‘ኢትዮጵያዊ ርስበርስ መባላቱን፥ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሊቀይር ይችላልን?’ /በፍቃዱ ዘ. ኅይሉ/

‘ኢትዮጵያዊ ርስበርስ መባላቱን፥ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሊቀይር ይችላልን?’ /በፍቃዱ ዘ. ኅይሉ/

ትላንት
ነብይ ባገሩ አይከበርም
ዛሬ
ነብይ ባገሩ አይኖርም
ነገ
ነብይ ባገሩ አይፈጠርም
(በዕውቀቱ ሥዩም)

ፌስቡክ የትውልዳችን ማንነት ገመና ገላጭ ነው። የመግቢያዬ ግጥም ገጣሚ፣ በትውልድ ፈርጥነቱ ሊወደስ ሲገባው፥ የሚናገረውን እንኳ በማያውቅ መደዴ ሲዘለፍ መዋል የጀመረው ፌስቡክ ላይ ከወጣ ወዲህ ነው። ነገሩ የኛ ትውልድ፣ የፌስቡክ መንደር ድክመት ብቻ ነው ብዬ ባምንና ባልፈው ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን እንደጨጓራ ራሱን የበላው ‘ያ ትውልድ’ም፣ የ‘ያ ትውልድ’ አሳዳጊም፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያው ሆኖ መሰለኝና ብዕሬን ለቁዘማ መዘዝኩ።

አሁን ኢትዮጵያ ‘ፈላስፋ’ ነበራት ለማለት የምናጣቅሰው፣ ፈረንጆቹ “ኢትዮጵያዊ አይደለም” ሲሉ ‘ዘራፍ’ ብለን የምንሟገትለት ዘርዐ ያዕቆብ፣ በሐሳቡ ምክንያት ከትውልድ አገሩ አኵሱም ተሰዷል፣ ለማኝ ሆኖ ዋሻ ውስጥ ኖሯል፣ ጎንደር ዘልቆ ራሱን ቀይሮ ዕድሜውን ለመጨረስ ተገዷል። እርግጥ ነው ይህ መልካም ሰው የማሳደድ አባዜ የዓለም አባዜ ነበር። ይሁን እንጂ አባዜው ዛሬ ለቀሪው ዓለም ‘ነበር’ ሲሆን ለኛ ግን ‘ነው’ ሆኖ ዘልቋል። የግሪኩ ሶቅራጠስ፣ አፍላጦንን፣ አፍላጦን አሪስጣጣሊስን… እየተኩ ሲያልፉ የእኛዎቹ ዘርዐ ያዕቆብ እና ወራሹ ወልደ ሕይወት በወላድ አገር ምትክ አጥተው መካን ሆነው ቆመዋል። ከዓለም በከፋ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ሐሳብ ይዞ መምጣት በንጉሡም፣ በጳጳሱም፣ በምዕመኑም ያስቀጣል(ነበር)። ልዩነቱ ይኼ ነው።

በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጊዜ ለንጉሥ አንሰግድም ያሉት አባ እስጢፋኖስ እና ደቂቆቻቸው ዕጣ ፈንታ መስዋዕትነት ነበር። በየዘመኑ የተለዩትን፣ የተሻሉትን ስንገድል ነው የኖርነው። እንደካሮት ቁልቁል የማደጋችንም ምሥጢር ይኸው ይመስለኛል። ዐፄ ዮሓንስ ፬ኛ በሐሳብ ልዕልና እንደሚያምን ሰው ታሪካዊውን የቦሩ ሜዳ የሊቃውንት ሙግት ካሰናዱ በኋላ አሸናፊውን ራሳቸው ቀድመው የሚደግፉትን ቡድን አድርገው ሲያበቁ፣ ፍርዳቸው የተቃወመውን ሁሉ ምላሱን እዚያው አስቆርጠዋል።

ሊቃውንቱም ርስበርሳቸው እንደተባሉ እና እርስበርስ እንደተጠላለፉ ነው የኖሩት – አንዱ አንዱን እየናቀ፣ እየጠላ፣ እያጣጣለ፣ እየስጣለ እዚህ ደርሰናል። ዋዘኛው አለቃ ገብረሐና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ አሁን ‘ተክሌ አቋቋም’ የሚባለውን ያሬዳዊ ዜማ ማጀቢያ ውዝዋዜ ቢፈጥሩም ያገራቸው ሰዎች (ጎንደሬዎች) አልቀበል ቢሏቸው፣ ልጃቸው ተክሌን በድብቅ አስተምረው ትግራይ ቢልኩት፣ ለነርሱ የባዕድ ትምህርት ሆነና ተቀብለውት፣ ዳግም ወደ ግርጌ ተስፋፍቶ ይኸው ዛሬ ‘ተክሌ አቋቋም’ ተብሎ በየቤተ ክርስቲያኑ ሽብሻቦ እናየዋለን። ምን ይሄ ብቻ?! የኢትዮጵያን ታሪክ በ1900ዎቹ ከመጀመሪያ ተነስተው ለመጻፍ የሞከሩት ጎጃሜ አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ “የያሬድ ጥበብ ብዙ ሰው አቦዘነ” ብለው ያስገርሙናል። “የያሬድ ዜማ ከተጀመረ ወዲህ በኢትዮጵያ ትምህርት ጠፋ። የኢትዮጵያ ሊቃውንት ሕፃናቱም ኑሯቸውን ብቻ በዜማና በቅኔ አርገውት ይኖራሉ” ብለው ትልቁን ውለታ እንደዋዛ ያራክሱታል። ነገሩ ተራ ትችት አይደለም። ከራስ ያልፈለቀን የማናናቅ ኢትዮጵያዊ አባዜ ነው ለማለት እደፍራለሁ።

አባዜው እስከትላንት ዘልቆ፥ ‘ያ ትውልድ’ መክኖ እንዲቀር ሆኗል። ደርግ፣ መኢሶን፣ ኢሕአፓ… የአንድ ርዕዮተ ዓለም ተከታዮች በእኔ እቀድም፣ እኔ እቀድም ተባልተው አልቀዋል። መባላቱ እንደሽንኩርት ልጣጭ ስር የሰደደ ነው። ቀድመው አንድ ወገን የነበሩት መኢሶንና ደርግ ቆይተው ርስበርስ ተባሉ። የኢሕአፓ አባላትም የተለየ ሐሳብ ይዘው የመጡትን የገዛ አባላቱን ‘አንጃ’ ብለው በመፈረጅ ርስበርስ ተባሉ። ሕይወት ተፈራ “ማማ በሰማይ ላይ” በተሰኘው ማስታወሻዋ “በፓርቲ ውስጥ የአንጃዎች ጥላቻ ከደርግ ጥላቻ በለጠ” ትለናለች። በዛ ክፉ ዘመን ለሽብር ቀለም እያወጡ ሲገዳደሉ፣ ከድቶ ገራፊ የሆነው ጓድ፣ የቀድሞ የትግል አጋሮቹን የሚገርፈው የደርጎቹ ደቀ መዛሙርት ከሚጨክኑት በከፋ እንደነበር ይነገራል።

ዛሬም ነገሩ ያው ነው። የተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስበርስ እና አንዳንዴም የአንድ ፓርቲ ፍሬዎች አንዱ ለሌላው ያላቸው ጥላቻ እንታገለዋለን የሚሉትን አካል ወይም ድርጊት ከሚጠሉት ይከፋል። ለርስበርስ መጠላለፍ የሚያባክኑት ጉልበትና ዕውቀትም ዓላማቸው ምን እንደሆነ ግራ ያጋባል። ለነጻነት፣ ዴሞክራሲና ዕኩልነት እታገላለሁ የሚለው የፌስቡክ ማኅበረሰብ፣ ለትግሉ ካለው ታማኝነት ይልቅ ያጠፋ/የተሳሳተ/የተለየ ሐሳብ ያራመደውን ለመዝለፍና ለማዋረድ ያለው ትጋት ለትግሉ ካለው ትጋት ይልቃል።

ጥላቻውና ዘለፋው ግለሰብ ለግለሰብ፣ ቡድን ለቡድን ብቻ ቢሆን ይሻል ነበር። ሕዝብ በጅምላ መፈረጅ ቀላል እንደነበር በሰነድ ሳይቀር ተሰንዶ እናገኘዋለን። የዘጔው አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ የጥላቻን ፅንፍ ለዳግማዊ ምኒልክ ጽፈውት በ1901 በሮም በታተመላቸው ‘ዳግማዊ አጤ ምኒልክ’ የተሰኘ መጽሐፍ አሳይተውናል። ትግርኛ ተናጋሪዎችን “ቋንቋቸው ጉሮሮ የሚፍቅ” ይሏቸዋል። አዋቂነታቸው በዚያ ረገድ እንዲሳሳቱ እንዳንፈቅድላቸው የሚያስገድደን “የምሁራን ስብስብ ቁንጮ” የተባሉት ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ ለአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ መልስ የተጻፈ የሚመስለው “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” የተሰኘ አጭር ጽሑፋቸው ላይ “እንኳን አእምሮ ያላቸው ነገሥታት ኦሮሞውም ቢሆን…” ብለው ሲጽፉ ጥቂት እንኳ የከበዳቸው አይመስል።

“እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ ፈጠረ” ብለው የሚያስተምሩት “ሊቃውንት”፣ የሚያሸረግዱለትን ነጋሢ ለማስደሰት፣ የሆነን ሕዝብ ከሴይጣን አዛምደው ሲጽፉ ትንሽም አልጎረበጣቸው። ነገር ግን በተመሳሳይ ዘመን ያለፈውን ታሪክ ከልሰው የጻፉት ሁለቱ ሊቃውንት አለቃ አፅሜ እና አለቃ ተክለየሱስ፣ ምንም እንኳን “በእውነት እንበለ ሐሰት ውዳሴ ከንቱ ሳንጨምር ጻፍን” በማለት የቀደመው ታሪክ አጻጻፍ ላይ እንከን እንዳለ ቢገልጹም እርምታቸው ለየቅል ነው። ይህን አንድን ሕዝብ ከሰይጣን የማዛመድ ታሪክ የአንድ ዘመን ፍሬዎቹ አለቃ አፅሜ “የእውነት ታሪክ አይደለም” ብለው ሲያርሙት፣ አለቃ ተክለየሱስ ግን የተጠራጠሩ ሳይመስሉ ደግመው ጽፈውታል። ችግሩ ያለው ከፍላጎታቸው ይመስላል። አለቃ ተክለየሱስ የጻፉት አፈወርቅ ገብረየስ የንጉሥ ተክለሃይማኖትን ሥም በክፉ በማንሳታቸው እሱን ለማረም ብቻ ነበርና የሌላው ሕዝብ ነገር አላሳሰባቸውም ነበር። አሁንም ለጥፋት መንስዔው ለአንድ ወገን ብቻ ተቆርቋሪነት ነው። የዛሬም ዘመን አባዜ ይኸው ለአንድ ወገን ብቻ ተቆርቋሪነት ነው። ፍትሕ ደግሞ እንዳለመታደል ሆኖ ወይ ለሁሉም ትመጣለች፤ ወይ ለሁሉም ትቀራለች።

አባ ባሕርይ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በጻፉት ለዛሬ ዘመን ጠቃሚ ባለ 20 አጫጭር ምዕራፎችን የያዘው “ዜናሁ ለጋላ” የተሰኘ ሰነድ መግቢያ ምዕራፍ ላይ፣ ሙስሊሙንም፣ ኦሮሞውንም ሕዝብ ሁለቱንም ባንዴ “ጠላቶቻችን” ብለው ይገልጿቸዋል። “የነገዱን ቁጥር፣ ሰውን ለመግደል የትጋቱን ነገር፣ የጠባዩን እንስሳነት ለማወቅ የጋላን ዜና ልጽፍ (እነሆ) ጀመርኩ። ‘የክፉውን ዜና እንደደጎች ዜና ለምን ጻፈ?’ የሚለኝ ካለ፥ ‘በሃይማኖት ጠላቶቻችን ሆነው ሳለ የመሐመድ ታሪክና የእስላሞች ነገሥታት ታሪክ እንደተጻፈ ታይ ዘንድ መጻሕፍትን መርምር’ ስል መልስ እሰጠዋለሁ” ብለዋል። አባ ባሕርይ ከነወገንተኝነታቸው ከዛሬ ሰው የተሻለ ለዕውቀት ያላቸውን ጉጉነት ግን ሳልጠቅስ ማለፍ አልችልም። ዛሬም ነገሩ ያው ነው። ሕዝብን በጥቅሉ መፈረጅ የዘመኑ አዋቂነት ይመስላል። ለግለሰብ የሐሳብ ነጻነት መስጠትም ተነውሯል።

የታሪካችን፣ የተራኪዎቻችን፣ የንጉሦቻችን አገዛዝ አድሏዊ መሆኑን ማስረጃ ሳያንስ፤ በአድሎው ላይ መተማመንና ያለፈውን ጠማማ ተባብረን ለማቃናት መትጋት ሲኖርብን፣ ያለፈውንም ይሁን የዛሬውን እኔ በምረዳበት እና በማከብረው (ወይም በምንቀው) ልኩ ካላከበርክ (ወይም ካልናቅክ) በሚል ሌላ ጥመት ለነገ እናሳድራለን። በሚገርም ሁኔታ “አንዴ ትክክል የሆነ ሁሌ ትክክል ነው፣ አንዴ የተሳሳተ ደግሞ ሁሌ ተሳሳች ነው” የሚል ፈሊጥ ተጠናውቶናል። በዚህ ረገድ የዘመኑ ማኅበራዊ ብልፅግና ደረጃ እና የመረጃ ፍሰት አቅም አይፈቅድልንምና ከአባቶቻችንና አያቶቻችን የከፋን፣ አውቆ አጥፊዎች ያደርገናል።

ለሥም “የኢትዮጵያዊነት መለያ” ከምንለው “ጨዋነት” ይልቅ ብልግናችን እና መረንነታችን በአደባባይ ይስተዋላል። የማይስማማንን ወይም የተሳሳተን ሐሳብ ባየን ግዜ፣ በሠላሙ ግዜ እንደምንፈክረው በጨዋነት ማረም ወይም ማስረዳት አልያም የማይገባው ሲሆን ንቆ መተው ስንችል፣ በብልግና በልጠን ለመታየት የምንሽቀዳደም ስለሆነ/ከሆነ ከአባቶቻችን ጥንካሬም፣ ድክመትም መማር ያልቻልን ከንቱዎች ሆነናል።

ዐብይ ችግራችን ሐሳቡን ከግለሰቡ ለይተን መመልከት አለመቻላችን ነው። አንድ ሰው የተሳሳተ ሲመስለን ገና ስለትክክለኛነታችን እንኳ እርግጠኛ ከመሆናችን በፊት የሰውየውን ማንነት በማራካስ፣ አጓጉል ሥም በማውጣት እና በመዝለፍ ብዙ ሐሳብ ያለውን ታዛቢ በዝምታ እንዲመክን ከወዲሁ እናስፈራራለን።

ለሰው ሰብኣዊ ነጻነት እና ክብር የምንሰጠው የረከሰ ዋጋ፤ ግለሰብን ከቡድን ነጥለን መመልከት አለመቻላችን፤ በሐሳብ ልዩነት እና በተቀናጀ ሴራ መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ያለን ዳተኝነት ‘የወል ሥነ ልቦናችን የተገነባበት መሠረቱ የተሳሳተ መሆን ወይስ የግለሰቦች ውድቀት?’ ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳል። በኔ ግምት ችግሩ ማኅበራዊ ሥሪታችን ውስጥ ያለ ይመስለኛል። እንደመፍትሔ የምመክረው እያንዳንዱ ሰው ራሱን ከዚህ ውድቀት ያውጣ በማለት ነው፤ ያኔ ሁሉም ነጻ ይወጣል።

LEAVE A REPLY