ከማርች ስምንት ጋር አያይዤ /አቤል ዋበላ/

ከማርች ስምንት ጋር አያይዤ /አቤል ዋበላ/

አንድ ማኀበረሰብ በዘልማድ ገንዘብ ያደረጋቸው ነገሮች ሳይጠይቅ መሄዱ ብዙ ዋጋ ያስከፍለዋል፡፡ የኛም ማኀበረሰብ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ብዙ ልማዶች አይጠየቁም እንዲሁ ሳይመረመሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ይደረጋል፡፡ ዛሬ ከማርች ስምንት ጋር አያይዤ ለመንቀፍ የተናሳኹት ይህንን ከአያት ቅድመ አያት የተላለፈልንን እንዲሁ ሳናላምጥ መዋጣችንን አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ትኩረቴን ያደረኩት ከዚህ በተቃራኒው የሀገር ልማድ ንቆ ዘመናዊ አስተሳሰብ የለበሰውን ተራማጁን ነው፡፡ እርግጥ ነው ከብዙኃኑ ተነጥሎ የእኔ የሚለው ማኀበረሰብን ስህተት ነቅሶ ማውጣቱ የሚያስመሰገነው ቢሆንም ወደ መፍትሔ ሲመጣ ግን የምዕራቡን አስተሳሰብ እንደወረደ መቀበሉ ግን የሚያስተቸው ነው፡፡ ፈረንጅ የነቀፈው ሁሉ ስህተት ፈረንጅ ያወደሰው ሁሉ ልክ ብሎ የማሰብ አዝማሚያ አለ፡፡

የሴቶች መብት የዚህ ዝንባሌ ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ እርግጥ ነው የኢትዮጵያ አብዛኛው ሀገር በቀልም ሆነ ከሀይማኖቶች ጋር ከውጭ የወረስነው ባህል ‘አባታዊ’ እና ሴቶችን የሚጨቁን መሆኑ ያስማማናል፡፡ ከላይ ያነሳውን ተራማጅም ይህንን መተቸቱ አያስነቅፈውም፡፡ ችግሩ አሁን ካለንበት ሴቶችን ከሚጨቁን ስርዓት ወጥተን እንዴት ወዴት ነጻነት ወዳለበት እንሸጋገር ሲባል የምዕራብ ልማዶች እንደ የገደል ማሚቶ ማስተጋባቱ ነው፡፡ አሁንም ጉዳዬን ጠበብ አድርጌ ትችቴን ለማስረዳት ከሴቶች ጉዳይ ጋር ተያይዘው ከሚነሱ ነገሮች ውስጥ አንዱን ላንሳ፡፡ ሴቶች እና ማጀትን ይመለከታል፡፡

የሀገራችን ሴቶች የማጀቱ ነገር ጫንቃቸው ላይ ለብቻቸው መወደቁ እንደ ካቴና ብረት አስሮ ነጻነት አሳጥቶ ኃላቀር አድርጓቸዋል፡፡ ከእያንዳንዷ የሀገሬ ሴት አቅም ማጣት ጀርባ ከኋላ የሚጎትታት ማድቤት ይታየኛል፡፡ ይህ እንዴት ይፈታ የሚለውን ከማሰላሰል ይልቅ ሴቶች ማጀት ላይ እንዲያምጹ እና ማጀት ገብተው የሚያገለግሉትን ተባዕት እንዲጠሉ የሚያደርግ ነው፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ከዚህ በታች ያያዝኩት “ስራ የላትም” የሚል ርዕስ ያለው ቪዲዮ በማኀበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ፕሮዳክሽኑን ከማድነቅ በዘለለ ብዙም ትኩረት አልሰጠኹትም ነበር፡፡ በኋላ ግን በአጋጣሚ የፍራንሲስ ፉኩያማን The Great Disruption; Human nature and the reconstruction of social order ሳነብ እንዲሁ ሳናላምጥ የምንውጠው ነገር ብዙ እንደሆነ ተገነዘብኩኝ፡፡

ፉኩያማ በዚህ መጽሐፉ ማኀበረሰባዊ ቀውሶችን ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡ ከላይ ባነሰኹት የማጀት ጉዳይ ከምዕራቡ ሴቶች ከማጀት እንዲወጡ እና እንዲወጡ ብቻ ከሚገፋፋው በተለየ መልኩ ተጨማሪ ሀሳቦችን ያነሳሳል፡፡ ወንዱን ልጅ በማሳድግ እና ከልጆች ጋር ቅርርብ የመፍጠር አቅም ልልነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ለቤተሰብ ጤናማነት የእናትየው ድርሻ የማይተካ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ቤተሰብም የተፈጠረው ማኀበረሰቡ ወንዱን ሴቷን እንዲረዳት በማሰብ እንደሆነም ይገልጽና ከዚህ ውጭ ዘሩን ከማበርከት በቀር ሌላ ሀላፊነትን ተፈጥሮ ለወንዱ አለመስጠቷንም ያትታል፡፡ ስለዚህ ሴት ልጅ ከማጀት ትውጣ ስንል በአጠቃላይ የሰው ልጅ እጣ ፈንታ ላይ እየፈረደን እንደሆነ እናስተውል፡፡ ይህንን ስል ሴቷ ፍዳዋን ስታይ ትኑር እያልኩኝ እንዳልሆነ አንባቢ ያስተውል፡፡ እርሴ ስላልሆነ ነው የዘለልኩት፡፡ ነገር ግን እዚያው ማጀት ትቅር በሚለው እና ትውጣ በሚለው መሀል የሚወድቁ በርካታ የመፍትሔ ስልቶች መንደፍ ይቻላል፡፡

ፉኩያማ የጃፓናውያንን ከምዕራቡ የተለየ ተሞክሮ ይገልጻል፡፡ ጃፓናውያን የሴቶችን የስራ ዑደት የእንግሊዘኛውን “M” ፊደል የሚመስል ነው ይላል፡፡ አንዲት የጃፓን ወጣት መደበኛ ትምህርቷን አጠናቃ የስራ ዓለሙን ከተቀላቀለች በኋላ ልጅ የመውለጃ እና የማሳደጊያ ጊዜዋ ሲደርስ ደግሞ ተመልሳ ወደ ማጀት ትገባለች፡፡ ልጆቿን አሳድጋ ስታበቃ ደግሞ ወደ ስራው ዓለም ተመልሳ ትቀላቀላለች፡፡ መንግስትም ይህንን ሂደት ለመደገፍ የተለያዩ የአሰሪ እና ሰራተኛ ግንኙነትን የሚገዙ መመሪያዎች ያወጣል ያስፈጽማል፡፡ ይህም በጃፓኖች ቤተሰብን ከነ እሴቶቹ የረጋ ሆኖ እንዲቆይ ያርዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ የእስያ ዕሴቶች (Asian Values) ከሚባሉት ጋርም መሳ ለመሳ ይሄዳል፡፡ እርግጥ ነው ይህ ሞዴል በርካታ ድክመቶች እና ነቀፋዎች እንዳሉበት መዘንጋት የለበትም፡፡

ይህንን ካነብበኩኝ በኋላ ሀኒባል አበራ ‘ስራ የላትም’ የሚለውን አጭር አስተማሪ ፊልም ሲሰራ ከሀገር ልማድ ነቃፊዎች የተለየ ሐሳብ እንዳላመጣ ተገነዘብኩኝ፡፡ ፊልሙ የአንድ ልበሙሉ ባተሌ እናትን (ከነቤተሰቧ) የአንድ የቀን ውሎ ያሳይና በመጨረሻ ባሏ የቀን ተሌት ድካሟን ዘንግቶ “ስራ የላትም” ሲል እርሷ ደግሞ በዚህ ሲከፋት ያሳይና ይጠናቀቃል፡፡ ለእኛ ወንዶቹ ግድየለሽ እና ንዝህላል መሆናችንን በተገቢው መልኩ ስለሚነግረን በዚህ በኩል ስኬታማ ነው፡፡ ለሴት እህቶቻችን ግን ጤናማ መልዕክት ያስተላለፈ አልመሰለኝም፡፡ ይህንን የያች ሁሉ ከማጃቷ እና ባልተቤቷ ጋር ጠላትነት ውስጥ ትገባለች፡፡ ምላሿም ማጀት ሆና ጤናማ ልጆች፣ ጤናማ ቤተሰብ እና ጤናማ ትውልድ ማፍራቷን ግምት ውስጥ ያላስገባ ይሆናል፡፡ ከዚህ ይልቅ ባለሙያው ታታሪ ነገር ግን አኩራፊ(ቂም የምትይዝ) ሴት ከሚስልልን ትንሽ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ጨምሮ የወንዱን የተሳሳተ አመለካከት የሚነድ የሴቶቻችንን መሪነት የሚያጎላ እና የማጀት ችግራችንን እንዴት መፍታት እንዳለብን የሚጠቁም መልዕክት ባስተላለፈልን ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ የማትተው ምን ለማለት ነው? ሴትነት ይከበር ግን እየተስተዋለ ለማለት ነው፡፡

LEAVE A REPLY