የአንደኛው አለም ጦርነትን ፍጻሜ ተከትሎ ለአራት መቶ አመታት ያህል የመካከለኛውን ምስራቅ በበላይነት ተቆጣጥሮ የነበረው የኦቶማን ኤምፓየር በመሸነፉ አካባቢውን የተቀራመቱት ባለተራዎቹ የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶቹ እንግሊዝና ፈረንሳይ እንደ ነበሩ ይታወቃል።
በሰሜን ሶሪያ ላይ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ስታነሳ የኖረችው ቱርክ የእርስ በርሱን ጦርነት ተከትሎ በግልጽም በስውርም ሲቻላት በግል ሳይቻላት ከሌሎች ጋር በመሻረክ ለላፉት ስድስት አመታት በተካሄደው ይኽ በሰው ልጆች ታሪክ አምሳያ በጠፋለት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ዋነኛውን ድርሻ ከተጫዎቱት ውስጥ አንዷ ናት። የአሸባሪዎቹን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በሚል ሽፋን ጦሯን በይፋ ወደ ሶሪያ ምድር ያስገባችው ቱርክ ከዚህ ጦርነት ፍጻሜም ቦኃላ ይህን ግዛት ለቃ ትወጣለች ማለት የማይታሰብ ነው፤ ይልቁንም እንደ እስስት የሚለዋወጥ መሰሪ መሪ ያላት ቱርክ የጥንቱን የኦቶማን ኤምፓየር ክብር አስመልሶ እራሱን የሃያ አንደኛው ክዘመን ሱልጣን ለማድረግ ካለው ቅዠት አንጻር የሰሜን ሶሪያ ግዛት ከእጁ የመውጣቱ ነገር እንዲህ በቀላሉ የሚሆን ነገር አይመስልም።
አሜሪካ በበኩሏ አለማቀፍ ህግን በሚጻጸር መልኩ ያለ ሶሪያ መንግስት ፈቃድ እስካፍንጫው የታጠቀውን ጦሯን በተወሰነው የሶሪያ ክፍል አስፍራለች። ሁኔታው በኮሶቮ ነጻነት ሽፋን በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ብብት ስር የጦር ቤዝ እንደመሰረተችው ሁሉ የሶሪያም ከዚህ የሚዘል አይሆንም። አሜሪካና ሳውዲ አረቢያ ኮትኩተው ባሳደጉት አይሲስ በተባለ አንገት ቆራጭ አውሬ ሶሪያን ሲያደሟት ከርመው ዛሬ ወደ ትቢያነት ከተለወጠችና ልጆቿም እንደ ሎጥ ዞረው ላያዩዋት አገራቸውን ጥለዋት እግራቸው ወዳደረሳቸው ሲሄዱላቸው ጥንባንሳዎቹ( እስካቬንጀርስ ) እግራቸውን መዘርጋታቸው የሚጠበቅ ነው።
የኢራቅን ስንመለከት ኢራን፣ ቱርክ እና አሜሪካን እርስ በእርሱ በሚጣረስ የግል አጀንዳ በሶስት ማእዘን ተፋጠውባታል።የደቡቡን ኢራቃዊ ክፍለ ግዛት ለብቻቸው መንግስት መንግስት መሽተት የጀመሩት ኩርዲስታኖች በበኩላቸው እራሳቸውን ማስተዳደር ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ያለበትን ይሕን ቦታ ከመቆጣጠራቸው በተጨማሪ የአውሮፓ፤ ደቡብ ምስራቅ እስያና ህንድ ዋነኛ የበረራ መገናኛ ማእከል የሆነው በፔሪሽያ ገልፍ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የባስራ አውሮፕላን ጣቢያ እንደ አደይ አበባ መፍካት መጀመሩና በአካባቢው የደራው የብላክ ጎልድ ገበያ ሁሉ ሲጨመርበት ለኩርዲስታኖች መጠናከራቸው በአሁኑ ሰዓት ከባግዳድ ም ንም አይነት መመሪያ የማይቀበሉ ብቻ ሳይሆን ለአይቀሬው የኩርዲስታን መንግስት ምስረታ መንገድ መጀመራቸውን እና በማንኛውም ሰዓት ነጻነታቸውን ሊያውጅ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ባጠቃላይ ከዚህ ሁሉ ውጥንቅጡ የወጣ ፍጥጫ ማግስት እራቅ አንድ ሆና ወደ ቀድሞ አንድነቷ የመመለሷ ነገር የሞተን ሰው የማስነሳት ያህል ባዶ ተስፋ ነው። በትንሹ ለሶስት ትናንሽ አገሮች ሊወጣት እንደሚችል ይጠበቃል።
እንግዲህ ለስድት አመታት ኢራቅና ሶሪያን ማእከል አድርጎ ሲንተከተክ የከረመው የጉልበተኞች ፕሮክሲ ዎር አሁን በተወሰነ ደረጃ ምህዋሩን ወደ አፍሪካ ቀንድ እና ኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ እያዞረ ይመስላል። በዚህስ ከእኛ ኢትዮጵያውያንስ ምን ይጠበቃል፤ በሃይል ቀጠናውስ ማን ከማን ጀርባ ተሰልፏል የሚለውን ሰሞኑን እመለስበታለሁ።