ዋዜማ ራዲዮ- በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያገኘው አዲሱ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር በፓርቲ ውስጥ መስንጠቅ አለመከሰቱን ይልቁንም ፓርቲው በዲስፕሊንና በምዝበራ ጥፋተኛ ያላቸው የአመራር አባላት ላይ እርምጃ የወሰደበት እንደነበረ አስታወቀ።
ለፓርቲውና ለቀድሞ አመራሮች ክብር ሲባል ጉዳዩን በዝምታ ይዞት መቆየቱን የገለፀው አዲሲ የፓርቲው አመራር ችግሩን በፓርቲው ውስጥ ለመፍታት የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ጉዳዩ ወደ አደባባይ መውጣቱንና በአሁኑ ወቅት ፓርቲው በአብላጫው የቀድሞ አመራር አባላትን ይዞ ስራ መቀጠሉን ገልጿል። ዝርዝር ዘገባው የሚከተለው ነው።
የካቲት 8/2009 በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተቸረው የሰማያዊ ፓርቲ አዲሱ ሥራ አስፈፃሚ በዛሬው ዕለት (የካቲት 19/2009) በጽ/ቤቱ በሰጠው የፓርቲው ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ፣ የፓርቲው የቀድሞ የፓርቲ መሥራችና የሥራ አስፈፃሚ አባላት የነበሩ፣ እንዲሁም አሁን የብሔራዊ ምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቶ ጌታነህ ባልቻ “ተከስቶ የነበረው ችግር መከፋፈል ሊባል አይችልም” በማለት አስተባብለዋል። “ጥቂት ሰዎች በዲሲፕሊን እና በንብረት ምዝበራ ቢሰናበቱም፣ አሁንም 37 ቋሚ እና 13 ጊዜያዊ አባላት ያሉት ብሔራዊ ምክር ቤት አለ። ሥራ አስፈፃሚውም የጠቅላላውን ጉባዔ እና የምርጫ ቦርድን ዕውቅና አግኝቷል” ብለዋል።
በአዲሱ የፓርቲው ሊቀ መንበር አጭር የመክፈቻ ንግግር የተጀመረው የማብራሪያ መድረክ፣ የተለያዩ ሰነዶችን በማቅረብ በቀድሞው ሊቀ መንበር አቶ ይልቃል እና ደጋፊዎቻቸው፣ እንዲሁም በአቶ የሺዋስ አሰፋ የሚመራው አዲሱ ሥራ አስፈፃሚ መካከል የነበረው ችግር በቀድሞው ሥራ አስፈፃሚ ድክመት የተፈጠረ እና አሁን ግን እልባት ያገኘ መሆኑን ለማስረዳት ሞክሯል።
አቶ የሺዋስ በመክፈቻ ንግግራቸው “እስካሁን ዝም ያልነው፣ አንደኛ የሰውን ክብር ላለመንካት እና ሁለተኛ የመታረቅ ትንሽ ዕድል ካለ ብለን ነበር።” ብለዋል። አቶ ጌታነህም የቀድሞው ሊቀመንበር እና ሌሎች የተባረሩ አባላቱ ለሠላማዊ ትግሉ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ፓርቲው ጉዳዩን ይፋ ከማድረግ መቆጠቡን ገልጸዋል።
አቶ ጌታነህ ባልቻ “የችግሩ መነሻ የፓርቲው የቀድሞ ሊቀ መንበር አቶ ይልቃል ጌትነት እና ሌሎቹም የድርጅቱን ንብረት መመዝበራቸው ነው” ብለዋል። “የንብረት መመዝበሩ ጥያቄ እንደተፈጠረ የሥነ ስርዓት አጣሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩን በመመርመር ያረጋገጠ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ ነባሩን ሊቀመንበር በማውረድ አዲስ ምርጫ በማካሔድ አቶ የሺዋስ የሊቀ መንበርነቱን ቦታ በውስጠ ደንቡ መሠረት ወስደዋል” ብለዋል። አቶ የሺዋስም በመግቢያ ንግግራቸው ከሊቀ መንበር በስተቀር ቀሪው የሥራ አስፈፃሚው ኃላፊዎች ባሉበት መቀጠላቸውን አስረድተዋል።
ከፓርቲው አስራ አምስት መስራች አባላት መካከል አንዱ ብቻ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የቀድሞውን ሊቀመንበር ጨምሮ ሁለት ተጨማሪ መሥራች አባላት በሥነ ስርዓት ጉድለት በመታገዳቸው መሥራች ዐሥራ አንድ አባላት የፓርቲውን ሥራዎች ለማከናወን በሚጥሩበት ሰዓት ፓርቲው እንደተሰነጠቀ መነገሩ ትክክል አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።
የድርጅቱን ንብረት መዝብረዋል የተባሉት 5 ሰዎች በድርጅቱ ደንብ መሠረት ክስ የቀረበባቸው እና በደንቡ መሠረት የተከራከሩ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ጥፋተኛ መሆናቸው ሲበየን፣ አቶ ይልቃልን ጨምሮ በይቅርታና በቅጣት ለመታለፍ ያልፈቀዱት አራቱ ከአባልነት ሲሰናበቱ አቶ ጌታነህ ባልቻ ግን በቅጣት ታልፈው የአዲሱ የሥራ አስፈፃሚ አባል ሆነው ቀጥለዋል።
የአጣሪው ኮሚቴ ገለልተኝነት፣ የተመዘበረው ንብረት ግምት፣ የጠቅላላ ጉባዔው ምልዓትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባላት ሲመልሱ የሥነ ስርዓት አጣሪ ኮሚቴው ሦስት አባላት በምክር ቤቱ የፀደቁ በመሆናቸው ገለልተኛ ናቸው ብለዋል። ተመዘበረ የተባለውን ገንዘብ ትክክለኛ መጠን ለመግለጽ በተደጋጋሚ ያመነቱት አቶ ጌታነህ፣ በመጨረሻ “ከመጀመሪያ ጀምሮ ከተደረጉት 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በሰነድ ሳይወራረድ የቀረ ነው” ብለዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አስቸጋሪ ገጽታ ምክንያት ለቅስቀሳ የሚታተሙ በራሪዎች እና ተመሳሳይ ወጪዎች የሦስተኛ ወገንን ደኅንነት ከመጠበቅ አንፃር ያለ ደረሰኝ ሊሠሩ እንደሚችሉ እና ችግሩ በዚህ ሳቢያ ተፈጥሮ እንደሆነ እና የአሠራር ክፍተት ካለ የተጠየቁት አቶ ጌታነህ፣ “እንደዚህ ዓይነት ወጪዎች በልዩ ቃለ ጉባኤ የሚፈፀምበት አሠራር አለን” በማለት የአሠራር ክፍተት ለምዝበራ እንዳላጋለጣቸው አስረድተዋል።
የጠቅላላ ጉባዔውን ምልዓት በተመለከተ በመተዳደሪያ ደንቡ የተወሰነ ቁጥር ባይኖርም ሰማያዊ ፓርቲ መዋቅሮቹን በዘጋባቸው ወረዳዎች ቁጥር ልክ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት እንደሚኖረውና በ2007 አቶ ይልቃል ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ በፀደቀው እና ከዚያ ጀምሮ ለ3 ዓመታት በሚያገለግለው 226 አባላት ያሉት ጠቅላላ ጉባዔ ዳግም ጥሪ ተደርጎ፣ 129 አባላት ተገኝተው ኮረም በመሙላቱ በተደረገው ምርጫ አቶ ይልቃል ወርደው አቶ የሺዋስ በምትካቸው ተመርጠዋል።
በአቶ ይልቃል እና ደጋፊዎቻቸው ከተነሱ ቅሬታዎች መካከል፣ የፓርቲው አባላት ያልሆኑ ሰዎች መገኘታቸው አግባብ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ አቶ የሺዋስ “ታዛቢ እንዲኖር በማለት ከቀድሞው አንድነት ፓርቲ፣ ከመኢአድ እንዲሁም ከምርጫ ቦርድ ታዛቢ ጋብዘናል። እነዚህ ግን በደምፅ ቆጠራው አልተሳተፉም። የአቶ ይልቃል ደጋፊ የነበሩ 13 ሰዎች ከ129ኙ በተጨማሪ ቢገኙም ጉባዔውን ለማስተጓጎል እንጂ ለመሳተፍ ፊርማቸውን ለማኖር ስላልፈቀዱ በጠቅላላው ጉባዔ ውሳኔ እንዲወጡ ተደርገዋል” በማለት ተሳታፊዎቹ የፈረሙበትን ሰነድ አሳይተዋል።
ጠቅላላ ጉባዔው የተካሔደው ምንጩ ባልታወቀ ገንዘብ ነው በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ የተራገበውን ዜና ሲያስተባብሉም፣ አቶ ጌታነህ ሁለት ደብዳቤዎችን አቅርበዋል። የመጀመሪያው ከፓርቲው ለሰሜን አሜሪካ የሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ሰጪ ጉባዔውን ለማካሔድ የተጠየቀበት ደብዳቤ ሲሆን፣ ሁለተኛው የሰሜን አሜሪካው ድጋፍ ሰጪ ድጋፍ ማድረጉን የገለጸበት እና ለአቶ ይልቃል ጌትነትም ግልባጭ የተወበት የኢሜይል መልዕክት ነው።
ከቀድሞው ሊቀ መንበር እና ደጋፊዎቻቸው ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት፣ በወቅቱ ከሁለት ዓመት እስር በኋላ በነጻ የተፈቱት አቶ የሺዋስ አሰፋ በግንቦት ወር 2008 ልዩነቱን በእርቅ ለመፍታት ንግግር ላይ የነበሩ መሆናቸውን አስታውሰው፣ በዚህ ውይይት መሐል ሊቀ መንበሩ አቶ ይልቃል ወደካናዳ መሔዳቸውን የውይይቱ አካላት እንደማንኛውም ሰው ከሚዲያ መስማታቸውን ተናግረዋል። የቀድሞውም፣ የአሁኑም ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ በውጭ ጉዳይ ኃላፊነት የሚያገለግሉት አቶ አበበ አካሉም “እኔ እንኳን አቶ ይልቃል በፓርቲው ሥም ሊሔዱ ስለመሆናቸው ምንም መረጃ አልነበረኝም። ፓርቲው የግለሰብ ንብረት የሆነ ያክል ነበር። እኔ የማገለግለው የኢትዮጵያ ሕዝብን እንጂ የፓርቲውን ሊቀመንበር አይደለም” በማለት በምሬት ተናግረዋል።
የገንዘብ ምዝበራው አሁንም እንደቀጠለ የተናገሩት አቶ ጌታነህ፣ “በቅርቡ ከሰሜን አሜሪካ ደጋፊዎቻችን የተላከልን 7,600 ዶላር ድጋፍ አቶ ይልቃል እጅ ከገባ በኋላ ወደ ፓርቲው ገቢ አልተደረገም። ደጋፊዎቹም እውነቱን ሲያውቁ ለማስመለስ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካላቸውም” ብለዋል። “ከዚህም ውጪ ሌሎች ምዝበራዎች አሉ” ያሉት አቶ ጌታነህ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሊወስዱት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
የቀድሞ የፓርቲ መሪ ይልቃል ጌትነት ግን የአዲሱ አመራር እርምጃ ፓርቲውን ለማፍረስ ባልታወቁ ሀይሎች የተቀነባበረ ሴራ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የፌስቡክ ገጽ ላይ 12 የቀድሞ የፓርቲ አባላትን የያዘ ሁለት ኮሚቴ መመሥረቱ ተነግሯል። የአቶ ይልቃል ደጋፊዎች የምርጫ ቦርዱን ውሳኔ በፍርድ ቤት ሊሞግቱት ይችላሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የኮሚቴው አባል እና ከሦስት ወራት የማዕከላዊ እስር በኋላ በቅርቡ የተፈቱት፣ የሕግ ባለሙያው አቶ አዲሱ ጌታነህ በትላንትናው ዕለት አመሻሹ ላይ ባልታወቁ ሰዎች በጩቤ ተወግተው ሆስፒታል መግባታቸው ተነግሯል።