ጋሞን ከኢትዮጵያ ኢትዮጵያን ከጋሞ፤
አጋምዶና አፋቅሮ አጣብቆና አሳስሮ፤
ላይለያቸው ምሎ፤
በስጋና ደሙ አዋህዶና አዝሎ፤
ውሸትን አዳፍኖ ሐቅንም ገላልጦ፤
በድፍረት ተናግሮ በድፍረትም ፅፎ፤
አካፋን አካፋ ዶማውንም ዶማ ብሎና መስክሮ፤
ልክ እንደ አባቶቹ ልክ እንደ አያቶቹ፤
ጀግና ሆኖ ሄደ ትውልድን ተሻግሮ፡፡
እውነትን ላይደብቅ ታሪክ ላያዛባ፤
ድርና ማግ አርጎ ሃሳብን ከሃሳብ ሲገምድ ሲሰፋ፤
ላጲስ ለሆነ ክንድ ለውድቅዳቂ ሃሳብ እጅ አልሰጠም ከቶ አንገትም አልደፋ፡፡
አምጦና ወልዶ ቀለም በሰጣቸው የሃሳቦቹ ወግ
ድንቅ በሆነ ቃል ጥዑም በሆነ ሃረግ፤
ትዝታችን ሆነ አሴ የእኛ አባት በትዝታ ፈለግ፡፡
አሴ
የገሮ አድባራችን የበኩር ልጃችን፤
ጀግናው አባታችን ….. ፤
ሃገሬን አፈሬን፤
ወገኔን ዘመዴን፤
ባህልና ቅርሴን፤
ብሎ እንዳለመ ብሎ እንደፃፈ፤
ከምድረ አሜሪካ ወደ ምድረ ኢትዮጵያ
ከፍታን ሊወጣ ከፍ ብሎ በረረ፡፡
በቅድስት ስላሴ በጀግኖቹ ሃገር፤
በአርበኞቹ ዕለት በአርበኞቹ መንደር
ተፅፎ ታትሞ አሴአችን ደረሰ
ምድርን ከሰማይ ጋር እኩል አሳዝኖ እኩል አስለቀሰ፤
ተውቦና ደምቆ በክብር ነገሰ፡፡
ሚያዚያ 28 ቀን 2009 ዓ.ም
መታሰቢያነቱ ለአቶ አሰፋ ጫቦ፡፡