ዛሬ ዕለተ አርብ ነው፡፡
ዛሬ በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ መድኃኒዓለም የሚከበርበት ነው፡፡
ዛሬ ሚያዝያ 27 ነው፡፡ የነፃነት ቀን ነው፡፡
ይገርማል፡፡
አጋጣሚዎች በራሳቸው ጊዜ ግጥምጥም ሲሉ ደግሞ ከማስገረምም ያልፋሉ፡፡ ዛሬ …. በእለተ አርብ፣ ወዳጃችን አሠፋ ጫቦ የ“ጋራ ቤታችን”ን ማህፀን ውስጥ አረፈ፡፡ በነፃነት ቀን በእናት ምድሩ የዘለዓለም እረፍት አደረገ፡፡ ከሳሽ፣ ወቃሽ ወደሌለበት፣ ሁካታና ግርግር ወደማይኖርበት … ወደማይቀርበት ወደዚያኛው ዓለም መረሸ፡፡ በአጭሩ – በነፃነት ቀን ነፃነቱን አወጀ፡፡ የቀኑ ግጥምጥሞሽ… ከ12 ቀን በላይ አፈር ያልቀመሰው “ነፃነቱ” ከነፃነት ቀን ጋር እንዲሰምር መሆን አለበት አሰኘኝ፡፡
.
ዛሬ ሚያዝያ 27/2009 እኩለ ቀን ሲሆን፡-
ፓርላማው አጠገብ፣ ቤተ-መንግስቱ አጠገብ ሥላሴ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በርካታ ሰዎች በ “ፀጥታ” ውስጥ ያለውን አሰፋ ለመሸኘት እየተጠባበቁ ነበር፡፡ እኔም በፀጥታ ውስጥ ሆኜ ከፍ ያለው አውደምህረት ላይ ቆሜ “በትዝታ ፈለግ” ውስጥ ወዳጄን እያሰብኩት ነው፡፡ ዕኩለ ቀን ጥቂት ደቂቃ እንዳለፈ የአሠፋ ጫቦን አስከሬን የጫነው መኪና ወደስላሴ ቅጥር ገባ፡፡ ከየአቅጣጫው የተሰበሰበው ሸኚ ወደመኪናው አቅጣጫ ፊቱን አዞረ፡፡ አስከሬኑ አውደ ምህረቱ ላይ አረፈ፡፡ ይኼኔ ከግቢው ውጪ፣ ከርቀት የሆታ የጭፈራ የሚመስል ድምፅ ተሰማኝ፡፡ የምን ጭፈራ፣ የምን ሆታ ይሆን? አልኩ ለራሴ፡፡
.
ሆኖም ለጥያቄዬ መልስ ማግኘት አልሻትኩም፡፡ ፊቴን ወደቀኝ፣ ወደ ቤተክርስቲያኑ በረንዳ አዞርኩኝ፡፡ ፍቅረስላሴ ወግደረስን (የደርጉን ጠ/ሚ/ር) አየሁ፡፡ እየገረመኝ ዐይኔን ወደግራ ከአውደምህረቱ በታች ሰደድኩ፡፡ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ከዘራ ይዘው መኪና ተደግፈው አቀርቅረው ቆመዋል፡፡ በዚያው መደዳውን አይኔን ላክሁት፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ዕይታዬ ውስጥ ገባ፡፡ ….. አለፍ ብሎ የቆሙት ወጣቶች መሃል በቅርቡ በኮማንድ ፖስቱ ለወራት ታስሮ የተፈታውና ከተፈታ በኋላ በኋላ ክስ ተመስርቶብሃል የተባለው ኢዩኤል ፍሰሃ ደምጤ ቆሟል፡፡…. ፍቅረስላሴ በአንድ ወቅት አሳሪ የነበረ ቢሆንም፣ ሁሉም እስረኛ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚች ሰዓት፣ በአሰፋ ጫቦ ፍፁም ፀጥታ ውስጥ ሁሉንም አሰብኳቸው፡፡ “ህይወት ማለት እስረኝነት ነው” እያሉ ይሆን? …ራሴን ጠየቅኩ፡፡
.
ነገር ግን የፀሎተ ፍታቱ መጀመር ከራሴ ሃሳብ አነጠበኝ፡፡
ፍታቱ ከተጀመረ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ከየት መጣ ሳይባል ዝናብ መዝነብ ጀመረ፡፡ ለቀብረ የመጣው ሰው ሁሉ ወደ ቤተክርስቲያኑ ውስጥና በረንዳ ተሰባሰበ፡፡ ዝናቡ ዋዘኛ አልነበረም፡፡ በረንዳው ላይ ችምችም ብሎ ከቆመው ሰው መሃል አጠገቤ የቆሙት አንድ አዛውንት እንዲህ አሉ፡-
“…. በገጠር ድንገት ዝናብ የሚዘንበው ትልቅ ሰው ሲሞት ነው፤ ይኼ ሰው ትልቅ ሰው ነው”
አዛውንቱ ለጓደኛቸው ነው ይኼንን የሚናገሩት፡፡ ገረመኝ፡፡
ፍታቱ አለቀ፡፡ የህይወት ታሪኩ ተነበበ፡፡ የተነበበው የህይወት ታሪክ የተለመደው ዓይነት አይደለም፡፡ በዚህ ዓመተምህረት በዚህ ቦታ ተወለደ፤ እዚህ ሰራ …ምናምን የሚል አይደለም፡፡ በጥበብ የተዋዛ፣ ደስየሚል፣ነገር ግን የሚያባባና የሚያስነባ ታሪክ ነበር የተነበበው፡፡ የሚገርመው ነገር የህይወት ታሪኩ ተነቦ ባበቃበት ቅፅበት እንደጉድ ይወርድ የነበረው ዝናብ ቀ…ጥ ብሎ ቆመ፡፡
.
በዚህ ዝናብ እንዴት ልንቀብረው ነው ሲል የነበረው ሸኚ ከያለበት ዝርግፍ ብሎ ወጣ፡፡ ይኼኔ ነው አስከሬኑ በመኪና ወደቤተክርስቲያኑ ሲገባ ከሩቅ የሰማሁት የሆታና የዘፈን የሚመስል ድምፅ ምንጭ ምን እንደሆነ የገባኝ፡፡
በርካታ የዶርዜ ባህላዊ ልብስ የለበሱ፣ ጦር እና ለምድ ትከሻቸው ላይ የደረቡ ሃዘንተኞች እጅብ ብለው አስከሬኑን ተከትለው ወደመቃብሩ ሲያመሩ አየሁ፡፡ ይኼኔ አሠፋ ጫቦ “እንደዶርዜ ወገኖቼ በሆታ ሸኙኝ” ብሎ የከተበው መጣጥፍ ትዝ አለኝ፡፡ እናም “እንደተመኘው ሆነለት” አልኩኝ፡፡ አባቶች “ትንቢት ከነገር ይቀድማል” እንዲሉ፡፡
.
በመጨረሻ
ቆም ብዬ አስከሬኑ ያለበትን ሳጥን በትኩረት አየሁት፡፡ “ወዳጄን በሞት አገኘሁት” አልኩ ለራሴ፡፡ “ሂድ” አልኩት፡፡ “በሞት መገናኘታችን አይቀርም” አልኩት፡፡ “እንኳን ከእኔ፣ እላይ ካሉትም፣ የሥልጣን አናት ላይ ቂብ ካሉትም ጋርም በሞት መገናኘትህ አይቀርም” አልኩት፡፡ እናም …. ወዳጄን አሠፋ ጫቦን ወደ ወዲያኛው ዓለም፣ ወደ ነፃነት ዓለም፣ “እዚያው እንገናኝ” ብዬ በነፃነት ሸኘሁት፡፡