ሰሞንኛው ጉዳይ ላይ። ለትግሉ ቅድሚያ በመስጠት /ዳዊት ዳባ/

ሰሞንኛው ጉዳይ ላይ። ለትግሉ ቅድሚያ በመስጠት /ዳዊት ዳባ/

የከፋ መሰዋትነት እየተከፈለበት ያለ ትግል ውጤታማ ይሆን ዘንድ ሁላችንም ሊያስጨንቀን የሚገባ ነው፤ መሉ ጭንቅላታችን የተባበረ
አቅማችን ትግሉ ላይ መዋል አለበት። ድርጊታችንም ንግግራችንም ሆነ ሀሳባችን ሁሉ ትግሉን አሸናፊ ከማድረስ አኳያ የተሰላ መሆኑ
ላይ እርግጠኛ መሆን አለብን። እንደዚህ መሆን እስካልቻልን የባርነት ዘመን ይቀጥላል። በትግሉ ሂደት የበዛ ሀላፊነትን የተሸከማችሁ
ወገኖች ትግሉ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሰ በሗላ አገዛዙ በሚወስዳቸው በየትኛውም አይነት እርምጃ ሊገታ አይችልም። አንድና አንድ
የትግሉ ከግብ መድረስም ሆነ መንቀራፈፍ የሚወሰነው ለለውጥ በቆመው አካል አያያዝ ብቻ ነው። ሀላፊነትና የበዛ ድርሻ ያለን ክፍሎች
ስኬት ወይም ብቃት የሚለካው በቀጥታ ትግሉን አሸናፊ ማድረግ ከመቻል ጋር ነው። ይህን አይነቱን ታሪካዊ እድል በተለያየ ጊዜ
አግኝተው ሳያውቁበት ቀርተው መሰዋትነት የተከፈለበትን ትግል አሸናፊ ማድርግ ያልቻሉት የበዙት ወድቀው እስከጭራሹ አልተነሱም
። መነሳት ከተባለ ተነሳን ያሉትም አሁን ያሉበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። የትኛውም አይነት ሰበብና ትንታኔ በሗላ
ፋይዳ አይኖረውም።

መሰራት ያለባቸውን ስራዎች ዜጋው የድርሻውን ማድረግ በሚፈልግበት አሁን አስተባብሮ ማሰራት ላይ መካን። ፈጣን አመራርና
አቅጣጫ ማስያዝ፤ በወረቀት ላይ በተቀመጠ እቅድ መንቀሳቀስ፤ ማስተባበርና ትግሉን ማቀናጀት። ቅራኔዎችን ማለዘብ ስህተቶችን
በቶሎ ማረም የአሸናፊነት ሚስጥር ነው። አገዛዙ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ፍጅት፤ ጅምላ እስር፤ ወታደራዊ ቀጠና፤
ኮማንዶ ፖሰት፤ ጥገናዊ ለውጥ፤ ካብኔ ማዘበራረቅ የመዳከምና ፍፃሜውን የሚያሳዩ ሂደቶችም ናቸው። ለለውጥ እያታገለ ያለውን
ክፍል በተመለከተ ግን ከትላልቅና ወሳኝ ጉዳዮች ተነስተን ብናይው ለአገር ሉአላዊነት ሲባል፤ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት
ለማስከበር ሲባል፤ ወደ አላስፈላጊ የርስ በርስ ግጭት ውስጥ እናዳንገባና ታላለቅ የመብት ጥያቄዎችና የተለያዩ የመሀበረሰቡ ከፍሎች
ፍላጎቶች የመሳሰሉ አገራዊ ቁም ነገሮችን ዛሬ ላይ ከትግሉ ፊት አብዝቶ ማሮጥ ውጤቱ ውድቀት ነው። ሲጀመር አብረውን የከረሙ
መፍትሄ ልንሰራላቸው የሚገቡ ቁምነገሮች ነበሩ። ማለፊያ የሆነ መፍትሄና በሰከነ ሁኔታ ሊያሻግረን የሚችለው ብለሀት ላይ
ተጮሆበታል። ዛሬ ላይ ችግሩን ሲናገሩ እንደመስማት የሚያስጠላ ነገር የለም። መፍቴሄ መስራት የሚገባቸው ወገኖች ችግሩን ሲናገሩ
እንደመስማት የሚያናድድም ነገር የለም። ውጤቱ ዜሮ ድምር በሆነ የፖለቲካ ጭቅጭቅ ምክንያት ተባብረን መታገል አቅቶን የህዘብ
ትግል ሲጎዳና የጭቆና ዘምን ቀጥሎ እንደማየትም የሚያሳዝን ነገር የለም። በዋናነት መፍትሄ የሌለው የማይታለፍ ችግርም አይደለም።
ስለወዘፍነው ዋዜማ ላይ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ያለን በመሆኑ ያልተለመደና ወሰብሰብ ያለ መንገድን አሽቷል።

1.ወሳኝ በሆኑ ክፍሎችና ዜጎች በተዘጋ በር፤ ከህዘብ ጀርባ፤ ከኔ ጀርባ፤ በጠረቤዛ ዙሪያ የሚሰራ እንጂ ባደባባይ ውይይት ሊሰራ
አይችልም። ለዚህ ጊዜውም ቅንጦቱም የለም። በተደራጀ መንገድ ትግሉ ላይ ሊያበረክት የሚቸለውን አስተዋፃ አንድ ሁለት ብሎ
ማስመዝገብ የቻለ ሁሉ እስከተካተተና የሚያሻግሩን ገለልተኞች ወይ ሁሉ ባይገባበትም በአመለካካት ደረጃ ሁሉ እሰከተወከለ በቂ
ነው። ውጪ ቀርቶ ጎታች አይኑር እንጂ ህዘብ በጭራሽ አይገደውም። ለዚህ ሁሌም ማናቸውንም ተባብሮ የመታገል ሙከራዎችን
ሲያሞግስና ስያበረታታ ነው በተደጋጋሚ የታየው።

2. አንድና አንድ ሰላማዊ ሽግግርን ስለመስራትና ትግሉን ስለማስተባበር እንጂ ላሉ የማያጣጣሙ ፍላጎቶች በሙሉ አንድ ሲደመር አንድ
አይነት መፍትሄ የላቸውም። ይቁረጥ። ቢኖራቸውም ሁለት ብሎ ማስቀመጡ አሁን ትክክል አይደለም። ለመወሰን ህዘባዊ ውክልና
ያለው ወገን የለምና። ጥያቄው ሆነ ማድረግ ያለብን እንዴት አድርገን ህጋዊ ሰላማዊና መዋቅራዊና መንግስታዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ
ሊስተናገድና ሊፈቱም ሆነ በቀጣይ በተሻለ ክባብ ልንታገልባቸው ወደሚችሉበት መድረክ እናሻግረው ነው። አለቀ። ካንተ የተሻለ
አቅምም ሆነ ህጋዊነት ከሌለው አካል ይህን ስጠኝ አትስጠኝ። ተቀበል አትቀበል። ተው አልተወም ብለን አንጨቃጨቅ። አንድም
እራስን ማሳነስ ነው። አልያም ባዶ ብራባዶ ነው። በዋናነትም ሁላችንም የሚጠየቀው ክፍል ቢፈልግም በጭራሽ ሊፈፅመው
የማይችለው መሆኑ ይግባን።

3.ፅንፈኛ፤ አቢዬታዊ፤ ግብታዊ ፤ ሰር ነቀል፤ ገንጣይ፤ ቅጂ የሆነ የመፍትሄ ሀሳቦች በሙሉ ተጨባጩን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት
ካለመረዳት፤ በይበልጥም ከተጣባ መጥፎ ልምድና ፖለቲካውን ወደኛ ፍላጎት ማዘንበል ይቻላል ከሚል የሚሰነዘሩ እብድ ሀሳቦች
ናቸው። እነዚህን አይነት ሀሳቦች በጦዙበት ትብብር መፍጠር አይቻልም። ካልተባበርን ደግሞ ማሸነፍ የለም። ከታገልን ለማሸነፍ
እንታገል። ወንዝ የማይሻገር የመፍትሄ ሀሳብ መወርወር እንጂ ተፈፃሚ ነው፤ ተቀባይስ፤ ጦሱስ የሚለውን አስፍተን እያየን አይደለም።
ህዝብ ነፃነቱን አምርሮ በመጠየቁ መራራ መሰዋትነት እየከፈለ ነው። ለዚህ ሁሉ የሚያስተባብረው ቀላሉና ጭቅጭቅን የሚቀንሰው
መንገድ ያለውን መነሻ ማድረግ ነው። ህገ መንግስቱ፤ ፌደራል ስርአቱ፤ መዋለንዋይ ድልድሉን ሆነ ውክልናን በተመለከተ ያለውን
የስልጣን ድልድል በተጨማሪም አዲስ አበባንም በተመለከተ ካለው መነሳቱ የተሻለው ምርጫ ነው።

ያለው፤- ዲሞክራሲ፤ ነፃ ሜዲያ፤ ነፃ የፍትህ ስርአትና ነፃ ምርጫ በሌለበትና ጭቆና በነገሰበት ሁኔታ ውስጥ በዛ ላይ በወረቀት ላይ
የሰፈረው አንዱም ቁም ነገር ተፈፃሚ ባልሆነበት ለሀያ አምስት አመት ስራ ላይ የዋለ ነው። ተግባር ላይ እንደዋለ ይሰራል አይሰራም
ብሎ መከራከር ቢቻልም ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ አይደልም። አገዛዙ ይባስ ብሎ ያለውን ወዲያና ወዲህ እየዘወረ ስልጣን
ላይ ለመቆየትና ተቀናቃኝ ያላቸውን ክፍሎች ሁሉ ለማሳደድ የተጠቀመበት ስለሆነ ተቀባይነቱ ላይ አስቸጋሪነቱ የሚጠበቅ ነው።
ላንዳንዶች ማሰቡም ሊከብድ ይችላል። መታወቅ ያለበት ግን ያለው ወደፊትም ሆነ ወደሗላ ለመውሰድ የተመቸ አይደለም። ወደሗላ
መሄድ የህዋልዬሽ መንገድ ይሆናል። ወደፊት ከተባል ወደገደል ሊሆን ይችላል። ወደሗላ በመንደርደር ጦሮ ሰብቆ በሚመጣም አካል
ሰላም ሊፀና አይችልም። ከህዘብ ፍላጎት ውጪ ይሆናልና። ስለዚህ ይህም ያው ገደል ውስጥ የሚከተን ነው።

የተሻለው መንገድ ለሁላችንም ካለው መነሳት ነው። ሰፋ አድርጎ ለሚያይ ለሀያ አምስት አመት እንግዳ የሆነ አገዛዝ በነገሰበት
እስከችግሮቹ መሬት ላይ ባለው እንደ አንድ አገር ህዝብ መቀጠል ችለናል። ይጨመሩ ከሚባሉት የመብት ጥያቄዎች በላይ በወረቀት
ላይ የተቀመጠው ተፈፃሚ ይሁንልን የሚለው ድምፅ ነው መሰዋትነት እየከፈለ ካለው ህዘብ ጎልቶ እየተሰማ ያለው። በዚህ ሀያ
አምስት አመት ተፈጠሩ የምንላቸውን ችግሮች ነቅዘን እያወጣን አግባብ ያለው ህዝባዊ ውክልና፤ ዲሞክራሲ፤ መብትና ነፃ የዳኝነት
ስርአት ተጨምሮበት ቢሆን ኖር በሚለው ውስጥ ብናሳልፋቸው አንዳቸውም ችግሮች ከመነሻውም አይፈጠሩም ነበር። ቢፈጠሩም
አግባብነትና ህጋዊነት በጠበቀ በቀላሉ መፍትሄ ሊሰራላቸው የሚችሉ ነበሩ። አሁን በመሬት ላይ ያለውን ወያኔ ሙሉ በሙሉ
ያስቀመጠውና ሙገሳ የሚያስገኝለት አይደለም። መፍትሄ በወረቀት ላይ ሰርቷል ቢባልም ለዚህን ያህል ጊዜ ስልጣን ተቆናጦ
ሊተገብረው አልቻለም። በዛ ላይ ለአገሩና ለህዘብ ድህንነት የምር ለሚቆረቆር መፍትሄውን ማን ሰራው ሳይሆን ይጠቅማል?
ልንጠቀምበት እንችላለን? ሊያሻግረን ይችላል? የሚለውን ማየቱ ነው ትክክለኛው።

ከዚህ በፊት አዲስ ህገ መንግሰት ለሽግግሩ አያስፈልግም ሲባል ሁሉም ያስፈልጋል አለ። መቅረፁም ብዙ ስራ ነው። እንዴትና መቼ
ሊፀደቅ የሚለው ስሌት ውስጥ ሳይገባ ስለነበር ሀሳቡ የሚገፋው የተሳሳተ ሆኗል። አሁን ከሽግግሩ በሗላ የሚለው ሃሳብ አስማሚ
ይመስላል። አዲስ ሳይሆን በረጅም አመታት ውስጥ ቀስ በቀስ በማሻሻል የሚለውም አማራጭ ሊሆን ይችላል። በአጠቃላይ ያለውን
ለሀያ አምስት አመት ተግባር እንደዋለ ሳይሆን እንደ አዲስ በፅንሰ አሳብ ደረጃ ወስደን መነሳቱ ነው ለሽግግሩ ጊዜ የተሻለ ነው። አንጃ
ክራንጃ ባልበዘበት ሊያሻግረና አስማምቶ ሊያስተባብረን የሚችል ነው። ከተባበርን እናሸንፋለን ተጭቆናና አስቀያሚ ከሆነው አድሎ
እንገላገላለን።

አሁን ያለው የያዛቸው አሰፈሪም አላስፈላጊም የማያስማሙ አንድና ሁለት የግድ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዬች አሉ። እነዛን የሽግግሩ
ቻርተር ላይ ማካተት ነው። በዋናነት በወረቀት ላይ ያለው በሙሉ በተገቢው ተፈፃሚ መሆን መቻሉን እናረጋግጥ። በተረፈ ነገ ቀጣይ
ትውልድና መታገል የሌለ ይመስል ድርቶ አናብዛ። ይህን በማድረግ በቀላሉ መስማማት ይቻላል። በቀናነት ስለእውነት ካየነው እንናገር
ከተባለ ያለው በአግባቡ ተግባር ላይ ውሎ ቢሆን ዛሬ ላይ በተቃዋሚነት ለብሄርና ብሄረሰብ መብት ብቻውን ተነጥሎ የሚቆም
ባልነበረ። ይህን የማነሳው ያአገሪቷ ሉአላዊነትና የአንድ አገር ዜጎች የመሆናችን ጉዳይ የምር ከሚያሳስባቸውና ለሁሉ ነገር መነሻ መሆን
አለበት ከሚሉት ዜጎችና ክፍሎች ስለመታባበርና ስለሰላም ሲሉ አሁን ካለው ላይ ጨምረው እሺ ይሁን ሊሉት የሚችሉት ነገር የለም
የሚለውን ለማሳየት ነው። ይህን ስል በጥሬው ነው። በአንዳንዶች በዚህ ፍላጎት ውስጥ የታጨቀ ሌላ ፍላጎትና ለወንድሞቻቸው
መብትና ፍላጎት ላይ ንፉግነት፤ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ ዜጎች ላይ ያለ አመኔታ፤ አልፎም መፍራት አንዳንዴም ጥላቻ እንዳለ
አውቃለው። አነሳሴ ሰከን ባለና ብልጠት ባለበት መራመድ በሚገባን ጊዜ ላይ መንቦጫራቅና መበሻሸቅ ስላየው ተንቦጫርቄ ማለዘብ
ከተቻለ በሚል ነበር። የተደጋገመ ቢሆንም የምር ወደሆነው ሳልፈልግ ብዙ ተስቤያለው። ወደሰሞንኛው በቀጥታ ልግባ።
“በተበታተነች ኢትዬጵያ ውስጥ ካልሆነ የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ማስጠበቅ ስለማይቻል የምትበታተን እንጂ ዲሞክራሲያዊት ኢትዬጵያ
የሚባል ነገር የለም”። ሊበን ዋቆ የድርጅቱን አቋም። የለንድን የኦሮሞ ህዘብ ኮንፈረንስ ላይ።

ብሄረሰብ የሚባል ነገር ኢትዬጵያ ውስጥ ስለሌለ የብሄረሰብ ጭቆና የለም። ያለተበረዘው የኦሮሞ ህዘብ ቁጥር ከሰባት ሚሊዬን
አይበልጥም”። ደ/ር ሀይሌ ላሪቦ ቀድመው ባስነበቡን ፅሁፍ ውስጥ።

“ሀይሌ ላሪቦ የኦሮሞ ህዘብ ቁጥር ከሰባት ሚሊዬን እንደማይበልጥ እቅጩን ነግረውናል። ሳይንሳዊ በሆነው መንግድ አይቼው
ትክክለኛው የኦሮሞ ህዘብ ቁጥር ሰባት ሚሊዬ ሊበልጥ እንደማይችል አሳምኖኛል”። ዶ/ር ፍቃዱ በቀለ።
አምልክ በኢትዬጵያዊነት እንጂ በኦሮሞነት፤ በአፋርነት በጋንቤላነት አያውቃችሁም። ምክንያቱም ኦሮሞ፤ አፋር የሚባል ስም በመፃሀፍ
ቅዱስ ውስጥ የለም። ፓስተር ቶለሳ ጉዲና ቀድሞ።

በዋናነት የፕ/ፌ መስፍን ወልደማርያም በቅርቡ ያቀረቡት መፍትሄ ሲጨመቅና መፃሀፋቸውንና ከዛም በሗላ የኦሮሞ ህዘብ አመፅ
ከጀመረ ጀምሮ የፃፏቸውን ፅሁፎች አጣምሮ ሊረዳ ለመኮረ እኔ እንደተረዳሁት ምን አልባትም ነገር የሚገባቸው ሌሎችም ሊረድት
እንደሚችሉት ከአማራ ክልል ወደትግራይ ያስገባችሁትን መሬት ብቻ መልሱና ከዛ ከባሰ የስልጣን ቅብብሎሽ እንጫወታለን ነው። ለኛ
ለሰዎቹ ሲባል ለቀጠፍናቸው ቄጠማዎች ገንዘብ እንሰጣቸዋለን አይነት ነው።

ከላይ የተቀመጡት ሀሳቦች የበዙት ሊነበቡ፤ ሊታዩ፤ ሊደመጡ የሚገባቸው ተብለው የተገለፁ ነበሩ። እማኝ ተደረገዋልም። ለሀሳቡ
አቅራቢዎች ተራሩጦ መድረክ ማዘጋጀት አለ። ሊበን ዋቂ ግን ተቀጥቅጧል። መብቱን የጠየቀ ህዘብ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ በሚል
እንዳገዛዙ በግልፅ አልተገለፅም እንጂ ዘመቻ የሚመስል ነግር ከጀመር ቆይቷል። ሊበን ዋቆ ቀድሞ ለጀመረ ዘመቻ ጭድ ነው
ያቀበለው። በተጓዳኝ አገዛዙ ወቃሽ በሌለበት ህዝብ ላይ ዘምቷል። የሚችለውን ያህል እየገደለም እያሰረም ነው። ተመችቶታልም።
ሊበን እንደገመትኩት የድሮ ካድሬ ነው። በየትኛውም አቅጣጫ ቢታይ ንግግሩ ላይ ትክክል የሆነ ነገር የለበትም። ባለጌም ነው።
ብሽሽቁ ላይ የመልስ ምት ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን ኦሮሞ እንደመሆኑ በሁን ጊዜ የበዛ ሀላፊነት ነበረበት። የህዝብን ትግል
ልፊያ ውስጥ መክተትና የኦሮሞ ህዝብ ከወገኖቹ እገዛን እንዲነፈግ መዶለት አልነበረበትም። ሌላው ሁሉ ቢቀር አቦይ ፀሀይዬ
“ይተገበራል” “ልክ እናስገባለን” ብሎ ለትግሉ ከጠቀመ እየተፈጀ ላለው ወገን ሲል እንኳ ሀላፊነት በተሞላበት ሊናገር በተገባ ነበር።
ብቻ መቀጥቀጡ ሲያንሰው ነው። ሌሎች የተሞገሱት ትክክል ስለሆኑ ግን አይደለም። ማንን? የሚለው ነው እንጂ በእኩል የሚያናድድና
ልፍያ ውስጥ እንድንገባ ያደረጉ ናቸው። ሰላሰፋው እያንዳንዱን በትንሽ መስመር።

ባለፈው ሀያ አምስት አመታት ውስጥ ኦሮሞ ነኝ ማለት በሚያስገድልበት፤ በሚያሳስርበት በሚያስገልልበት እውነታ ውስጥ አንድ ሰው
ሳይሆን ኦሮሞ ነኝ ለማለት ተሯርጦ እጅን አያወጣም። ከአገሪቷ ህዘብ ግን ግማሹ በቃ እኔ ኦሮሞ ነኝ ብሏል። ይህን ተራራ የሚያህል
እውነትና ዛሬን ሊያይ ያልቻለ ትናንት ላይ ተመራምሮ የታሪክ ምሁር ቀልድ ነው። ስለዚህ ዶ/ር ሀይሌ ላሬቦ እራሱ አለ ወይ ?።
አለምነው መኮንን ሲባሽር አማራ ሆኖ አማራን ሲሳደብ ባለጌ እንደነበረና መብት ተደርጎ እንዳልተወሰደለት ፓስተር ቶለሳም ትክክል
የሆነን ነገር የመናገር ግዴታ አለበት። ካልክ መፀሀፍ ቅዱስ ውስጥ ዳዊት እንጂ ቶለሳ የሚል ስም የለምና አያውቅህም አታውቀውም
ሊባል በተገባ ነበር። በእርግጥ ይህን ለማለት እንደምናመልከው አምላክ ነው። የብዙዎቻችን አምላክም እምነታችንም ቶለሳንም፤
ዳዊትንም በእኩል ያውቋቸዋል። በዛ ላይ ፓስተር ቶለሳ አገሪቷ ውስጥ ያለውን ግፍና በደል አላውቅም ሲል እውነትን አልተናገረም።
እየተፈጀ ካለው ወገኑ ጉዳይ ሳይገደው ለቁስ ሲያለቅስ ሁላችንም ሰምተንዋል።

ምንም መሰረትም እውነታም ባይኖረው ብዙዋቻችን ዘረኝነትን ካለማወቅ ጋር ነው የምናገናኘው። መቼ የት ቦታ ላይ ነው ካለማወቅ
ጋር የተቆራኘው ቢባል መልስ ያለው አይመስለኝም። ዘረኝነት የተሻለ የሚዛመደው ከእውቀት፤ ከስልጣን፤ከመሳርያ፤ ከሀብት፤
ከተደማጭነት ብቻ ከሀይል ጋር ነው። እኛ ሰዎች ነን። እኛ የተሻልን ሰዎች ነን የሚለውን የሚያመጣውም ይህው ነው። ጊጂም
የሚሆነው ያኔ ነው። አንድ ሰው ስለአንድ አገርና ህዘብና አገር እያወራ ለኛ ለሰዎቹ እያለ ቢቀኝም ምን ለማለት እንደተፈለገ ገብቶናል
ፅድት ያለ ንቀትና ጥላቻን እያራመደ ነው። ስህተትም ነው። አይጠቅምም። እኔ ነፃ ኦሮሚያን የማያት ሊበን ዋቆ ጭንቅልት ውስጥ
ሳይሆን ፕ/ፌ መስፍን ወለደማርያም ጭንቅላት ውስጥ ነው።

ሳይንሳዊ እንጂ ምክንያታዊ አይደለም መሆን ያለብን ከሚለው ክርክር ጀምሮ ሁሉም ፅሁፎቾት ላይ ሳይንስ የገባበት ቦታ ስደርስ ሁለት
ሶስቴ ተመላልሼ አነብ ነበር። ሳይንስ ሆኖ ስላልገባኝ ነበር የእስካሁን ግምቴ። አሁን ግን አልመሰለኝም። ዶ/ር ፍቃደ በቀለ ነኝ ብለው
አራሶትን ይገልፃሉ። ለዚህ የሚሰጡትን ሳይንሳዊ ትንታኔ እኔ ኦሮሞ ነኝ ለሚል ግለሰብ የማይሰራበትን የሚለይበትን መንገድ ሳይንሳዊ
በሚሉት መንገድ ሊያሳዩት አይችሉም። “እንደ ኢትዬጵያዊ እንጂ እነደ ኦሮሞ ማሰብ ሳይንሳዊ አይደልም”። “የገዳ ስርአት የከብት
አርቢዎችና የዘላኖች የሆነ ለእድገትና ለሳይንስ የማይሆን ስርአት ነው”። እነዚህ የመሳሰሉ ትንታኔዎች አንድን ሰው ሳይንሳዊ አይደለም
ባህላዊስ አዋቂ ሰው እንዴት ያደርጉታል። በሳይንስ ለመደብደብ በመጀመርያ ሳይንሳዊ መሆን አያስፈልግም ወይ?። ሌላው ቢቀር እዚህ
የቆየ ስርአት ውስጥ ያሉ ብዙዎቹ እሴቶች ይህው እሰከ ሀያአንደኛው ዘመን ብንመኘውም ልናመጣው ሆነ ልንተገብረው ያልቻለነው
ነው። የሰለጠነው ማህበረሰብ ግን የሚጠቀምባቸው ናቸው። በዋናነት ሰዎች ያስቀመጡት ስርአት ነው። አሁንም ሰዎች ቁጭ ብለው
ማሻሻል አይደለም ለሌላ 21 ክፍለ ዘመን ደግሞ የሚሻል አድርገው ሊሰሩት ይችላሉ። አሁን ባለበትም እስካሁን ካልን ግን በእጅጉ የላቀ
መሆኑ እውነት ነው።

የቢሾፍቱ ፍጅት ተደማጭነት ከለከለው እንጂ ከሊበን ዋቆ በፊት ዳዊት ኢብሳ በትእዛዝ ተናግሯል። ሰምቼው ንግግሩ ጎጂ እንደሆነ
አውቄ ፈርቼም ተናድጄም ነበር። ለምን እንደው አላውቅም ትግሉ አለቆ ከስልጣን የተገፋ አይነት ብቻ ነብስ ይማርና እ/ር ሀይሉ
ሻወልን አስታውሶኛል። ሊበንም ዳውድም የተናገሩትን የተናገሩት በዋናነት ለኛ አልነበረም። ያነጣጠረው ሌላ ቦታ ነው። ትግሉ ላይ
አንጋፋ ከሆንክ ስራ ካልሰራህና አስተዋፆ ከሌለህ የተረሰህ ስለሚመስልህ ቀላሉ መንገድ እኛ ከነሱ የተሻልን ኢትዬጵያዊያን ነን
እንደሚሉት አይነት እኛ የተሻልን ኦሮሞ ነን ነው ጉዳዩ። እነሱ ግን?…….አይነት ነበር መልእክቱ የነበረው። መረሳት፤ አለመፈለግ፤ እኛም
አለን፤ ለፍተን ለፍተን… የተራዘመ ትግል የሚያመጣው የዚህ አይነት ውስብስብ የሆነ የአስተሳሰብ አይነቶች ስለሚኖር ሀላፊነት
ተስምቷቸው ለባለተራዎች ትግሉን ይመሩ ዘንድ መተው አቅቷቸዋል። የዚህ አደገኛነቱ ትግሉ ላይ እንዳየነው ሳንካ መሆን ብቻ
አይደለም። ጭቆናው ቢቀጥል ይሻላልን ምርጫቸው ሊያደርጉ ሁሉ ይችላሉ። እነዚህን ጥሎ መሄድም እንደማይቻል ወይ ቀላል
እንዳልሆነ በቅንጀት ጊዜ አይቼዋለው። ትግሉ ቢተውላቸውም ደግሞ መቼም ታግለው አያሸንፉም። ሁላችንንም ተሸናፊ አድርገው
ይሞታሉ። እጅግ የከበደ ቀላል መፍትሄ የሌለው ችግር ነው።

ውስጥ አዋቂ አይደለሁም። ከርቀት ሆኜ እንደምረዳው የኦሮሞወች ጉባኤ አነሳሱ አስፈላጊም፤ ጠቃሚም፤ ለመልካም አላማም የታሰበ
ነበር። ነግር ግን ይህ አይነት ጥረት ይሳካ ዘንድ የታደሙት ሁሉ እኔና እኝ የሚለው ፍላጎትን ማሸነፍን ይፈልግባቸው ነበር።
በይበልጥም የምንታገለውን አካል ባህሪ በማወቅ ፍጅትን ማስቆም ቅድሚያ መሆን ነበረበት። ዋና አላማ መሆን የነበረበት ትግሉን
መሰዋትነት በቀነሰበት ባጭር ጊዜ ባለድል ማድረግ ነበር። ይህ ይሆን ዘንድ በኦሮሞዎች ዘንድ ጠንካራ ህብረትን ከመፍጠር በዘለለ
ትግሉን አገራቀፋዊ መልክ ማስያዝ አስፈላጊ ነበር። እውነታው የኦሮሞ ህዝብን አንድነት ትግሉ ሰርቶታል። ስለዚህም ጉባኤው
ታሳክቷል ቢባልም በታለመለት መሰረት ስኬታማ አልሆነም የሚል ነው ግንዛቤዬ። ለዚህ ማን ተጠያቂ እንደሆነ ደግሞ ግልፅ ነው።
የሰው ልጅ ትልቁ ጉልበት ጭንቅላቱ ነው። ማንም እዚህ ትግል ላይ አስተወፆ የምር ማድረግ የሚፈልግ ከሆነ ተቀበሉትም አልተቀበሉት
በጭንቅላቱ ያድርግ። የኛ ትግል የጎደለውም አሸናፊም የማይሆነው ጭንቅላት ስለሚጎድለው ነው ብዬ ከደመደምኩ ቆይቻለው።
የኦሮሞ ህዝብ አቢዬት በአገር ደረጃ ትግሉ ላይ በግማሽ የሰው ጭንቅላት ሲንንቀሳቀስ እነደነበር አሳይቶኛል። ትግሉን ከትብያ
አንስተው አሁን ያለበት ደረጃ አድርሰውታል። በየቀኑ አዳደዲስ አዋቂዎችን ሲጎርፉ አይቼ ተደምሜያለው። እነዚህን ቄሮዎች በአማርኛ
የሚናገሩትን አይደለም በኦሮሚኛ የሚናገሩት ቋንቃውን ባይሰሙም በጉጉት ጠብቀው የሚያዳምጡ ብዙዎች ገጥመውኛል።

ከጥቂት መሪዎቻችን በቀር ባህል የሆነው ትግሉንም እንመራለን ፖለቲካውንም እናካሂዳለን የሚሉት ከቁም ሳጥን ጀርባ ተደብቀው
ነው። ደፍረው እራሳቸውን ለህዘብ ቅርብ ያደረጉት በመጨረሻ የተሻሉ ሆነው ቢወጡም ተቀጥቅጠውና አንዱን ሲያልፉት በሌላ ሾኬ
እየተዳፉ ነው። ሰርጎ ገብ ወያኔዎች ነበሩ፤ ሲአኤዎች ነበሩ። ከወያኔ ጋር ተሞዳሟጆች ነበሩ፤ ለምን ብሎ መጠየቅ አይጠቅምም አገርን
ወይ ይህን ወይ ያን ማህበረሰብ ክፍል ለመጉዳት ነው አላማቸው…..በዚሁ አይነት ሁኔታ አሁንም ማደናቀፉ ቀጥሏል። ቄሮዎች ለአንድ
አመት ሌሎቹ በሙሉ ባንድ ላይ ለህዝብ እራሳቸውን ከገለጡት በላይ እራሳቸውን ገልጠዋል። ለህዝብ በዚህ ደረጃ ቅርብ ስትሆን
ለመሳሳት ትክክልም ሆነህ ይህን ወይ ያን ወገን የማስቀየም እድልህ የበዛ ነው። ጥያቄው ይጎርፋል። አንዳንዴ እየተዶለተ መሆኑንም
አንርሳ። አስቸጋሪ በሆነ የፖለቲካ ባህል እጅግ በተከፋፈለ ማህበረሰብ ውስጥ እንደሚሰሩ ግምት ውስጥ እናስገባ። ሰው ሲናገርና ፅፎ
የሚሳሳተውን በእኩል አንመዝን። ሲሳቱ እያረምናቸው ለኛ ቅርብ መሆናቸውን እንውደደው።
ብሔራዊ ጭቆና ይብቃ።

LEAVE A REPLY