፡ “አንተ ለሰላማዊ ትግል የጸና አቋም እንዳለህ አውቃለሁ፡፡ ሰላማዊ ትግል ዕድል ተሰቶት ሌላኛውን አማራጭ እንድንጠቀም ባንገደድ መልካም ነበር፡፡ ከሰላማዊ ትግል ሁልጊዜ ትርፍ እንጅ ኪሳራ የለምና፡፡ ነገር ግን ሰላም ትግል በኢትዮጵያ እንዲሠራ በፍጹም አልተፈቀደለትምና በከንቱ ጊዜን ማባከንና አላስፈላጊ መሥዋዕትነት መክፈል ነው የሚሆነው!” ስለው በሰላማዊ ትግል ለውጥ የመጣባቸውን ሀገራት ጠቀሰልኝና “በእነኝህ ሀገራትም እኮ በሰላማዊ ትግል ለውጥ እንዲመጣ ሰላማዊ ትግል ዕድል አልተሰጠውም አልተፈቀደለትምም ነበር፡፡ ሕዝቡ እራሱ ነው የፈጠረው፡፡ ስለሆነም እኛም መፍጠር እንችላለን!” አለኝ፡፡ እኔም “ትክክል ነህ! በእነኝህ ሀገራት በሰላማዊ ትግል ለውጥ መጥቷል፡፡ ነገር ግን እነኝህ ሀገራት መንግሥታቶቻቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ የየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታም ወያኔ ከፈጠረው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ እዚህ ወያኔ ሕዝቡን በዘር በሃይማኖት ከፋፍሎ አጣምዶታል፡፡ ይህ ሁኔታ በጠቀስካቸው ሀገራት በአንዳቸውም አልነበረም፡፡
እዚህ ግን ደንቆሮውና ሸፍጠኛው ወያኔ ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ለሚጻረረው ለራሱ ርካሽና ነውረኛ ጥቅም ሲል በዘር በሃይማኖት አናክሶ ሁሉንም ቀን እንዲጠባበቅ አድርጎታል፡፡ በዚህ በሰሞኑ ሕዝባዊ እምቢተኝነት አዲስ አበባ ግንባር ቀደም መሆን ሲኖርባት እንኳን ግንባር ቀደም ተከታይ እንኳ ልትሆን ያልቻለችው ለምን ይመስልሀል? ሌላ ምንም አይደለም ወያኔ የቀበረብንን፤ ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን የብሔረሰብና የሃይማኖት የእርስ በርስ ግጭትን በመሥጋቷ ነው፡፡ ይሄ ወያኔ የቀበረብን ፈንጅ ሊከሽፍ ወይም ልንቆጣጠረው የምንችለው ሀገር አቀፍ ርእይ ያለው፣ ለጎሳ ተኮር ፖለቲካ ፊቱን ያዞረ፣ የታጠቀ ኃይል ሲኖር ነው፡፡
ይህ የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርጎ የያዘ ኃይል ሊከሰት የሚችለውን አደጋ እንዳይከሰት ለማድረግና ለመከላከል የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ሕዝቡ ይሄ የታጠቀ ኃይል መኖሩን ሲያውቅ ሲያረጋግጥ ነው የእርስ በእርስ ፍጅት ሊከሰት እንደማይችል መተማመን ሊያድርበት የሚችለውና በሕዝባዊ ዐመፅ አገዛዙን ለማስወገድ መድፈር የሚችለው፡፡ በዚህ መንገድ ካልሆነ በስተቀር በወያኔ የአገዛዝ ዘመን በሰላማዊ ትግል ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው!” ስለው ምን አለ እስክንድር “ሰላማዊ ትግል እኮ ሲጀመር የከተማ ነዋሪዎች ትግል ነው! የገጠር ነዋሪዎችን የሚያካትተው የትጥቅ ትግል ነው! ይሄ ያልከው በዘር ተከፋፍሎ የመናቆር ችግር የከተማው ሕዝብ ችግር አይደለም!” አለ፡፡ እኔም “ከኢትዮጵያ ሕዝብ 85 እጁ የገጠር ነዋሪ ነው ቀሪው 15 እጅ ብቻ ነው ከተሜ 85 እጁ የገጠር ነዋሪ በጎሳ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) የተመረዘ ከሆነ በቀሪው በ15 እጁ ለውጥ ሊመጣ አይችልም! ከፍተኛ የሆነ የኃይል አለመመጣጠን ችግር አለና፡፡ ይሄንን እንዲሁ አልኩህ እንጅ የከተማው ነዋሪም ከጎሳ ተኮር የፖለቲካ ችግር ነጻ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን (የእምነተ አሥተዳደር ቡድኖችን) ተመልከት! ሁለት ወይም ሦስት ቢኖሩ ነው ሀገር አቀፎች፤ ከ60 በላይ የሚሆኑት ግን የሚያቀነቅኑት የዘር ፖለቲካን ነው፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች ያየህ እንደሆነ ከተሜው ከገጠሬው በጣም በከፋ መልኩ በዘር ፖለቲካ የተመረዘ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡
ገጠሩ ደግሞ ከናካቴውም የዘር ፖለቲካን ጨርሶ የማያውቅ ቅን የዋህ ሕዝብ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ ሁሉም ገጠሬ በዘር ፖለቲካ መርዝ የሚለከፈው ከተማ ሲገባ ነው፡፡ እንዴትና ለምን እንዲህ ሊሆን የቻለ ይመስልሀል?” ብየ ጠየኩት እንዳለመታደልሆኖ እስክንድር ይሄንን ጥያቄ ሊመልስልኝ ሲል ኮማንደሩ (አዛዡ) እጁን ይዞ ጎተተው፡፡ እስክንድር እጀን ያዘኝ፡፡ እኔም ላለመልቀቅ እጃችንን እስከ ክንድና ክንዳችን ድረስ አቆላልፌ በመያዝ አጥብቄ ያዝኩት፡፡ የኮማንደሩ (የአዛዡ) እጅ በመሀላችን ገባና ፈልቅቆ በማለያየት በታጣቂዎቹ አስይዞ ወደበሩ ሲወስደው ዳኛው “የት ነው የምትወስዱት? መልሱት! ገና ትዕዛዝ እያነበብኩ አይደለም እንዴ? ማነው ከቆመበት ጎትቶ የወሰደው?” በማለት በቁጣ ጠየቁ፡፡ አዛዡ “አይ አልቋል ብየ ነው!” አለ፡፡ ዳኛው “ምኑ ነው የሚያልቀው? ገና እያነበብኩ አይደለም እንዴ!” አሉና በንባብ ያሰሙ የነበረውን በዚህ ቀጠሮ ያልቀረቡትን ጋዜጠኛ ተመስገንንና ውብሸትን የዝዋይ እስር ቤት ዛሬ ካላቀረበበት ምክንያት ጋር ጨምሮ ለቀጣዩ ቀጠሮ እንዲያቀርብ፣ ጋዜጠኛ እስክንድርም ገና ምስክርነቱን ያልሰጠ በመሆኑ በቀጣዩ ቀጠሮ እንዲያቀርቡት የሚያዘውን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አንብበው ጨረሱና እስክንድር ተወሰደ፡፡
በኋላ ላይ ስሰማ እኔና እስክንድር እየተንሾካሸክን ከላይ የተወያየነውን ነገር ስናወራ አዛዡ የምንነጋገረውን ነገር ሊያስቆመን ሦስቴ ከመቀመጫው እየተነሣ እንደተቀመጠ ሰማሁ፡፡ ከእስክንድር ጋር ከላይ የገለጽኩትን ስናወራ ዳኛው የቀሩ ምስክሮችን፣ የኤልያስን፣ የጠበቃችንን፣ ቀጣዩን ቀጠሮ ስለመወሰን ወዘተረፈ. ጉዳዮች በሚያቀርቡልኝ በርካታ ጥያቄዎች እያቋረጥን እንደገናም እየቀጠልን ነበር የተነጋገርነው፡፡ ወንድሜ እስክንድር ሆይ! አይዞህ!
ነጻ የምትወጣበት ቀን ሩቅ አይደለም!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com