/ሊያነቡት የሚገባ/ የቆሼው አደጋ ሐዘን ውስጥ ከከተታቸው እናቶች አንዷ

/ሊያነቡት የሚገባ/ የቆሼው አደጋ ሐዘን ውስጥ ከከተታቸው እናቶች አንዷ

/በሃይሉ ገብረእግዚአብሔር/

ደሴ አለሙ ትባላለች፡፡ ብዙዎች የሚያውቋት ‹‹አበባ›› በሚለው መጠሪያዋ ነው፡፡ የሦስት ልጆች እናት ናት፡፡ በኤሆፕ ኢትዮጵያ የህፃናት ማሳደጊያ ድርጅት ውስጥ በሞግዚትነት ትሠራለች፡፡ የምትኖረው በቆሼ አካባቢ አንድ አነስተኛ መኖሪያ ቤት ተከራይታ ነው፡፡ ወደዚህ መንደር ከመጣች ሁለት ዓመት ገደማ ይሆናታል፡፡

አበባ ወደ ቆሼ ከመምጣቷ በፊት ለረዥም ዓመታት የኖረችው ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ባለ የጨረቃ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ያ ብዙ ደክማ፣ በራሷ ላብ የሠራችው ቤት ‹‹ሕገ ወጥ ግንባታ ነው!›› ተብሎ በደንብ አስከባሪዎች ፈረሰባት፡፡ በዚህ ጊዜ ቤተሰቧን ጠቅልላ፣ እንዳቅሟ፣ በአነስተኛ ዋጋ የሚከራይ ቤት ወዳገኘችበት ቆሼ መንደር መጣች፡፡

መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም አበባ እቤት ውስጥ የስምንት ወር ልጇን ገላ ለማጠብ እየተሰናዳች ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ልጇ አልጋ ላይ ተኝቷል፡፡ ‹‹ይበልጣል ተመስገን›› ይባላል፡፡

ይበልጣል የቤተሰቦቹ ቤት ለሚማርበት ዩንቨርሲቲ ያለውን እርቀት እና የመኖሪያ ቤቱን ጠባብነት አስረድቶ እዛው ዩንቨርሲቲ ማደሪያ ክፍል እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ የዛን ቀን ግን ወላጆቹ ቤት ለእረፍት መጥቶ ጋደም እንዳለ ነው፡፡

ይበልጣል ተመስገን በትምህርቱ ብርቱ እንደመሆኑ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚመረቅ እሱም ሆነ ቤተሰቡ እርግጠኞች ነበሩ፡፡ በአነስተኛ አቅም ኑሮውን ለሚገፋው፣ ከጨረቃ ቤት ወጥቶ ቆሼ መንደር ለወደቀው የአበባ ቤተሰብ አጠቃላይ ተስፋ እሱ ነው፡፡

አበባ ውሃ እያቀራረበች ነው፡፡ የጨቅላ ልጇን ልብስ አወላልቃ ገላዋን ለማጠብ በመዘጋጀት ላይ ናት፡፡ ውጪ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጇ የቤተሰቡን ልብስ እያጠበች ነው፡፡ አበባ ቤት ውስጥ እንዳለች ድንገት ከውጪ ያልተለመደ ድምፅ ሰምታ ደነገጠች፡፡ ምን እንደሆነ ለማየት በር ከፍታ ስትወጣ ከበላያቸው ያለው የቆሻሻ ተራራ እየተናደ ነው፡፡

በድንጋጤ ወደ ቤቷ ፈጥና ገባች፡፡ ገላዋን ልታጥባት ያዘገጃጀቻትን የስምንት ወር ህፃን አንጠልጥላ ወጣች፡፡ አካባቢው ታውኳል፡፡ ትልቁ ልጇ ይበልጣል ቤት ውስጥ እንደተኛ ነው፡፡ አበባ ድንጋጤ ላይ ናት፡፡ ትኩረቷ የነበረው ጨቅላ ልጇ ላይ ነበር፡፡

ጨቅላዋን ታቅፋ እየሆነ ያለውን ስታስተውል የበኸር ልጇና ትልቁ ተስፋዋ ይበልጣል ቤት ውስጥ እንዳለ ተረዳች፡፡ በሰዓቱ እየሆነ የነበረውን ሁሉ አሁን ላይ ብዙም አታስታውስም፡፡ ስሙን እየተጣራች፣ ‹‹ውጣ! ኧረ ውጣ! ይበልጣል ውጣ እባክህ!›› ብላ የጮኸች ይመስላታል፡፡

የዛው ዕለት፣ በዛው ሰዓት በመካኒክነት ሙያው እየሠራ ቤተሰቡን የሚደጉመው የልጆቿ አባት ካለበት መጣ፡፡ በግርግሩ መሃል ሚስቱን፣ ጨቅላ ልጁን እና የአስራ ስድስት ዓመቷን ታዳጊ አስተዋለ፡፡ አንድ ሰው ጎድሏል፡፡ ትልቁ ልጁ ይበልጣል፡፡

‹‹ይበልጣልስ?›› ጠየቀ፡፡

‹‹ቤት ውስጥ ነው!››

አባት እንደ ሰማ አልዘገየም፡፡ ልጁን እየተጣራ ወደ ቤቱ ዘልሎ ገባ፡፡ ይሁን እንጂ ልጁን ከተኛበት ቀስቅሶ ይዞ ለመውጣት አልታደለም፡፡ ገና ወደ ቤት ከመዝለቁ የቆሻሻው ተራራ ተንዶ አባትና ልጅን ተጫናቸው፡፡ ከዚች ቅፅበት በኋላ አበባ እና ልጇ የደረሰባቸው ሐዘን በቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡ የአባት እና የተስፈኛ ልጁ የይበልጣል ሬሳ የተገኘው ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ ነበር፡፡

አሁን ከነሐዘናቸው የቀሩት አበባ፣ ጨቅላ ልጇ እና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ልጇ ብቻ ናቸው፡፡ ለጊዜው መንግሥት በዘረጋው መጠለያ ድንኳን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በዚያ ድንኳን ውስጥ የስምንት ወር ልጅ ይዞ መቆየት ከባድ ነው፡፡ አበባ ልጇን ጥቂት ሜትሮች ራቅ ያለ መኖሪያ ቤት ውስጥ አኑራታለች፡፡ ጡት የምታጠባው ለሐዘን ከተቀመጠችበት ድንኳን እየተመላለሰች ነው፡፡

አበባ ከነልጆቿ መጠጊያ የላትም፡፡ የሥራ ባልደረቦቿ ያቅማቸውን ለማድረግ እየተባበሩ ነው፡፡ እኔም በቅርበት አውቃታለሁ፡፡ በቅርብ የሚረዳት ባለቤቷን አጥታና እንዲህ ያለ ሐዘን በላይዋ ላይ አረብቦባት ይቅርና ኑሮዋ ከእጅ ወደ አፍ የሚሉት ዓይነት ነው፡፡

የምንችለውን፣ ያቅማችንን እናደርጋለን የምትሉ ካላችሁ ከመሥሪያ ቤቷ ደመወዝ የምትቀበልበትን የግል የባንክ አካውንቷን ከዚህ በታች አኑረናል፡፡

ስም፡- ደሴ አለሙ አበሻ
የባንክ ሒሳብ ቁጥር፡- 1000182168746
ቅርንጫፍ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

Name: Dessie Alemu Abesha
Account number: 1000182168746
Branch: Commercial Bank of Ethiopia

አበባ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ይሁን፤ እርሱ ሁሉን አድራጊው መፅናኛውን ይስጥሽ!
ቤተሰቦቼ የኤሆፕ ኢትዮጵያ ህፃናትም በአክስታችሁ ላይ በደረሰው ሐዘን እናንተም ተጎድታችኋልና ብርታቱን ይስጣችሁ!

አሜን!

LEAVE A REPLY