አህያ እና የ አህያ ሥጋ /ቴዲ አትላንታ/

አህያ እና የ አህያ ሥጋ /ቴዲ አትላንታ/

አህያ በኢትዮጵያ እየታረደ ወደ ውጭ አገር እንዲሸጥ የአህያ ቄራ መከፈቱ የሰሞኑ ወሬ ሆኗል። አንዳንዱ “እንዴት ተደርጎ የአ ህያ ሥጋ በተቀደሰው መሬት ላይ ታርዶ ይሸጣል?” ሲል፣ ሌላው “የውጭ ምንዛሪ እስካመጣ ድረስ ምን ችግር አለው?” ሲል ይከራከራል።

ሁለቱም መከራከሪያዎች አንዱ ከሞራልና ከግብረገብ ፣ ሌላው ከገንዘብ ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ከነዚህ ውጭ ደግሞ ሌላ ጉዳይ እኔ ላንሳ። አህያ እና ኢትዮጵያ።

download (4)በቅርብ በደረገ ጥናት በኢትዮጵያ 5 ሚሊዮን አካባቢ አህዮች እንዳሉ ተመዝግቧል። ዳገትና ቁልቁለት፣ ገደላገደልና ጅረት በበዛበት አገር ገበሬው ብቸኛ መተማመኛው አህያ ነው። እህል ገበያ ወስዶ ሸጦ፣ ሲመለስም ላምባና ዘይት ጭኖበት የሚመለሰው በአህያው ነው። ጭዱና እንጨቱን የሚጭነው በአህያው ነው።

ለከተማው ሰውም በየመንደሩ ከሰልና እንጨት እያመጣ፣ አሁን አሁን ውሃ እንኳን ሲጠፋ ጀሪካን ተሸክሞ ውሃ ፍለጋ አብሮ የሚዞረው አህያ ነው። የአዲስ አበባ የ እህል ገበያዎችን በየሳምንቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አህዮች ከከተማዋ 25 ኪሎሜትር ርቀት ድረስ ካሉ አካባቢዎች እየመጡ እህል በማራገፍ ቀጥ አድርገው ይዘዋል።

በመርካቶ የአህዮች ሆቴልና ምግብ ቤት አለ። ዛሬ የአህያ ቄራ ታስተናዳለች በተባለችው ደብረዘይት ከተማ እንኳን ከዓመታት በፊት የአህያ ሆስፒታልም መከፈቱ የሚታወቅ ነው። ባለፈው 2002 ዓ.ም ብቻ 40ሺ የሚደርሱ አህዮች ታክመውበታል ይላል አንድ ዘገባ።

አህያ ለኢትዮጵያ ገበሬ ውድ ንብረት፣ ለኢትዮጵያ ገበያም የጀርባ አጥንት ናት – ዛሬም ድረስ። አሁን አህያ ታርዶ ለውጭ ገበያ ሊቀርብ ነው መባሉ ብዙዎችን ያስደነገጠውም ለዚህ ነው። የኔ ጥያቄ እነዚህ የሚታረዱ አህዮች ከየት የመጡ ናቸው ? የሚል ነው።

ፈቃድ ተሰጠው የተባለው የቻይና ኩባንያ የአህያው ምንጭ ከየት እንዳደረገው አልተነገረም። ከማረዱ በፊት ማርባቱ ቀድሟል? ወይስ እነዚህ በመቶና በሺዎች የሚቆጠሩት መታረድ የጀመሩት አህዮች ከገበሬው እየተገዙ፣ ከየከተማው እየተለቀሙ ነው? ይህ የቻይና ቄራ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ 300 አህዮች ማረዱም ተነግሯል። እንግዲህ በወር 600 አህዮች ይታረዳሉ ማለት ነው። ዛሬ አንድ አህያ 3ሺ ብር ድረስ ያወጣል ይባላል፣ እነዚህ ቻይናዎች “እኛ በ5ሺ እንገዛለን” ማለት ከጀመሩ የትኛው ገበሬና ነጋዴ አቅም ኖሮት ይፎካከራቸዋል? ነገ ለቻይኖቹ ለመሸጥ ሲባል የአህያ ሥርቆት ቢጧጧፍስ ገበሬውና ነጋዴው በምን አቅሙ ይቋቋመዋል?

ሌላው ደግሞ “የሥጋው ነገር” ነው። አንድ ሰው አህያ ሲያርድ ቢታይ “ለቻይኖች ላቀርብ ነው” ብሎ ሊያመልጥ ይችላል። የአህያ ሥጋ በቦሌም በባሌም ብሎ ሥጋ ቤቶቻችን ውስጥ ብቅ እንደማይል ዋስትናው ምንድነው? የቻይናዎቹን የአህያ ሥጋ ማረጃን በታንክ ልንጠብቀው ነው? የ20ሺ ብር በሬ ከማረድ የ3ሺ ብር አህያ ካሰፈለገም በ9ሺ ብር ሶስቱን ማረድ ሊያዋጣ ይችላል። ይህ ደግሞ “እንጀራን በሰጋቱራና ዱቄት ቅልቅል ተጋገረ፣ በርበሬ ውስጥ ሽክላ ተጨመረ” በሚባልበት አገር አይሆንም የሚባል አይደለም። አንዳንዱ እኮ “ለካ የ አህያን ሥጋ ጅብ ብቻ ሳይሆን ሰውም ይበላል” ብሎ ጓሮው ማረድ ሊጀምርና ምግብ ቤቱ ውስጥ ሊቀላቅልም ይችላል። ለዚህ የተደረገው ጥንቃቄ ምንድነው?

በርግጥ የውጭ ምንዛሪ ለአንድ አገር ዋና ተፈላጊ ነገር ነው። ይህ የአህያ ቄራ ሊያመጣ ይችላል የሚባለው የውጭ ምንዛሪ ስንት እንደሆነ ባላውቅም ለኔ ጥሩ መፍትሄ የሚመስለኝ [ገንዘቡም እንዳይቀርብን – የሞራሉም ነገር እንዳይሰማን – አህዮቻችንም እንዳይመናመኑ] .. ለቻይኖቹ ለብቻ መሬት መስጠትና አህያውንም ራሳቸው እያረቡ፣ ያንንም አገራቸው ወስደው አርደው እንደፈለጉ እንዲያደርጉት ማድረግ ነው – ከዚያ ካለፈም ደግሞ ራሳችን ልዩ የአህያ እርባታ ቦታ ከፍተን የምናረባቸውን አህዮች በመርከብ እየጫንን መላክና በዶላር መሸጥ – እዚያ እነሱ እንደፈለጉ ያድርጉት። ያን ጊዜ ገንዝቡም ይመጣል፣ እዚሁ ምድራችን ላይ ባለማረዳችን ከሞራል ጉዳቱም እንድናለን – የገበሬውም ሆነ የነጋዴው አህያም ባለበት ማንም ሳይነካው ይቀጥላል። የአህያ ሥጋ ባለመታረዱም ሥጋና ምግብ ቤቶቻችንን መፍራት እናቆማለን።

የኔ የደንቆሮ ሃሳብ እንዲህ ነው። አቋም መቀየር ሞት በሆነበት ማህበረሰብ፣ ሁለት ጥግ የያዙ ሃሳቦችን ይዘን ብንፋጭ ምንም መፍትሄ አናመጣም። መቀራረብ ግድ ነው። ሌላ መፍትሄም ካለ ክፍት ሆነን እንየው።

LEAVE A REPLY