ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዞን ዘጠኞች ይግባኝ ጉዳይ ውሳኔ አሳለፈ /በፍቃዱ ዘ ኃይሉ/

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዞን ዘጠኞች ይግባኝ ጉዳይ ውሳኔ አሳለፈ /በፍቃዱ ዘ ኃይሉ/

★ ናትናኤል ፈለቀ እና አጥናፉ ብርሃኔ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 257/ሀ እና ሠ መሠረት “የአመፅ ማነሳሳት” ክስ ይከላከሉ ተብሏል።

★ ሶልያና ሽመልስ እና አቤል ዋበላ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በነጻ እንዲሰናበቱ በወሰነው መሠረት ነጻ እንዲወጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ዛሬ (መጋቢት 28, 2009) ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት፣ ጥር 27/2008 በይግባኝ ባይ ዐቃቤ ሕግ እና መልስ ሰጪዎች ሶልያና ሽመልስ (በሌለችበት)፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፉ ብርሃኔ እና አቤል ዋበላ መካከል ለተደረገው ክርክር ውሳኔ አሳልፏል።

ፍርድ ቤቱ ሶልያና ሽመልስን በተመለከተ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትክክለኛ ነበር በማለት ሲያሰናብታት፣ ዐቃቤ ሕግ ክሱን የሚያስረዳ በቂ ማስረጃ አለማቅረቡን ተናግሯል። ከሶሊያና መኖሪያ ቤት በሌለችበት በተካሔደው ብርበራ ተገኙ የተባሉ ሰነዶች ላይ የፈረሙ የደረጃ ምስክሮች ቀርበው ባለማስረዳታቸው እንዲሁም በወቅቱ ቤቱ ሲበረበር የነበሩት እናቷ ወ/ሮ ይካኑ ሰነዱ ከቤቴ ስላልተገኘ ሰነዱ ላይ አልፈርምም በማለታቸው የመረጃውን ተአማኒነት እንደሚያጎለው ተናግረዋል። በሶሊያና ላይ የቀረበው ቪዲዮውን እንደተመለከቱት የገለጹት ዳኞቹ፤ የግንቦት 7 አመራሮች ያደረጓቸውን ንግግሮች የያዘ ቢሆንም ሶሊያና የሽብር ሥልጠናዎችን ስለመሠልጠኗ እና ስለማመቻቸቷ አያስረዳም ብለዋል። በፍቃዱ ኃይሉን በተመለከተ በስር ፍርድ ቤት በወንጀል አንቀፅ እየተከላከለ ስለሆነ ይግባኝ ማለት የሥነ ስርዓት ሕጉ ስለማይፈቅድ በሚል ከዚህ በፊት ውድቅ ተደርጓል።

3ኛ መልስ ሰጪ ናትናኤል ማዕከላዊ በሰጠው ቃል መሠረት “ከዞን ዘጠኝ ሥያሜ አመጣጥ አንፃር፣ በጽሑፎቹ በመንግሥት እና ተቋማቱ ላይ የተደረገው ዘለፋ፣ በብርበራ የተገኙ ጽሑፎችም በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 ከተደነገገው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ጋር ያለፈ፣ በተከሳሹ የተጻፉት ጽሑፎችም በበጎ አመለካከት ያልተቃኙ፣ በሕግ የተፈረደባቸው ጋዜጠኞችን ነጻ ናቸው እያለ ለማስፈታት በመሞከሩ፣ የጻፋቸው ጽሑፎች እና የወሰዳቸው ሥልጠናዎች የረዥም ግዜ ግዙፍ ያልሆነ ለወንጀል መሰናዳት ስለሚያስረዳ” በሚል ምክንያት የሽብር ክሱ ቢነሳለትም በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 257/ሀ እና ሠ መሠረት መከላከል አለበት የሚል ውሳኔ አሳልፏል።

ናትናኤል ማዕከላዊ ሳለ ተገዶ በሰጠው ቃል “ተፀፅቻለሁ” ማለቱ “ራሱን ለመጥቀም በማሰብ ነው…” በማለት፣ “እንዲሁም ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት ስለማያድን” በሚል ምክንያት ወንጀሉን ያስረዳል የሚል ድምዳሜ ላይ ፍርድ ቤቱ ደርሷል።

4ኛ መልስ ሰጪ አጥናፍ ብርሃኔ “ለናትናኤል በተሰጠው ተመሳሳይ ምክንያት” በሚል በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሰጠው ቃል ላይ በመመሥረት “በፍሪደም ሃውስ፣ ሲቪል ራይት ዲፌንደርስ፣ አርቲክል 19 እና አይሬክስ ከተባሉ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች የወሰዳቸው ሥልጠናዎች ማለትም አመፅ እንዴት ማነሳሳት እንደሚቻል፣ በአመፅ ወቅት ጉዳት የደረሰበት ሰው እንዴት እርዳታ መስጠት እንደሚቻል፣ በአመፅ ወቅት ምን ማድረግ እንደሚገባ እና ሌሎችም የወሰዳቸው ሥልጠናዎች ለወንጀል ድርጊት የረዥም ጊዜ ዝግጅት ማድረጉን ስለሚያስረዳ” የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ግዙፍ ላልሆነ ወንጀል መዘጋጀቱን ያሳያል በሚል በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 257/ሀ እና ሠ መሠረት ይከላከል ተብሏል።

5ኛ መልስ ሰጪ አቤል ዋበላ፣ “ምንም እንኳን የዞን ዘጠኝ አባል መሆኑን ቢያምንም እና የተጠቀሱትን ሥልጠናዎች መውሰዱን ቢያስረዳም፣ ሌሎቹ መልስ ሰጪዎች እንዳሉት ለአመፅ መሰናዳቱን የሚያስረዳ ማስረጃ ስላልቀረበ፣ እንዲሁም በሥልጠናው እንደሌሎቹ “የሚለዋወጣቸውን መልዕክቶች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንዳይደርሱባቸው የሚያደርግ ሥልጠና መሆኑን ስለማያስረዳ” በሚል የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን ተቀብለን በነጻ አሰናብተነዋል” ብለዋል።

በጥቅሉ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸው እና ወንጀሉን ያስረዳሉ የተባለው መልስ ሰጪዎቹ በማዕከላዊ የሰጡት ቃል ነው። ሶልያና በሌለችበት በመከሰሷ ቃል አልነበረባትም፣ አቤልም ለመስማት ችግር እስኪጋለጥ ድረስ ተደብድቦ “እኔ ያልኩት ላይ ካልሆነ አልፈርምም” በሚል በፊርማው ራሱን እንዳልወነጀለ ከዚህ በፊት በዞን ዘጠኝ ተገልጾ ነበር።

LEAVE A REPLY