ባንዳ ማነው ? /ይገረም አለሙ/

ባንዳ ማነው ? /ይገረም አለሙ/

የጽሁፉ ርዕስ  “ለባንዳዎች ፕሮፓጋንዳ  ምላሽ  አለን  በአሥራ  አንደኛው ሰአት ላሉት – ለይገረም አለሙ”  ይላል፡፡  መለስ ያሉት እኔ ዶ/ር ታየ ወልደሰማያት በአስራ አንደኛው ሰአት በሚል ርዕስ ላቀረብኩት ጽሁፍ ሲሆን ጸሀፊዎቹ  ደግሞ ነጠላ ይሁኑ ብዙ በማይታወቅ ሁኔታ ከኢትዮጵያ አንድነት ራዲዮ ስዊድን ነው የሚለው፡፡

ቅድመ ነገር-

ጽሁፉ መልስ ተብሎ ይቅረብ እንጂ  መነሻ ምክንያት ከሆነው ከእኔ ጽሁፍ ጋር አይገናኝም፣ አይዛመድም፡፡ እንደውም እኔን  ባንዳ ብለው ፈርጀው የጀመሩት ጸኃፊዎች በምንና ስለምን ከዚህ ጽሁፍ ጋር ሊያገናኙዋቸው እንደበቁ የማይታወቅ ሰዎችን በጅምላና በግል በመፈረጅና በመሰድብ ነው ጽሁፋቸው ተጀምሮ የተጠናቀቀው፡፡ለዶ/ር ታዬ ጥብቅና መቆም አንድ ነገር ነው፡፡የሚወዱትን ለማሞገስ ግን የሚጠሉትን ሁሉ በጅምላ መወንጀልና መዘለፍ ያውም ምንም ማስረጃ ሳይጠቅሱ የራስን ማንነት ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ የሚኖረው አይመስለኝም፡፡

ቅዱስ መጽኃፍ “መከበርና መዋረድህ ከቃልህ የተነሳ ነው” ይላል፡፡ ( መ/ሲራክ/20/6) ስለሆነም ለእንደነዚህ አይነቶቹ ስድብ፣ ዘለፋና፣ ፍረጃን እውቀትም ብልጠትም አድርገው ለያዙና በእውነት ላይ ተመስርቶ ለመወያየትና በመረጃና ማስረጃ ለመሟገት ለማይደፍሩ ሰዎች መልስ መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ ይህችም ጽሁፍ  የመልስ መልስ ተደርጋ መታየት ይኖርባትም፡፡ የዚህች ጽሁፍ ዓላማም ሆነ ግብ አንድም የስዊድን ወዳጆቼ ከለመዱትም ይሁን ካደጉበት አሉባልታ፣ ፍረጃና መዘላለፍ ወጥተው  በመረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ውይይት እንድናካሂድ ለማበረታት፣ ሁለትም በዚህ መንገድ እውነትን ውሸት፣ ውሸትን እውነት ማድረግ እንደማይቻል ለማስታወስና ሶስተኛ ደግሞ በፍረጃ፣ በዘለፋና በስድብ ዝም ለማሰኘትም ሆነ ከመድረኩ ለማባረር እንደማይቻል ለመንገር ነው፡፡ ትናንት ከትናት በስቲያ ድብቅ ማንነታችንን ያጋልጣሉ፣ ለፍላጎታችን እንቅፋት ይሆናሉ ያሉዋቸውን ሰዎች በእርዳ ተራዳ አሉባልታና ፍረጃ ዝም አሰኝተው ከመድረክም አባራው እፎይ ብለው ለመኖር ችለው ይሆናል፡፡ ያ ግዜ ግን አልፏል፣ትናንት ዛሬ አይደለም፣ ዛሬም ነገ አይሆንም፡፡

በቅሎ አባትሽ ማነው ቢሏት ፈረስ አጎቴ ነው አለች፣

በቅሎዋ የተጠየቀችውን ትታ ሌላ የመመለሷ ምክንያት አባቴ አህያ ነው ለማለት አፍራና ፈርታ ነው፡፡ የስውዲኖቹ ወዳጆቼ እኔ በጽሁፌ ከአነሳሁት ሀሳብና ጥያቄ  በተቃራኒ ብዙ የማለታቸውን  ምክንያት የሚያውቁት እነርሱ ቢሆኑም በጽሁፉ የተገለጸውን አምነው ለመቀበል ድፍረት፣ ሀሰት ብለው ለመከራከር እውነትም፣ መረጃና ማስረጃም የሌላቸው በመሆኑ ነው ለማለት ግን ይቻላ፡፡  ቅኔው ቢያልቅበት ቀረርቶ ጨመረበት እንዲሉ መሆኑ ነው፡፡

የእኔ ጽሁፍ በአጭሩ “የማከብራቸውና የማደንቃቸው የነበሩት የሙያ ማህበሩ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታየ ወልደሰማያት አስራ አንደኛው ሰአት ሊባል በሚችል ወቅት በ1999 ዓ.ም መልቀቂያ ደብዳቤም ሳያስገቡ የፖለቲካ ፓርቲው ቅንጅት ዓለም አቀፍ ም/ቤት ፕሬዝዳንት በመሆናቸው ራሳቸውንም ሁለቱንም ድርጅቶች ጎድተዋል፡፡ላለፉት ሰባት ዓመታት ከመድረክ ያጠፋቸውም የዛ ጦስ ይመስለኛል፣ የሚል ሀሳብ ሰንዝሮ የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ዶ/ር ታዬ አሁን ከሰባት ዓመት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ አስራ አንደኛው ሰአት በሚባልበት ወቅት ብቅ ያሉት ከዛ ስህተት ተምረው፣ የሚሰሩትን በቅጡ አስበውና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር መዝነው፣ ወይንስ ወቅት ጠብቀው”  በሚል ጥያቄ ነው የተቋጨው፡፡

በወዳጆቼ መልስ ተብሎ የቀረበው ጽሁፍ ግን በአስራ እንደኛው ሰአት ላሉት ለይገረም መልስ ከማለቱ በስተቀር እኔ ያነሳሁዋቸውን ጉዳዮች አንዱንም አልነካ፡፡ በርግጥ ጽሁፌ በእጅጉ እንዳበሳጫቸው ጽሁፋቸው ያሳብቃል፡፡ ግን የቱንም ያህል ቢበሳጩ ከእኔ አልፈው በህልማቸውም በእውናቸውም በጥላቻ የሚያዩዋቸውን ሰዎች ሁሉ መዝለፍና መፈረጅ አልነበረባቸውም፡፡ አንባቢያን ከጽሁፋቸው  ለአብነት እነዚህን ተመልከቱና ፍረዱ፡፡

  • በዲያስፖራው አናት ላይ ቁጢጥ ካለው የክህደት ደቀመዛሙርቶች፣
  • በዲያስፖራው የተደበቁትን ከሃዲዎች ማንነት ተሃድሶ ለመስጠት፣
  • ባንዳዎች ውሸት እንዲነግስ ይሰራሉ፣
  • የዲያስፖራው ጀሌ፣
  • የዘመኑ ባንዳዎች ከወያኔ ጋር በአንድ አልጋ ሲተኙ በነበረበት ወቅት
  • ዘመኑ የባንዳ ዘመን ለመሆኑ፣
  • ከደቂቅ እስከ ምሁር የግል ጥቅም አሳዳጅና አፋሽ አጐንባሽ በመሆን በወያኔ ጫማ ሲወሸቅ፣
  • በዘመናችን በፍርሃት ተሸመድምደው ራሳቸው በጥፍራቸው ውስጥ ለመደበቅ ለሚዳዳቸው፣ ይብቃን፣ብዙ ነው፡፡

ለመሆኑ ባንዳው ማነው?

ከላይ ለአብነት የቀረቡት ከጽሁፉ የተወሰዱ ሀረጎች እንደሚያሳዩት ከኢትዮጵያ አንድነት ራዲዮ በማለት የጻፉት ሰዎች ራሳቸውን እውነተኛ ሀገር ወዳድና ታጋይ አድርገው  ዲያስፖራውን በሙሉ ወንጅለዋል ፈርጀዋል፡፡ ከዚህ ተነስቶ  በእኔ ጽሁፍ ምክንያት ዲያስፖራውን በጅምላ ባንዳ ለማለት ያበቃቸው ምክንያት ምንድን ነው? ዶ/ር ታየን ማሞገስም ሆነ ማወደስ መብታቸው ነው፣ ግን እርሳቸውን ለማድነቅ የጠሉትን ሰው ሁሉ መስደብ መወንጀልና መፈረጅ በምን አግባብ ነው ተገቢ የሚሆነው?  ወዘተ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ እነዚህን  እነርሱ እንጂ እኔ ልመልሳቸው የማልችል ጥያቄዎችን እያብሰለሰልሁ ሳለሁ  ጽሁፉ ውስጥ ከርዕሱ  አስከ ግሱ ብዙ ቦታ የሚገኘው ባንዳ የሚል ቃል ለምን፣እንዴትና በምን ሁኔታ በሰዎቹ ላይ ቤቱን ቢሰራ ነው የሚል ሌላ ጥያቄ ተጫረብኝ፡፡ እናም በሀሳብ ላይ እንጂ በሀሳቡ ባለቤቶች ላይ ማተኮር አይገባም የምለው ሰው ሳልወድ በግድ እኒህን ባንዳ የሚል ቃል በውስጣቸው የበቀለ የሚመስል ሰዎችን ማንነት ለማወቅ ትንሽ ሙከራ አደረግሁ፡፡ በተለይ ወደ ድረ-ገጻቸው ጎራ ብዬ ያገኘሁት ምላሽ “የመርካቶ ሌባ ሰርቆ ሲሮጥ ሌባ ሌባ ይላል” የሚለውን አባባል የሚያስታወስ ሆነብኝና በእነዚህ ሰዎች ብዕርና አንደበት አኔም ሆንኩ መላው ዲያስፖራ ባንዳ የመባሉ ምስጢር ተከሰተልኝ፡፡ ጉድ ነው! የስውዲን ወዳጆቼ የዛን ዘመን ሰዎች ትመሱልኛላችሁና አመልካች ጣት የሚለውን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን ታስታውሱታላችሁ ፡፡ አንዷን ጣትህን ወደ ሰው ስትቀስር አራቱ አንተን ይመለከቱሀል ነው የሚለው አይደል! ወዶ አይስቁ አሉ!

ለአውነት ስለ እውነት እንነጋገር ፤

የጥላሁን ገሰሰ ዘፈን ስል ሌላም ትውስ አለኝ፡፡ ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነፍሴ የምትለዋ ፡፡ ቅዱስ መጽኃፍም እውነት ነጻ ያወጣችኋል ይላል፡፡ ለዘመናት ለትግል እንጂ ለድል ያለመብቃታችን አንዱ ምሥጢር ከእውነት መጣላታችን ሳይሆን ይቀራል ትላላችሁ፡፡ ድጋፋችን የጥቅም፣ የእከክልኝ ልከክልህ፣የአምቻ ጋብቻ ወዘተ፣ተቃውሞአችን የጥላቻ የምቀኝነት ወዘተ እየሆነ በእውነት ላይ ቆመን ከመነጋገር አሉባልታ ማረገብን፣ በመረጃና  በማስረጃና ከመከራከር ዘለፋ ፍረጃና ውንጀላን የሙጢኝ ብለን ይዘን ስንት ትውልድ ተሸጋገርን፡፡ የሚያሳዝነው ከእኛ የቀደሙትንም ሆነ እኛን እንዳልጠቀመ እያወቅን እንደ ቁም ነገር ለቀጣዩ ትውልድ ልናወርሰው መሆናችን ነው፡፡ መረጃና ማስረጃ በቀላሉ በሚገኝበት ዘመን አሉባልታ መጻፍና መናገር       (መረጃም ሆነ ማስረጃ ያልቀረበበት ነገር አሉባልታ ነው) እንዴት እንደማያሳፍረን አይገባኝም፡፡ ምን አልባት ጸኃፊዎቹ ከዓላማቸው አንጻር ይሆናል፣ለንባብ የሚያበቁት ጋዜጦችም ሆኑ ድረ ገጾች ግን ይህን ሁኔታ የመለወጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም በተለይ አንዳንዶቹ የሚያበረታቱ ነው የሚመስለው፡፡ይህን ባህል መለወጥ ባለመቻሉም  በአንባቢው ዘንድ አምስቱ ወርቃማ ጥያቄዎች የሚባሉትን (መቼ፣የት፣ማን/በማን፣እንዴት፣ለምን) የመጠየቅ ልምድ ማዳበር አልተቻለም፡፡ ይህ ደግሞ አሉባልታ ቁም ነገር ሆኖ፣ጥላቻ መዝራት መወገዙ ቀርቶ፣ስድብ ዘለፋና እሽኮለሌ አስነዋሪ ምግባር መሆናቸው ቀርቶ በየጋዜጣው በየድረ-ገጹ ይጻፋሉ፡፡

ትንሽ ስለ ዶ/ር ታዬ፤

ዶ/ር ታዬ  በጽሁፉ ላይ ምንም ስላሉ አድናቂና አድማቂ ነን ያሉ የፈለጉትን ቢሉ ሊወክሉዋቸውም ሊተኩዋቸውም ስለማይችሉ ምንም አልልም፡፡ ለአድናቂ ነን ባዮቻቸው ግን የምላቸው አንደኛ ይዘታችሁ ደጋፊ ሳይሆን አቃፊ መሳይ ገፍታሪ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የዚህ አይነት ድጋፍ ወደ ገደል ሲከት እንጂ ወደ ሰገነት ሲያወጣ አላየንምና፡፡ ምን አልባትም በ1999 ዓም ዶ/ር ታዬ ከአንድ የፖለቲካ ሳይንቲስት የማይጠበቅ ስህተት የሰሩት በእናንተ ጊዜን ያላገናዘብ ሆይ ሆይታ ይሆን ብዬም ተጠራጠርኩ፡፡ የዶ/ር ታዬ ብቅ ማለት ያስደነገጠህ ትመስላለህ ላላችሁትም በፍጹም ነው መልሴ፡፡ የሰው ድርቅ የመታው የተቃውሞው ጎራ ያውም የፖለቲካ ሳይንቲስት፣ ያውም በወያኔ እስር ቤት መከራ የቀመሰ ታጋይ ሲያገኝ ለምን እደነግጣለሁ፡፡ ግን እኔ የምሻው ታዬ እንደ 1999ኙ ድንገት “ይሄ ወቅት አይለፈኝ” ብሎ በአስራ አንደኛው ሰአት ብቅ የሚለውን ሳይሆን ትናንትን አስታውሶ ዛሬን በቅጡ ገምግሞ ስለ ነገም ተንብዮ ከዚህ በመነሳት በሰፊው አቅዶ በረዥሙ ተዘጋጅቶ የሚመጣውን የፖለቲካ ሳይንቲስት ዶር ታዬ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በሰዎች ትከሻ ተንጠላጥለው ወንዝ መሻገር ከሚሹ፣አጉል ሙገሳና ውደሳ ከሚደረድሩ፣ ሳያዳምጡ ከሚያጭበጭቡ ሰዎች ጎራ ወጥቶ በሀሳብ ከሚሞግቱ፣ተገቢ ትችት ከሚሰነዝሩ፣ለምን ብለው ከሚጠይቁ ወዘተ ጋር መስራትን የሚመርጥ ታየን ነው የምሻው፡፡

በመጨረሻ፣

በእድሜአችን እንዳየነውም ሆነ ከታሪክ እንደምንረዳው ከአንባገነን አገዛዝ እንዳንላቀቅ ያደረገን የሀገራችን ፖለቲከኞች ዋናው ችግር አንደበታቸውና ልባቸው አንድ አለመሆን ነው፡፡ በቃላቸው ህዝብን የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ እንደሚታገሉ ይነግሩናል፣በተግባር ግን አልሆነላቸውም አንጂ ራሳቸውን ምንይልክ ቤተ መንግሥት ለማገባት ይማስናሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ማለት በሚቻል መልኩ ያችን አንድ ወንበር ይመኛሉ፣ ለዚህም ርስ በርስ የጠላላሉ፣ አንዱ ለሌላው እንቅፋት ይሆናል በዚህ መሀል ዋናው ጠላት ይረሳል፡፡ደጋፊ ነኝ ባዩም ለምንና ስለምን እንደሚደግፍ እንኳን በቅጡ ሳያውቅ ወይንም በመሪዎቹ ሰብከት እየተታለለ ጎራ ለይቶ ይሻኮታል፡፡የእኔ የሚለው የፈለገው ገሀድ የሚታይ ስህተት ቢሰራ እንዲነካበት አይፈልግም፡፡ ስህተቱን የሚጠቁሙ ድክመቱን የሚተቹ ከተገኙ በእርዳ ተራዳ የስድብና የዘለፋ ናዳ ይወርድባቸዋል፡፡ በተቃራኒው የሚጠሉት ወይም የሚቀኑበት ወገን የቱንም ያህል በጎ ነገር ይስራ አይታያቸውም፣ብቻ ጥላቻቸውን በአሉባልታም በፍረጃና ውንጀላም ባላተገራ ምላስና ብዕር ይለቁታል፡፡ ከዚህ አይነቱ ነውር ተግባር መውጣት ካልቻልን ከወያኔ አገዛዝ መላቀቅ አንችልም፡፡ በርግጥ የወያኔ አገዛዝ እንዲቀጥል የሚሹ በፖለቲካውም  ፖለቲካዊ ባልሆነውም መስክ ያሉ ተቀዋሚ ተብየዎቸ መኖራቸው ሳይዘነጋ ነው፡፡

LEAVE A REPLY