ሰላምና ጤና አብዝቶ ይስጣችሁ!
በቅድሚያ ይህን አስተያየት የምሰጠው የቴዲ አፍሮ ቲፎዞ ሆኜ እንዳልሆነ ያዙልኝ። በእርግጥ ከቴዲ አፍሮ ዘፈኖች ሁሉንም ባይሆን ጥቂት የማይባሉትን እወዳቸዋለሁ። ለኔ ከዘፈኑ ይልቅ አርቲስቱ ለህዝቡ ባለው ክብርና ለሃገሩ ባለው ፍቅር ላይ መሰረት ያደረገው ድንቅ ስብዕናው ከሙያ ብቃቱ በላይ ግዝፈት አለው። የአስተያየቴም ዙሪያ ይኽው ነው።መነሻዬ ደግሞ ባለፈው እሁድ በጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ርዕዮት ፕሮግራም የተደረገው ውይይት ነው። ወደ ውስጥ ዘለቅኩ፦
የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ለፋሲካ ይወጣል የሚል ማስታወቂያ ከተለቀቀበት ቅጽበት ጀምሮ በአርቲስቱና በስራዎቹ ላይ የተቀሰቀሰው አቧራ አሁንም ድረስ ጋብ ያለ አይመስልም።ፖስተሩ ይህን …ይህን…አላካተተም! ፋሲካ ለቴዲ ምኑ ነው…? በሚሉ ውኃ የማይቋጥሩ ወቀሳዎች ቅድመ ፋሲካ የጀመረው ግርግር ድህረ ፋሲካም ቀጥሏል።
በዚህ ጽሁፍ ማተኮር የፈለኩት ግን በተለይ “ኢትዮጵያ” የሚለው አልበሙ መጠሪያ የሆነው ክሊፕ ለህዝብ ጆሮ ከበቃ 48 ሰአት ሳይሞላው ለግምገማ በተጣደፈው በርዕዮት የቅርብ ዝግጅት ላይ ነው።
ከሶስት ሳዕታት በላይ የዘለቀውን የርዕዮት የቀጥታ ስርጭት አብዛኛውን ክፍለ ግዜ የወሰደው በቴዲ አፍሮ አዲስ ክሊፕ ላይ የተደረገው ውይይት ነው።
ይህ ውይይት፦ ዋና ተወያዮቹ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬና ባልደረባው ዳኝነት ከወትሮው በተለየ ከምክንያት ይልቅ ለስሜት ቅድሚያ ሲሰጡ ያስተዋልኩበት ውይይት ነበር ።
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬን መከታተል የጀመርኩት በቅርቡ ቢሆንም እስካሁን ባደመጥኳቸው ፕሮግራሞቹ ሙያዊ ብቃቱን አስተውያለሁ። በያንዳንዱ ዝግጅት ላይ የቤት ስራውን አጠናቆ ሰርቶ እንደሚመጣ ከእንግዶቹ ጋር የሚያነሳቸው ሃሳቦች ብስለትና ሞጋችነት መረዳት ከባድ አልሆነብኝም፡፡ በተለይ እንግዶቹ ለሚናገሯቸው የእንግሊዘኛ ቃሎች የአማርኛ አቻቸውን ለመፈለግ የሚያደርገው ጥረት በግልም ቢሆን የሚያስመሰግነው ነው። ባጠቃላይ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ከእድሜውም አኳያ ገና ብዙ ሊሰራ የሚችል፤ ጥሩ አቅም ያለው ጋዜጠኛ ስለመሆኑ መመስከር እችላለሁ። ይህን በዚህ ላብቃና ወደ ተነሳሁበት የቅርብ ዝግጅቱ ይዘት ልመለስ።
(በነገራችን ላይ የሁለቱም ስም ቴዎድሮስ በመሆኑ አንባቢን እንዳያምታታ ቴዎድሮስ ጸጋዬን ሙያውን ከስሙ እያስቀደምኩ ጋዜጠኛው በሚል እጠቅሰዋለሁ)
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት (የቴዲ አዲስ አልበም ፖስተር በወጣ ሰሞን ይመስለኛል) በዚሁ ፖስተር ዙሪያ በተነሳ ውይይት ላይ ፦ ቴዲ አፍሮ ታሪክ ሰርተው ባለፉ ሰዎችና በጉልህ ታሪካዊ ክስተቶች ዙሪያ ከማቀንቀን ባለፈ ኢትዮጵያን እንደ ሃሳብ ዘፍኖ አያውቅም። ይህን ማድረግ ይጠበቅበታል! ይህን የማድረግም ብቃት አለው ፡፡ የሚል አስተያየት መሰንዘሩን አስታውሳለሁ። (ቃል በቃል አይደለም)
በግዜው አስተያየቱ የቀረበበት መንገድና አገላለጹ ብዙም ባይጠመኝም ( ቴዲ አፍሮ ታዋቂነትን ያገኘው ታሪክ ሰርተው ባልፉ ሰዎች ትከሻ ላይ ነው አይነት ድምጸት ስለነበረው) ለጋዜጠኛው ካለኝ ጥሩ አመለካከት አኳያ አስተያየቱንም በቀና ተቀብዬ ለማለፍ አልተቸገርኩም።
በሌላ በኩል ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ይህን አስተያየቱን የሰጠው የቴዲ ፖስተር ከመውጣቱ በፊት ቢሆን ኖሮ የጋዜጠኛውን አስተያየት እንደ ምክር ወስደን፤ኢትዮጵያ የሚለውን ዘፈን ስንሰማ ደግሞ፤ የጋዜጠኛው ምክር መሬት አልወደቀችም! በማለት አድናቆት በቸርነው ነበር። ነገር ግን ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ይህን አስተያየት የሰጠው “ኢትዮጵያ” የሚለው ፖስተር ከተለቀቀ በኋላ በመሆኑ አስተያየቱን እንደ ምክር መቀበል ያስቸግራል። ምክንያቱም የአልበሙ መጠሪያ ኢትዮጵያ የሚል ከሆነ “ኢትዮጵያ” የሚል ስራም እንደሚካተትበት መገመት ከባድ አደለምና ነው።
ከዚህ ተነስተን አሰብ ስናደርግ ደግሞ ሊታየን ግድ የሚለው፡ የጋዜጠኛውን አስተያየት የወለደው የቴዲ ፖስተር መሆኑ ነው።ስለዚህ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ የሰነዘረው አስተያየት “ምክር” የሚለውን ዋጋ ሊያገኝ አይችልም ማለት ነው።
የቴዲ አፍሮ ዘፈን በወጣበት ዕለት ጋዜጠኛው በፌስ ቡክ ገጹ ኢትዮጲያን እንደ ሀሳብ መዝፈን ማለት ይህ ነው! ቴዎድሮስ ካሳሁን በአዲሱ አልበሙ ላይ ኢትዮጲያን ከየትኛውም ቀድሞ ከሚታወቅ ግለሰብ ጋር ሳያዛምድ፣ ቀድሞ ከገነነ ልዩ ክስተት ጋር ሳያገናኝ እንደ ጽንሰ ሀሳብ ቢዘፍናት እወዳለሁ ብዬ ነበር፡፡ እነሆ ኢትዮጲያ የተሰኘውን ዘፈን አደመጥኩ፡፡ እናም፣ የሻትኩትን አገኘሁ፡፡”
የሚለውን ቀና አስተያየት ካስነበበን በኋላ እሱን ተከትሎ በርዕዮት ገጹ ላይ ባደረጉት ውይይት በጽሁፍ የገለጸውን የአድናቆት አስተያየት እንደ መግቢያ መጀመሪያ ላይና እንደ አዝማች በየመሃሉ “ኢትዮጵያን እንደ ሃሳብ መዝፈኑ አስደስቶኛል” በሚል እየጠቀሱ፤ ባብዛኛው ግን እየተቀባበሉ የጭቃ ጅራፋቸውን ማስከተላቸው እጅግ በጣም አስገርሞኛል፡፡ አሳዝኖኛል። አግራሞቴና ሃዘኔ ደግሞ ተባብረው እንሆ ይህን ጽሁፍ ወልደዋል።
ወደ ውይይቱ ጭብጥ ልዝለቅ፦
የትችቱ መነሻ ኢትዮጵያ የሚለው ክሊፕ ዜማ ነው። የተለያዩ 3 እና 4 ዜማዎችን ገጣጥሞ ተጠቅሟል፤ ቀድሞ የተጠቀመበትን የመግቢያ ስታይል በድጋሚ ተጥቅሟል እና የመሳሰሉት ትችቶች ተሰንዝረዋል። የሙዚቃ ባለሙያ ስላልሆንኩ በዚህ ላይ ምንም ማለት አልችልም፡፤ እንደ ግለሰብ ግን 4 ሆነ 8 ዜማ ይገጣጠም ክሊፑን ወድጄዋለሁ።
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስና ባልደረባው ዳኝነት አንዴ ጥላሁን ገሰሰን አንዴ ጂጂን እያነሱ የቴዲን ክሊፕ በራሳቸው መንገድ እያወዳደሩ ብዙ ብዙ አሉ። ይህም የግል አስተያየታቸው ስለሆነ መብታቸው ነው።
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስን የምሞግተው ግን በዚህ አስተያየቱ አይደለም።
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስን የምሞግተው፦ ደረጃውን ያልጠበቀ ዜማ መጠቀሙ (በባንድ ባለመጠቀሙ)፤ ቴዲ አፍሮ የሚወደውንና ያሚያደንቀውን በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አላከበረም ወደሚል ከቁንጽል ነገር ተነስቶ ግዙፍ ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ነው፡፤ አንድነት ናፋቂውን ኢትዮጵያዊ የሚያከብር ከሆነ ሳውንድ ኢንጅነር ሳይቀር የተካተተበት ስራ መስራት ይጠበቅበታል በሚለው መመሪያ መሰል አስተያየቱ ነው ልሞግተው የምሻው።
ለመሆኑ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ሆይ! ስለ ህዝብ ሆነህ የመናገር መብት ማን ሰጠህ ? እሺ ይሁን ስለ ህዝብ ሆነህ ተናገር፤ እንዴት ነው ዘፈኑ ከወጣ 48 ሰዓታት እንኳ ሳይሞላው የቴዲን አድናቂ ህዝብ ስሜት ገምግመህ ቴዲ ህዝብን አለማክበሩን አፈ-ህዝብ ሆነ መናገር የቻልከው? ችኩልነት አይደለምን? ደግሞስ ከአንድ ክሊፕ ዜማ ላይ ብቻ ተነስቶ እንዲህ አይነት ድምዳሜ ላይ መድረስስ ትክክል ነውን?
የአርቲስቱ አድናቂ ህዝብ ሙዚቃውንም ወደነዋል! አርቲስቱንም እናከብረዋለን እያለ በኮሜንት ሳጥናችሁ ላይ እየተቃወማችሁ እያያችሁ ይህን ማለታችሁ፤ አይ እናንተ ብታከብሩትም እሱ አላከበራችሁም እያላችሁ መሆኑ ገብቷኋል? ይህ ማለት ደግሞ እኛ እናውቅልሃለን ማለት አይደለምን?
በመረጃና በማስረጃ ያልተመሰረቱ ድምዳሜዎችና ኢ-ምክንያታዊ የሆኑ ሃሳቦች ሲያጋጥሙት በጥያቄ ናዳ ሲፈትንና ሲሞግት የማውቀው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ፤ ከቁንጽል ነገር ላይ ተነስቶ እንዲህ አይነት ግዙፍ ድምዳሜ ላይ መድረሱ፡ በጣም በጣም አስገርሞኛል።
ከዚህ በመነሳት ለጋዜጠኛ ቴዎድሮስም ሆነ ለባልደረባው ላስተላልፍ የምሻው ሌላው መልዕክት፦
እናንተ እያላችሁ ያላችሁት፦ ቴዲ አፍሮ እኛ ስለ ሙዚቃ ባለን እውቀትና ችሎታ ልክ አልዘፈነም ነው። እየነገራችሁን ያላችሁት እኛ ድንቅ በምንላቸው ስራዎች ልክ አላቀነቀነም ነው። ስለዚህ አናደንቀውም ነው ያላችሁን ። ይህ አንጡራ መብታችሁ ነው። አንዱና ትልቁ ስህተታችሁ የሚነሳው ህዝብን የሚያከብር ከሆነ እኛ ባልነውና በኛ ዕውቀት ልክ መስራት አለበት ከማለታችሁ ላይ ነው። ይህን ክላደረገ አድናቂውን አላከበረም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳችሁ ነው።
ሁለተኛው ስህተታችሁ ደግሞ፦ ዘፈኑን የሚወድለት በሚሊዮን የሚቆጠረው ህዝብም በናንተ የሙዚቃ እውቀት ልክ እንዲመለከተው/እንዲገመግመው መጠበቃችሁ ነው። የህዝብ ዋና መለኪያው የዜማ ቅንብር አለመሆኑን ካለማስተዋላችሁ ላይ ነው። በዚህ አጋጣሚ በእንግድነት የተሳተፈው ሃብታሙ ስዩም ህዝብ ለቴዲ ያለው ፍቅር አርቲስቱ ለህዝብ ድምጽ በመሆኑ ከተቀበለው ፈተናም ጭምር የሚመነጭ መሆኑን በማሳየት በቴዲ አድናቂዎች ላይ አትፍረዱ ሲል በመጠኑም ቢሆን እየሄዳችሁበት ያለው መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ሊያሣያችሁ መሞከሩን ሳላደንቅ አላልፍም።
ህዝብን ያላከበረው ማነው? ቴዲ ወይስ እናንተ?
በተለይ ዳኝነት የተባለው ተወያይ የቴዲን አድናቂዎች “አምላኪዎች” በሚል የጠራበት ቃል በራሱ ጸያፍና ህዝብን ካለማክበር የሚመነጭ ነው።
ዳኝነት የቴዲን አድናቂዎች “አምላኪዎች” ብሎ የመጥራትን ያህል ድፍረት ካለው ደግሞ “አምላካቸው” በመነካቱ የተቆጡት የቴዲ አድናቂዎች ያወረዱበትንም የስድብ ናዳ በጸጋ የመቀበል ትዕግስትም ሊኖረው በተገባ ነበር፡፤ የሆነው ግን ይህ አይደለም። እሱ የቴዲ አምላኪዎች ብሎ የዘለፋቸው አስተያየት ሰጭዎች ግብረ-መልስ እንደ ሳማ እንዳንገበገበው ነው ያስተዋልኩት።
የምንናገረው ቃልም ሆነ ቃሉ የሚያዝለው ሃሳብ የሚያስከትለውን መዘዝ ለመቋቋም ካልቻልን አፋችንን ሸበብ ቃላችንንም ከርከም ማድረግ አለብን ለማለት ያህል እንጂ ቴዲ አፍሮን የሚያደንቁ፤ ከፍ ካለም የሚያፈቅሩ እንጂ የሚያመልኩ ሰዎች ሊኖሩ እንደማይቹሉ ይጠፋችኋል ብዬ አይደለም። ፍቅር ያሸንፋል የሚለው ቃለ-መርህ በራሱ ብዙ አፍቃሪ ሰራዊት አፍርቶለታል።
የቴዲ አፍሮ ተወዳጅነት መሰረቱ ምንድነው?
ቴዲ አፍሮ በሙያ ረገድ ድምጻዊ ዘፋኝ ነው፡፡ እድሜው 40 ስለተጠጋ የአዲሱ ትውልድ አንጋፋ ድምጻዊ ልንለው እንችል ይሆናል። የሆነው ሆኖ ከድምጻዊነቱ በተጓዳኝ ጥሩ የግጥም ችሎታ እንዳለው አስመስክሯል። የራሱን ዘፈኖች ዜማ የሚደርሰው እራሱ መሆኑም ሌላው ድርብ ችሎታው ነው። ባጠቃላይ ድምጻዊ ለመሆን የግድ ከሚለው የተፈጥሮ ጸጋ(ድምጽ) በተጨማሪ ሌሎችም ችሎታዎችን የታደለ ብቁ አርቲስት ነው። ይህ ዕውነት እንደተጠበቀ ሆኖ፡ በዚህም ሆነ በቀዳሚው ትውልድ በድምጽ ቃላጼም ሆነ በዜማ ቅመራ ከቴዲ አፍሮ የሚበልጡ በርካታ ድምጻዊያንና ሙያተኞች እንዳሉም እውነት ነው። ይሁንና በተለይ በዚህ ትውልድ የሱን ያህል የህዝብ ፍቅር ያለው ድምጻዊ ያለ አይመስለኝም።
ይህ የሚነግረን ደግሞ የቴዲ ተወዳጅነት መሰረቱ የድምጹ ቅላጼ፤ የግጥሙ ይዘት አልያም የዜማ ቅመራ ችሎታው ብቻ እንዳልሆነ ነው።
እንደ እኔ አመለካከት የቴዲ ተወዳጅነት ዋና መሰረት ድንቅ ስብዕናው ነው። ሙያውን ከህዝብ ፍላጎትና የልብ ትርታ ጋር አጣጥሞ ለመሄድ መትጋቱ ነው!፤ የህዝብን ስሜት በሙዚቃው ለማንጸባረቅ መሻቱ ነው!፤ ይህን ማድረጉ ደግሞ ያስከተለበትን/ሊያስከትልበት የሚችለውን ፈተና በጸጋ የመቀበል ጽናቱ ነው። ባጠቃላይ የቴዲ ተወዳጅነት የተገነባው በሙያዊ ብቃቱ ብቻ ሳይሆን ከወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ በተጓዘባቸው መንገዶች ሁሉ ባሳየው ድንቅ ስብእና ጭምር ነው።
ቴዲ በሙያው ስለ ህዝብ ኡ!ኡ! ብሏል፤ ስለ ሃገር አልቅሷል። ይህን ማድረጉ ደግሞ ዋጋ አስከፍሎታል። ህዝብ ደግሞ በአጸፋው ለአርቲስቱ ያለውን ክብር በተለያዩ መንገዶች ገልጿል፤ እየገለጸም ነው።
የኮፒ ራይት ችግር አርቲስቶቻችን የልፋታቸውን እንዳያገኙ አድርጎ ፤ እንደ ሱቅ በደረቴ ስራቸውን አዙረው ለመሸጥ በተገደዱበት በዚህ አስቸጋሪ የዲጂታል ዘመን ፤ የቴዲ አፍሮ ሥራ በኢትዮጵያ የአልበም ሽያጭ ታሪክ ተሰምቶ የማያውቅ ባለ 7 አሃዝ ዋጋ ማውጣቱ በራሱ ህዝብ ለአርቲስቱ የሰጠው ክብር መገለጫ ነው። ይህን ስል ግዝፈቱ ለማሳየት እንጂ ሌሎቹን አርቲስቶቻችንን ህዝብ አያከብራቸውም ማለቴ እንዳልሆነ አይጠፋችሁም።
በህዝብ ለመወደድ ህዝብ የሚወደውን ነገር መሥራት ግድ ነው። ህዝብ የሚወደውን ነገር መስራት ደግሞ ድንቅ ስብዕና ነው። ድንቅ ስብዕና በራሱ ለተወዳጅነት ያበቃል። ስብዕና የሌለው ሙያዊ ብቃት ግን ብቻውን ተወዳጅ አያደርግም።ድንቅ ስብዕናና ሙያዊ ብቃት ሲጣመሩ ደግሞ የተወዳጅነቱ እርከን ከፍ ይላል ፤ አድማሱም ይሰፋል፤ መሰረቱም ይጠብቃል። በድምጽ ቅላጼም ሆነ በዜማ ቅመራ ችሎታቸው ከቴዲ የሚበልጡ ሙያተኞች የቴዲን ያህል ተወዳጅ ያልሆኑበት ምክንያትም ይኽው ነው።
በበቀደሙ የርዕዮት ዝግጅት ላይ ያልተጤነው ጉዳይ ይኸው ይመስለኛል። ተወያዮቹ በቴዲ አንድ ዘፈን ዜማ ላይ ብቻ ተመስርተው በችኮላ የሰጡት በጣም የጮኽ አስተያየት ቴዲ በድንቅ ስብዕናው ሲሚንቶነት ከገንባው የተወዳጅነት ግንብ ጋር አላትሟቸዋል።
ይህን ስል ቴዲ በህዝብ ተወዳጅ መሆኑ አይነኬ ያደርገዋል የሚል ጭፍን አመለካከት ይዤ አይደለም። በጭራሽ! በሙዚቃው ሙያ ከሱ የተሻለ እውቀትና ችሎታ ያላቸው ሙያተኞች ቢተቹትና ቢመክሩት ምንም ክፋት የለውም።እሱም ቢሆን የሚጠላው አይመስለኝም። ነገር ግን ገና ሙዚቃውን አጣጥመን ሳንሰማው፤ ለዚያውም ለአርቲስቱ ተወዳጅነት ዋና ምክንያት ባልሆነው በአንድ ዘፈኑ ዜማ አቀማመር ላይ ብቻ ተመርኩዞ ይህን መሰል የቅብብሎሽ ውርጅብኝ አግባብ አይመስለኝም ነው የምለው። አይመስለኝም ብቻ ሳይሆን አግባብ አይደለም። ገና አንድ ዘፈኑ በወጣ ማግስት በዜማው ላይ ያቀረባችሁትን ይህን ትችት ትንሽ ታግሳችሁ ቢያንስ ቢያንስ ሙሉው አልበም ከወጣና ህዝብም ከሰማው በኋላ ከጥላሁንም ሆነ ከጂጂ ጋር ሳይሆን ከራሱ ቀዳሚ አልበም ጋር እያነጻጸራችሁ ፤ ቴዲ ተሻሽሏል ወይስ አልተሻሻለም በሚል ብታቀርቡት ኖሮ ይህን ያህል ቁጣም ባላስከተለ ነበር። ትችታችሁን በቀናነት ለመመልከት ባልተቸገርን ነበር።
ሌላው ያስገርመኝ ነገር ደግሞ በውይይቱ ወቅት፡ ከኛ ይልቅ ቴዲ እንዳይሻሻል ወይም እንዳያድግ የሚፈልጉት በቴዲ አፍሮ ሥራ ላይ ትችት ለምን ቀረበ? ብለው የሚቆጡት ናቸው። የሚል አስተያየት በጋዜጠኛ ቴዎድሮስም ሆነ በባልደረባው በኩል በተደጋጋሚ ሲገለጥ ማድመጤ ነው።
በተለይ ዳኝነት የሚባለው ተወያይ ከዚህም ዘለል አድርጎ ቴዲ ራሱ በሚዲያ ቀርቦ እንኳን ተቹኝ፤ መተቸቴ ትክክል ነው ብሎ ሊመስክርልን ይገባል ብሎ ሲመጻደቅም አድምጫለሁ። ለመሆኑ ዳኝነት የአድማጩን የግንዛቤ መጠን ምን አድርጎ ቢገምት ነው? ራሱንስ ማን አድርጎ ተመልክቶ ነው ይህን አይነት ግብዝ አስተያየት የሰነዘረው የሚሉ ጥያቄዎች ሳያጭርብኝ አልቀረም።
መቋጫ፦ እንደ ምክር ለርዕዮት ዝግጅት ክፍል፦
የፈለጉትን የመናገርና የመጻፍን ፍቃድ በሚቸረው የማህበራዊ ሚዲያ ላይ በአወያይነት የሚሳተፍ ሰው ቆዳው ጠንካራ ሊሆን እንደሚገባው በተለይ ዳኝነት የተረዳው አይመስልም። በአድማጮች የሚጻፉ አስተያየቶችን እያነበበ እልህ ተጋብቶ አብዛኛውን ሰአት እንደ ክፉ ጎርቤት ሲነዛነዝ መዋሉ የፕሮግራሙን ይዘት አጠልሽቶታል። ይህ ለወደፊቱ መሻሻል ያለበት ይመስለኛል። አልፎ አልፎ አላሳፈላጊ ጉዳዮች በፌዝ መልክ ሲገለጹ ይስተዋላልና ይህም ቢታረም መልካም ነው። በተረፈ አገልግሎታችሁ የህዝብን የልብ ትርታ ያደመጠ ይሆን ዘንድ እግዚአብሄር ይርዳችሁ! በማለት የዛሬውን ጽሁፍ ስቋጭ አስተያይቴን በቀናነት እንደምታዩት ተስፋ በማድረግ ነው።
አዜብ ጌታቸው!