የቆሼ ወገኖቻችን የውሸት ኖረው የእውነት ሞተዋል! /አርኪቴክት-ዮሐንስ መኮንን/

የቆሼ ወገኖቻችን የውሸት ኖረው የእውነት ሞተዋል! /አርኪቴክት-ዮሐንስ መኮንን/

አንዲት እድሜ ልኩዋን በድህነት ስትማቅቅ የኖረች አሮጊት በነ አለቃ ገብረሃና ሰፈር ውስጥ ሞታ ኖሮ መንደርተኛው ለቀብር ላይ ታች ይላል፡፡ አለቃ በዚያው መንገድ ሲያልፉ “ምንድን ነው እጅብ እጅቡ?” ብለው ይጠይቃሉ።
“እንዴ! አለቃ አልሰሙም እንዴ ?” “ምኑን?” “ያቺ ምስኪን አሮጊት መሞቷን?” አለቃም ቀበል ያደርጉና “አሄሄሄ… ተኖረና ተሞተ ¡” ብለው ተናግረዋል ይባልላቸዋል፡፡

በአዲስ አበባዋ “ቆሼ” መንደርም የሆነው ይኸው ነው፡፡ ተበጀ አስረስ የተባለው የቆሼ “ነዋሪ” ለፈረንሳዩ AFP ሲናገር “የቆሻሻው ክምር ሲናድ ቆሜ እመለከት ነበር፡፡ ናዳው ቤታችንን ሲከድነው እናቴ እና ሦስት እህቶቼ ከውስጥ ነበሩ” ብሏል፡፡

እንደ ቢቢሲው ኢማኑኤል ኢጉንዛ ዘገባ በቀን በመቶዎቹ የሚቆጠሩ “ዝጎች” (ዜጎች ማለትማ ይከብዳል፡፡) ሕይወታቸውን ለማቆየት ከአዲስ አበቤዎች በሺዎች ቶን የሚገመት የጥራጊ ክምር ስር ደፋ ቀና ሲሉ ይውላሉ፡፡ የሟቾች ቁጥር እስካሁን በውል ባይታወቅም ዛሬ ምሽት FBC “አረጋገጥኩት” እንዳለው፥ እስካሁን በፍለጋ የተገኙት አስከሬኖች 60 ደርሰዋል፡፡ ያው እንደተለመደው ባለሥልጣናት እና እነ “አር-ቲስቶች” (ነብሱን ይማረው እና ተስፋዬ ካሳ “አት ሊስቶች” ይላቸዋል) ቀብር ማስፈጸም እና ንፍሮ ለመቀቀል በመረባረብ ላይ መሆናቸውን ፋና አብስሮናል፡፡ እሰይ! ኑሩልን እናንተን ባያቆይልን ማን እንዲህ እያሠማመረ ይቀብረን ነበር ?

አንድ የአህጉሩ መዲና ነኝ የምትል ከተማን ለማስተዳደር፣ ለዜጎችም ምቹ የመኖሪያ እና የሥራ ቦታ ለማደራጀት ቀረጥ ለሚሰበስብ የከተማ መስተዳድር በአደራ የተቀበላቸውን ዜጎች አስከሬን ከቆሻሻ ክምር ስር እንደመሰብ ምን አሳዛኝ እና አሠቃቂ ክስተት አለ? መሞታቸውስ አደጋ ነው፡፡ ግን ግን እነኚህ “ወገኖቻችን” መጀመሪያስ ኖረው ያውቃሉ? ከሞቱ እኮ ቆይተዋል፡፡ አሁን የተፈጸመው ቀብራቸው ነው፡፡ ተኖረና ተሙቷል ! ይህን ያህልስ ዜጎቹን ከቱቦ ስር፣ ከየበረንዳው እና ከቆሻሻ ክምር ሰር ጥሎ መሬት በጨረታ ሲቸበችብ የሚውል መዘጋጃ ቤት ደርሶ ቀብር አስፈጻሚ እና አጽናኝ ሆኖ መሰየሙ ፌዝና ስላቅ አይሆንም? ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ ከሶስት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በላይ ጨረታ በሚቀርብባት እጅግ ዝቅተኛ የተባለች 150 ካሬ ሜ. ቦታ በጨረታ በ 10 ሚሊዮን ብር በሚሸጠባት ከተማ ለምስኪናኑ ከቆሻሻ ክምር ስር የተሻለ “የመኖሪያ” ቦታ ከወዴት ይገኝላቸዋል? የቆሼ ወገኖቻችን የውሸት ኖረው የእውነት ሞተዋል፡፡

ቢያንስ ከቀብር መልስ ንፍሮ ለመቀቀል ድንኳን ለመጣል ተፍ ተፍ ማለቱ ይቆይና ከኗሪ በታች ከሙታን በላይ የሆኑ፣ በየጎዳናው፣ በየቆሻሻው ገንዳ ሥር እና በየጥጋጥጉ ወድቀው የእለት ጉርሳቸውን ከውሾች ተናጥቀው ነፍሳቸውን ለማቆየት የሚቃትቱ ነፍሳትን ለመታደግ በተግባር የሚታይ የምር ሥራ ይጀመር፡፡ እነኚህም ሰሚ አላገኙም እንጂ ህላዌ ተደርምሶባቸው በሞት እና በሕይወት መካከል የሚያጣጥሩ ናቸውና፡፡ የከተማዋን የመኖሪያ ቦታዎች ድንገቴ “ባለሀብቶች” የሚናጠቁት መሆኑ ጋብ ብሎ ዜጎች እንደአቅማቸው ማረፊያ የሚያገኙበት መንገድ ይፈለግ፡፡ ያ ትውልድ “መሬት ላራሹ” እንዳለው የኔ ትውልድ “ቤት ለነዋሪው” ይላል!!!

LEAVE A REPLY