Bilisummaa adda-ዋ!
***
“የቆምኩበት መሬት፥
ዛሬ በነጻነት”
አያቶቼ ባይገሉለት፣
አያቶቼ ባይሞቱለት፣
ከኔ በላይ ፈሪ ጥቁር፥
ነበር እሚቆምበት። :-
ወርሐ የካቲት በጠባ ቁጥር ልደቴን በተድላ እንዳላከብር የዳግማዊ ምኒልክ አድናቂዎች እና ነቃፊዎች የፌስቡክን ሠላም በስድብ ተኩስ ልውውጥ ያደፈርሱታል። የአድዋ ድል ‘የጥቁር ሕዝቦች የሚያኮራ ታሪክ’ መሆኑ ይቀርና ለምኒልክ ወዳጆች የእርሳቸውን ሥም ከፍ ከፍ ማድረጊያ መልካም አጋጣሚ፣ ለነቃፊዎቻቸው ደግሞ ሥማቸውን ዝቅ ዝቅ ማድረጊያ አጋጣሚ ይሆናል። ፈረንጆቹ “there is no such thing as bad publicity” እንደሚሉት ሆነና፣ በደግም ይሁን በክፉ ሥሙን ሳታነሱት ማለፍ የማትችሉት ሰው ካለ እሱ ‘ታላቅ ሰው’ ነው ማለት ነው።
ዳግማዊ ምኒልክ በታሪክ አጋጣሚ የአድዋ ድል የተበሰረበትን ጦርነት በንጉሠ ነገሥትነት መርተዋል። ይሁን እንጂ ንጉሠ ነገሥቱ ብቻቸውን ጦርነት ገጥመው አላሸነፉም። ከጦር መሪነት ባሻገር መስኩ ላይ በግል ወርደው ከጣልያን ጋር መሳ ለመሳ መጋጠማቸውንም እርግጠኛ አይደለሁም። ያኔ ብሔራዊ (አገር ዐቀፍ ማለቴ ነው) ጦር ሠራዊት ስላልነበረ ሁሉም አዝማች የየራሱን ጦር ይዞ ነበር የሚዘምተው። ከምኒልክ ጋር ከመሐል አገር የዘመቱት 2/3ኛውን የአድዋ ዘማች ሠራዊት እንደሚሸፍን ተጠቅሷል። የምኒልክ አዝማቾች ታዲያ በአብዛኛው ኦሮሞዎችን ከኋላቸው ያስከተሉ ኦሮሞ አዝማቾች ነበሩ፤ እንደአብነትም ሀብቴ ዲነግዴን እና ባልቻ ሳፎን መጥቀስ ይቻላል። ኦሮሞዎች ደግሞ ኃይለኛ ተዋጊ መሆናቸውን አባ ባሕርይ እና አለቃ አፅሜን ጨምሮ ስለኦሮሞ የጻፉ ሁሉ ጠቅሰውታል። ድሉ የሌላው ኢትዮጵያዊ የመሆኑን ያክል የኦሮሞዎችም መሆኑን ለማስታወስ ነው እንግዲህ ይህን ማለቴ። ጥቂት የኦሮሞ አክቲቪስቶች እንደሚሉት በምኒልክ ጥላቻ ብቻ የአድዋን ባለታሪክ (ኦሮሞን) ከአድዋ መነጠል አይቻልም።
አድዋ – ‘የጨቋኝ ምርጫ’?
ሌላው ክርክር አድዋ “የጨቋኝ ምርጫ እንጂ የነጻነት ድል አይደለም” የሚለው ነው። ይህንን መከራከሪያ ከታምራት ነገራ ጦማር የዛሬ 6 ዓመት ስሰማው ያናደደኝን ያክል ሊያናድደኝ ቀርቶ ዛሬ ‘ልክ ነው’ የምልበት ቀን ላይ ደርሻለሁ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የዛሬ 121 ዓመት የደረሰበት ዕድገተ ማኅበረሰብ (social evolution) ደረጃ ገዢነትን ከንጉሥ ለተወለደ ብቻ ትቶ የኔ ለሚላቸው ሰዎች እና ወጎች ወግኖ ከመሞት ያለፈ ርዕዮተ ዓለም አልነበረውም። የጦርነት አዋጅ መቀስቀሺያ ቃሎችም “ሃይማኖት”፣ “ርስት”፣ “ሚስት” የመሳሰሉት ነበሩ። በተለይ ለነገሥታቱ ቅቡልነትን የቀባው ሃይማኖታቸው እንዳይለወጥባቸው ነበር ምስኪን ሕዝቦች ከንጉሣቸው ጎን የሚሰለፉት። ምናልባት የመኳንንቱን ሹመት፣ ሽልማትና ሙገሳ ለማግኘት ድል ወዳደላበት የሚዋደቁም አይጠፉም። የትግራይ ሰው ለትግራይ ንጉሥ፣ የሸዋ ሰው ለሸዋ ንጉሥ፣ የወሎው፣ የጎጃሙ ሰው… ለየራሱ አካባቢ ንጉሥ ተዋድቋል። ተዋድቆ ለንጉሡ በሚያስገኘው ድል ግን ከገባሪነት በላይ ማዕረግ ተሸልሞ አያውቅም። የውጪ ወራሪ ኃይል ሲመጣ፣ ከወገን የበለጠ የከፋ ሰው መጣ በሚል ስሜት ነው የሚዋጉት እንጂ የዛሬ ሰዎች የቅኝ ግዛት ጉዳቶችን በምንቆጥርበት መሥፈርት ቆጥረውና ፈርተው አይደለም። ለዚህም ነው አውሮጳ ቀመስ ኢትዮጵያውያን ‘ሊያሠለጥኑን ይችላሉ’ በሚል ባንዳነትን የመረጡት። ስለዚህ የአድዋ ጦርነት ‘የማውቀው ሰይጣን ይሻለኛል’ የሚሉት ዓይነት ምርጫ ነው እንጂ ዛሬ እኛ ወይም ያኔ አውሮጳውያን ያኔ ጀምሮ ነጻነት የምንለውን ለማግኘት አልነበረም።
ከዚህ ውጪ እንደ ገዳ ባሉ አገር በቀል ስርዓቶች ለረዥም ምዕተ ዓመታት ሲተዳደሩ የቆዩት በአሁኒቷ ኢትዮጵያ የደቡብ አካባቢ ሕዝቦች ከዚህ የሥልጣን ሽኩቻ ተገልለው ቢቆዩም በማዕከላዊው መንግሥት የመዋጣቸው ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነበር። ይህም በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ባይጀመርም፣ በርሳቸው ጊዜ የተፈፀመ ሌላ የታሪክ አጋጣሚ ነው። (በእርግጥ ኦሮሞውም ወደሰሜን ዘልቆ በመግባት የመንበረ ንግሥናው ተሻሚ መሆን ከጀመረ ሰንብቷል።) ደቡብን በኃይል ማስገበር በወቅቱ የምኒልክን ኃያልነት ቢያጠናክርም፣ ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ግን ፈታኝ የታሪክ አረዳድ ክፍፍል ጥሎ አልፏል። የሆነ ሆኖ ታሪክ አይቀለበስም። የምኒልክ ታላቅነትም፣ ትውፊታዊ ስርዓቶችን አፍርሰው በራሳቸው አስተዳደር መተካታቸውም፣ አልገብርም ብለው ያስቸገሯቸውን ማኅበረሰቦች ከራሳቸው ሰዎች መሐል በመለመሏቸው ተዋጊዎች መቅጣታቸውም፣ ሁሉም ከነትርፉ እና ኪሳራው እዚህ ደርሷል። በዕውቀቱ ሥዩም “ዘንድሮ የሚለው ቃል ያለነገር አይደለም ድሮ የሚለውን ቃል በውስጡ የያዘው እንዳለው፣ የዘንድሮ ሰዎች የድሮ ግዞተኞች ከመሆን አልተረፍንም። ዳግማዊ ምኒልክም ከዙፋናቸው አልወረዱም፤ ምክንያቱም እስከዛሬ ያወዛግቡናልና። ምኒልክ ደግ አረጉ የሚሉትም፣ ደግ አላደረጉም የሚሉትም ሁሉም የእርሳቸው ውሳኔ ውጤት ናቸው።
ዳግማዊ ምኒልክ – ጨካኝ፣ ስኬታማ!
ዳግማዊ ምኒልክ በዘመናቸው፣ በኢትዮጵያ ከነበሩት የተሻለ ብልኅ እና ኃያል ንጉሥ ነበሩ። የእርሳቸው ሕልም ከአያት ቅድም አያቶቻቸው የወረሱት ትልቅ ግዛት (empire) የመመሥረት ሕልም ነበር እንጂ ፅድቅን ማድረግ አልነበረም። ከሕልም አንፃር እንደርሳቸው የተሳካላቸው የለም። ከጎናቸው ጠላቶቻቸውን ሳይቀር ማሰለፍ ችለዋል። በታሪክ አጋጣሚ የአድዋ ድል ባለቤት ሆነዋል። በዚህም በቅኝ ገዥ አውሮጳውያን ዛሬ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ከየትኛውም አፍሪካዊ ሉኣላዊ አገር በፊት ድንበሯ የታወቀላት እንድትሆን ማድረግ ችለዋል። ከአድዋ መልስ ዘመነኝነትን በከፊል ለማስገባት ከምኒስትሮች ሹመት አንስቶ እስከ ቴክኖሎጂ የማስመጣት መሠረታዊ ሥራዎችን ሠርተዋል። ተከብረውም ይሁን ተፈርተው እስከ‘ለተ ሞታቸው ተቀባይነታቸውን ሳያጡ ኖረዋል። ከሞታቸው በፊት ሥልጣናቸውን ያወረሱት ልጅ እያሱ በኦሮሞ እና ሙስሊም አክቲቪስቶች ሹመቱ ቢፀና የተሻለች ኢትዮጵያ ተወልዳ በሆነ ነበር እያሉ የሚቆጩለት ውርሳቸው ነበር። ምንም እንኳን በጊዜው የተሻለ ፍትሐዊ ስርዓት የሚያራምዱ አገሮች ስለመኖራቸው መረጃው ቢኖርም የራሳቸውም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የወቅቱ ሕዝብ ብስለትም ወደዚያ አልወሰዳቸውም።
በመሆኑም፣ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የሚባልላቸውን ያክል “እምዬ” አልነበሩም። ለንግሥናቸው ቀናተኛ ነበሩ። የተቃወሟቸው እና ያልገበሩላቸው ላይ የማያዳግም ርምጃ የሚወስድ ሠራዊት ይልኩ ነበር። ንጉሠ ነገሥትነትን ለመቆናጠጥ እና ለማጠናከር እየተጣደፉ ባለበት ወቅትም ነው ለአይቀሬው የአድዋ ጦርነት ሰበብ የሆነውን የውጫሌ ውል ከነስህተቱ የፈረሙት። ከነመኳንንቶቻቸው ባሪያ አሳዳሪም ነበሩ። ባሪያ ንግድ ውስጥም ነበሩበት። ለባርነት ይሸጡ የነበሩበት ደግሞ የገዛ ዜጎቻቸውን ነበር።
አድዋ ዕድል ነበር!
ያም ሆነ ይህ አድዋ ለኢትዮጵያውያን ቀስ በቀስ የምናሸንፈው፣ የራሳችንን ጨቋኝ የመምረጥ ዕድል የሰጠን ዕድል ነበር። የሰው ዘር የሚሊዮን ዓመታት ጉዞ ከባርነት ነጻ ለመውጣት የሚደረግ ጉዞ ነበር/ነው። የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ፈተና እና ከድንቁርና በከፊል ነጻ ሲወጣ፣ ነጻ ያወጡኛል ብሎ የመሠረታቸው መንግሥታዊ ስርዓቶች በተራቸው ነጻነቱን የሚገድቡ ፈተና ሆነውበታል። ከእነርሱ ነጻ የሚወጣበት ሒደት ውስጥ አድዋ አለ።
በአውሮጳውያን ቅኝ ግዛት የተገዙ አገራት ነጻ ሲወጡ የሚመኩበት ወግና ባሕል አልነበረም። ወግ፣ ቋንቋ እና ባሕል ቋሚ ነገር አይደሉም። ዛሬ በዓለማችን ካሉ 7000 ቋንቋዎች ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ ከመቶ የበለጠ አይተርፍም። ነገር ግን ቋንቋዎች/ባሕሎች በሕዝቦች ፈቃድ፣ ተፈጥሮን ለማሸነፍ ሲፍጨረጨሩ እንደተወለዱ ሁሉ በሕዝቦች ፈቃድ ተዘንግተው ሲጠፉ ብቻ ነው ጤናማ የሚሆነው። የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎች ይህ ተፈጥሯዊ ሒደት ውስጥ ነው ጣልቃ የገቡት። አፍሪካውያን ቅኝ ገዢዎቻቸውን በአምባገነኖች ተክተዋል። ሆኖም ወደቅኝ ገዢዎቻቸው ከመመለስ አምባገነን መሰሎቻቸውን ይመርጣሉ። ያስመለሱት ‘ነጻነት’ ግን የዕኩልነት የወል ሥነ ልቦናቸውን ከተሰለበበት አላስመለሰም። ለእኛ በአድዋ የተሰጠን ዕድል ይህ ዕድል ነው። ‘ነገሥታቱ የአውሮጳ የቅኝ ገዢዎቹን ሚና እዚህ ተጫውተዋል’ የሚለኝ አይጠፋም፤ መደሰት ያለብን ‘እንኳን የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎችን ያክል አቅም አልነበራቸው’ እያልን ነው። ‘የተሻለ ጨቋኝ‘ ብለን የመረጥናቸውስ ለዚያ አይደል?!
የአድዋ ድል ባይኖር ኖሮ፣ እኔና እናንተም አንኖርም ነበር። የምንጨቃጨቅበት ጉዳይም አይኖርም ነበር። በማንነት ቀውስ የሚባክኑ፣ የተለየ ሥነ ልቦና ያላቸው፣ የተለዩ የሰዎች ስብስብ ነበር እዚህ የሚኖሩት።
Cheers ስለመኖራችን!
Cheers ይህን እውን ላደረጉት አያቶቻችን!
[…] የዐድዋ ድል መታሰቢያ 121ኛ ዐመት የሚዘከርበት ወቅት ነው። በፍቃዱ ዘ. ኀይሉ የተሰኘ ከታቢ (blogger) “Bilisummaa adda-ዋ!” በተሰኘ እና በድረ ገጽ እና በፌስ ቡክ በተሰራጨ አነጋጋሪ […]