ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ያሆነኝ ባለፉት ጊዜያቶች “የለውጥ ሐይሎችግልጽና ደፋር ውይይት ለመፍትሄና የጋራ ድል” በሚል ርእስ ተዘጋጅተው ከተሰራጩት ግብረ-መልሶች በመነሳት ነው። መጣጥፎቹ ከቀረቡና በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ላይ ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ሃሳቡን በመደገፍም ሆነ በመቃወም የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በተደጋጋሚ እንደተጠቆመው ከተራ ስድብ ባሻገር የቀረቡትን ሃሳቦች በሙሉ ከፍተኛ አክብሮት የሚሰጣቸው ናቸው። የተፈለገውም “ግልጽና ደፋር ዉይይት” ማድረግ ስለሆነ አላማው በከፊል እንደተሳካ ሊወሰድ የሚችል ነው።ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ለማለት አፌን ሞልቼ መናገር ስላልቻልኩ ነው። ለሁሉም እንደሚታየው አንድ መጣጥፍ ለህዝብ ሲቀርብ የተወሰነውን አንባቢ ያስደስታል። ከፊሉን ምንም ትርጉም አይሰጠውም። ግማሹ ደግሞ ከመናደድ አልፎ ጸሃፊውን አግኝቶ ለመተናኮል ያስባል። የኢትዮጵያን ችግር መፍትሄ አንዲት ገጽ ጻፍ ቢባል እንደ ሎጥ ሚስት የሚሆነው ሌሎች ባቀረቡት ላይ ቡጡ ካልተሰረዝኩ ይላል። ስሙን በደበቀበት ፌስቡክ ለጽሁፍ አቃቂርና ለንግግሩ ለናቲካ ለማውጣት ይሯሯጣል። ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ያላልኩት እንደዚህ አይነት ትናንሽ ሰዎች በየቦታው በመኖራቸው ነው። አብዛኛው ህዝብ ግን በችኮላና ስሜታዊነት ሳይሆን በጥንቃቄ እውነቱን መርምሮ ለመረዳት በመፈለጉ ትልቅ ጉልበት ሰጥቶኛል።
ከዚህ በተረፈ ከመጣጥፍ ፍሬ ሃሳብ በመነሳት የፖለቲካ አቋሜን ለጠየቃችሁኝ ግለሰቦች ግልጽ አድርጌ መሄድ የምፈልገው ነገር አለ። አጭርና ግልጽ በሆነ አማርኛ ለማስቀመጥ ከኢትዮጵያዊነት የወረደ ብሔርና ማንነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አደረጃጀት አልደግፍም። የብሔር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ችግር ዘላቂ መፍትሄ አይሰጥም ብዬ አምናለሁ። የብሄር ፖለቲካን ማንም ጤናማ ሰው ሊመኘው የማይገባ እንደሆነ እገነዘባለሁ። መጨረሻውም ቢሆን በፉክክርና ሽሚያ ላይ የተመሰረተ ጠላትነትና ውድመት ሊያስከትል ይችላል። በነገራችን ላይ ይህን በተመለከተ ከዛሬ ሁለት አመት በፊት በተጻፈው “የመለስ ትሩፋት ባለቤት አልባ ከተማ” በሚለው መጽሃፍ ላይ በግልጽ ተመልክቷል። በመጽሃፉ ገጽ 186 ላይ ማንነትን ማጥናትና ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ ግን ደግሞ የፖለቲካ አደረጃጀት ለመፍጠር መሳሪያ ሆኖ ማገልገሉን እንደማልቀበል፤ ይህን ደግሞ ንድፈ ሃሳብ ሳይሆን በተግባር አይቼው መግለጤን መመልከት ይቻላል። በሌላ አገላለጽ እኔ የምደግፈውና የማበረታታው የፖለቲካ አደረጃጀት የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፍሎ ለማደራጀት የሚያስብ ሳይሆን በዜጋ ላይ የተመሰረተና “ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት” ህብረ-ብሄራዊ የሆነውን ነው። ለማንኛውም በመጽሀፉ ላይ በተጠቀሰው ገጽ የተገለጸው በከፊል እንዲህ ይላል፣
“ማንነትን ማጥናትና ማወቅ ነውር አይደለም። ክፋት የሚሆነው የፖለቲካ መሳሪያ ካደረግነው ብቻ ነው። የፖለቲካ ግብ ሳይቀመጥ በህሊናችንየሚንገዋለሉ እና ያልተመለሱ ጥያቄዎችን አንስቶ መነጋገሩ የሚያበረታታ ነው” በማለት ተገልጿል። በመሆኑም የእኔ ፍላጎት በኢትዮጵያ የሚገኙ የበርካታ ብሄረሰብ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና እምነቶች ላይ በመነጋገርና የውበታችን መገለጫ እንጂ የልዩነታችን መሰረቶች ሆነው ለሁላችንም ድክመትና ክፍት መሳሪያ ሆኖ እንዳያገለግል ነው።
እዚህ ላይ ሌላም ነገር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ። በግለሰብ ደረጃ “ብሔርን ማእከል” ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት ውስጥ መታቀፍን አለመፈለግ ማለት ሌሎች በዚህ መልኩ የተደራጁትን መንቀፍ ማለት እንዳልሆነ በመጽሃፉ በማሻማ መንገድ ተመልክቷል። ይልቁንስ አንዳንድ አካባቢዎች ከመካከለኛን አጭር ጊዜ አኳይ ብሄር ተኮር አደረጃጀቶች ከነባራዊ ሁኔታ ተነስተው ተገደው የሚገቡበት አሊያም ለስልጣን ማግኛ አቋራጭ መንገድ እንደሆኑ ተጠቁሟል። ተገደው የሚገቡበት ሃይሎች ወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትኩሳት ገፍቷቸው እንደሆነ እገምታለሁ። ባለፉት ሩብ ክፍለ-ዝመናት በኢትዮጵያ ምድር የተዘራው የብሄር ፖለቲካ የፈጠረው ጫና እንዳስገደዳቸው እገምታለሁ። በምርጫ 97 በነበረው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በኦሮሚያ ከሚገኙት ዋን ዋና ከተሞች ውጭ የህዝቡን ውሳኔ በምሳሌ መውሰድ ይቻላል።
እንደ ኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) አይነት የመጨረሻ ግባቸውን በዜግነት ላይ የተመሰረተ ስርአት መመስረት ያደረጉ ድርጅቶች ይህ ነባራዊ አስገዳጅ ሁኔታ ወደዛ እንደከተታቸው ከሩቅ ሆኖ መገመት ይቻላል። እንደዚህ አይነት ድርጅቶችን መዳረሻቸው ላይ ቶሎ እንዲደርሱ መደገፍ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። መንገዱ አባጣ ጎርባጣ ቢሆንም ዜግነትን መዳረሻ ያደረገና በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተመሰረተ ግብን የሚያስቀምጥ ድርጅት አባላት የሆኑ ግለሰቦች በሂደት ወደ “ኢትዮጵያዊ ማንነት” እንደሚመጡ መገመት ይቻላል። የማንነት ውሳኔው የግለሰቦች ስለሆነብኝ እንጂ አፌን ሞልቼ “ናቸው!” ብዬ መናገር እችላለሁ። “ኢትዮጵያዊ ማንነት” ማለት አብዛህነትን መቀበልና ማጎልበት በመሆኑ ከዛ በታች ያሉ ማንነቶችና መገለጫዎችን እንደ ቅርንጫፍ የሚወስድ ነው። ግንዱ ውሃ ከጠማው ቅርንጫፎቹም ይጠማቸዋል። ግንዱ ከደረቀ ቅርንጫፎቹም ይደርቃሉ። ግንዱ ከሞተ ቅርንጫፎቹም ይሞታሉ። መዳረሻ ማለት ይሄ ነው።
ከዚህ በተቃራኒ የብሄር ፖለቲካን ለጥቅምና ስልጣን መወጣጫ ሊጠቀሙበት የሚችሉ ሃይሎች መኖራቸው መሬት የተነጠፈ እውነት ነው። ይሄንን አላማ ያደረጉ የቡድኑ ኤሊቶች ደጋግመው ቁርሾን በቀልና ጥላቻን እያነሱ በጊዜያዊነት ከጎናቸው ማሰለፍ ይችላሉ። በውስጣቸው ያለው ልዩነትም አንደኛው ከሌላኛው ይበልጥ ተቆርቋሪና ጠበቃ ማሳየት ነው። እዚህ ላይ ከቡድን አስተሳሰብ ተጣምሮ ልንሄድባቸው የሚችሉ ጥያቄዎች እንደሚኖሩም የተዘነጋ አይደለም። የጋራ ማንነቶች እየተዳፈሩ በሄዱ ቁጥር በተደራጀ መንገድ ጭቆናውን ለመገርሰስ የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል። እርግጥ የዜጋ መብት ሙሉ በሙሉ በተከበረበት ሁኔታ በቡድን ደረጃ የሚጎድል ነገር ያለ አይመስለኝም።
በአጠቃላይ መልኩ “የግለሰብ ማንነትን” የመወሰንም ሆነ በየትኛው አደረጃጀት ብታቀፍ ይሻለኛል የሚለው ጥያቄ የራስና የራስ ውሳኔ ብቻ ነው። በመሆኑም የእኔን “ግለሰባዊ ማንነት” የመወሰን ብቸኛ መብት የራሴ ብቻና ብቻ እንደሆነ፤ ማንም ሊሰጠኝና ሊነፍገኝ እንደማልፈቅድ ሁሉ የሌላውንም በተመሳሳይ ማክበር እንዳለብኝ ለጥያቄ የሚገባ አይደለም። እኔ በውቢቷ አዲስ አበባ ውስጥ የተወለደ፣ ያደገና የጎለመሰ “ኢትዮጵያዊማንነት” አለኝ። ባለቤቴም እንደነገረችኝና እንዳወኳት ከእኔ ጋር ማንነቷ ተመሳሳይ ነው። ኑሮአችንን የምንመራው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ይህም ባስገኘልን ተጨባጭ እሴቶች ላይ ተመስርተን ወደፊት እንራመዳለን።በተቃራኒው ልጃችን ደግሞ ለእኔና ለባለቤቴ ባእድ በሆነ “አሜሪካዊ ማንነት” ውስጥ እያደገችና እየጎለመሰች በመሄድ ላይ እንደሆነች መመልከት ይቻላል። በ21ኛው የግሎባላይዜሽን ክፍለ-ዘመን ደግሞ “አሜሪካዊ ማንነት” ማለት “አለም አቀፋዊ ማንነት” ነው።
***
ልጄ ከመደበኛ የእንቅልፍ ሰአቷ ውጭ አብዛኛውን ጊዜ እንድታጠፋ የምትገደደው በዚሁ ማንነት ዙሪያ ነው።በግለሰብ ማንነት ላይ የተመሰረተው የአሜሪካን የትምህርት ስርአት ቀን ከሌት “ሰው” በመሆኗ የምታገኘውን የማይገረሰስ መብት ከመንገር አልፈው ወደ ተግባር እንድትለወጥ ያስተምሯታል። በዚህ ምክንያት “ሰው” የሚባለውን መሰረታዊ ማንነቷን እና ሰው በመሆን ያገኘችውን መብት ለማንም አሳልፋ ሳትሰጥ ተግባራዊ ታደርጋለች። አሁንም በትምህርት ቤቷ ስለ አሜሪካዊ ዜግነት፣ የዜግነቱ መብት እሴቶችና ጥቅሞቹን ያስተምሯታል። በአመት አራት ጊዜ በትምህርት ቤቱ አዳራሽ ተማሪዎች በሙሉ በተሰበሰቡበት በሩብ ሴሚስተሩ “ተምሳሌታዊ ዜጋ” የሚል ሽልማት እንዲሰጥ ያደርጋሉ።
“በተምሳሌታዊ ዜጋ” ለሽልማት የሚቀርበው ተማሪ አሜሪካንና ባንዲራውን እንዲሁም ዜጎቿን የሚወድ፤…ለአሜሪካ መስራች አባቶች ክብር የሚሰጥ፤…ለአሜሪካ መስዋእት የሚሆኑ ወታደሮችን የሚያከብር፤… ዜጎችን በዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት የማይለይ፤…ጓደኞቹን፣ቤተሰቡንና አዛውንቶችን የሚረዳ፤…አካባቢውን የሚያውቅና የሚንከባከብ..፤…የእንግሊዘኛ ቋንቋን የሚጠቀምና የሚያሳድግ፤… ነገ መሆን የሚፈልገውን ነገር የሚያውቅና ዝግጅት የሚያደርግ ወዘተ በመመዘኛነት የሚወሰድ ነው። በእነዚህ ተመጋጋቢ ማንነቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ ተማሪ በትምህርት ቤት ማህበረሰቡ (የትምህርት አመራሩ፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆቹ) ፊት ስሙ ተጠርቶ በሞቀ ጭብጨባ “Good Citizenship” ሪባን ይጠልቅለታል። ወደ ቤቱ ይዞ የሚሄደው የክብር ሰርተፊኬት ይሰጠዋል። ብዙዎችም በፍሪጃቸው ላይ ይለጥፉታል።
አሜሪካውያን ማንነትን እየገነቡ ያሉት በዚህ መልኩ ነው። በሰማዩ ጋሪ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ተሻግራ የመጣችው ልጄ ባለፈው የትምህርት አመት ከአራቱ የሽልማት ወቅቶች ሶስት ያህል ጊዜ አሸንፋለች። “የአሜሪካ ተምሳሌታዊ ዜጋ” የሚል ክብርም ተጎናጽፋለች። በአእምሮ፣ በመንፈስና በተክለ-ሰውነቷ የሰው ልጅ ሁሉ እኩልነት በመገንዘቧ፤ የዜግነት መብትና ግዴታዋን በማወቅ፤ ነገ መሆን የምትፈልገውን በመለየቷና እውን መሆን በመትጋቷ ባገኘችው ክብር እደሰታለው። ለሰው ልጅ የምታሳየውን ርህራሄ፣ ደግነትና የመሳሳት ስሜት ስመለከት የህሊና ወቀሳ ይሰማኛል። ይሄንን ሙሉ ሰውነቷን ጠብቃ እንድትኖር እመኛለሁ። ይሄ እውነታ የእኔ ልጅ ብቻ አይደለም። እንደውም አመቱን ሙሉ በየሩብ አመቱ በሚሰጠው ሽልማት አንድም ያላመለጣቸው የኢትዮጵያውያን ልጆች እንዳሉ አይቻለሁ። ከቤተሰቦቻቸው አዳምጫለሁ። ከዛም በላይ በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች በመጋበዝ ልምዳቸውን የሚያካፍሉ ወጣቶች ተመልክቻለሁ። ብርሃናማ ውጥናቸውን ሲናገሩ አዳምጫለሁ። እግዜብሔር ይርዳቸው!!
በሌላ በኩል የእኔ “ኢትዮጵያዊ” ማንነት በልጄ ደረጃ መቆም ባለመቻሉ አዝናለሁ። በተለይም ጠዋት ጠዋት ወደ ትምህርት ቤቷ ስወስዳት የአሜሪካ ወታደሮችን በዩኒፎርማቸው ካገኘች “ስለ አገልግሎትህ አመሰግናለሁ!” “Thank you for your service!!” የሚል ቃል ከአንደበቷ ሲወጣ ልቤ እጥፍ ይመታል። ባለ ዩኒፎርሙ ኮስተር ብሎ “Thank you! Have a nice day!” ሲላት ውስጤ ይርዳል። እንዳየሁት ከሆነ ለልጄ በዩኒፎርም ውስጥ ያለው ወታደር የዘር ግንድ ነጭ ይሁን ጥቁር፤ ጃፓን ይሁን ቻይና፤ አፍሪካ ይሁን ስፓኒሽ፤ ፍልስጤም ይሁን እስራኤል፤ ኤርትራዊ ይሁን ኢትዮጵያዊ ደንታዋ አይደለም። ወንድ ይሁን ሴት ቁብ አይሰጣትም ፥ የምታውቅም አይመስለኝም። ለእሷ ትልቁ ነገር ባለዩኒፎርሙ አገሩን ሊያገለግልና መስዋእት ለመሆኑ ዝግጁ የሆነው ሰው ነው። ለእሷ ትልቁ ነገር የዜግነት ግዴታዋን በመወጣት አርአያ የሆነውን ሰው መመልከቷ ነው። ለእሷ ትልቁ ነገር የማንነቷ መገለጫ የሆነውን ሰው ከነሙሉ ጀግንነቱ ማየቷ ነው። ለእሷ ትልቁ ነገር ባለዩኒፎርም ውስጥ አሜሪካዊነት (“the sky is the limit”) ለማየት፣ ለማሽተት፣ ለመቅመስና ለመዳሰስ በመቻሏ ነው። ለእሷ ትልቁ ነገር አርሊንግተን መካነ-መቃብር ለመጎብኘት በሄደች ሰአት ለአገራቸው መስዋእት የሆኑ ሰማእታት መቃብር ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የክብር የአበባ ጉንጉን ከሚያስቀምጥላቸው ሰዎች አንዱን በመመልከቷ ነው። የልጄ ተጨማሪ ደስታ እየሰለጠነች ያለውን የካራቴ ትምህርት አጠናክራ ከቀጠለች ነገ ከነገ ወዲያ የባለ ዩኒፎርሙ አይነት ተክለሰውነትና ቁመና እንደሚኖራት እርግጠኛ መሆኗ ነው። ታዲያ የእለት ጥንካሬዋን ለመፈተሽ ባለዩኒፎርሙ(ሟ) ከአይናችን ከመራቁ(ቋ) በፊት ክርኗን አጨማዳ አይጧን እየነካካች ታሳየኛለች።
***
የልጄ የማንነት ግንባታ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ከትምህርት ቤት ስትመጣና በእረፍት ቀናት ከቤተሰቦቿና ቤተ-ዘመዶቿ ጋር ትገናኛለች። ቤተ-ዘመዶቿ የብዙ ነገዶች ቅልቅል በመሆናቸው የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች ትመለከታለች።ከዚህ በተጨማሪም ቤተ-ዘመዶቿን በእድሜያቸው፣ በጾታቸው በስራቸው አይነት ለይታ ትቀርባለች። ራሷንም ከሁኔታዎች ጋር ለማዛመድ ጥረት ታደርጋለች። በትምህርት ቤት በሰፊው የምትጠቀምበትን ቋንቋ እና የቤተ-ዘመዶቿን ቋንቋ በማዛመድና ማወራረስ ለመጠቀም ትሞክራለች። በተለይም ከምትወዳቸው አያቶቿ ጋር በቋንቋ ለመግባባት የምታደርገው ፍትጊያ በአካባቢዋና ት/ቤት ከለመደችው ጋር ግጭት እየፈጠረ ትምህርት የመቅሰሚያ ቦታ ሆኗታል። በቅርብ ተዟዙሬ እንደተመለከትኩት እንዲሁ አይነት በመማር ማስተማር ሂደት የሚገነባ ማንነት በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቤት ይገኛል። በተለየ የወንድና የሴት አያቶቻችን የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም። ምስጋና ይድረሳቸው። ፈጣሪ ረጅም እድሜና ጤናአይንፈጋቸው!
ለራስ ሲቆርሱ ካልተባለ በስተቀር መቼም እንደ እኔ ልጅ ክትፎ፣ አዋዜ ጥብስ፣ ገንፎ፣ ቡላ፣ ጨጨብሳ፣ ዶሮና ሽሮ ወጥ የሚወድ ያለ አይመስለኝም። ጊዜና ሁኔታው በፈቀደላት ወቅት ሁሉ ምርጫዎቿ እነዚህ ናቸው። ከአባትና እናቷ ጋር ስትሆን ምንም ሳትሸማቀቅ ጊዜውና ሁኔታው ያቀረበላትን መርጣ ትበላለች። ሰርግ፣ ልደት፣ ክርስትና፣ ምርቃትና የቤተ-ዘመድ ጥሪ ከሄደች ወላጆቿን አስፈቅዳ ከላይ ከተቀመጡት ምግቦች መርጣ ትመገባለች። ወላጆቿ ጥሬ ስጋ እየቆረጥን ስንበላ እሷም 18 አመት ሞልቷት ጥሬ- ስጋ መብላት የሚፈቀድላትን ቀን በአይነ-ልቦናዋ ትቆጥራለች። ከቤተሰቦቿ የተነገራትን ታስታውሳለች። በእሷ እድሜ ያሉ ልጆች“ጥሬ ስጋ መብላት አለብን” ብለው ሲያስቸግሩ ካየች ጣቶቿን እየቆጠረች የትኛው ምግብ በየትኛው እድሜ መበላት እንዳለበት ታስተምራለች።ለትምህርት ቤት መምህራኖቿና የክፍል ተማሪዎቿ ሳይቀር ከላይ የተጠቀሱትን ምግቦች እንደምትወድ አንዳችም ሳትፈራ ትገልጣለች።በቅርብ እንደምታስታውሰው ከሆነ በትምህርት ቤት ለታዘዘችው የባህላዊ ምግብ የፕሮጀክት የቤት-ስራ ጠጅ በብርሌ፣ ክትፎና ጨጨብሳ በጣባ የሚያሳይ ስእል ሰርታ አቅርባለች። በክፍል ጓደኞቿ ፊት ቆማ ከኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብና መጠጦች ውስጥ ተወዳጅ እንደሆኑና እንዴት እንደሚዘጋጁ አብራርታለች። የማንነቷ መግለጫ እንደሆነ በኩራት አሳይታለች። በዚህ ብቻ አታበቃም። ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ጓደኞቿ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ብቻ ስለሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት፣ የአየር ንብረት፣ የህዝቡ አኗኗርና የቤተሰብ ሁኔታ ትገልጣለች። ሌሎቹም አብረዋት ስለ ሀገራቸው ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ለማብራራት ይተጋሉ።
ወደ ሃይማኖት ጉዳዮች ስንሸጋገር ተመሳሳይ ሁኔታዎችን እንመለከታለን። ልጄ ወደ ቤተክርስቲያን ሲኬድ ምግብ መበላት ኣንደሌለበት ታውቃለች። የሚለበሰው ልብስ በተቻለ መጠን ረዘም ያለ ቀሚስና ነጠላ እንደሆነ በመገንዘብ አስቀድማ ማታ ታዘጋጃለች። የቅዳሴው ትርጉም ምን እንደሆነ ባታውቀውም በእርጋታና ማስተዋል ታዳምጣለች። ትጸልያለች። ትሰግዳለች። ትቆርባለች።የቤተክርስቲያን ጠበል ጻዲቅ በፍቅር ቀማምሳ ወደ ቤት ትመጣለች። ቁርባኗ እንዳይስተጓጎል ሙሉ ቀን ውሀ ሳይነካት ጨዋ ሆና ትውላለች። እዚህ ላይ የሃይማኖት ውርስ በተመለከተ ኑሮአቸውን ከኢትዮጵያ ውጪ ያደረጉ በጣም የሚያስቀኑ ቤተሰቦች መኖራቸውን መስክሮ ማለፍ ያስፈልጋል። በሰሜን አሜሪካ ተወልደው ቅዳሴ የሚቀድሱ፣ ዘመሪ የሆኑና ማህሌት የሚቆሙ ወጣቶች በርካታ ናቸው። ፈጣሪ ጽናቱን ይስጣቸው!!
እኔ እንዳየሁትና እንደሚሰማኝ ከሆነ ልጃችን እያዳበረች ባለችው “አገራዊና አለመቀፋዊ ማንነት” ሙሉ ሰው እያደረጋት ሄደ እንጂ ያጣችው ነገር የለም። ከቤተሰቦቿ እየወረሰች ያለችው “ኢትዮጵያዊ ማንነት” በአሜሪካ የማንነት ዘውድ ላይ የተሰካ እንቁ ነው።በሌላ አነጋገር ልጃችን እየገነባች ያለችው ማንነት በአንድ በኩል ኢትዮጵያዊ ኩራትና አትንኩኝ ባይነትንና ፍቅር የተጎናጸፈ፤ በሌላ በኩል በአለም አቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን የመሪነትና የሃያልነት ሚና እንዲኖራት የሚያስችል ነው። የዚህን ሁሉ መቀናጀት ሳይ የልጄ ማንነት እየተገነባ ያለው በዛሬና ነገ ላይ ነው።በአንድ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ሳይሆን ሁሉን አቀፍ እይታ ያለው ነው።…ዘወትር እየተገነባ ያለው የአእምሮ ስእሎቿ አዳዲስ እና ተለዋዋጭ ማንነቶችን ለመማር ብርቱ ፍላጎት ያለው ነው።…የአእምሮ ስእሎቿ ጽናትን፣ የሃላፊነት ስሜትን፣ ቀና እምነትን፣ አንድን ነገር በማከናወን የሚሰማ ክብርን፣ ከመቀበል ይልቅ ለመስጠት ያለ ፍቃደኝነትን፣በራስ የመተማመን ስሜት ማጎልበትን፣ አስተውሎትን…ወዘተ ድምር ውጤት የያዘ ነው። በሌላ አገላለጽ “ሲነርጂ” ነው:: The whole is greater than the sum of individual parts!…ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!!
***
ከልጆቻችን በኢትዮጵያ መሰረት ላይ ከተገነባው “አሜሪካዊነት”(አለም አቀፋዊ ማንነት) ትርክት ወጥተን ወደራሳችን ስንመጣ ብዙ መባል ያለባቸው ቁምነገሮች ይኖራሉ። በዚህ እድሜያችንና አስተዳደጋችን ኢትዮጵያዊ እና አለም አቀፋዊ ማንነትን አቀናጅተን መሄድ ቢሳነንም በጠንካራ ትስስር ላይ የተመሰረተ “ኢትዮጵያዊነት” መወራረስ ችለናል። ተወደደም ተጠላ እኛ ኢትዮጵያዊያን በጋብቻ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና ባህል የሚወራረሱ ማንነት አለን። እርግጥ ፕሮፌስር መስፍን ወ/ማሪያም “የክህደት ቁልቁለት” በሚለው መጽሃፋቸው ውስጥ ከላይ ከተጠቀሱት ጎላ ያሉ የማንነት መገለጫዎች በተጨማሪ ሌሎችም እንዳሉ ያስተምራሉ። በትክክልም ከአንጋፋው ምሁር ትንታኔ በመነሳት ማንነትን ስንመረምረው ዘርፈ ብዙና በአንድ ነገር ላይ ብቻ የተቋጠረ አይደለም። ከብዙና ከተወሳሰቡ ማንነቶች መሀከል የትኛው ገፍቶና ጎልቶ እንደሚወጣ የሚወስነው ጊዜና ሁኔታው ነው። በመደምደሚያው ግን “ኢትዮጵያዊነት” ነው።የዚህ አመት ኮከብ የነጠላ ዜማ ባለቤት አርቲስት ይሁኔ በላይ መቋጠሪያውን በዚህ መልኩ አንጎራጉሮታል፦
ማንነት የራስ ነው፣
ሐይማኖት የግል ነው፣
ሀገር የጋራ ነው፣
ቁልፍ ማሰሪያው
ኢትዮጵያዊነት ነው።
***
ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛው የትስስር መስተጋብር እርስ በራስ በመጋባትና ማንነትን በመወራረስ የተፈጠረ ነው። እርግጥም ወደ ራሳችን መጥተን ወደ ቤተሰብና ቤተ-ዘመድ ስንወስደው እያንዳንዳችን ለመቀበል አንቸገርም። ወላጆቻችን ከተለያየ ብሄረሰብ ተወልደው በፍቅር ተጋብተው፣ ስጋና ደማቸውን አዋህደው እኛን መፍጠራቸውን በግለሰብ ደረጃ ለመቀበል ብዙ ችግር የለብንም። ከዚህ በተጨማሪም ከቤተሰብ አልፈን ቤተ-ዘመዶቻችንም ዉህድ (Compound) መሆናቸውን ለመመስከር አርቆ ማየት አይሳነንም። በተቃራኒው ከቤተሰባችንና ቤተ-ዘመዳችን ተሻግረን ስለ ሌላው ሰው ስንናገር እንዲሁም ወደ ጎሳ፣ ብሄረሰብ፣ ብሄር፣ አገር ወዘተ ስንመጣ ግን ልዩነታችን ለማጉላት ደረታችንን ነፍተን ለመናገር አንቦዝንም።የቤተሰብና ቤተ-ዘመዳችንን ህብረትና አንድነት ለመጠበቅና ከዚህ ውህደት የሚገኘውን ጥቅም ለማጉላት የምንሯሯጠውን በተቃራኒ በብሄርና አገር መካከል የመጎዳዳትና መነጣጠል ታሪክ አጉልቶ ለማሳየት እንተጋለን። የማፈራረስና የመለያየት ሙሾ በማውረድ የዝቅተኝነት ስሜታችንን በአደባባይ እንገልጣለን። አስረግጦ ለመናገር በማንነት ላይ በሚደርስ ጥቃት መሰባሰብ ሌላ! ማፈራረስ ሌላ!…ውግዝ– ከመሊበን!!
እውነታው ግን ሀገር የመሩ ነገስታት ሳይቀሩ “ልጅህን ለልጄ” በመባባል አንድነታቸውን ጎሳ ሳይመርጡ ያጠነክሩ ነበር። ንጉስ ዘረ ያእቆብ፣ አልጋ ወራሽ ልጃቸው በእደማሪያምና ልጅ ልጃቸው ልብነ-ድንግል ያገቡት የሀድያ ብሄረሰብ ተወላጆችን እንደሆነ አንብቤያለሁ። የንጉስ ሲሲኒዮስ ሚስት ኦሮሞ እንደሆነች የታሪክ ድርሳናት ይገልጣሉ። በአጼ ቴዎድሮስና ተዋበች መካከል የነበረው ትስስር ተመሳሳይ እንደሆነ ሲነገር ሰምቻለሁ። በልጅ እያሱና አባ ጅፋር፤ ራስ መንገሻ ስዩምና በአጼ ሃይለስላሴ መካከልም የጋብቻ ትስስር መፈጠሩ በየጊዜው የሚወሳ ነው። ይህን ታሪካዊ ሐቅ መቀበል ለማንነታችን መወራረስና ለኢትዮጵያዊነት አንድነታችን መሰረት ይሆናል። የራሴ ግል ንብረት የሆነውን ዛሬና ነገን ትቼ በትላንት ላይ ሙጭጭ ያልኩ ባልሆንም በጎ በጎውን ለመውሰድና መጥፎውን እንዳይደገም ለመኮነን ትላንትናን ማንሳት የሚከፋ አይመስለኝም።
የቅርብ ጊዜውም ቢሆን አንጋፋው ኢትዮጵያዊ የስነ-ጽሁፍ ሰው ሰለሞን ደሬሳ “በሴት አያቶቻችን ደጃፍ እነማን እንዳለፉ ማን ያውቃል?” እንዳሉት ነው። አሁንም ከተለያዩ መጣጥፎች እንዳነበብኩት ከሆነ የኦነጉ አመራር አቢዩ ገለታ እናታቸው አማራ ናቸው። የአቶ አቢዩ ሚስትም አማራ ናቸው። የንጉስ ሃይለስላሴ፣ መንግስቱ ሃይለማሪያም፣ ጸጋዬ ገ/መድህን፣ ተስፋዬ ዲንቃ እናቶች በሙሉ አማራ ናቸው።በተመሳሳይ ሁኔታ የኢንጂነር ሃይሉ ሻወል እናት ኦሮሞ ናቸው። እንደዚህ እያሉ ብዙ መዘርዘር ይቻላል። በዚህ ደረጃ መውረድ የሚቀፍ ቢሆንም። ሆኖም ቅሉ በማንነት ሽፋን የሚያገኙት ጥቅም ህሊናቸውን ጋርዶት የእናታቸውንም ሆነ የአባቶቻቸውን ወገኖች የማንነት መግለጫና የጋራ ማህበራዊ እሴቶችን እስከመካድ የደረሱትን በእነሱ በወረዱበት ደረጃ ወርዶ በሃሳብ መነጋገሩ አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ወደራሳቸው ግለ-ህሊና ተመልሰው ዞር ብለው እንዲመለከቱ በማሰብ ነው። በአካልም ሆነ በአእምሮ ከዙሪያቸው ሳይወጡ ህይወታቸውን የሚጨርሱ ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ነው። እናቶቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲያስታውሱ ነው። መነታረክ ባይሆንብኝ ይሄን ሳስበው በጣም ያመኛል።
***
ከጋብቻ ቀጥሎ የሃይማኖት መወራረስ ለኢትዮጵያ ህዝብ የማንነት መወራረስ አስተዋጽኦ እንዳለው መካድ የሚቻል አይደለም።የሚገርመው ነገር ብሄርም ሆነ አገር መፈራረስ አለባት በማለት ስንፍናቸውን የገለጡ ግለሰቦች እዛው ሳለ የኢትዮጵያ ህዝብን የሃይማኖት መስተጋብርና መወራረስ ለማጥፋት እየፈለጉ መሆኑን ነው:: በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በማህበረሰብ ደረጃ የሃይማኖት መስተጋብርና ሽግግር የተደረገ መሆኑን ለማየት የታሪክ ተማሪ መሆን አይጠይቅም። ዛሬም ቢሆን በጋብቻና ሌሎች ምክንያቶች ከአንደኛው ሃይማኖት ወደ ሌላኛው የሃይማኖት የማንነት ለውጥ የሚሸጋገሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በተጨማሪም በተለይ በሶስቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች አማኞች ለስብከትም ሆነ ትምህርት ለመቅሰም በየቦታው ሄደው ለመኖራቸውና የገነቧቸው የሃይማኖት ተቋማት የፈጠሩት ውህደት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሃይማኖት ተቋማት፣ አባላትና አባቶች “ኢትዮጵያዊነትን” ለመገንባት፤ አደጋ ሲመጣም ለመከላከልና መቀልበስ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ጥላቻ፣ በቀለኝነት፣ በዘር መከፋፈልና መገዳደል “ኢትዮጵያዊ” ማንነት እንዳልሆነ ሳይታክቱ አስተምረዋል። ልቡ እየደማ ያለውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ለማከም ጥረት አድርገዋል። የኢትዮጵያዊ ሞራልና የመንፈስ እሴቶች እንዲያብቡ አስተምረዋል። የኢትዮጵያ ህዝብና ኢትዮጵያዊነት ጥቃት በሚደርስበት ሰአት አገራዊ ጥሪ በማድረግ ያንቀላፋውን ኢትዮጵያዊነት ለማትባት፣ የጨለመ ተስፋውን ብርሃን ለመስጠትና መውጪያ መንገዱን ለማሳየት ጥረት አድርገዋል። በዚህ ዘመንም ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ይሄን እያደረሁ ነው። ለዚህ አገላለጥ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት ቄስ ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና ናቸው።
ዶ/ር ቄስ ቶሎሳ ጉዲና በአንድ ስብከታቸው እንዲህ ይላሉ፣
“በዚህ በ21ኛው ክፍለ–ዘመን አለም ወደ ግሎባላይዜሽን በሄደ ሰአት እኛ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ሃድያ እንላለን። የአሜሪካን ተማሪዎችበዩንቨርስቲ ደረጃ የቻይናን ቋንቋ እንደሚያጠኑ ልነግራችሁ አልችልም። ምክንያቱም ከእንግሊዘኛ አልፎ የቻይናን ኢኮኖሚ፣ የቻይናን አመለካከትየሚያጠኑ መኖር አለባቸው። እኛ ግን አሁንም አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ከንባራ፣ ሃድያ፣ ሲዳማ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ይሄን ያን እያልን ከድንጋይ ዘመንትዝታ አልወጣንም። ትዝታችን ይሄ ነው። የምናውቀው ይሄን ያህል ነው። የምንተገብረው ይሄን ያህል ነው። ለልጆቻችንና ለትውልዳችንየምናተርፈው ያን ያህል ነው። ከዚህ መውጣት አልቻልንም። አንድ ነገር ልንገራችሁ። እግዜብሄር የሰየመን፣ መጽሃፍ ቅዱስ የሚጠራን፤ የአለምህዝብ የሚያውቀን ኢትዮጵያ ብሎ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ስም እኔ አላውቅም። እነዚህ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሃድያ፣ ከንባታ በማለት የሚሰብኩጣኦቶች በመጽሃፍ ቅዱስ አንዲት ቃል አልተጻፈላቸውም። እግዚአብሔር ምድሪቷን የሚያውቀው እንደ ኢትዮጵያ ነው። እግዚአብሔር ምድሪቷን “ኢትዮጵያ” ብሎ ነው የሚጠራት። እኛ ከዚህ ሌላ የምናውቀው የለም። የምንሰራውን፣ የምናስበውም፣ የምናገለግለውም፣ የምንኖረውም ለዚህችእግዚአብሔር ኢትዮጵያ ብሎ ለሚጠራት ምድር ነው። አለቀ!!”
በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ተምሳሌታዊ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ አውቃለሁ። የቅርብ ጊዜውን ብንወስድ እንኳን ሙስሊሙ ጋዜጠኛ አክቲቪስት ሳዲቅ አህመድን እናገኛለን። ይህም አክቲቪስት ሳዲቅ አህመድ ባለፈው ጊዜ በለንደን ተገኝቶ ያሰማው ንግግር ነው። መቼስ “የአላህ ሰላምና እዝነቱ በነቢያት መደምደሚያ ነብዩ መሃመድ (ሰ.አ.ወ.) አይለየው!” ከማለት ውጪ። ሳዲቅ አህመድ ስለ ኢትዮጵያ አገራችን ልዩ ባህሪያት ለመግለጥ የመጨረሻውን እንቁ የሆኑ ቃላት አፍስሶ ሁላችንንም ከተቀመጥንበት ቁጭ ብድግ አስብሎናል። ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያን ካጋጠማት አደጋ ለመታደግ በአንድነት መንፈስ መነሳት እንዳለብን አስተምሯል።ኢትዮጵያ በአንድነት ጸንታ እንድትኖር ጀግኖች አያቶቻችን የከፈሉት መስዋእትነት በወርቅ ቀለም ሊጻፍና በልጅ ልጆቻችን ሊታወስ እንደሚገባ አመልክቷል። ሳዲቅ አዳራሽ በሞላ ህዝብ ፊት ቆሞ እንደተናገረው ኢትዮጵያ የሙስሊሙ፣ የክርስቲያኑ፣ የዋቄ ፈታው፣ የሃይማኖት አልባው…ወዘተ የጋራ አገር መሆንዋንና “ኢትዮጵያዊነት!” በሚባል ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት የተሳሰርን እንደሆነ አስረድቷል።ሙስሊሙ አክቲቪስት ሳዲቅ አህመድ ነብዩ መሃመድ(ሰ.አ.ወ.) ተከታዮቻቸው ለማጥፋት ጠላቶቻቸው ሲሯሯጡ “ወደ ኢትዮጵያሂዱ። መልካም አቀባበል ይደረግላችኋል። በኢትዮጵያ መጠጊያና መጠለያ የሚሰጣችሁ ንጉስ አለ።ኢትዮጵያን አትንኩ” ብለው ትእዛዝ መስጠታቸውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱን ዋቢ በማድረግ ገልጧል። አሁንም ለወጣቱ አክቲቪስት “የአላህ ሰላምና እዝነቱ” አይለየው!!
***
ይሄ ብቻ አይደለም።ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ጠንክረን ኣንስራ የሚሉ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ውስጥ የቋንቋ መወራረስና ማደግ የተፈጠረ መሆኑን ማየት አይፈልጉም። በአማርኛና በትግርኛ መካከል ያለው መወራረስ በግልጽ የሚታይ ነው። በኦሮምኛ ጉራጊኛ፣ ከምባትኛና ሲዳምኛ መካከል ያለው መወራረስ ከቋንቋ ተሻግሮ በሙዚቃና ጭፈራ የተደገፈ ነው። ለማስታወስ ያህል “የመለስ ትሩፋት” በሚለው መጽሃፍ እንደተገለጸው የአባቴ ወገኖች በኦሮምኛ እየዘፈኑ በጉራጊኛ የሚጨፍሩበት ሁኔታ ተመልክቻለሁ። መደጋገም አይሁንብኝና ዘፈኑና ጭፈራው የመጀመሪያው ባለቤት ማነው የሚል ክርክር የእንቁላልና የዶሮው አይነት ማን ይቀድማል ከሚለው ጋር ይዛመዳል። ትልቁ ቁምነገር አብሮ በመኖር ምክንያት በመስጠትና በመቀበል የተፈጠረው መስተጋብር ነው። በአካልም ሆነ አእምሮ ከአካባቢያዊነት ልቆ መሄድ ነው። ሙሉ ሰው የመሆን ጽኑ ፍላጎት ነው።
በአጠቃላይ መልኩ በዚች አነስተኛ መጣጥፍ ለመግለጥ የምሞክረው የኢትዮጵያን ህዝብ ሁለገብ ትስስር በአሸዋ ላይ እንደተሰራው ቤት አቃሎ ማየትና ለማፈራረስ መዛት ትልቅ ስህተት መሆኑን ነው። በአጉል ሆይሆይታና ጭብጨባ እየተነዱ በኢትዮጵያውያን መካከል ጥላቻ መፍጠር የሚፈልጉ ግለሰቦች የለውጡን ድልድይ ከመሰባበር ያለፈ ፋይዳ የላቸውም። የህዝቡን የስርአት ለውጥ ሞራል ከመንካትና የኣገዛዙን ተጨማሪ እድሜ ከመሸመት የዘለለ ወቅታዊ ትግሉ ወደፊት እንዲራመድ ሊጫወቱት የሚችሉትን አዎንታዊ ሚና ወደኋላ በመውደቃቸው እንቅፋት መሆናቸው ነው። ይሄ እኩይ ተግባር ደግሞ ለባለቤቶቹ በግልጽ ተነግሮ በህዝብ ሊተችና ነውሩ ሊገለጥ ይገባል። ትልቁ ችግር በብሄር ፖለቲካ ውስጥ ባህል ተደርጎ የተወሰደው ከጥፋተኛው ይልቅ ስለ ጥፋተኛው ጥፋት የሚናገረው ጥፋተኛ ሆኖ የሚቆጠር መሆኑ ነው። ከነውረኛው ሰው ይልቅ ነውሩን የገለጠው ሰው ከፍ ዝቅ መደረጉ ነው። ጥርጣሬና ጥላቻ እያረገቡ ወደ ማያሻግረው ድልድይ የሚመሩት እየተወደሱ በተቃራኒ የተሰለፈው እንደ ከሃዲና የበላበትን ወጪት ሰባሪ መቆጠሩ ነው። ለማንኛውም የለውጥ ንፋስ በነፈሰ ቁጥር የለውጡን ነፋስ አቅጣጫ አሳቻ መንገድ ለማስያዝ የሚጥሩ መኖራቸው ነባራዊ ሃቅ ነው። ከለውጥ አደናቃፊዎች እግዜር ይጠብቀን!!
(የዚህን መጣጥፍ ማገባደጃ ስደርስ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ትራምፕ በዓለ-ሲመት እየተካሄደ ነበር። ተሾሚው ፕሬዚደንት ለአሜሪካና አለም ህዝብ ንግግር እያደረጉ ነው። መጣጥፌን አቁሜ ሰዓቴን ስመለከት 12:00PM ይላል። ወደ ቴለቪዥኑ መስኮት ቀና ስል አዲሱ ፕሬዚደንት “America First! America First!” ሲል ሰማሁት። በጣም ደነገጥኩኝ። የቴለቪዥን መስኮቱ በወፍ በረር ደጋግሞ የታደሙትን አሜሪካውያንን እንዳሳየን ከሆነ አፍሪካን አሜሪካን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። በመድረኩ ላይ ከኦባማ፣ ባለቤቱ፣ ቄሱና ህግ አስከባሪዎች በስተቀር ማየት አልቻልኩም። ጓደኞቼንም ጠይቄ ተመሳሳይ ስሜት እንደተሰማቸው ገለጡልኝ። “አሜሪካን ፈርስት” ከሚለው የሲልቨር ቨርስትስ የፋሺዝም መርሆ የተቀዳ የሚመስለው የትራምፕ የፖለቲካ አቅጣጫ ከመነሻው አስደነገጠኝ። የሲልቨር ቨርትስ “አሜሪካ ፈርስት” ፍልስፍና፣ እጅግ በጣም ዘረኛ፣ አግላይና የዜጎችን አብዛህነትና እኩልነት የማይቀበል ነበር። ከቨርስት መማር ያልፈለገው አዲሱ ፕሬዚደንት አለምን የመምራት፣ የመደገፍና፣ የማስተባበር ራዕይ ይናገራል ተብሎ ሲጠበቅ ጆሮውን በጥጥ ደፍኖ፣ “አሜሪካን ፈርስት” የሚል ዲስኩር አሰማ::
ከጅምሩ ሟርትና አጉል ተስፋ መቁረጥ አይሁንብኝ እንጂ ምን ያህል አሜሪካዊ ወደፊት ተስፋና መልካም ምኞት ልቡን ከፍቶ “የአሜሪካ ፈርስትን!” ፍልስፍና እንደተቀበለ ማወቅ ይሳነኛል። ለአዲሱ የትራምፕ መንግስት ደግሞ ዋናው ጉዳይ የህዝቡ አቀባበል ሊሆን ይገባል። ዋናው ጉዳይ “አፍሪካ አሜሪካው”፣ “ስፓኒሹ”፣ “ቻይና አሜሪካው”፣ “አረብ አሜሪካው” ፣ “ሙስሊም አሜሪካው”፣ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ወረቀት የሌለው ኢምግራንቱ…ወዘተ የወደፊት ተስፋው ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ነው። አጀማመሩ እንዲያምር ጥንቃቄው ይኸ መሆን ነበረበት። እንጃ እንጂ!!)