ሀገር የሚፈርሰው በዜጎች ነፃነት ሳይሆን በአምባገነኖች ፍርሃት ነው!

ሀገር የሚፈርሰው በዜጎች ነፃነት ሳይሆን በአምባገነኖች ፍርሃት ነው!

የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ዛሬ ወደ አንድ አቃቢ-ሕግ ቢሮ ሄዶ የታዘበውን ነገር በፌስቡክ ገፁ ላይ አስነብቦናል። በእርግጥ አቶ ግርማ ወደ ተጠቀሰው ቢሮ የሄደው የእነ ኤሊያስ ገብሩ እና ዳኒኤል ሺበሺ ጉዳይን ከምን እንደደረሰ ጠይቆ ለማጣራት ነበር። ነገር ግን፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊ የሰጡት ምላሽ ግን እጅግ በጣም የሚያስገርም ከመሆኑም በላይ የአምባገነን መንግስትን ትክክለኛ ባህሪን በግልፅ የሚያሳይ ነው።

እነ ኤሊያስ ከታሰሩ ስድስት ወር ሊሞላቸው ነው። ለመታሰራቸው በዋና ምክንያትነት የተጠቀሰው ደግሞ ‘በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አመፅና ሁከት የሚያነሳሳ ተግባር ፈፅመዋል’ የሚል ነው። በዚህ ጉዳይ፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ጦማሪያን፣ ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ለእስርና እንግልት መዳረጋቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ፣ “ሕዝብን ለአመፅና ሁከት በማነሳሳት” በሚል ሰበብ ከዚህ ቀደም፣ አሁንም፣ ወደፊትም የሚታሰሩ ሰዎች ሁሉም “የፍርሃት ሰለባዎች” ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

በእርግጥ አብዛኞቻችሁ “የምንና የማን ፍርሃት?” የሚል ጥያቄ በውስጣችሁ እንደምታነሱ እገምታለሁ። መልሱ “የአምባገነኖች ፍርሃት” የሚል ነው። ፅንሰ-ሃሳቡን በግልፅ ለመረዳት በአምባገነን መንግስት እና በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መካከል ያለውን ባላንጣነት በአጭሩ መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡ በመሰረቱ አምባገነን መንግስታት እና የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች አይን እና ናጫ ናቸው። ለምን?

አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን በ1989 ዓ.ም በምስራቅ አውሮፓ ሕዝቦች ላይ ተጭኖ የነበረው የሶቬት ሕብረት አምባገነናዊ ሥርዓት እንዳልነበር ሆኖ የተገረሰሰው በቴሌቪዥን አማካኝነት እንደሆነ ይገልፃሉ። በጉዳዩ ዙሪያ በወቅቱ የአሜሪካ ፕረዜዳንት የነበሩት ሮናልድ ሬገን በለንደን ከተማ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር፡- “The Goliath of totalitarianism will be brought down by the David of the microchip” እንደ ሬገን አገላለፅ፣ ቴሌቪዥን፣ ራዲዮ፣ ኮምፒውተር፣ ሞባይል፣ እና ሌሎች የኤሌከትሮኒክስ መገናኛ ቴክኖሎጂዎች መሰረት የሆነው “ማይክሮቺፕ” (microchip) ለአምባገነን መንግስታት ልክ እንደ “ኤች.አይ.ቪ” (HIV) ቫይረስ ነው። ምንም ያህል ጥንካራና አይበገሬ ቢመስሉ አንዴ በማይክሮቺፕ ቫይረስ ከተያዙ ቀስ-በቀስ እየገዘገዘና እያመነመነ ለውድቀት ይዳርጋቸዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ማይክሮችፕ ከፈጣን የኢንተርኔት ግንኙነት መረብ ጋር ሲያያዝ ደግሞ የአምባገነኖችን ውድቀት በእጅጉ ያፋጥነዋል። እ.አ.አ. በ1996 በተካሄደው የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም ይፋ የተደረገው የኢንተርኔት ነፃነት አዋጅ፦ “the global social space we are building to be naturally independent of the tyrannies [governments] seek to impose on us” የሚል መርህ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ፀረ-አምባገነናዊ ሥርዓት ስለመሆኑ በግልፅ ይጠቁማል።

አሁን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀገራችን ዜጎች የዕለት-ዕለት እንቅስቃሴ ከማይክሮቺፕ እና ከኢንተርኔት ጋር የተቆራኘ ነው። ከገጠር እስከ ከተማ በመኖሪያ ቤታቸው፣ በሥራ ቦታ ወይም በመዝናኛ ቦታ ከአጠገባቸው በማይለየው ሞባይል ስልክ አማካኝነት ሃሳብና መረጃ ይቀያየራሉ።

በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያዎች ነፃ የውይይት መድረክ እየሆኑ መጥተዋል። አንዳንድ የጥናት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለሕትመትና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች የመረጃ ምንጭ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም፣ በፖለቲካ ንቁ-ተሳትፎ የሚያደርገው የሕብረተሰብ ክፍል በአብዛኛው የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ አየሆነ መጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ፣ አብዛኞቹ የሙያና ሲቭል ማህበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የሙያና ሲቭል ማህበራት፣ እንዲሁም የአለም-አቀፉ ማህብረሰብ የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

አብዛኞቹ የሀገራችን ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት በመግለፁ ግንባር-ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። ይህ በወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ፣ በፖለቲካ ቡድኖችና የሲቭል ማህበራት፣ እንዲሁም በአለም-አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ ተሰሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። የአምባገነን መንግስታት ፍርሃት የሚመነጨው ከዚህ ነው። በኢንተርኔት አጠቃቀም እና በአምባገነን መንግስታት መካከል ስላለው ግንኙነት የተሰራ ጥናት የአምባገነኖችን ፍርሃት እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“Four separate areas of Internet use threaten authoritarian regimes: mass public use, civil society organizations (citizens’ pressure groups), economic groups and the international community.”

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ በሆነው ውይይት፣ አቃቢ-ሕግ እነ ኤሊያስ ያለ ምንም ውሳኔ ለረጅም ግዜ መታሰራቸውን አስመልክቶ ከአቶ ግርማ ሰይፉ ለቀረበላቸው አቤቱታ የሰጡት ምላሽ “እነዚህ እኮ ሀገር ሊያፈርሱ የነበሩ ናቸው” የሚል ነው፡። በእርግጥ ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ስለ ገለፁ የሚፈራውና የሚፈርሰው ሀገር ሳይሆን አምባገነናዊ ሥርዓት ነው። ሀገር የሚፈርሰው እንደነ ኤሊያስና ዳኒኤል ያሉ ፀሃፊዎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ስለገለፁ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ ሀገር የሚፈርሰው አምባገነኖች በፍርሃት በሚወስዱት እርምጃ፣ በዚህም በዜጎች ላይ በሚፈፅሙት በደልና ግፍ ነው። በአጠቃላይ፣ ሀገር የሚፈርሰው በዜጎች ነፃነት ሳይሆን በአምባገነኖች ፍርሃት ነው!

LEAVE A REPLY