ሲሳይ አጌና ያቀናበረውን የወያኔ ፓራዶክስ እያዳመጥኩ ነበር። በቡድን አባት ተከፋፍሎ እንደ ልጅነት ኳስ ጨዋታ በዚህ የመከራ ቀንበር በከበደበት ህዝብ ላይ ጢባጢቦ ስለሚጫወቱት የወያኔ ዘለፈቶዎች እና በህዝቡ ብሶት ላይ የእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ስለሚሆኑበት የዛሚ ሬዲዮና ኢቢስ የእርስ በርስ ፍትጊያ ነበር። ጌታቸው አሰፋ በስርአቱ ሞልቶ የፈሰሰው ዘረፋ እራሱን ወያኔን ሳይቀር እንደጋንሪን እየበላው እንደሆነ ነገር ግን የህግ አስፈጻሚ አካል የመጥፋቱ ነገር እንቅልፍ እንደነሳው በምሬት መናገሩን በድምጽ ጭምር የተቀዳ ዘገባ ኢሳት አሰምቶናል።አገሪቱን ከመጋረጃ ጀርባ ተደብቀው የሚመጠምጡት የጨለማ አበጋዞች ደግሞ ሃይለመሪያም ደሳለኝ በተባለና መቀሌ በሚገኘው መስፍን እንጂነሪንግ ውስጥ ተቀጥቅጦ በተሰራው ቱቦ በኩል ወደ ህዝቡ የደፉት አተላ “ለዚህ መረጃ የለንም” የሚል ነው። እርሱ ይህን የሚለው የውጭ አገር ባንኮችን ሳይቀር ያጨናነቀው የዶላር ክምችታቸው ገብርኤል ያየው ሚስጥር በሆነበትና ድፍን የአዲስ አበባ ጉዳናዎች በወያኔ ጀነራሎች ስም በተገነቡ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ጭምር በተወረረ ከተማ ውስጥ ተቀምጦ ነው።
ይኽ እንግዲህ እንደ ወያኔ ፖሊሲ የግምገማ ውጤት መሆኑ ነው። የግምገማ እውነታ ግን የህግ አውጭውን, የህግ አስፈጻሚውን እና የህግ ተርጓሚውን አካላት እንዲሁም የሲቪል ሰርቪሱን ተቋማት እንዳይላወሱ በማድረግ ከህዝቡም በላይ በሎሌነት የቀጠሯቸውን የራሳቸውን አስክከሮች ጭምር አንገት አስደፍተው በለየለት ባርነት ውስጥ ጠፍንገው የሚያቆዩበት.. ከደደቢት ጀምሮ እስከ በአዲስ አበባው ደንቦስቃ የዘለቀ ፍጹም አረመኔያዊ የሆነውን የግምገማ ልማድ ቢሆንም ቅሉ የውስጣቸው የእፍረት ጽንሱ የጨነገፈባቸው እንደ ልደቱ አያሌው በመሳሰሉ ግዜው ያለፈባቸው ማደንዘዣ መርፌዎች ሳይቀር ሲወደስና ሲደነቅ ሰምተናል። እኔ ግን ስለዚህ ግምገማ የማውቀውን አንድ በጣም አስቂኝ ግን አሳፋሪ ገጠመኝ በዚህ አጋጣሚ ላንሳና ልጨርስ። ነገሩ እንዲህ ነው፣
አንድ በጥቁር አንበሳ በማእረግ የተመረቀ የኢንተርናል ሜዲሲን ዶክተር አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ እድል እያለው ነገር ግን ለተወሰነ ግዜ ከፍተኛ የሃኪም እጥረት ባለበት ሪሞት ኤሪያ ላይ መስራት አለብኝ የሚል የሞራል አቁዋም ይይዛል። በዚህ ደግሞ ጋምቤላና ሰቆጣ በከፍተኛ ደረጃ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ሰራተኛ የሚለቅባቸው ከተሞች ናቸው። እርሱ ሰቆጣን መረጠ። በሃኪም ቤቱ ውስጥ ዋነኛ የሚባል ሃኪም ቢሆንም ቅሉ የነርሶቹንም የድሬሰሮቹንም ስራ ደርቦ ይሰራል። ከብዙ ኪሎ ሜትር እርቀት እንደ አስከሬን በሰው ትከሻ ተጭነው የሚመጡ ነፈሰ ጡሮችን ሳይቀር ሲያዋልድ ይውላል። ከተከራየው ቤት መመላለስ ስላልቻለ ሃኪም ቤቱ ውስጥ አልጋ ዘርግቶ ሰባት ቀንና ሌሊት ከእንቅልፍ ሳይቀር እየተቀሰቀሰ ይሰራል።
የሃኪምቤቱ አስተዳደር ሰራተኛ ተብለው የተሾሙት ደግሞ በወያኔ የትግል ዘመን ቁስለኛ ላይ ፕላስተር ሲለጥፉ የነበሩ ከሶስተኛ ክፍል በላይ ያልተማሩ ታጋዮች ነበሩ። አለቆቹ መሆናቸው ነው። ማለቂያ የሌለው የስብሰባ አጀንዳ አላቸው። ዘጠና ከመቶ በላይ የሚሆነው አጀንዳቸው ደግሞ ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው። ይኽን ሃኪም ደግሞ ሁልግዜ በስብሰባቸው ላይ እንዲገኝ መመሪያ ቢሰጠውም እርሱ ግን ሃኪም መሆኑን፣ እንዲህ አይነት ነገር እንደ ማይመለከተው በተደጋጋሚ በመናገሩ ግጭት ውስጥ ገብቶዋል። በመጨረሻም ተንቀናል የሚል ስሜት ያደረባቸው እኒህ ሚኒሻዎች በዚሁ ሃኪም ጉዳይ ግምገማ ተቀመጡ። ውሳኔያቸውም እንዲህ የሚል ነበር። “ተከሳሽ በተደጋጋሚ የሰጠነውን መመሪያ ከቁብ ያልቆጠረ፣ ለታገልንለት አለማ ክብር የማይሰጥና ከትምክህተኝነት አስተሳሰብ ገና ያልተላቀቀ ሆኖ ስላገኘነው ካዛሬ ጀምሮ ዶክተር መባሉ ቀርቶ ነርስ እንዲሆን በሙሉ ድምጽ ወስነናል።
ከስራ ሳይሰናበት የቀረውም ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን እናስታውቃለን” የሚል ነበር። በዚህም የሆስፒታሉ ታጋዮች ተሰብስበው አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በሙሉ ሜዲካል ዶክተርነት የሾመውን ሰው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቀመር ገምግመው ነርስ ሲያደረጉት ሃኪሙም ቀስ ብሎ ድምጹን አጥፍቶና አለሳልሶ በሌሊት ጠፍቶ ወደ ባህርዳር አመለጠና ለአለቆቻቸው ዝርዝሩን አስረድቶ ላይመለስ አዲስ አበባ ላይ ቀረ። የወያኔ ግምገማ ለዘገምተኛው ሳሞራ “ፕሮፌሰርነት ማእረግ” ገዝቶ የሚሰጠውን ያህል መደበኛውን የህክምና ዶከተርም እንዲህ አውርዶ “ነርስ” ማድረግ እንደማይሳነው ያሳየበት ኩነት ነበር።