በኢትዮጵያ የመንግሥት ተጠያቂነት እስክ ምን ድረስ ነው /ከሀ. ህሩይ/

በኢትዮጵያ የመንግሥት ተጠያቂነት እስክ ምን ድረስ ነው /ከሀ. ህሩይ/

የኢትዮጵያ ህገ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ዝርዝር ህጎች በሀገሪቷ የሚወጡት ህግ እና ሥርዓት በሀገሪቱ ለማስፈን እና መንግሥትም ሆነ እያንዳንዱ ዜጋ በተገቢው መንገድ በኃላፊነት እንዲጠየቁበት ነው። ነገር ግን በሀገራችን እየታየ ያለው በህግ ተጠያቂ ናቸው ተብለው የሚከሰሱ፣ የሚታሰሩ እና የሚቀጡ ዜጎች ብቻ ሲሆኑ በተለይ ደግሞ ለኢህአዴግ አገዛዝ ያልተመቹት ናቸው።

የኢትዮጵያን ህጎች እና ህገ መንግሥቱ ለህዝብ ማስፈራሪያነት የታወጁ እስኪመስሉ ድረስ የኢህአዴግ ብቸኛ የመጨቆንኛ መሣሪያ ከሆኑ ሰንብተዋል። ድሮ ወላጆቻችን ሲያስፈራሩን ” ዋ! አያ ጅቦ ይበላሃል” ይሉን እንደነበር እሁንም የኢህአዴግ መንግሥት ዜጎች መብታቸውን በጠየቁ ቁጥር “ዋ! ህገ መንግሥቱ ይበላሀል” በሚል ዐይነት ህገ መንግሥታዊ ሥርዕቱን ለመጣስ አሲረዋል…. በማለት ዜጎችን በሀሰት እየወነጀለ የሚያስርበት አይነተኛ መሣሪያው አርጎታል።

ከዚህ ቀደም መንግሥት በሙስና ወንጀል የከሰሳቸው የራሱ ባለስልጣናትም ቢሆኑ የተከስሱት ለአህአዴግ በተለይም ለህዋሀት ስላልተመቹ እንጂ ለህዝብ እና ለሀገር ታስቦ እይደለም።

እንግዲህ ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት እንዲሁም በሙስና የተዘፈቁት ባለስልጣናቱ በ26 ዓመታት የሥልጣን ጌዜ በሀገሪቷ እና ብህዝቡ ላይ የፈፀሙአቸው እጅግ ብዙ ውንጀሎች እያሉ አንድም ጊዜ በእውነተኛ ሀገራዊ ተቆርቋሪነት ለፈፅሙት ወንጀልም ይሁን ጥፋት በህግ ሲጠየቁ እልታየም። ምክንያቱም ነፃ የፍትህ ሥርዓት እና እውነተኛ የህዝብ ተውካይ በፓርላማው ውስጥ ስለሌለ ነው።

የኢትዮጵያ ፓርላማ በመንግሥት የቀረበለትን እጨብጭቦ ከመቀበል እና ከማፅደቅ ውጭ የሚፈይደ አንድም ነገር የለም። እውነተኛ የህዝብ ተወካዮች ያሉበት ፓርላማ ቢኖር ኖሮ: (ዜጎች አላግባብ ሲታሰሩ፣ ከመኖሪያ ቦታቸው ሲፈናቀሉ፤ የሀገር ዳር ድንበር ተደፍሮ ዜጎች ታፍነው ሲወሰዱ፤ የሀገሪቷ ለም መሬት እየተቆረሰ ለውጭ ባለሀብት ሲሰጥ፣ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲጣሱ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሙስና ሲዘፈቁ እና በሥልጣናቸው ከህግ በላይ ሆነው ሲባልጉ፤ በመንግሥት ቸልተኝነት ዜጎች ላይ አደጋ እየደረሰ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሞት ሲያልቁ……. ) ምንም እንኳ ፓርላማው በኢህአዴግ አባላት ቢሞላም እንደ ህዝብ ተወካይነታቸው ከላይ የተዘረዘሩትን እና ሌሎች በርካታ ሀገራዊ ጥያቄዎችን በማንሳት እልባት መስጠት ይገባቸው ነበር።

ነገር ግን የፓርላማ አባላቱ ከሀገር እና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የህዋሀትን ቃል ኪዳን የሚያስቀድሙ፣ ለህዝብ ህልውና ሳይሆን ለፓርቲ ህልውና የቆሙ ናቸው። የሀገሪቷ ዓቃቤ ህግም ሆነ ፍርድ ቤቶች በህግ መመራት ከተዉ ውለው አድረዋል። ተጠያቂነት ቢኖር ኖሮ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በቆሼ አካባቢ በደረሰው አደጋ ምክንያት ብዙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብተከሰሱ ነበር። ነገር ግን የተደረገው የተገላቢጦ ሆኖ እራሱ ሊጠየቅ የሚገባው አካል የአደጋውን መንስኤ እንዲያጣራ ተደርጎአል።

ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ወይም ባለሥልጣኖቹ በህግ ይጠየቃሉ ማለት ዘበት ስለሆነ ብቸኛው መፍትሄ ልዩነትን አጥብቦ በእንድነት ይህንን የተበላሸ ሥርዓት ለመለወጥ መታገል እንጂ በዘርና በጎሳ መከፋፈሉ አይጠቅምም።
በቸር ይግጠመን

/ሚያዝያ 2017 ቶሮንቶ – ካናዳ/

LEAVE A REPLY