አንዳንድ ጨዋታ የዕውነት ያህል አሳማኝ ነው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ ከፍተኛጭቅጭቅይነሳል፡፡በኃይልጭቅጭቁንያካረሩትአራትአገሮችናቸው፡-
1ኛ/እንግሊዝ
2ኛ/ፈረንሣይ
3ኛ/እሥራኤል
4ኛ/ሩማኒያ
እንዲያ በኃይል ያጨቃጨቃቸው አጀንዳ፤ “አዳምና ሔዋን የየት አገር ሰዎች ናቸው?” የሚለው ጉዳይ ነው፡፡
በመጀመሪያ ሙግቷን ያቀረበችው እንግሊዝ ናት፡፡ እንዲህ ነው ያለችው፤ በተወካይዋ አማካኝነት፤ “አዳምና ሔዋን ያለጥርጥር እንግሊዞች ናቸው፡፡ ለምን ቢባል፤ እንግሊዛዊ ሰው ብቻ ነው አንዲት ሴት ትፈጠር ዘንድ በጨዋነት የገዛ ጎድኑን አሳልፎ የሚሰጥ” ይሄኔ የፈረንሳዩ ተወካይ ከመቀመጫው ተፈናጥሮ ተነሳና፤ “በጭራሽ እንደዛ አይሆንም! እስቲ የአዳምን ቁመናና ቁንጅና ተመልከቱ፡፡ ራቁቱን ሆኖ እንኳን እንዴት እንደሚያምር ልብ – በሉ፡፡ ይሄ ሊኖረው የሚችለው ፈረንሳዊ ብቻ ነው” አለ፡፡ ቀጥሎ የቀረበው ተሟጋች እሥራኤላዊው ተወካይ ነበር፡፡ እንዲህ አለ፡-“በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በትክክል እንደተቀመጠው፤ፍጥረት የተፈጠረው በቅድስቲቱ ምድር ነው፡፡ ስለዚህም አዳምና ሔዋን የተመረጡት ህዝቦች ናቸው! ስለሆነም አይሁዳውያን ናቸው!”ይሄኔ የሩማኒያው ተወካይ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ብድግ አለና፤ “የለም! በእኛ በሩማንያን ዕምነት አዳምና ሔዋን ሊሆኑ የሚችሉት ሩሲያዊ ነው!”“እንዴት? አስረዳና?” ብለው ሁሉም ጮሁበት፡፡ የሩማንያው ተወካይም፤ “ምክንያቴን ላቅርብላችሁ፡፡ በዓለም ላይ ሩሲያዊ ብቻ ነው በደንብ ሳይበላና በደምብ ሳይለብስ ገነት ውስጥ ነው ያለሁት የሚል!” ሲል ገለፀ፡፡ ተጨበጨበለት!!
* * *
አገርን ከሌላ አገር ማስበለጥ፣ የራስን ፓርቲ ከሌላው ፓርቲ የበላይ ነው ለማለት መሞከርና እኔ እሻል እኔ እሻል መባባል፣ ጥንትም ነበረ፣ አሁንም ያለ እና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ያም ሆኖ ያላንዳች ምክናዊነት፣ አንዱ ሌላውን መብለጥ አይችልም፡፡ አመክንዮ ይፈልጋል፡፡ በሀገር ደረጃ ሲታይ ከፖለቲካ ጥንካሬ እስከ ኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ ከዚያም የወታደራዊ አቅም፣ እንዲሁም ማህበራዊ መሰረትን ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ለማሟላት ብርቱ ድካም፣ የረዥም ጊዜ ባለታሪክ መሆንንም ይጠይቃል፡፡ በሀገራችን ያየናቸው ለውጦች ከወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት፣ እስከ ተማሪ እንቅስቃሴ፣ ውለው አድረውም የተደራጁ ወታደራዊ ኃይሎች አመራር ሥር የወደቁ ነበሩ፡፡
በዚሁ ዙሪያ የተደራጁ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ተወልደዋል፡፡ ወደ ትጥቅ ትግልም ያደጉ ታይተዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን እርስ በርስ ከመቆራቆስና ከመጠላለፍ፣ አልፎ ተርፎም ከመጨራረስ በስተቀር ሁነኛ የፖለቲካ መድረክ ፈጥረው፣ ሁነኛ ክርክርና ሀቀኛ ሙግት ተሟግተው፣ እዚህ ስምምነት ላይ ደረሱ የሚባልላቸውና የሚያኮሩ አልተገኙም፡፡ መንግሥትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣አይጥና ድመት ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፡፡ ክፍተቱ ሰፊ ነው፡፡ እስከ ዛሬ ስናይ የኖርነው፤ የቂም በቀል፣ የደባና የሤራ፣ ከእኔ በላይ ላሣር እና የደም መፈላለግ ፍጥጫ በመሆኑ የሰላማዊ ትግል ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ፣በሰለጠነ መልክ ተነጋግሮ ዳር መድረስ ያልተሞከረ ነው፡፡ አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤ “የኢትዮጵያ ፖለቲከኛ ሁሉ በየኪሱ ትናንሽ ዘውድ ይዞ ነው የሚዞረው!” ከተማሪ እንቅስቃሴ ጊዜ ጀምሮ እንደመሪ መፈክር ሲያገለግል የኖረው፤ ‹‹unity is power›› ‹‹አንድነት ኃይል ነው›› የሚል ነበር፡፡ “United, we standSeparated, we fall!›› የሚልም ነበር፡፡ (‹‹ከተባበርን እንቆማለን፤ከተነጣጠልን እንወድቃለን!›› እንደ ማለት ነው፡፡) በአጭሩና በተለመደው የአማርኛ አባባል፤‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር›› ማለት ነው፡፡ ይሄ ዛሬም ይሠራል፤በአግባቡ የሚጠቀምበት ከተገኘ፡፡ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ በሆይ ሆይታና በግርግር፤ በችኮላ የሚፈጠር አካሄድ መጨረሻው አያምርም፡፡
የፖለቲካ ድርድር የአንድ ወገን ብልጠት አይደለም፡፡ የሀገር ጉዳይ ነውና ሁሉም ወገን በልባዊነት ሽንጡን ጠበቅ ሊያደርግበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ በተንኮል ሽረባም የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ ‹‹ነገር በሆድ ማመቅ ለትውልድ መርዝ መጥመቅ›› የሚለን ለዚህ ነው!
ከሁሉም በላይ መቻቻል የሚፈተንበት፣ሆደ-ሰፊውና አስተዋዩ የሚለይበት ነው። የፖለቲካ ብልህነት ጠርቶ የሚወጣበት ነው፡፡ ዲሞክራሲ የተሸናፊዎች መብት መሆኑን በእርግጥ የምናጣራበት ሂደትም ነው፡፡ ገዢው ዘራፍ ሳይል፣ተገዢው በቂምና በቅሬታ ሳይወጣ ማየት እንሻለን፡፡ ሰላማዊ ትግል የሰላም አገር መለያ ነውና፣ከትንቅንቁ ባሻገር ግልፅ ውይይት እንጠብቃለን፡፡ ስለታሰሩ የተቃዋሚ አባላት ምን ሀሳብ እንደሚነሳ ለመስማት እንጓጓለን፡፡ ስለምርጫ ህግጋት ለውጥ ምን እንደሚወሳ ለማዳመጥ እንተጋለን፡፡
በመጨረሻ ግን አንደበተ ርቱዕነት ብቻውን የአሸናፊነት መገለጫ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ቀናነት፣ ቁጡነትን ማስወገድ፣ የቤት ሥራን በሚገባ ሰርቶ መምጣት፣ ወቅታዊ (timely) የሆነውን ጉዳይ፤ ጊዜ ከማይሽረው (timeless) ጉዳይ ለይቶ ማየት ወሳኝነት አላቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፤ ‹‹በርበሬ አይሆንም ዕጣንንግግር አይሆንም ሥልጣን››የሚለውን አባባል አለመዘንጋት ነው! ይሄን ልብ እንዲሉም አደራ ጭምር እናስታውሳለን፡፡
Administrator