በማንኛውም ጊዜና በየትም የዓለም ክፍል የተከሰቱ አምባገነኖች በአንድ ማህፀን ውስጥ እንደተፈጠሩ ፍፁም መንትያዎች (አይዴንቲካል ትዊንስ) በገፅታና በባህርይ በጣም ይመሳሰላሉ። አዲስ የተፈጠሩ አምባገነኖች ታሪክ ሆነው ካለፉት ጨካኞች ብዙ ትምህርት ቀስመውና ልቀው ግፍን ያለገደብ በህዝብ ላይ ይፈፅማሉ።
ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አገር ሆና ባታውቅም በተለይ ባለፉት አርባ ዓመታት የታዩት ደርግና ወያኔ አገራችን በታሪኳ አይታ የማታውቀን ግፍ የሚፈፅሙ ተመሳሳይ አምባገነኖች ናቸው። መንግስቱና ጓዶቹ ሳያስቡት አድባር የጣለችላቸውን ስልጣን ለማቆየት ተቀናቃኞቻቸውን ጨፍልቆ ለመያዝ እስታሊን ሚሊዮኖችን የፈጀበትን ስልት የሚያስተምሩ መጻህፍት ብቻ ሳይሆን አማካሪና መሳርያውንም አሟልታ እናት ሩስያ አስረክባቸው ነበር። ከዚያም በተጨማሪ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የፈጀው የካምቦድያው ፖልፖት፤ በህዝብ የተመረጠውን ሳልቫዶር አየንዴን በአሜሪካ ድጋፍ ገልብጦ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ቺሊያውያንን የፈጀው አጉስቶ ፒኖቼ እንዲሁም የጎረቤታችን የዑጋንዳው ጨካኝ ኢዲያሚን ዳዳ ሥራዎች ምርጥ ምርጡን ለመተግበር ደርግ አሳሳም። እንደ ግበት ተጠቀመበት።
ደደቢት ላይ መሽጎ ራሱን ለደርግ ዙፋን ያዘጋጀው ህወሃት ለአምባገነኖች ቁንጮነት የሚያበቃውን ስልጠና የጨረሰው ባዶ ስምንት ሚባሉት እስርቤቶችና በሌላም የማሰቃያ ቦታዎች በተቃዋሚዎቹና በህዝቡ ላይ በሚተገብረው ልምምድ ነበር። የምኒልክን ግቢ ከተቆጣጠረ በኋላ አገሪቱን ወደ እስርና የስቃይ ማዕከልነት ቀየራት። ከዚህ ቀደም ፅሁፎቼ የደርግንና የወያኔን በብዙ መንገድ መመሳሰል ገልጨ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ደግሞ ሁለቱም አምባገነን ስርዓቶች ምንም የህግና የህሊና ዳኝነት ሳያግዳቸው በመዳፋቸው የወደቀን ህዝብ ጨፍልቆ ለመያዝ ስጋት በገጠማቸው ጊዜ የተጠቀሙባቸውን ሁለት ተቋማት መመሳሰል ለማሳየት እሞክራለሁ። ኮማንድ ፖስትንና አዘአኮን።
ህወሃት ጭንቀት ውስጥ ሲገባ አስቸኳይ አዋጅ አውጆ ሰሞኑን ኮማንድ ፖስት ማቋቋሙንና ህዝቡን በከፍተኛ ጭካኔ ቀስፎ መያዙን ሁላችሁም የምታውቁት ሲሆን በደርግ አገዛዝ ሥር ያለፋችሁትም አብዮታዊ ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ (አዘአኮ) የፈፀመውን ጭፍጨፋና አፈና ስታስታውሱ ውስጣችሁን እንደሚነዝራችሁ እገምታለሁ።
ደርግ መጀመርያ ህዝባዊ ለመምሰል የህዝብ ብሶቶችን አጉልቶ እያሰማ ከወደቀው ንጉሣዊ ስርዓት ተጠያቂ ያላቸውን ባለስልጣናት አስሮ የምርመራ ኮሚሽን በማቋቋም ጉዳያቸውን ማጣራት ጀመረ። ህጋዊ መንገዶችን ተከታትሎ ሊያስወግዳቸው የሚፈልገውን ሁሉ መግደል እንደማይችል ሲያረጋግጥ ያለምንም ህጋዊ ፍርድ በአንድ ለሊት ጨፈጨፋቸው። አገሪቱ በትምህርትና በልምድ ያሳደገቻቸው ዜጎቿን በቅፅበት ተነጠቀች። በዚህም አላበቃም። ተቃውሞ በመላ አገሪቱ ሲንጠው አሁን ወያኔ እንዳደረገው የጦር ካምፕ፣ ወህኒ ቤት፣ ቀበሌ እንዲሁም ትልልቅ መጋዝኖች በወጣትና በተማሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞች ሞላው።
ይህንን ሁሉ ወጣት ጭዳ ለማድረግ ህጋዊ መንገድ መከተሉ እንደማያዛልቀው ሲያውቅ የታዘዘውን ሁሉ አድርግ ሲባል የሚያደርግ አብዮታዊ ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ (አዘአኮ)የሚል ተቋም በየደረጃው መሠረተ። አዘአኮ የሚባለው የግድያና የስቃይ ተቋም መንፈስ ሆኖ በመላ አገሪቱ ጥቁር ደመናውን አጠላ።
በሁሉም ቦታ ያሉ ወጣቶችና ምሁራን ደም እደጎርፍ ምድሯን እስኪያጨቀይ ጨፈጨፈ። የአንድን ሰው ጉዳይ አዘአኮ ይዞታል ከተባለ ቤተሰቡና በወዳጆቹ አጥንት ውስጥ ቀዝቃዛ ፍርሃት ይሰዳል። ሰው ብቻ ሳይሆን ግድግዳው፣ ጣራውና አየሩም አዘአኮ ለተባለው አስፈሪ መንፈስ የተገዙ መሰሉ። በአንዱ ክፍለሃገር ወይንም አውራጃ የተቋቋመ አዘአኮ ሌላ ቦታ ካለው ላለማነስ የግድያ ኮታ እስከማውጣት ደረሰ። ጎንደር በሻለቃ መላኩ ተፈራ የሚመራው አዘአኮ የገደለውን ያህል ለመግደል የጎጃሙ፣ የወሎው፣ የትግራዩ፣ የሸዋው፣ የወሎው፣ የኤሊባቦሩ፣ የአርሲው፣ የወለጋው … ወዘተ አዘአኮ ሰበብ ፈጥሮ ንፁሃንን በመግደል ውድድር ውስጥ ገቡ። አዘአኮ ተቃዋሚ ያላቸውን የህዝቡን ልጆች ከጨረሰ በኋላም ለመፈጠሩ አስተዋፆና ከፍተኛ ተሳትፎ የአደረጉትን መኢሶኖች፣ ማልሬዶች፣ ወዝሊጎችን… ቆረጣጥሞ ሰለቀጣቸው። ስርዓቱን ለማገልገል ለጊዜውም ቢሆን ዋስትና ያገኙ የመሰላቸው ካድሬዎችም ጓዶቻቸውን ካስበሉ በኋላ ህዝቡን ሰብስበው “ አብዮት ልጆቿን ትበላለች!” ብለው መፈክር ሲያሰሙ “ ቱ ድመት ይመስል?” ሲሉ እናቶች ቀለዱባቸው ይባላል።
የአዘአኮን ቲያትር ጫካ ሆኖ ሲከታተልና ስልጣን ከያዘም በኋላ ትልልቆቹን የደርግ ሰዎች ቤተመንግስት አቅርቦ ስልጠና የወሰደው ወያኔ የደህንነቱን ሚኒስትር ተስፋዬ ወልደስላሴን በሚገባ እንዲያስተምራቸው ከአደረጉት በኋላ መወርወራቸውን፤ አሁንም ድረስ ፋሲል ናሆምን የመሳሰሉ ለሁሉም አምባገነን ስርዓቶች የሚያገለግል ተለዋዋጭ ነፍስ ያላቸውን መጠቀማቸውን ሳንዘነጋ) ሁሉንም የደርግ ወንጀሎች በረቀቀ መልክ ተጠቅሞ ህዝባዊ አመፁ ሲጎለብትና ማጣፊያው ሲያጥረው የደርግን አዘአኮ ስም ቀይሮና አሽሞንሙኖ ኮማንድ ፖስት ብሎ አቀረበልን።
ኮማንድ ፖስት መዋቅሩ ሆነ የሥራ መመርያው የአዘአኮ ግልባጭ ነው። ኮማንድ ፖስቱን የተለየ የሚያደርገው ከፈረስ ስምነት የተለዬ ተግባር የሌላቸው፤ የራሳቸውን ስብዕና የተሰለቡ ግለሰቦችን ፊት ለፊት አቅርቦ ከኋላ ዋናውን ተግባር የሚያዝዙት የትግራይ ልጆች ህወሃቶች መሆኑ ነው። አባቶቻችን አባ ዳኘው፣ አባ ታጠቅ የሚል የፈረስ ስም እንደነበራቸው ሁሉ የአሁኑ ኮማንድ ፖስት መሪ “ፕሮፌሰር ጄኔራል” ሳሞራ የኑስ ሲራጅ ፈርጌሳ የሚል የፈረስ ስም ቢኖራቸው ልንገረም አይገባም።
በደርግ ጊዜ የጎንደርን አደባባዮች በለጋ ወጣቶች ደም ያጨቀየው የሻለቃ መላኩ ተፈራ አዘአኮ ነበር። አሁን ደግሞ የወያኔ ኮማንድ ፖስት የጎንደርን ከተሞችና ገጠሮች፣ የባህርዳርን አስፋልትና እስር ቤት፣ በመላ አማራና ኦሮሞ ወጣቶችን፣ የአዲስ አበባ ብሩህ ታጋዮችን፣ ቤንሻንጉል፣ በደቡብ እምቢ ለአምባገነን አንገዛም ባዮችን የሚገድል፣ የሚያስርና የሚያሰቃይ ኮማንድ ፖስት ሆኗል። በአብዮታዊ ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋሙና በገዳይ ቡድኑ ብዙዎችን ጭዳ ያደረገው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም “ትንኝ አልገደልኩም” ቢና ቢፈረጥጥም የመግደያ እጀታ ሆነው ያገለገሉት በርካታ የአዘአኮ አባላት በእስርና በኅብረተስቡ በመገለል የህሊና እረፍት በማጣት ተቀጥተዋል።
የዛሬዎቹ የኮማንድ ፖስት አባላት በተለይም ወገኖቻቸውን ለወያኔ የመግደያ እጀታነት የሚያገለግሉ የየአካባቢው ተወላጆች በቅርቡ መሞቱ እርግጠኛ ከሆነ ስርዓት ጋር ተሰልፈው ዛሬ አይነኬነትና ጀግንነት ቢሰማቸውም በዝምታ እየታዘባቸው ያለው ህዝብ ነገ ሊቀጣቸው እንደሚችል ሊዘነጉ አይገባም። በአሁኑ ሰዓት መያዣና መጨበጫ ያጣው ወያኔ በመላ አገሪቱ ተቃውሞ ስለተነሳበት የሚያስራቸው የሚገድላቸው፣ ቶርች የሚያደርጋቸው ንፁሃን ቁጥር የትየለሌ ነው። ባህርዳር ላይ ጭንብል አጥልቆ በልጆቹ ፊት እስማኤልን እንዲሁን በሕግ ጠለላ ስር ያሉትን አራት እስረኞች የመግደል ወንጀል ስርዓቱ ተስፋ መቁረጡን እንጂ ሌላ አያሳይም። ለዚህ ሁሉ ግፍ ከፋይ አለው፤ አስከፋዩ ህዝብም ራሱን እያዘጋጀ ነው።
ኮማንድ ፖስቱ እያደረገው ያለውና ለወደፊቱ የሚያደርገው ወንጀል በህዝብ ልብ እየተመዘገበ የሚቀመጥ በመሆኑ እንኳንና ዛሬ ቴክኖሎጅውና የህዝቡ እውቀት በተሻለ ሁኔታ ባለበት ጊዜ ይቅርና የከዚህ ቀደም ወንጀሎችም ተዳፍነው አልቀሩም። የአሁኑን ለአሁኖቹ ልተወውና ያየሁትንና ያለፍሁበትን የደርግ ጊዜ አዘአኮ ግፍ ለናሙና ላሳያችሁ። ትናንት የሄድንበትን መንገድ ዞር ብለን በማየት ለዛሬ ጥሩ ማስጠንቀቂያና ትምህርት ይሆነነል ብዬ አስባለሁ። በሰባዎቹ ደብረማርቆስ እስር ቤት ነበርሁ። በተለያዩ ወንጀሎች ተከሶ በፍርድ ቤት ከታሰረው የሚበልጠው በአዘአኮ ተበይኖበት ከሞት የተረፈው ወጣት ነበር። አብዛኞቹ በኢህአፓነት የታሰሩ በመሆናቸው በነሱ ላይ የተፈፀመውን ግፍ የሚታወቅ ነውና ልለፈው። የሚያሳዝነው በርካታ ከተቀመጡበት መነሳት የማይችሉ አዛውንቶች፣ ዐይነ ስውራን ሳይቀሩ ወህኒ ተወርውረው ተረስተው መገኘት የስርዓቱን ፍርሃትና ጭካኔ ያሳይ ነበር። በብዙ የሚገርሙ ዐይነት ወንጀሎች እየተከሰሱ ከታሰሩት ውስጥ አንድ ምስኪን ኢትዮጵያዊን ላስታውሳችሁ። የዚህ ሰው እጣ ፈንታ የብዙ ኢትዮጵያውያንን የሚመሳሰል ነውና ለሁላችሁም አዲስ አይሆንም። ይህ ቅን ሰው በሚሠራበት መስሪያ ቤት ሰራተኛው ሁሉ ተሰብስቦ የካድሬን ድንፋታ በፍርሃትና በፀጥታ ያዳምጣል።
የስብሰባው ድባብ ጭንቀት የተሞላበት፣ ፀጥታው መርፌ ብትወድቅ የምታደፈርሰው በሚመስል ሁኔታ ተሰብሳቢው ትንፋሹና የልቡ ትርታ እንዳይሰማበት በተጠነቀቀበት በዚያ አሰልቺና አስፈሪ አዳራሽ ያልታሰበች የፈስ ድምፅ ከአንዱ አመለጠች። በቋፍ ላይ የነበረው አዳራሽ በሳቅና በሁካታ ተደባለቀ። ተሰብሳቢው በፍርሃት ቆፈን የሚከታተለውን የካድሬ ስብሰባ ስርዓት በሳቅ ሰበረው። ሳያስበው ፈስ ያመለጠው ምስኪን አብዮቱን ለማደናቀፍ ሆነ ብሎ የፈሳ ፀረ አብዮተኛ ተብሎ ወደ እስር ተወርውሮ ተረሳ። ፈስቶ የታሰረ መባል ከእስር ቤት ውስጥም ቢሆን ሌላ እስር ነው።
ሌላም የዚያን ጊዜ የእስረኛ ህይወት ላካፍላችሁ። ደርግ ተቀናቃኞቹን ለመፍጀትና ለማሰቃየት የዘረጋው ጨካኝ ስርዓት ተራ ዜጎችን ሁሉ አሰቃይቷል። በንጉሡ ጊዜ ሰላማዊ በሆነ ፖሊስ ምርመራ አልቆ ፍርድ ቤት ይቀርብ የነበረው ክስ ሁሉ የኢህአፓ ልጆች በተሰቃዩበት የቶርቸር ምርመራ ማለፍ ባህል ሆነ። ሞላ በደብረማርቆስ ቋጠሮ በመሸከም የሚተዳደር ድሃ የልጆች አባት ነው። አንድ ቀን በወጉ ከማያውቃቸው ሦስት ሰዎች ጋር ፖሊስ ጣብያ ተወረወረ። በቀበሌው የጠፋ በግ የበላችሁ እናንተ ናችሁ ተባሉ። ያላደረጉት በመሆኑ አላመኑም። ወፌ ኢላላ ተገልብጠው የውስጥ እግራቸው በጎማ ግርፋት ተተላተለ። ከተደብዳቢዎች አንዱ የስልሳ ዓመት አዛውንት ናቸው። ውስጥ እግራቸው ደም እያዘራ ከእስረኞች ተቀላቀሉ። ይህንን ግፍ ያለፉበት እስረኞች “ለምን በግርፋት ትሰቃያላችሁ። ፖሊስ ያአላችሁን ሁሉ አምናቸሁ ፍርድ ቤት ስትደርሱ ተገድደን ተደብድበን ነው እንጂ አልፈፀምነውም ብላችሁ መካድ ትችላላችሁ” ሲሉ መከሯቸው። (የዚያን ጊዜ ፍርድ ቤት ከዛሬ አንፃራዊ ነፃነት ነበረውና)። በጣም የቆሰለውና ያበጠው እግራቸው አላስኬዳቸው እያለ በሁለተኛው ቀን ተጠርተው ምንም ሳያናግሯቸው ወፌ ኢላላ ገልብጠው ቁስላቸው ላይ ጨው እየነሰነሱ ህሊናቸውን እስኪስቱ ደበደቡአቸው።
እስረኞቹ በመከሯቸው መሰረት ዳግም ላለመመታት አራቱም “አዎ በጉን በልተናል” አሉ። “እንኳን በግ በቀበሌው የጠፋ አህያም ከአለ ብልተነዋል” አለ ሞላ። አዛውንቱም “አዎ በልቻለሁ” አሉ። “ሌላስ ምን በልተሃል” ብሎ ቁስላቸው ላይ የጎማውን ዱላ ሊሳርፍ ሲል ደንግጥው “ሰው በልቻለሁ ልጄ” ሲሉ ብፍርሃት ተርበተበቱ ሽማግሌው፤ “ማንን?” ብሎ ያላሰቡት ጥያቄ አቅርቦ ሊደግማቸው ሲል “ጣልያንን ነው ልጄ አትምታኝ በፈጠረችህ” አሉ ሌላ ጣጣ እንዳይመጣባቸው በመጠንቀቅ። አምባገነን ስርዓት እንዲህ ያሉ ነፍሰበላ አገልጋዮቹን ተጠቅሞ ህዝቡን ያምሳል። ስለ ኮማንድ ፖስቱ ገድል በቦታው ያላችሁ ብዙ የምታሳውቁን ቢሆንም ከአሁኑ የምንሰማው ሁሉ ከደርግ በባሰ እንጂ ባልተናነሰ በዜጎች ላይ ብዙ ግፍ ሲፈፀም ነው። በወለጋ እናትን በልጇ ሬሳ ላይ አስቀምጦ የሚደባደብ፣ ባህርዳር እስማኤልን በልጆቹ ፊት የሚገድል፣ አስሮ በእሳት የሚያቃጥል አምባገነን ስርዓት ነውና ኮማንድ ፖስቱ ብዙ ያልተሰሙ ግፎችን ለመፈፀም የተቋቋመ ተቋም ስለሆነ ብዙ ዘግናኝ ነገር ማየትና መስማታችን የማይቀር ነው።
ህወሃት አገሪቷን ይዟት ሊወድቅ የማይወጣበት ጥልቅ ጉድጓድ እየቆፈረ፣ የመጨረሻ ካርዱን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ገዳይና አፋኝ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ህዝብ እያስጨነቀ ባለበት ሰዓት በተቃውሞ ጎራ አለን የሚሉ ቡድኖች ሆነ ግለሰቦች ትኩረታቸው ይህንን አረመኔ አርዓት ለማስወገድ ከሚያደርጉት ትግል የበለጠ ጊዜ የሰጡት የጎንዮሽ ትግል ላይ መሆኑ ድክመታቸውን ብቻ ሳይሆን ሊነግሩን ያልፈለጉትን የህዝብ ጠላትነታቸውንም የሚያሳይ ይሆናል። አንድ ድርጅት ሆነ ግለሰብ ማንነቱን ከሚነግረን ቃሉ አለጠ የብድርጊቱ እውነቱን ይናገራልና። አንአንዳንዶቹ በዚህ ግርግር ወቅት በህዝብ መከራና ስቃይ ርካሽ የግል እውቅና ለማትረፍ የሚንደፋደፉ ደካሞች ሲሆኑ ከፊሎቹ አውቀውም ይሁኑ ሳያውቁ የህወሃትን ሥራ የሚሠሩ ናቸው። የህወሃት ኮማንድ ፖስት የሚፈራቸውንና የሚጠላቸውን ግለሰቦች፣ ድርጅቶች ሆነ ተቋማት ላይ ኢላማ ማድረጉ የታወቀ ሲሆን የእሱን ሥራ ተቀብሎ መሥራት ከህዝብ ጠላትነት የተለየ ምን ስም ይሰጠዋል። ድክመት ያለባቸውን ከድክመታቸው እንዲታረሙ መምከር የተገባ ሲሆን ለማጥቃት ሌት ተቀን መፍጨርጨር ግን በግልፁ በሃገር ላይ መዝመት ነው። ለዚህ ደግሞ ወያኔ አጋዥ የሚያስፈልገው አይደለም። በቀን ሺ ማሰርና ሺ የመግደል ፍላጎትና ብቃት አለው። ያ ብቃቱ እየተመናመነ ፍፃሜው እንደደረሰ አውቆ ሲንፈራገጥ ተረባርቦ እንደመጨረስ ለወያኔ የነፍስ አድን ሥራ የምትሠሩ ይህ ህዝብ በትዝብት እያያችሁ ስለሆነ ውልታችሁን የሚረሳው አይደለም።
ጃኗሪ 2017
Amerid2000@gmail.com